Print this page
Saturday, 18 February 2023 19:48

ለሁላችንም ልቦናውን ይስጠን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

“ስሙኝማ.... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አንዱ ፈረንጅ የጻፈው ነው... ሀያ ዓመት ሲሞላን፣ ዓለም ሁሉ ስለ እኛ የሚያስበው
ነገር እንዳለ እናምናለን፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሞላን ዓለም ሁሉ “ስለ እኛ ምን እያሰበ ይሆን!” የሚል ስጋት ይወጥረናል፡፡ ስጋት ይገባናል፡፡ አርባ ዓመት ሲሞላን ግን ዓለም ስለ እኛ ቅንጣት ያህል እንደማያስብ ይገባናል፡፡--”
     
         እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ዓቢይ ጾም ሊገባ ነው፡፡ ሁላችን ወደ ልቦናችን የምንመለስበት መልካም የጾምና የጸሎት ወራት ይሁኑልን፡፡ ሁላችንም በዚች ህይወት ውስጥ መጓዝ  የምንችለው የተወሰነልንን እርቀት ብቻ እንደሆነና ማናችንም ዘላለማዊ እንዳልሆንን የምንገነዘብበት ይሁንልንማ!!
አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ፣ የሆነ አሁን ታሪክ ሆኖ የቀረ የሚባል አይነት ሬስቱራንት ነበር፡፡ እናላችሁ፣ የሆነ ሽክ ያለ ሰው ቢራ ምናምኑን ቀማምሶና ሂሳቡን ከፍሎ በርከት ያሉ ብሮች ‘ቲፕ’ ያስቀምጥና ይወጣል፡፡ ወዲያው ሌላ እንደሱ ሽክ ያለ ሰው በተለቀቀው ቦታው ላይ ይቀመጣል፡፡ እነኛ የበፊተኛው ሰውዬ የተዋቸውን የቲፕ ብሮች አሳላፊዎቹ አላነሱ ኖሮ አዲሱ ሽክ በሽክ ሰውዬ፣ ሸፈን ያደርጋቸዋል፡፡ እሱም በበኩሉ አንድ ሁለት ቢራ ይገጭላችሁና ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው! የራሱን ሂሳቡን ይከፍልና የበፊተኛው ሰውዬ የተወውን ‘ቲፕ’ እንደራሱ ‘ቲፕ’ ሰጠላችኋ! አዎ፣ ግራ ግብት ያለን ነገር እኛ ባስቀመጥነው ‘ቲፕ፣’ ከእኛ ከሳሳች ቦርሳችን የተለቀሙ ሳንቲሞችና ብሮች ስናስቀምጥ፣ ሌሎች ሸፈን እያደረጉ፣ ከኪሳቸው እንዳወጡት ያህል እየሰጡ፣ ለእኛ የተባለውን ጭብጫቦ ወደ ራሳቸው ማዞራቸው ነው፡፡
ለሁላችንም ልቦናውን ይስጠንማ!
እናላችሁ...ቲፕ እኮ የሚሰጠው ለመልካም አገልግሎት ወይም የልብ ለሚያደርስ ሥራ ምናምን “የሰቀለ ጉደኛ ሥራ!” ለሚባል አይደል! የእኛ ነገርማ...ምንም እንኳን ለምግቡ በሚጠይቁን ሂሳብ ልክ አገልግሎት ባይሰጡንም፣ አንዲት በዘይት ይሁን በውሀ ብቻ መሠራቷ የማይለይና “የራበው ሆድ ምግብ አያማርጥም፣” የሚባልላት ምስኪን ፍርፍር አፈርፍሮ ሳይሆን ለዋውሶና ሞቅ አድርጎ ለማምጣት አንድ ሰዓት ከአስር ደቂቃ ቢያስጠብቁንም፣ ለውሃ መጠጫ የሰጡን ብርጭቆ ጠርዝ አማሪካና አጃቢዎቿ ሰሞኑን ለዩክሬይን እየሰጡ ያሉትን “አይምሬ!” የተባለለት ታንክ ሥር የተገጠመ ‘ጎማ’ ቢመስልም፣-- በይሉኝታም ከሂሳብ የተረፈችንን ፈረንካ ጣል አድርገን መውጣታችን አይቀርም! 
ለሁላችንም ልቦናውን ይስጠንማ!
እኔ የምለው... አለ አይደል እነኚህ ትላልቆቹ ቦታዎች ከምግብና ከመጠጥ ሂሳቡ ጋር ‘ቲፕ’ የሚባለውን ምናምን ፐርሰንት ደምረው የሚያመጡት እኛ ተገልጋዮቹ መች በመስተንግዶው ተደሰትን አልናቸው! (በዚህ ዘመን ቋንቋ ‘የጥንቃቄ መልእክት’... “እኛ ተገልጋዮቹ፣” የሚለው እንዲሁ ለ‘አጣጣፉ’ እንዲመች ተብሎ እንጂ በቀጥታ ትርጉሙ በቦታው እንደነበርን ተደርጎ  እንዳይወሰድማ!)
ለነገሩማ እኛ ብቅ በምንልባቸው ስፍራዎች ‘ቲፕ’ በሚሰጡና ሁሏንም ሳንቲም ለቃቅመው በሚሄዱ መሀል ቅልጥ ያለ ‘ዲስክሪሚኔሽን‘ አለ። ልከ ነዋ...‘ቲፕ’ የማትሰጡ አይነት ከሆናችሁ አስራ አንድ ቀን ፍሪጅ ውስጥ ተከርችሞበት የከረመ እጅግ በጣም ‘ስትሬንጅ’ የሆነ ጣዕም ያለው ምንቸት አብሽ የሚሉት ‘ዲሽ’ ይቀርባላችኋል፡፡ ‘ቲፕ’ የምትሰጡ አይነት ከሆናችሁ ግን “ምን ልታዘዝ?” የሚለው የአስተናጋጆች ጥያቄ በስውር ማሲንቆና ክራር የታጀበ ነው፡፡
“ቆንጆ ምንቸት አብሽ ታመጭልኛለሽ የእኔ እህት?” ትሉ የለ፣ ይሄኔ ነው ያቺ ያስለመዳችኋት ‘ቲፕ’ ሥራዋን የምትሠራው! እሷዬዋ ድምጹዋን አሳንሳ “እሱ የከረመ ስለሆነ ይቅርብዎት፣” ብላ ‘ሹክ’ ትልዎታለች፡፡ እናንተ ደግሞ... አለ አይደል... በሆዳችሁ አባብላችሁትም ሆነ እጁን ጠምዝዛችሁ በምትሞክሩት የፈረንጅ አፍ ለራሳችሁ “ሎንግ ሊቭ ማይ ቲፕ!” የሚል መፈክር ታሰማላችሁ፡፡ ካለበላዛ ግን ወላ መጠምዝዝ ወላ ምናምን የማያስፈልገውን  “ሰውን ሰው ያደረገው ‘ቲፕ’ ነው!” ብላችሁ ቁጭ ነዋ!
የምን አገር ትሁን የምን እንጃ እንጂ ይቺን ነገር ስሙኝማ፡፡ ፀሀይና ነፋስ ናቸው አሉ፡፡ በሀይል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እየተባባሉ ይከራከራሉ። በዚህም ጊዜ መሬት ላይ ወፋፍራም ልብሶች ምናምን ተከናንቦ ይሄድ የነበረ ሰው  ያያሉ፡፡ ለምን በእሱ አይለየንም ይባባላሉ፡፡ እናላችሁ...ፉክክሩ የትኛቸው ሰውየው የደራረበውን ልብስ እንደሚያስጥለው ነበር፡፡ የመጀመሪያው ተራም ለነፋስ ይሆናል፡፡ ነፋስ ሆዬ ያንን የተጀቧቦነ ሰው ራቁቱን ሊያስቀር ለሌሎች ነገሮች ሁሉ በሚተርፍ ሀይል ወደ ምድር ይወረወራል፡፡ እጅግ ሀይለኛ ከመሆኑም የተነሳ በአካባቢው ያገኛቸውን ነገሮች ሁሉ ይገነጣጥላል፡፡ ግንማ... ምን ያደርጋል፣ ልብሱን ይጥላል የተባለው ሰው ብርዱን ለመከላከል ጭርሱን የደራረባቸውን ልብሶች በሁለት እጆቹ ግጥም አድርጎ በሰውነቱ ዙሪያ ጠቀለላቸው፡፡
ቀጥሎ የፀሀይ ተራ ነበር፡፡ ፀሀይ በአንድ ጊዜም ሀይሏን ሳትለቅ ረጋ ብላ ቀስ በቀስ እየጋለ የሚሄድ ሙቀት ለቀቀች፡፡ ሰውየው አንድ በአንድ እያለ ከላይ ደራርቧቸው የነበሩ ልብሶቹን ሁሉ አወላለቀ፡፡ ፀሀይም ፉክክሩን አሸነፈች ይባላል። ዋናው ታሪክ ግን የፀሀይ ማሸነፍ ሳይሆን ከ‘ስቶሪው’ ጀርባ ያለው ምሳሌያዊ መልእክት ነው፡፡ መልእክቱ ምን መሰላችሁ... በዚህኛው ዘመን ማንኛውንም ነገር በውጤታማነት ሠርቶ ለማጠናቀቅ ዋነኛው አስፈላጊ ነገር ጉልቤ ሳይሆን ጥበብ ነው የሚል ነው፡፡
ስሙኝማ ቢሮክራሲ የሚሉት ነገር  አይደል መከራችንን የሚያበላን! ይቺን እዩልኝማ...“አንድ የተቃጠለ አምፖልን ለመለወጥ ምን ያህል ቢሮክራቶች ያስፈልጋሉ?” ለሚለው ጥያቄ የተሰጠች መልስ ነች፡፡ አንደኛው ቢሮክራት አምፖሉ መቃጠሉን ቀድሞ የሚያይ፣ ሌላኛው የተቃጠለው አምፖል እንዲለወጥ የሚቀርበውን ጥያቄ በፊርማው የሚፈቅድ፡፡
ሌሎች አሥራ ሁለት የሚሆኑ የተፈቀደበትን ደብዳቤ እያባዙ ለየክፍሎቻቸው ቅጂ የሚያስቀሩ፡፡ አንድ ደግሞ የተፈቀደበትን ደብዳቤ ለግዢ ክፍሉ የሚያቀርብ፤ ሌላኛው ደግሞ አምፖሉ እንዲገዛ የሚታዘዝበትን ደብዳቤ የሚፈርም፤ እንዲሁ ደግሞ ሌላው ይህንን የትዕዛዝ ደብዳቤ ለሚመለከተው ክፍል የሚያስተላልፍ፤ ደግሞላችሁ የትዕዛዝ ማስፈጸሚያውን ቅጽ የሚሞላና በመጨረሻም የተገዛውን አምፖል ፈርሞ የሚቀበል፡፡
 እናላችሁ...ቢሮክራሲው እንዲህ ግራ የገባው ጥልፍልፎሽ ስለሆነ የትሪፓችሁን ጤንነት ጠብቁ ለማለት ነው፡፡
ለሁላችንም ልቦናውን ይስጠንማ!
ስሙኝማ... ፌይር ወይ ‘ሚዛናዊ’ (ያልተሸቀበ ከስሩ ሚጢጢ ማግኔት ያልተደረገበት ‘ሚዛን’ እስከሆነ ድረስ) የሚባለውን ነገር ለመሆን ያህል...ማለትም “ገና ለገና ብዕሩ ያለው በእነሱ እጅ ስለሆነ የራሳቸውን ጉድ እየሸፈኑ ስለሌላው ብቻ ያወራሉ፣” እንዳይባል ይቺን እዩልኝማ... “አንድ የተቃጠለ አምፖልን ለመለወጥ ምን ያህል ጋዜጠኞች ያስፈልጋሉ?” የሚለውን ለመመለስ ያህል...
ሦስት ያስፈልጋሉ፡፡ አንደኛው አምፖሉ  ቶሎ፣ ቶሎ የሚቃጠልም ቢሆን መንግሥት ብርሀን ለህዝቡ ለማዳረስ የሚያደርገው የማያሰልስ ጥረት ማሳያ መሆኑን አብራርቶ የሚጽፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቀላሉ የሚበላሹ አምፖሎችን በየቦታው በማድረግ መንግሥት ድሀው ህዝብ በጨለማ ውስጥ እንዲኖር ስለማድረጉ ማስረጃ ነው ብሎ የሚጽፍ ነው፡፡ ሦስተኛውና የፈረንጆቹን ከፍተኛ የጋዜጠኝነት ሽልማት ‘ፑሊትዘር ፕራይዝ’ የሚሉትን ሽልማት የሚያገኘው ደግሞ አምፑልን የሚሸጠው የኤሌትሪክ ኩባንያ ሽያጩን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ቅጥር አምፖል ሰባሪዎችን እንዳሰማራ እንደተደረሰበት የሚያብራራ የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ (“የሴራ ትርክት” ማለትም ይቻላል!) የሚያቀርብ፡፡  አሪፍ አይደል!
ስሙኝማ.... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አንዱ ፈረንጅ የጻፈው ነው... ሀያ ዓመት ሲሞላን፣ ዓለም ሁሉ ስለ እኛ የሚያስበው ነገር እንዳለ እናምናለን፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሞላን ዓለም ሁሉ “ስለእኛ ምን እያሰበ ይሆን!” የሚል ስጋት ይወጥረናል፡፡ ስጋት ይገባናል፡፡ አርባ ዓመት ሲሞላን ግን ዓለም ስለእኛ ቅንጣት ያህል እንደማያስብ ይገባናል፡፡
እናማ... ዓለም ስለእኛ ምን እያሰበ ይሆን የምንለው ሁላችንም “አይ ላቭ ኒው ዮርክ” የሚል ባርኔጣና ቲ-ሸርት ስለተደረገ ብቻ አማሪካን ስለእኛ ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ ዓለም ከእነመፈጠራችንም እንደማያውቅ ልብ ማለቱ ሸጋ ይሆናል፡፡
ለሁላችንም ልቦናውን ይስጠንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1598 times