Saturday, 18 February 2023 19:50

ይቅርታ ለሰጭውም ለተቀባዩም ሸክም ያቀላል!

Written by  በአስናቀው አሰፋ
Rate this item
(2 votes)

 “--ይቅር ማለትንም፣ ይቅርታ ማድረግንም እንለማመድ። ይቅርታ መጠየቅን እንደ ሽንፈት አንቁጠረው። ይቅርታ ማድረግን እንደ
አሸናፊነት ቆጥረን፣ ከዚህ በኋላ በቁጥጥሬ ስር ሆነሃል አንበል። ይቅርታ ለሰጭውም ለተቀባዩም ሸክም ያቀላል፡፡ ለመጭው ትውልድ
እንስራ። ችግሮች በሙሉ በኛ ትውልድ ይብቃ እንበል፡፡ መጭው ትውልድ እንዲዘፍንብን ሳይሆን፣ እንዲዘፍንልን እንጣር፡፡ “
        
       ከወራት በፊት ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ ጽሁፍ አነበብኩ፡፡ በኋላ ተቃውሞ ቢደርስበትም ነገርዬው የሚገርም ነው፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው። በደቡብ አፍሪካ በምትገኘው ናሚቢያ፣ ሂምባ የሚባል ጎሳ አለ፡፡ የዚህ ጎሳ እናቶች ከማርገዛቸው በፊት ለሚወልዱት ልጅ ብቻ የሚሆን ሙዚቃ ያቀነባብሩለታል  (እናት ለልጅ ማለት ነው)፡፡ ሙዚቃው ልጁ ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ የግሉ ነው፡፡ ከሌላኛው ድረ ገጽ ያነበብኩት ጽሁፍ፣ ይህ ዓይነት ባህል በሂምባ ማህበረሰብ ውስጥ የለም ቢልም፣ በሌላ አፍሪካ አገር የነበረ ወይም ያለ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ለዚህ ጽሁፍ ዋናው ቁም ነገር ሙዚቃውን የሚጠቀሙበት ጉዳይ ነው፡፡
ልጁ ሲወለድ ሙዚቃው ይዘፈንለታል። በኛ አገር “እልልል!” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ መልካም ተግባር ሲፈጽምም በኩራት ይዘፈንለታል፡፡ ቤተሰቡ ዘመድ አዝማዱ በኩራት “ምድር ቁና ትሁን” ይላሉ፡፡ በህይወት ሲለይም ደረት መምታት ወይም ማንጎራጎር የለም፡፡ ሙዚቃው ግን ሲወለድ እንደተቀበለችው ሲሞት ትሸኘዋለች፡፡ እሷም የመጨረሻዋ ይሆናል፡፡
የሚገርመው ነገር ግን ሙዚቃው ለመቅጫነት ማገልገሉ ነው፡፡ ልጁ/ሰውየው/ሴትየዋ ካጠፋች ሙዚቃው ይዘፈንለታል/ይዘፈንላታል፡፡ ይዘፈንበታል/ይዘፈንባታል ማለቱ ይሻላል፡፡ አንገት ደፍቶ ማዳመጥ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሙዚቃ ማወደሻም መቅጫም መሆኑ አይገርምም?  እንዴት? ዋናው እምነት ነዋ፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት የተሰበከው፤ እጅና እግር ያለው እውነት ሆኗል፡፡ እምነት ደግሞ ከምንም በላይ ነው፡፡ ደግ ነገር ሳትሰራ ደግ አድርገሃል ተብሎ ቢዘፈንልህ እንኳ፣ አትቀበለውም፡፡ ውስጥህ ይናወጣል፣ ይረበሻል።
በአሁን ዘመን የሰው ልጆች የሚለኩት፣ የሚወደሱት ወይም የሚነቀፉት ባላቸው ቁሳዊ ሃብት እየሆነ መጥቷል፡፡ ቁሳዊ ሃብት ግን የመጨረሻውን እርካታ እንደማይሰጥ ከሃብት ማማ ላይ ከደረሱት ሰዎች መማር እንችላለን፡፡ ከአለማችን ከፍተኛ ባለሃብቶች አንዱ የሆኑት አሜሪካዊው አቶ ዋረን ቡፌ፣ ባለፈው ሰኔ ወር በአንድ ጊዜ ብቻ 4 ቢሊዮን ዶላር ለእርዳታ ድርጅቶች ለግሰዋል፡፡ ይህም እስከ አሁን የለገሱትን የገንዘብ  መጠን ወደ 48 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል፡፡ .... ቢሊዮን ነው ያልኩት! ልግስናቸው አስደመማችሁ! የኢትዮጵያ አመታዊ በጀት ስንት ነበር? ብዙዎች ለዚህ ተግባራቸው አክብሮት ቸረዋቸዋል፡፡ እሳቸው ግን ምን እየተሰማቸው ይሆን? እንደ አፍጋኒስታኖች “ከፈን ኪስ የለውም” ብለው ይሆን? ወይንስ የሰበሰብኩት  ገንዘብ  ደስታን ካልገዛልኝ ምን ያደርግልኛል ብለው ይሆን? ... ውስጣቸውን እራሳቸው ያውቁታል፡፡ እኛ ግን “ዘፍነልናቸዋል”፣ እርሳቸው ከፈለጉ “ዘፈኑብኝ” ይበሉ።
አሁን ወደ  ወደ ርእሰ ጉዳዬ የሚያንደረድረኝን ገጠመኝ ላውራችሁ፡፡ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነው ታሪኩ የተፈጸመው፡፡ የምኖረው መገናኛ ነበር፤ መሥሪያ ቤቴ ደግሞ ውሃ ልማት ጀርባ፣ ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ ት/ቤት አካባቢ፡፡ ለመሥሪያ ቤቴም ለቤቴም አማካይ ከነበረው፣  ከጌታሁን በሻህ ህንጻ ላይ ከሚገኘው  ፖስታ ቤት ሳጥን ተከራይቻለሁ፡፡ ሰዓት ካለኝ ጠዋት፣ ከሌለኝ ከቢሮ ስመለስ  ፖስታ ሳጥኔን አይቼ እሄዳለሁ፡፡ አንድ ቀን ወደ ክፍለ ሃገር የሚላክ ጥቅል በኔ በኩል ከውጭ ይላካል፡፡ በነጋታው ጥቅሉን የሚወስድልኝ ሰው ስላገኘሁ፣ በጠዋት ቀደም ብዬ ጥቅሉን ተረክቤ፣ ከስራ ስወጣ ክፍለ ሃገር ለሚወስድልኝ ሰው ለማስረከብ አቀድኩ፡፡
እንዳሰብኩትም በጠዋት ተነስቼ ወደ ፖስታ ቤቱ አመራሁ፡፡  ሁለት ሰዓት ሲሆን ደረስኩ፡፡ እንደ ሁሌው ከፍት ሆኖ አገኘሁት፡፡ እኔም እንደ ልማዴ ሰላምታ አቅርቤ ወደ ሳጥኔ አመራሁ፡፡ ሳጥኔ ውስጥ ጥቅል እንደመጣልኝ የምታሳውቅ ብጣሽ ወረቀት ይዤ ወደ ፖስተኛዋ  (ሰራተኛዋ) ሄድኩና ወረቀቷን አቀበልኳት። የመታወቂያ ኮፒ ስለሚያስፈልግ፣ ኮፒ ለማስደረግ ስወጣ ሁሉም ሱቆች ዝግ ነበሩ፡፡ ተመለስኩና ሁለት መታወቂያ ስላለኝ አንዱን ይዛ ጥቅሉን እንድትሰጠኝ፣ ከዚያም የሌላኛውን ኮፒ ሳመጣላት እንድትመለስልኝ ለመንኳት፡፡ “ከአሰራር ውጭ ስለሆነ አይሆንም” አለችኝ፡፡ ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ ወደ ቢሮዬ  አመራሁ፡፡
ቢሮ ስደርስ ኮፒ የሚያደርጉልን ሰራተኞች ቀድመው ገብተው አገኘሁ፡፡ ደስ አለኝ። ኮፒ አስደርጌ ቦታው ቅርብ ቢሆንም፣ ሰዓት ለመቆጠብ ኮንትራት ታክሲ ይዤ ወደ ፖስታ ቤቱ አመራሁ፡፡ ኮፒውን ለፖስታ ቤቱ ሰራተኛ ስሰጣት የሚሞላ ባዶ ቅጽ ሰጠችኝ። በአጋጣሚ እስክርቢቶዬን ከጃኬቴ ጋር ቢሮ ትቼዋለሁ፡፡ ስለዚህ ሰራተኛዋን እንድታውሰኝ ጠየኳት፡፡  እርሷ ግን  ወይ ፍንክች  ያባ ቢላዋ ልጅ፡፡ አልሰጥም አለች፡፡ “መስሪያ ቤቴ ለኔ እንድጠቀምበት እንጂ ላንተ እንዳውሰህ አልሰጠኝም” አለችኝ፡፡ በጣሙን ተናደድኩ፡፡ “እናንተኮ እስክርቢቶ ለተጠቃሚው ማስቀመጥ ነበረባችሁ” ስላት፣ ይባስ ብላ፤ “እሱን መሥሪያ ቤቱን ጠይቀው” አለችኝ፡፡ በንዴት ጦዤ አካባቢው ከነበሩ ሰዎች ተውሼ፣ ፎርሙን ሞልቼ፣ እቃውን ተረከብኩ፡፡
ከዚያች ቀን በኋላ እረፍት አጣሁ፡፡ ፖስታ ቤት የማደንቀው መሥሪያ ቤት ነበር፡፡ ዘመን አመጣሹ የኤሌክትሮኒክ ግንኙነት ሲፈታተነው፣  አውቶብሶችን ገዝቶ፣ ሌላ አገልግሎት መጀመሩን አደንቅለት ነበር፡፡ የፈጣን መልእክት አገልግሎትም አጠንክሮ የያዘበት ጊዜ ነበር። በእርግጠኝነት ይህ ተግባሩ ብዙ ሰራተኞችን ከመቀነስ አድኗል፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰራተኞች ግን መሥሪያ ቤቱን በማገዝ ፈንታ ተግዳሮት እንደሆኑበት ተሰማኝ፡፡ ስለዚህ ለቅሬታ ሰሚ አቤት ለማለት ወሰንኩ፡፡
በኔ እይታ አብዛኛዎቹ ከተጠቃሚዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የፖስታ ቤት ሰራተኞች ከጡረታ የተመለሱ ወይም ወደ ጡረታ እድሜ የተቃረቡ ነበሩ፡፡ ለኔ ደግሞ እነዚህ “የዶክተሮችና የኢንጅነሮች” እናቶች፣ የልጆቻቸውን እኩዮች በትህትና ማገልገሉ ፈተና ነው የሚሆንባቸው ብዬ እራሴን አሳመንኩት፡፡
... አንድ ጓደኛዬ የምርቃት ድግስ ተጠርቶ “ኢንጂነር ሃብታሙ እንኳን ደስ አለህ!” የሚል ጽሁፍ ግድግዳ ላይ አይቶ እንደተገረመ ነግሮኛል። ነገ ድዷን ስታሰጣ የምትገኘው ሃብትሽ፣ ለጊዜውም ቢሆን “ኢንጅነር” ተብላለች፡፡ ይህችም ሰራተኛ “የኢንጂነር ሃብታሙ” እናት ሆና ታየችኝ፡፡
ዛሬ ስል ነገ ስል፣ ብዙ ጊዜ አለፈ፡፡ ፖስታ ቤቱ አስጠላኝ፡፡ እንደ ድሮው ቶሎ ቶሎ መጎብኘት ትቻለሁ፡፡ ስሄድም ሁሌ የማገኛቸውን ሁለት ሰራተኞች ሰላም ማለት አቁሜያለሁ፡፡ ጀርባዬን ሰጥቼ እገባለሁ፣ ጀርባዬን ሰጥቼ እወጣለሁ፡፡  
ከወራት በኋላ አሁንም ከውጭ የተላከ ጥቅል እንዳለ ተነገረኝ፡፡  የጠላኋትን ሴት ፊት ለፊት ላገኛት ነው፡፡ መታወቂያዬን በሁለት ኮፒ አድርጌያለሁ፡፡ ሁለት እስክሪቢቶ ይዣለሁ፤ አንደኛው ጥቁር ሌላኛው ሰማያዊ የሚጽፉ። ይህ ሁሉ ዝግጅት ምንም ዓይነት ንግግር ሳላደርግ የመጣውን እቃ ተረክቤ ለመሄድ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እላፊ ንግግር ብትናገረኝ፣ “ላስታጥቃት” ታጥቄያለሁ፡፡  
የመታወቂያዬን ሁለት ኮፒዎች ከዋናው ጋር በአንድ ላይ ሰጠኋት፡፡ አንድ ብቻ እንደሚያስፈልግ ነግራ፣ አንደኛውን መለሰችልኝ። ከዚያም ከመታወቂያዬ  ላይ ስሜን እያነበበች ወደ ስራ ባልደረባዋ ዘወር ብላ፤ “ይሄውልሽ፣ አንድ ቀን ተቀይሞብን ሲመጣ ሰላም አይለን ....” አቋረጥኳትና፤ “ጥፋተኛ እኮ ....” ብዬ ንግግሬን ሳልጨርስ ድንገት ከመቀመጫዋ ብድግ ብላ፣ እጇን አጣፍታና በትህትና አንገቷን ደፍታ “ይቅርታ!” አለችኝ፡፡ ... የምገባበት ጠፋኝ፡፡ ሰውነቴ በማላውቀው ሃይል ራደ! ... ዝግጅቴ  ሁሉ ውሃ በላው! ... “እረ ጥፋተኛው እኔ ነኝ!” አልኳት፤ አፌ እንዳመጣልኝ፡፡ ተሸነፍኩ! ለመጀመሪያ ጊዜ በይቅርታ ሃይል ተመታሁ፤ ቆሰልኩ ... በድን ሰውነት!
የፖስታ ቤቱ ሰራተኛ የእናትነት ምክር መከረችኝ፡፡ “ባቄምክ ቁጥር መጀመሪያ እራስህን ነው የምትጎዳው፡፡ ያንድ ቀን ጥፋትስ የፈጣሪ ሰላምታ እንዴት ያስከለክላል?” አለችኝ፡፡ ትክክል ነበረች! የሰው ልጅ እንደ ኮምፒውተር ፕሮግራም አይደረግ፡፡ ከቤት የገጠማት ነገር ሊኖር እንደሚችል፣ ጊዜያዊ የጤና እከል ሊገጠማት እንደሚችልና እነዚህና ተመሳሳይ ጉዳዮች በሥራ ላይ አለመረጋጋትን ሊፈጥሩባት እንደሚችሉ እንዴት አላሰብኩም፡፡ ይህች ሰው የሂምባ አባል ብትሆን ኖሮ፣ “አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ” ይዘፈንላት ነበር።  እኔም በዳንኪራ አቀልጠው ነበር፡፡
ውስጤ በሃሴት ተሞልቷል፡፡ የማደርገውን አሳጥቶኛል፡፡ “ምን ልጋብዛችሁ! ሻይ? ቡና? ማኪያቶ?” ጠየኳቸው፡፡ “ምንም!” አሉ ሁለቱም። “ከጎረቤት ካፌ እልክላችኋለሁ የምትፈልጉትን ንገሩኝ” እያልኩ ብወተውትም፣ እምቢ አሉኝ፡፡ እኔ ደግሞ ዝም ብዬ መሄዱ ከይቅርታው በኋላ ያገኘሁትን ንጽህና ማጉድፍ ስለሆነብኝ፣ ሃያ ብር ጠረጴዛው ላይ ጥዬላቸው ወጣሁ፡፡ ቀኔ ሙሉ ሆነ! ሃያ ብር ብዙም ኢምንትም ነበር፡፡ ብዙ ነበር፤ ምክንያቱም በአንድ ብር አንድ ስኒ ቡና ይገዛ ስለነበር። ኢምንት ነው፤ ምክኒያቱም ምን አልባትም ዋረን ቡፌት ከሃብት ማማ ላይ በመቀመጡ ወይንም ሰዎች አድርገውት የማያውቁትን ልግስና በማድረጉ ከሚሰጠው ደስታ በላይ ያችን ቀን ተደስቻለሁ፤ እስካሁንም አብራኝ አለች፡፡ ካለበለዚያማ ሃያ ብር ሰጠሁ ብሎ ጋዜጣ ላይ መጻፍ መታበይ ነው የሚሆነው፡፡
ቅሬታዬን ለዋናው ፖስታ ቤት ሪፖርት አለማድረጌ ሁሌም ደስታዬን ያበዛልኛል። ለነገር አለመቸኮል፣ ማስተዋል፣ በሌሎች ቦታ ሆኖ ማሰብ፤ .... ብዙ ብዙ ነገር ያች ቀን አስተማረችኝ፡፡ ላደርግ የነበረውን ሁሉ ዘክዝኬ መጻፌ አንድም የጉዳዩን ጭብጥ ለማስያዝ፣ ሁለትም ንስሃ መግባቴ ነው፡፡ በርግጠኝነት ፖስተኛዋም ይቅርታ ስለጠየቀችኝ ሸክም ቀሎላታል፡፡ ይቅርታ ላድራጊውም፡ ለተቀባዩም ሸክም ያቀላል!
አገራችን ውጥረት ላይ ከረመች፡፡ በየወቅቱ የማይነሳ አጀንዳ የለም፡፡ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የገጠሙንን (ያስነሳናቸውን) ችግሮች የሚመረምር መጭው ትውልድ ምን የሚለን ይመስላችኋል? “የቸሸ ዘረኛው ትውልድ” የሚሉን ይመስለኛል፡፡ ሲተርኩም፡ “ከዘመናት በፊት ‘እናቸንፋለን’ የለም ‘እናሸንፋለን’ ነው የሚባለው በሚል እርስ በእርሱ የሚገዳደል ትውልድ ነበር፡፡ ፖለቲከኞች 99% አንድ የሚያደርጋቸው ነገር እያለ በ1% ልዩነታቸው እየተነታረኩ ተጨራረሱ፡፡ ሁሉም ‘ሶሻሊዝም’ ስርዓትን እንከተላለን ቢሉም፣ ‘በቸሸ’ ይጣዛጠዙ ነበር፡፡ በዚህ ‘የቸሸ’ ትውልድ፣ ፈጣሪ በመቆጣቱ ኤድስ የሚባል በሽታ ለቀቀበት፡፡ ኤድስ ሰውንም የአገሪቱንም ሃብት ሙልጭ አድርጎ በላው፡፡ ያ የተረገመ ትውልድ ግን ምንም አልተማረም፡፡ እንዲያውም ባሰበት፡፡ የዘር ዛር ያዘውና ያጓራው ጀመር፡፡ ሰዎቹ አንድ ዐይን፣ አንድ ጆሮና አምስት ምላሶች ስለነበሯቸው፣ አይደማመጡም ነበር፡፡ ትውልዱ መቧደን ስለሚወድ፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጾታ .... ብቻ በተገኘው ሁሉ ሲቧደን ይኖር ነበር፡፡ ፈጣሪ ቁጣው አልበረደም፡፡ ኮቪድ በሚባል መድሃኒት የሌለው በሽታ ደገመው፡፡ ያ ትውልድ ስሙን አድሶ ከ’ቸሸ’ ላይ ‘ዘረኛነት’ ጨምሮበት ‘ቸሸ ዘረኛው ትውልድ’ ሆነ፡፡ ይህ ትውልድ  አብዝቶ የታበየ ስለነበር፣ ሰተት ብሎ መቅደስ ውስጥ ገባ ...” ከዚህ በኋላ ያለው ታሪክ እንዲቀየር ምኞቴ ነው፡፡
ሰሞኑን አብዛኞቻችን ያሳዘነ፣ ተስፋ ያስቆረጠ ነገር ተከስቶ ነበር፡፡ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን ጫማ መለካካት፣ ብዙዎችን እንድንታዘብ አድርጎናል፡፡ አንዳንዶቻችን የተከዳን ያህል ተሰምቶናል፡፡ ሙሉ በሙሉ እምነት የጣልንባቸው ሰዎች ስለተንሸራተቱ ወይም የተንሸራተቱ ስለመሰለን ከልባችን ተጸጽተናል። ጸጸት ደግሞ ያማል፡፡ የሂምባ ጎሳ አባል ቢሆኑ ኖሮ ባደባባይ እናቶቻቸው ያቀናበሩላቸውን ሙዚቃ እንዘፍንባቸው ነበር፡፡
የሰው ልጅ ከስህተት አይጸዳም፡፡ ግን ስህተቱ በንስሃና በይቅርታ ይታጠባል፡፡ ሁለቱ አካላት ቁጭ ብለው ተነጋግረው ነገሮችን መልክ መልክ ማስያዛቸው ትልቅነት ነው። መነጋገር፣ መወያየት፣ ሁከትን ማስወገድ፣ ለሌሎች ጆሮ መስጠትና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን አለማለት የአዋቂ ሰው ተግባር ነው። ይቅር መባባል ለብልህ ሰው የተሰጠ ጸጋ ነው። ለሞኞች አልተሰጣቸውም፡፡ ብልህ ሰው ከሰዎች ይማራል። ከልቤ ልንገራችሁ፣ ይቅርታ ላድራጊውም፡ ለተቀባዩም ሸክም ያቀላል!
ሌላውና ሁሌም የሚገርመኝ ነገር፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተከታዮች ጉዳይ ነው፡፡ በብዙዎች የሃይማኖት መርሆዎች (እምነቶች)፣ ይህች ዓለም የኪራይ ቤት ናት፡፡ የዘለዓለም ቤታችን ከሞት በኋላ የሚመጣው ነው፡፡ የሰማዩን ቤታችንን ምድር ላይ ሆነን ነው የምንሰራው ይላሉ፡፡ በተለይ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ፣ እየሱስ ክርስቶስ ከአሥሩ በጎች አንዱ ቢጠፋበት ሌሎችን ጥሎ የጠፋውን ፍለጋ ሂደ፣ ይላሉ፡፡ ይህን በሰውኛ ስተረጉመው፣ እኔ የአንዱ ሃይማኖት ተከታይ ብሆን፣ ከኔ ሃይማኖት ውጭ ያሉ ሰዎች በሙሉ የጠፉ በጎች ናቸው፡፡ ስለዚህም ለኔ የተሰጠኝን ጸጋ ባለማግኘታቸው  ማዘን፣ የኔን መንገድ እንዲከተሉ መስበክ እንጂ ጥላቻን ምን አመጣው? እንዴት ህልማችን ሁሉ “የጠፋው በግ ድርግም ብሎ ይጥፋ!” ይሆናል?  እንዴት የጠፋውን በግ አንዳንች ሃይል ወርዶ ከሁለት ሲተረክከው ይታየናል? ይሄስ ቢታይ “ህልም እልም” ይባላል እንጂ እንዴት ባደባባይ ይወራል? ይቅርታ መልካም ነውና ይቅር እንባባል፡፡ ካለበለዚያ “እናቶቻችሁ ያወጡላችሁን ሙዚቃ እንሞዝቅባችኋለን” እወቁት፡፡ “ነግ በኔ” በሚል ሃሳብ ሳይሆን የሃይማኖት ትርጉም ጠልቆ ስለገባችሁ የዘር ጦስ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገባ የታገላችሁ፣ ድምጻችሁን ያሰማችሁ  የሌሎች ሃይማኖቶች ምእምናን - ቁጥራችሁን ያብዛልን ብለናል፡፡ ከፈጣሪያችን ጋር የምንቀርበው ሌሎችን እንደ ወንድም እንደ እህት፣  በቀረብነው ልክ ነው።
ይህች አገር የሁላችንም ስለሆነች፣ የሁላችንም ሃሳብ እንዲደመጥ፣ ሁላችንም እንትጋ፡፡ ይቅር ማለትንም፣ ይቅርታ ማድረግንም እንለማመድ። ይቅርታ መጠየቅን እንደ ሽንፈት አንቁጠረው። ይቅርታ ማድረግን እንደ አሸናፊነት ቆጥረን፣ ከዚህ በኋላ በቁጥጥሬ ስር ሆነሃል አንበል። ይቅርታ ለሰጭውም ለተቀባዩም ሸክም ያቀላል። ለመጭው ትውልድ እንስራ። ችግሮቹ በሙሉ በኛ ትውልድ ይብቃ እንበል፡፡ መጭው ትውልድ እንዲዘፍንብን ሳይሆን፣ እንዲዘፍንልን እንጣር፡፡



Read 1354 times