Saturday, 18 February 2023 19:58

ከዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤት ባሻገር…

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(0 votes)

  በባቱረስት አውስትራሊያ በሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ 50 አገራትን በመወከል 453 አትሌቶች ይሳተፋሉ። የዓለም ሻምፒዮናው ከመላው ዓለም  ከ140 በላይ ሚዲያዎች በስፍራው ተገኝተው ይዘግቡታል። ዛሬ የሚካሄዱት አምስት የውድድር መደቦች  በዓለም አቀፍ የቲቪ ስርጭት ከ5 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾችን ያገኛሉ፡፡ በዋናዎቹ ውድድሮችና ሌሎች መርሃ ግብሮች ከ2ሺ በላይ ሯጮችን በሚያሳትፈው ሻምፒዮና ላይ አዘጋጅ ከተማ ድረስ በመገኘት ከ10ሺ በላይ የአትሌቲክስ አፍቃሪዎች ላይ በስፖርት ቱሪዝም በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር በሰራው ጥናት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት አስፈላጊውን የመወዳደርያ ስፍራና የስፖርት መሰረተልማቶች ከማሟላት ባሻገር እስከ 2.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደብን ይጠይቃል፡፡     ከስታድዬም የመግቢያ ትኬቶች፤ ከስፖንሰርሺፕ እና ከሚዲያ መብት በአጠቃላይ ከ 3.07 ሚሊዮን ዶላር በላይ በቀጥታ ገቢ ይሆንበታል።  ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር 45ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ2024 እኤአ በክሮሽያ ሜድውሊንና ፓውላ ከተሞች  እንዲሁም 46ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ2026 እ.ኤ.አ ላይ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ታላሃሴ ከተማ ላይ እንደሚካሄዱ አስታውቋል፡፡
በርካታ አሰልጣኞች በጋራ የሰሩበት የኢትዮጵያ ዝግጅት
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናው የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን በታህሳስ 23 ሱልልታ ላይ በተከናወነው 40ኛው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውጤት ተመርጧል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ተወካይ የሆነው ዮሃንስ እንግዳ ለስፖርት አድማስ በሰጠው ማብራርያ በሱልልታው ውድድር ደረጃ ውስጥ የገቡ አትሌቶች ለዓለም ሻምፒዮናው ብቁ ሆነው ተመልምለዋል፡፡ የሱልልታው አገር አቋራጭ በአምስት የውድድር መደቦች የተካሄደ ነበር። በወጣት ሴቶች 6ኪሜ፤ በወጣት ወንዶች 8ኪሜ፣ በአዋቂ ወንዶች 10ኪሜ፤ በአዋቂ ሴቶች 10 ኪ.ሜ እንዲሁም የሁለቱም ፆታዎች ድብልቅ ሪሌይ 8 ኪ.ሜ ውድድሮች ናቸው፡፡  በሱልልታው የአገር አቋራጭ በየውድድር መደቡ ከ1-6ኛ ደረጃ ያገኙት የሚከተሉት ናቸው። በሴቶች 10 ኪ.ሜ ለተሰንበት ግደይ፣ ጌጤ አለማየሁ፣ መቅደስ አበበ፣ ፅጌ ገ/ሰላማ፣ ፍተዊን ተስፋዬ እና ውዴ ክፍሌ፣ በወንዶች 10 ኪ.ሜ በሪሁ አረጋዊ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ጌታነህ ሞላ፣ ሞገስ ጥዑማይ፣ ጨምዲሴ ደበሌ እና ኃይለማርያም አማረ ናቸው። በወጣት ሴቶች 6 ኪ.ሜ ለምለም ንብረት፣ መልክናት ውዱ፣ ሰናይት ጌታቸው፣ ትነበብ አስረስ፣ ብርቄ ሐየሎም፣ መዲና ኢዮሳ፤ በወጣት ወንዶች 8 ኪ.ሜ ደግሞ በረከት ዘለቀ፣ ቦኪ ድሪባ፣ አቤል በቀለ፣ ይስማው ደሱ፣ ኩማ ግርማና በርከት ነጋ ናቸው።
ለብሄራዊ ቡድኑ የተመለመሉት አትሌቶች ከጥር 23 ጀምሮ ተሰባስበው ኔክሰስ ሆቴል በመግባት መልካም ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም የፅህፈት ቤት ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኞች በሱሉልታው ውድድር ላይ ባሳተፏቸው ውጤታማ አትሌቶች መሰረት ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። የልምምድ መርሐ ግብራቸውን በማውጣት ከ1 ወር በላይ እንደሰሩና አትሌቶች ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውንም የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ተወካይ ገልጿል፡፡
 በትራክ ላይ ከሰሯቸው  ልዮ ስልጠናዎች ባሻገር ወደመስክ በመውጣትም የዓለም ሻምፒዮናውን ካዘጋጀው ከተማ በሚመሳሰል ቦታ በተለይ ጃንሜዳ ላይ ዝግጅት አድርገዋል።   የአየር ንብረቱን ለመቋቋም በሚያስችል ጥናትም ልምምዱን በማካሄድም ትኩረት ተሰጥቷል።  የአውስትራሊያ ባቱረስት ከተማ ሙቀቷ ከአዲስ አበባ ትንሽ ከፍ እንደሚልና አንዳንዴም ተቀራራቢ የአየር ሁኔታ  መኖሩን ፌደሬሽኑ ማገናዘቡንም አቶ ዮሃንስ እንግዳ ይገልፃል፡፡ ስለሆነም ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በሚገኙ ሞቃታማ ስፍራዎች ላይ እንዲሰሩ ነው የተደረገው። ስልጠናው ያለምንም መቆራረጥ በወጣው ፕሮግራም መሰረት መካሄዱን በሁሉም አትሌት በጤና በኩልም ምንም ሁኔታ አለመፈጠሩ ባቱረስት ላይ ጥሩ ውጤት ለመጠበቅ ምክንያት እንደሚሆንም አስረድቷል።
እንደፅህፈት ቤት ተወካዩ ገለፃ ለዓለም ሻምፒዮናው የተመረጡት አሰልጣኞች በክለብና በክልል ደረጃ የሚሰሩ ናቸው፡፡ ለዓለም ሻምፒዮናው ባስመረጧቸው አትሌቶች ብዛት ሀላፊነት ተሰጧቸዋል፡፡ በስራቸው ያሉ የሚያውቋቸውን አትሌቶች ይዘው በብቃት እንደሚሰሩ ታምኖበታል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች የድብልቅ ሪሌይ ላይ የተመረጡት አትሌቶች በአመዛኙ የመካከለኛ ርቀት ሯጮች በመሆናቸው ጥሩ ልምድ ያላቸው የመካከለኛ ርቀት አሰልጣኞች ተመድበዋል፡፡  በአጠቃላይ ለቡድኑ በብቸኛነት ሃላፊ ሆኖ የተመደበ ዋና አሰልጣኝ የለም፡፡ ሁሉንም አሰልጣኞች አስተባብሮ የሰራው  የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑበ የቴክኒክ ኮሚቴ ነው፡፡ ቴክኒክ ኮሚቴው ሲሆን አጠቃላይ ስልጠናውን በበላይነት ሲመራ በስሩ የሚገኙት የስልጠናና የውድድር ክፍሎች እገዛ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚም በስልጠና ቦታዎችና በሆቴል በመገኘት  ቅርብ ክትትል ማድረጉን የጠቀሰው ዮሐንስ እንግዳ  የአትሌቶች አመጋገብ፤ የቡድን መንፈስና አጠቃላይ ቆይታ በሚያረካ መንገድ መሠራቱን አስረድቷል።  የጤና ባለሙያዎችና የማሳጅ ቴራፒስቶች ተሟልተው በመመደብ ጤንነታቸውን በየጊዜው ክትትል እያደረጉላቸው ለዓለም ሻምፒዮናው ደርሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች  በዓለም አትሌቲክስ አመራር ወይም አምባሳደር ለምን አይሆኑም?
ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ስትሳተፍ ዘንድሮ ለ36ኛ ጊዜ ነው፡፡ ባለፉት 35 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች የኢትዮጵያ ቡድን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል። የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የስታትስቲክስ መፅሐፍ እንደሚያለክተው ኢትዮጵያ ባለፉት 35 የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች 275 ሜዳልያዎች (105 የወርቅ፣ 108 የብርና 62 የነሐስ) አግኝታለች። 4ኛ ደረጃ 40፣ 5ኛ ደረጃ 39፣ 6ኛ ደረጃ 45፣ 7ኛ ደረጃ 36 እና 8ኛ ደረጃ 40 ጊዜ ተመዝግቧል።  ይህም በ2571 ነጥብ በከፍተኛ ውጤት ኢትዮጵያን ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።  በየሻምፒዮናው ከ1-3 ባለው ደረጃ በመጨረስ ስኬታማ መሆኑን ፌደሬሽኑን አንደጥንካሬ ይመለከተዋል፡፡ በሻምፒዮናው ታሪክ በአጠቃላይ የሜዳልያ ስብስብ ከኬንያ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምንገኝ እናውቃለን የሚለው ዮሃንስ እንግዳ በዓለም አትሌቲክስ ላይ ኬንያን የምንበልጠው በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የቤት ውስጥ ውድድር ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከፍተኛ  ውጤት ያስመዘገቡ ቢሆንም ስፖርቱን በሚያስተዳድኗ የተለያዩ የአመራርነት ሃላፊነቶች በሚገኝባቸው ተቋማት ያላቸው ውክልና የሚያረካ አይደለም። የኢትዮጵያ አትሌቶች ይህን በማከናወን ያላቸውም ፍላጎት የተዳከመ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማህበር በሚከተለው አሰራር ምናልባት ውጤታማነትን እንደዋና መስፈርት ላይከተለው ይችላል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በኃላፊነትና በአምባሳደርነት የሚሾሙ አትሌቶች  በልዩ ልዩ መስፈርቶችን ሊመረጡ ይችላሉ። በኢትዮጲያ አትሌቲክስ በእነዚህ ዓለም አቀፍ ኃላፊነቶች በመንቀሳቀስ ደረጃ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የላቀ እና ታሪካዊ ውጤት ያስመዘገቡ የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በተለያዩ የሃላፊነት ድርሻዎች ለሚያገለግሉባቸው ስራዎችትኩረት አልሰጡም፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  ኢትዮጵያ አትሌቶች በቡድንም በግልም የተሻለ ውጤት አላቸው የሚለው ዮሃንስ እንግዳ፤ እነ ቀነኒሳ፤ እነ ወርቅነሽ እነ ደራረቱ እነ ገ/እግዚአብሔር እና ጥሩነሽ በርካታ የሜዳልያ  በውጤታቸው ልክ ራሳቸው ማስተዋወቅ ይቀራቸዋል፡፡ እንደዮሃንስ እምነት የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋና ትኩረታቸው ሩጫው ላይ ነው፡፡ ከሩጫው ባሻገር ባሉት በስፖንሰርሺፕ፤ ትምህርት እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ብዥታ አላዳበሩም። ስለዚህ በዓለም አትሌቲክስ ላይ በአመራር ደረጃና በስም ባሳደጉት ጉልህ ሚና ለመጫወት የሚችሉበት እድል አልተጠቀሙበትም።
ወደፊት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ስለማዘጋጀት
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ማዘጋጀት ብትችል በአትሌቲክስ ዙሪያ ያለን ባለድርሻ አካላት አንጠላውም ይላል ዮሃንስ እንግዳ፡፡ ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ  ግን የፌዴሬሽኑ ፍላጎት  አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማዘጋጀት የመንግስት ፍላጎት  ሲሆን ነው ሊሳካ የሚችለው። የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማህበር ኢትዮጵያ ውድድር እንድታዘጋጅ ዕድሉን የሚሰጣት መንግስት ይህን ዕድል ለመጠቀም ኃላፊነቱን ተቀብሎ የሚሰራ ከሆነ ነው፡፡
ብዙዎቹ አገራት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማዘጋጀት የቻሉት በፌዴሬሽን ፍላጎት ብቻ አይደለም፤ የአገራቱ መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮች ሙሉ ኃላፊነቱን ወስደው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የአለም አቀፍ ውድድር አዘጋጅ ፌዴሬሽኑ ሊሆን ቢችልም በጀቱን መሰረተ ልማቱንም በመንግስት ሊያሟላ ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ተወካይ ዮሃንስ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዞናዊና አህጉራዊ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በማዘጋጀት የነበረውን ልምድ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። 6ኛውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ውስጥ 12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በተሳካ ሁኔታ መስተናገዳቸውን በማስታወስም በእነዚህ አህጉራዊ ውድድሮች አዘጋጅነቱን ፌዴሬሽኑ የመራው ቢሆንም በዋናነት መስተንግዶው ስኬታማ ያደረገው መንግስት ትኩረት መሆኑን ያብራራል፡፡ ስለዚህም ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ በአጠቃላይ የመንግስት ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ትልቁ ተግዳሮት መሰረተ ልማት ነው። የአገር አቋራጭና የጎዳና ላይ ውድድሮችን ለማዘጋጀት አያስቸግር ይሆናል፡፡ ከትራክ ጋር የሚያያዙ ውድድሮችን ለማድረግ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም በቂ መሰረተ ልማት የለንም፡፡  
እንኳን የዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ይቅርና የአገር ውስጥ ውድድሮችን ለማካሄድ በቂ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሉም፡፡  የውድድር ስታድየም ብቻ ሳይሆን በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ የለም፡፡ አትሌቶቻችን በተሰጦአቸው ያሸንፋሉ፡፡ በስፖርት መሰረተ ልማትና በቲክኖሎጂ የተጠናከረ ስልጠና ቢኖራቸው ውጤታቸው የላቀ ሊሆን ይችላል፡፡
የስፖርት መሰረተ ልማትን በማስፋፋት አሁንም ስለፌዴሬሽኑና ከአትሌቶች ባሻገር ዋናው ድርሻና ኃላፊነት የመንግስት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓም አትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች አገር ብትሆንም አዲስ አበባ ላይ እንኳን ለስፖርቱ የሚሆን የውድድር ስታድዬም ወይም ማዘውተሪያ ቦታ የለም፡፡ ምናልባት በሆቴልና በትራንስፖርት ያሉ መሰረተ ልማቶች ብቁ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በአትሌቲክስ ግን የውድድሩ ስታድየም  መሰረተ ልማት የለም፡፡ ከስፖርት መሰረተ ልማቶች ባሻገር ሌላው ፈተና የፋይናንስ አቅም ነው፡፡ ትላልቅ ሻምፒዮናዎችን ለማዘጋጀት መንግስት አቅም ያስፈልገዋል፡፡  ዓለም አቀፍ ውድድር ለማዘጋጀት በፌዴሬሽን በኩል የሚታሰብ አይደለም ገና ብዙ ይቀራል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት ብዙ ጠቀሜታዎችን ይኖሩታል፡፡ የአገር ገፅታ መገንባት ይቻላል። አትሌቲክስ ስፖርቱን ወደተሻ የዕድገት ደረጃ ይወስዳል። በዓለማቀፍ ውድድሮች መስተንግዶ ስፖርት መሰረተ ልቶችን ከማስፋፋት በላይ ለትውልድ የሚሆኑ የቴክኖሎጂ የዕውቀት ሽግግሮች ይገኛሉ፡፡  

Read 673 times