Saturday, 18 February 2023 19:43

“አገር ለመሸሸጊያ አልበቃ ካለችህ ቤተ-መንግሥቱ ሥር ገብተህ ተደበቅ!”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 በፈረንሳይ  አገር የሚገኘው “ቱር ኤፌል” ዘመናዊ ሐውልት፣ የአያሌ ጎብኚዎች መስህብ ነው። በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን  አንድ ታሪክ በየጊዜው ይተረካል።
ነገሩ እንዲህ ነው።
ሐውልቱ የተሠራው አያሌ አንጋፋና ወጣት ዲዛይነሮች ከተወዳደሩ በኋላ ነበር።  “ያለ ጥርጥር የውድድሩ አሸናፊ የምሆነው እኔ ነኝ” የሚል አንድ አንጋፋ ሰዓሊ ውጤቱን ይጠባበቃል።
የዳኞቹ ውጤት ብዙ ቆይቶ ተገለጠ። የዚያ የአንጋፋው ሰዓሊ ስም ግን ከዳኞቹ አፍ አልተሰማም። ይልቁንም  የውድድሩ አሸናፊው አንድ ወጣት ዲዛይነር ሆነ። ዓለምም ተደመመ።
ታላቁ ሰዓሊ አዘነ። አፈረ።  ሐውልቱ ሕመም ሆነበት። ስለዚህም፤ “ከእንግዲህ ይህን ሐውልት የማላይበት ሰፈር ፈልጌ መሄድ አለብኝ” ብሎ ቤት ቀየረ። ሐውልቱ ግን ግዙፍ ነው። ከመነሻውም፣ ከድፍን ፓሪስ ከየትኛውም ቦታና አቅጣጫ እንዲታይ ታስቦበት ስለተሰራና ስለቆመ ከየትም ቦታ ይታያል።
አንጋፋው ሰዓሊ፡- “እንደዚህ ከምሰቃይ ለምን ቤቴ ውስጥ ቁጭ አልልም” ብሎ ከቤቱ ላይወጣ ቆርጦ ተቀመጠ።
የአንጋፋው ሰዓሊ ሁነኛ ጓደኛ የሆነ የታወቀ ፈላስፋ አለ። ሰዓሊውን አጥቶት ከረመ። ጨነቀውና ወደ ቤቱ ሄዶ ሊያገኘው ወሰነ።
እቤቱ ሄዶም አገኘው።
እንዲህም ሲል ጠየቀው፡-
“ወዳጄ ሆይ፤ ወዴት ሄደህ ጠፋህብኝ? ወዳጅነታችን እንዲህ የአጭር ጊዜ ነውን?”
አንጋፋው ሰዓሊም የሆነውን ሁሉ አወራለት። ስሜቱ ከመጠን በላይ እንደተጎዳ  አስረዳው። ወደፊትም ከዚህ አገር ወጥቶ እንደሚሄድ ነገረው።
ፈላስፋው በነገሩ አዝኖ፡-
“አይዞህ! እኔ መፍትሔ አበጅልሃለሁ። አንድ ቦታ እጠቁምሃለሁ። ከዚያ ቦታ በጭራሽ ቱር ኤፌልን ሐውልት አታየውም” ሲል መተማመኛ ሰጠው። አንጋፋው ሰዓሊ በጣም ተደሰተ። ቸኩሎም ያንን ቦታ አሳየኝ አለው። ወተወተው።
በነጋታው ፈላስፋው ሰዓሊውን ይዞት ሄደ።
የወሰደው ቦታ ግን አስገራሚ ነበረ። ወደ ቱር ኤፌል ነው ይዞት የሄደው። ከግዙፉ ሐውልት ውስጥ ወደምትገኝ ወደ አንዲት ካፌ ውስጥ ነበረ ወስዶ ያስቀመጠው። ዕውነትም ያቺ ካፌ ውስጥ ሐውልቱ የለም። ካፌ ውስጥ ሆኖ ዙሪያ ገባውን ቢያማትር እንኳን፣ ግዙፉ ሐውልት አይታየውም!
***
“ከካሜራ ውስጥ ያለ ሰው ራሱን አያይም” ይባላል።
ማናቸውም ብርቱ ጉዳይ ውስጥ ስንሆን፣ ሌላው ሰው ያየናል እንጂ እኛ ራሳችንን አናይም። የፖለቲካ ዋና ቁምነገር ይህ ነው። መሪዎቻችን ይህንን ዕውነት ጠንቅቀው መገንዘብ ይገባቸዋል!
በተከታታይ ያየናቸው አብዮታዊ ንቅናቄዎች ያስተማሩን ትምህርት፣ እኛን የሚያዩን በመሰላቸው ቁጥር፣ እኛ የበለጠ እንደምናያቸውና የባሰ እንደምንታዘባቸው ነው!
ይህም ያገናዘብነው የፖለቲካ ሚዛን፣ የተሻለ ራዕይ እንዲኖረን ማድረጉን እናምናለን።
በሀገራችን አንድ አዲስ መሪ በመጣ ቁጥር ዙሪያውን መኮልኮልና አበጀህ! አበጀህ! ማለት፣ እንዲሁም “ጎሽ- ጎሽ - ኮሚቴ” ማቋቋም፣ እጅግ የተለመደ ከሆነ ውሎ አድሯል! አዲስ በር ከማስከፈትም አሮጌውን መዝጊያ መጠጋገን ለምዶብናል። ሂደቱ በተደጋገመ ቁጥር ለውጥን እንዘነጋለን።
ስለዚህ “የተሻለ ዓለም ይታያል” እንላለን እንጂ ፈሊጣችን “ባለህበት  እርገጥ” ነው!
የአዲስ ክስተት ጉዞ እንደተጀመረ ሳናረጋግጥ፣ በአዲስ መሪ ዙሪያ በመሰለፋችን፣ ለውጥ የመጣ ይመስለናል።
መሪውም ለውጥ ያመጣ ስለሚመስለው፣ ከለስላሳ ንግግር ወደ ጠንካራ፣ ከለሆሳስ ወደ ጩኸት፣ “ከእባካችሁ ስሙኝ” ወደ  “አርፋችሁ ቁጭ በሉ”፤… መንደርደሩን ይቀጥላል።
መግደሉና ደም መፋሰሱ ባህላዊ መንገድ እስኪመስል ድረስ በመቀጠሉ የከትላንት ወዲያውን ስርዓተ ጭፍጨፋ የትናንትናውን፣… የአምናውን ስርዓተ ሲኖዶስ ከዘንድሮ የካህናት ግጭትና እልቂት ወዘተ ማወዳደራችንን በመቀጠል ጉዳዩን ከቤተክህነት አሳልፈን አገር አፋፍ ላይ እናደርሰዋለን። ፈሪሃ እግዜሩ ይቀራል።
ሰውና ዕምነት ይደበላለቃል።
የጥፋት አገር ይፈጠራል!
አቦ ይቅር ይበለን።
“አገር መሸሸጊያ አልሆን ሲልህ፣ እነሆ ቤተ-መንግስቱ ስር ገብተህ ተደበቅ” የሚባል ደረጃ ያደርሰናል።
ቤተመንግሥት ተገብቶስ ምን ያማክሯል? ግጭት?! ጠብን?! ሞት?! መርዶ?!
ከዚህ ሁሉ ይሰውረን!
የተሻለ ቀን ያምጣልን!

Read 2077 times