Saturday, 18 February 2023 19:51

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ቤተ ክርስቲያን ውስጧን በጥበብ ትመልከት
                              ሙሼ ሰሙ


       ከብዙ ውጣ ውረድና ፈተና በኋላ የአባቶቻችን ጽኑ እምነት፣ ጥልቅ አስተምህሮት፣ አስተዋይነት፣ ትዕግስት፣ አይበገሬነት፣ የይቅርታ ሃያልነትና የምዕመናን መስዋእትነት ታክሎበት፤ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያናችንን መሰረት እንደ አለት ማጽናትና ሀገራችንንም ከመከፋፈልና የሕዝባችንንም ደም ከመፍሰስ መታደግ ተችሏል።
ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ስናጤነው እምነታችን፣ ቤተ ክርስቲያናችንና ምዕመን ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ መታደግ እንደቻልን ግልጽ ሆኗል። እንደ ዛሬው ሁሉ ስለ ነገው የሚያውቅ እግዚአብሔር በመንፈስ አብሮን ቢሆንም፤ ቤተ ክርስቲያናችን እራሷን፣ ምዕመንና ሀገርን ከመሰል አደጋ ትጠበቅ ዘንድ ውስጧን በጥንቃቄና በጥበብ ትመልከት። ምዕመናንም የእምነት፣ የእውቀትና የተጋድሎ ምዕራፋችንን በትጋትና በጥልቀት እንፈትሽ።

____________________________________________


                በሞዛምቢክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀናት እጾማለሁ ያለው ፓስተር ህይወቱ አለፈ

                    በናይጀሪያ ለደህንነቱ የሰጋ ፓስተር ክላሽ ይዞ መስበኩ አነጋጋሪ ሆኗል


       በሞዛምቢክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀናት እጾማለሁ ያለው ፓስተር ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል። ፍራንሲስኮ ባራጃህ የተባለው ፓስተር፣ ከባዱን ነገር ተጋፍጦ ምዕመኑን ለማስደመም ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ባለፈው ረቡዕ  ህይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል።
ማኒካ በተባለችው ግዛት ነዋሪ የሆነው ፍራንሲስኮ፥ ለ25 ቀናት ከጾመ በኋላ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ህይወቱ ማለፉን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡
ፓስተሩ ቀናት እየገፉ ሲሄዱ መራመድም ሆነ መቆም ተስኖት እንደነበር የተናገሩት ቤተሰቦቹ፥ ቤይራ በተሰኘችው ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል ወስደውት ህክምና ሲደረግለት ቆይቷል።
ቤተሰቦቹም ሆነ የሚያገለግለው ቤተእምነት ምዕመናን እንደማይተርፍ የገባቸው አስቀድሞ መሆኑን የጠቀሰው የቢቢሲ ዘገባ፥ በህልፈቱ ብዙም አለመደናገጣቸውን አመላክቷል።
በደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ ሙከራ ያደረገው የ44 አመቱ  ፓስተር ህይወቱ ማለፉ የሚታወስ ነው። አልፈርድ ንድሎቩ የተባለው ፓስተር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ቆይታው የጾመውን 40 መአልትና ሌሊት ጾም ሪከርድ እሰብራለሁ ብሎ ቢዝትም ቀድሞ ተሰብሯል።
አልፈርድ ከሰዎች ርቆ ጫካ ውስጥ ጾምና ጸሎት መጀመሩን የሚጠቅሰው የዚምባቡዌው ኒውስዴይ ጋዜጣ፥ ከቤቱ ከወጣ ከ30 ቀናት በኋላ አስከሬኑ መገኘቱን አውስቷል።
ጓደኞቹም ሆነ ቤተሰቦቹ ጠንካራና ጤናማ አገልጋይ የነበረው አልፈርድ ለሞት እጁን ይሰጣል ብለው ያለመገመታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ራሱን በጫካ ውስጥ መደበቁ ለህክምና እንኳን ሳይበቃ ለህልፈት እንደዳረገውም አመልክቷል፡፡
አልፈርድ ለምን ያህል ቀን ጾሞ ህይወቱ እንዳለፈም ማወቅ ሳይቻል ይህቺን አለም ተሰናብቷል።
በአፍሪካ እንደ እነ ፍራንሲስኮ እና አልፈርድ ሁሉ የማይቻሉ የሚመስሉ ተአምራትን ለመፈጸምና ቀልብን ለመሳብ ጥረት የሚያደርጉ ፓስተሮች እየተበራከቱ መምጣታቸው ይነገራል። በሌላ በኩል፤ በናይጀሪያ ለደህንነቱ የሰጋ አንድ ፓስተር ክላሽ ይዞ መስበኩ አነጋጋሪ ሆኗል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ አንድ የክርስትና ሀይማኖት ሰባኪ (ፓስተር) ክላሽ ይዞ መታየቱ ብዙዎችን አስገርሟል። ኡቼ አግቤ የተሰኘው ይህ ናይጀሪያዊ፣ በአቡጃ ለደህንነቴ ሰግቻለሁ በሚል ክላሽ ታጥቆ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
“የተወሰኑ ሰዎች እኔን ማጥቃት ይፈልጋሉ፣ ስለዚህ ይህን ክላሽ ታጥቄ መጥቻለሁ” ሲል ለአምልኮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመጡ ተከታዮቹ ተናግሯል ተብሏል።
በናይጀሪያ ህግ መሰረት አንድ ግለሰብ የጦር መሳሪያ መታጠቅ የሚችለው ከፖሊስ ፈቃድ ካገኘ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና ይህ ፓስተር የጦር መሳሪያውን የታጠቀው በህጋዊ መንገድ ይሁን አይሁን እስካሁን አልተረጋገጠም።
ግለሰቡ አክሎም፤ “ከጌታ ስልጣን የተሰጠን አገልጋዮች፣ ህዝቡን የመጠበቅ ግዴታ ተጥሎብናል፣ የጦር መሳሪያ መታጠቄም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎችን ደህንነት የመጠበቁ አካል ነው” ሲልም ለአምልኮ ለመጡ ናይጀሪያውያን ተናግሯል ተብሏል።
በናይጀሪያ ቦኮሀራም በሚል የሚታወቀው የሽብር ቡድን፣ ብዙ አደጋዎችን በዜጎች ላይ በማድረስ ላይ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የክርስትና ሀይማኖት ተከታዮችና አገልጋዮች የጥቃቱ ኢላማ እየሆኑ መምጣታቸው ተጠቁሟል፡፡  
(አል ዐይን ኒውስ)

_______________________________________________


                  የነነዌ ለቅሶ መልስ ሲያገኝ ካኮረፍን ...


      የጥርጣሬ ጥያቄዎች ቢመጡና ብንሰጋ፣ የሚጠበቅ ነው።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በታሪክዋ አይታው የማታውቀው ሐዋርያዊ ሰንሰለትዋን የሚበጥስ አንዳች ዱብ ዕዳ ገጥሞአት በብዙ ጭንቀትና መከራ ውስጥ ሳምንታትን አሳልፋለች፡፡ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ተደናግጦ ለእናት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት የሚችለውን ሁሉ ለመክፈል ታይቶ በማይታወቅ ህብረት ተረባርቦአል፡፡
የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እስካይ ድረስ ለዓይኖቼ ዕረፍትን ለሽፋሽፍቶቼ እንቅልፍን አልሠጥም ብላችሁ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በምትችሉት ቆማችኋል፣ ብርድ ላይ አድራችኋል፣ ለመሞትም ቆርጣችኋል፡፡ ዓይናችን እያየ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አትደፈርም ብላችሁ ሰማዕታት የሆናችሁት ልጆችዋም በረከታችሁ ይድረሰን፡፡ አካላችሁ የጎደለ፣ አሁንም ድረስ በአልጋ ላይ ያላችሁ፣ ቤተሰቦቻችሁን ያጣችሁ፣ ከቀዬያችሁ የተፈናቀላችሁ፣  በወኅኒ ቤት ሆናችሁ ከእናንተ መፈታት ይልቅ የችግሩ መፈታት ያስጨነቃችሁ ወንድምና እኅቶቻችን ሥራችሁ በልበ ሥላሴ የተጻፈ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስለተገደሉ ልጆችዋ ስታለቅስና ማቅ ስትለብስም ከዳር ዳር ጥሪዋን ተቀብላችሁ ‘ቤተ ክርስቲያን ሆይ ማቅ ልልበስልሽ’ ብላችኋል። በአደባባይ በጥፊ የተመታላት የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ይህን አይቶታል፡፡
ግራ ቀኝ የሚናፈስ ወሬ ነገሩን ሊያደፈርሰው ሲሞክርም፣ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምእመናን ‘ከሲኖዶስ ሌላ ማንንም አንሰማም’ ብላችሁ ታዝዛችኋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ክብርና የቅዱስ ሲኖዶስ ምንነት ሰምተው የማያውቁ ሰዎች ሳይቀር በዚህ የተነሣ የጉዳዩ መሠረታዊነት ግልፅ ሆኖላቸው፣ ግድ የማይሰጣቸውና ሲኖዶስን ሲሳደቡ የነበሩ እንኳን ‘እኔ ነኝ ያስደፈርኩሽ ቤተ ክርስቲያኔ፤ ይቅር በይኝ’ ሲሉ ሰንብተዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኔን ነገር አደራ ብሎ ያነባውና ንስሓ የገባው ሕዝበ ክርስቲያን እልፍ አእላፍ ነበረ። መተዳደሪያ ሥራቸውን፣ ዝናቸውን፣ ሙያቸውን አደጋ ላይ ጥለው ብዙዎች ለቤተ ክርስቲያናቸው ጮኸዋል፡፡ እምነታቸው ሌላ ሆኖ እንኳን ለቤተ ክርስቲያን የቆሙ ባለውለታዎችም ብዙዎች ናቸው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ምንም ዓይነት ማስፈራሪያና ጫና ያልበገራቸው ብፁዓን አበው፣ ታሪክ በማይረሳው መንፈሳዊ ጥብዓትና ጽናት፣ በአንድ ልብ ሆነው በመናገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠበቆች ሆነዋል፡፡ ሁላችሁም ‘ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ እግዚአብሔር አመጸኛ አይደለም’ ዕብ. 6፡10
‘ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?’ አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሚል መርሕ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ለማስከበርና የቅዱስ ፓትርያርኩን አባትነት ለማጽናት፣ በዚህም በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት የተሻገረችውን ቤተ ክርስቲያን ሳትፈርስ እንድትቀጥል ለማድረግ ነው፡፡ ያ ሁሉ ዕንባና ልቅሶ፣
ያ ሁሉ ሰማዕትነት አንድ ፓትርያርክ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቀኖናዊ ዶግማ (Canonical Doctrine) ለማስከበር ነበር፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ እንደሰማነው በእግዚአብሔር ቸርነት ለሳምንታት ቤተ ክርስቲያንን እስከ ሰማዕትነት ድረስ ብዙ ዋጋ ያስከፈለው ችግር ተፈትቶ ‘አንድ ፓትርያርክ፣ አንድ ሲኖዶስ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መርሕ ተከብሮአል፡፡  ፓትርያርካችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ሲኖዶሳችን አንድ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም አንዲት ናት የሚለው ጸንቶአል፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ስለ ክብሩ መደፈር ተቆርቁረን ብዙ የጮኽንለት ቅዱስ ሲኖዶስን የእውነት ማክበራችንና መውደዳችን በተግባር የሚፈተነው አሁን ነው፡፡ ከአባቶቻችን ጎን እንደነበርን ከዚህ በኋላ በሚመጣው ነገር ሁሉም አብረናቸው እንሆናለን? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ በሰማናቸው መግለጫዎች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ተከብሯል፣ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የነበረው ሹመትም መሻሩን ሿሚዎቹ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበውን የመመለስ ጥሪ ተቀብለው ይቅርታ ጠይቀውም የተወገዙት ሊቃነ ጳጳሳት ተመልሰዋል። ልባችንን ያደማው የቤተ ክርስቲያን መከፈል ጉዳይ ባልተጠበቀ ፍጥነት ተፈትቶ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሰማ አይተናል፡፡
የጥርጣሬ ጥያቄዎችና ስጋቶች።
በሒደቱ ላይ ነገሮች በጣም በፍጥነት ከመለዋወጣቸው የተነሣ ብዙ ጥያቄ የሚፈጥሩ ዝርዝሮችና ከልባችን ገና ያልወጡ ሥጋቶች መኖራቸው የማይካድ ነው፡፡ ተመለሱ የተባሉ ሰዎች ሲወላውሉ ባየንበት ማግሥት የሆነ ነገር እንደመሆኑም ለማመን የቸገረንና በሙሉ ልብ ለመደሰት የፈራን ብዙዎች ነን፡፡
ቤተ ክርስቲያን በውግዘት የለየቻቸውን አበው መልሳ የምትቀበልበት አካሔድ እንዴት ነው?
ከዚህ በኋላስ ምን ይፈጠር ይሆን?
ወደነበርንበት ለመመለስ የከረምንበት ሁኔታ ይፈቅድልን ይሆን? መንግሥት በቃሉ ባይገኝስ? በፍርድ ቤት የታዩ ጉዳዮችስ? ይቅርታ የሚጠይቁ ሰዎች እያታለሉን ቢሆንስ? የቤተ ክርስቲያኑ ነገር እንደ እግር እሳት ሲያንገበግበው ከሰነበተ ምእመን የሚጠበቁ ውስጣዊ ጥያቄዎች ናቸው።
መንግሥትን እንዴት ማመን እንችላለን? ለሚለው እኛ ሁልጊዜም የምናምነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ አምነነው አሳፍሮን አያውቅም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ስለ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: በእግዚአብሔር መንፈስ ይመራሉ ብለን የምናምንባቸው አባቶቻችንንም እስከ አሁን ያዘዙንን ስናደርግ ሰንብተን፣ ከዚህ በኋላ አባትነታቸውን ብንጠራጠርና በስሜታዊነት ብንሳደብ፣ ‘ለሦስት ሳምንታት ቅዱስ ሲኖዶስ ክብርና ልዕልና ተነካ’ ብለን የጮኽነው ለምን ነበረ? ያስብላል፡፡
በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ከመንግሥት ጋር በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሆነው ‘ቤተ ክህነቱ ሊወረር ነው፣ አባቶች ሊታፈኑ ነው’ የሚል የሚያሸብር ዜና እየሰሙ በዚያ የጭንቅ ሰዓት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሰነበቱ አባቶ፣ ጠባቂዎች ቢነሡባቸው እግዚአብሔር ጠባቂያችን ብለው ስለ ሕገ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ በድፍረት የቆሙ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዋናው ችግር ከተፈታ በኋላ በሚኖረው ሒደት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው ይሠጣሉ ብሎ መደምደም የሚያሳዝን ነው፡፡
አባቶችን ላታልላቸው ብሎ እንደ ሀናና ሰጲራ መንፈስ ቅዱስን ሊያታልል የሚሞክር ሰው የሚያታልለው ራሱን ነውና ይቀሰፋል፡፡ አርዮስ አባቶችን አታለልኩ ብሎ ሳያምን አምኛለሁ ብሎ የደረሰበትን ስንማር ኖረናልና ቤተ ክርስቲያንን ሊያታልል የሚሞክር ሁሉ በእርሱ እንደሚብስበት እናምናለን፡፡ ስለዚህ ተመለሱ በሚል ዜና እንደጠፋው ልጅ ወንድም አኩራፊ ፣ እንደ ሀናንያ ተጸያፊ ሳንሆን፣ የእውነት ያድርገው ብለን በመጸለይ እንበርታ::
የነነዌ ለቅሶ መልስ ሲያገኝ ካኮረፍን ኩርፊያችን የዮናስ ኩርፊያ ይሆንብንና ትርፉ ቅላችንን ማድረቅና በፀሐይ መለብለብ ይሆናል::  (ዮና. 4:1-11) ልጅ ጠፍቶ ሲገኝ ደስ የሚል ከሆነ አባት ጠፍቶ ሲገኝ እንዴት ደስ አይልም? እንደ ልጅነታችን ዳግም አባት አልባ እንዳንሆን መለመን ነው እንጂ::
አባቶቻችን በኀዘን ተውጠው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲያለቅሱ አምነናቸው አብረን ካለቀስን፣ ደስ ሲላቸውና ደስ ይበላችሁ ሲሉንም እንዲሁ ልናምናቸው ይገባል፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት አልቅሰን ከጾምን፣ አንድ ሆነች ሲባል ‘አይዋጥልኝም’ ማለትም ‘ታዲያ የጸለያችሁት ምን ይሁን ብላችሁ ነው?’ ያስብላል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳቱ ‘አምላካችን ሆይ ስማን በሉ’ ሲሉ እንደተቀበልናቸው ‘ሰምቶናል’ ሲሉንም አብረን ማመስገን የልጅነት ግዴታችን ነው፡፡ ነገሩ ምንም ያልተዋጠልን እንኳን ብንሆን አባቶቻችንን አትንኩብን ስንል በከረምንበት አፋችን ለመሳደብ ብንነሣ እንኳንስ እግዚአብሔር ሶሻል ሚድያውም ይታዘበናል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስን ሌላው ሲያቃልለው ከተቃወምን እኛም የማቃለል መብት የለንም፡፡ ሁሉም ሰው መሪ ሊሆን ስለማይችል ጉዳዩን በትኩረት ለያዙት አባቶች ሥራቸውን እንደ ጀመሩት እንዲፈጽሙ እየጸለይን በምንችለው ማገዝ እንቀጥል፡፡
ከዚህ በኋላ ያለው ጊዜ የተሰበረውን የምንጠግንበት፣ ቤተሰቦቻቸውን ያጡትን የምንደግፍበት፣ ሰማዕታቱን የምንዘክርበት፣ በመከራዋ ቀን ለጮህንላት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁለንተናዊ ድጋፍ የምናደርግበት ነው፡፡
እስካሁን የገጠሙን ችግሮች ያልተሠሩ ሥራዎች ውጤት መሆናቸውን በማሰብ፣ ሌላ ሰው አጀንዳ እስኪያቀብለን በመጠበቅ ሳይሆን እኛ አጀንዳ ሠጪ እየሆንን የተቀጣጠለውን  ፍቅረ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል አገልግሎት የምናውልበት ዕድል አሁን ነው፡፡ 
መጪው ዐቢይ ጾም ነውና እያበጣበጠ ሲያፌዝብን የከረመውን ዲያቢሎስ በርትተን የምንቀጣበት እድልም ከፊታችን ነው::
አሁንም ደግመን እንላለን :-
አንድ ፓትርያርክ
አንድ ሲኖዶስ
አንዲት ቤተ ክርስቲያን
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት 8 2015 ዓ.ም.

Read 1566 times