Saturday, 18 February 2023 20:01

ያልታወሱ አስታዋሾች - “ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የኢሞ ግሩፕ”

Written by  ጸጋዬ ደሳለኝ
Rate this item
(3 votes)

 “--ይሄን መሰል ሌሎች ሥራዎችም በብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የimo group ተከናውኗል። የማይተዋወቁ በአካል ያልተያዩ ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያን እንዲህ ለበጎ ነገር መጠቀም ችለዋል። ከአካል መቀራረብ ይልቅ የሀሳብ መቀራረባቸው የአላማ አንድነት እንዲላበሱ አድርጓቸዋል። --”
    
      እ.ኤ.አ በ2022 የወጣ መረጃ፣ የዓለም ህዝብ ቁጥር 7.91 ቢሊየን መድረሱን  ይጠቁማል። እዚህ መጠን ላይ ኢትዮጵያ 119.3 ሚሊየን ህዝብ አዋጥታለች። ይሄም በ2021 ከነበረው ግምታዊ አሀዝ በ 2.5% ብልጫ ያለው ነው። ከዚህ ውስጥም 22.7% ከተሜ እንደሆነ ይነገራል። ዕድሜያቸው ከ 18-34 የሚሆኑት 30% ይሸፍናሉ።
25% የሚሆነው ህዝቧ ኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆነባት ኢትዮጵያ፤ 5.3% የሆኑት ማህበራዊ ሚዲያን ይጠቀማሉ። የፌስቡክ (facebook) ተጠቃሚው አብላጫውን ቁጥር ይይዛል።  ኢንስታግራም ፣ ሜሴንጀር፣ ሊነክዲን እና ትዊተር በቅደም ተከተል ከፍተኛውን ቁጥር ይሸፍናሉ። ይሁንና ... እንደ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም እና ኢሞ ያሉትም ጥቂት የማይባል ተጠቃሚ አፍርተዋል።
ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን  በርከት ያለ ህዝብ የሚገለገልባቸው ከመሆናቸው አንፃር በርካታ ጥቅምና ጉዳት እንዳላቸው ይጠቀሳል። እነዚህን መገልገያዎች ተጠቅሞ ለፈጠራ ስራ የሚተጋ እንዳለ ሁሉ ለጥፋት የሚሯሯጠውም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ቁጥሩ ቀላል የሚባል አይደለም።
አቶ እዮብ ውብነህ በ ነሐሴ 2 ቀን 2012 “የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በአዲስ ማለዳ ይዘውት በወጡት መጣጥፍ፤ “በኢትዮጵያ እየታየ ከሚገኘው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለጠፉ ሐሳቦች ጥላቻ አዘል፣ ግለሰብን ወይንም ቡድንን በብሔር እና በሃይማኖት የሚፈርጁና ብጥብጥ እና ሁከትን የሚሰብኩ ናቸው። ሐሰተኛ መረጃዎችም እንደዛው።” ይሉናል።
በአገራችን ከተፈጠሩ ክስተቶች እማኝ በመጥራት የአቶ እዮብ ውብነህ  የመደምደሚያ ሀሳብን ማመሳከር እንችላለን። በ ኮቪድ 19 ምክንያት መራራቅ ግድ በሆነበት ዘመን ተማሪዎችን በያሉበት ሆነው ከእውቀት ለማገናኘት ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ እድል እና ጥንካሬ ሆነውት ነበር። ወዲህ ደግሞ የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሄራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር በኩረጃ ምክንያት በአያሌው ሲቸገር አስተውለናል።
ትዊተር (Twitter) እና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም  ስለ ህዳሴ ግድቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተሰርቶ ዐይተናል። ግጭትና እልቂትን የሚቀሰቅሱ  አንቂ (activist) ነን ባዮችም ገጥመውናል።
በዘመነ ኮቪድ 19 ንክኪ እና መቀራረብ እርም ሲባል፤ አካላዊ መራራቅን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት የተሞከረው ምስጋና ይግባቸውና በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል ነበር። የፖለቲካን ትኩሳት ተከትሎ ሰው ከሰው በማራራቅና በማለያየቱም ቢሆን አይታማም።
ይሄም ፅሁፍ ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ምግባር ከተጠቀሙ ትጉሀን መሀከል አንዱን ለማስተዋወቅ ይሞክራል። መልካም ንባብ።
አሁን የምወስዳችሁ ወደ Imo መንደር ነው። ከማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን መካከል አንዱ ወደሆነው።
ባንግላዴሽ፣ ሲንጋፖርና ኢራን ከፍተኛ የImo ተጠቃሚ ሀገሮች ሲሆኑ የዋና መስሪያ ቤቱ መቀመጫ የሆነችው አሜሪካ በ4ተኛ ደረጃ ትከተላለች። ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንም የሚውሉበት ስፍራ ነው። በዚህ የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን በኩል መልከ ብዙ፣ ፈርጀ ብዙ ስብስቦች የየግላቸውን ደሴት መስርተው ይኖሩበታል።
እንደ ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ ሁሉ፣ በimo መንደርም እኩይና ሰናይ ማንነትን የተላበሱ ቡድኖች መፈጠራቸው አልቀረም። ሁሉን ትተን ወደ አንዱ የ imo ደሴት እናምራ። “ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የimo group” ይሰኛሉ። የበጎ አድራጎት ስራን በዋነኛነት ይሰራል። ከተመሰረተ 10 ወራት ብቻ ያስቆጠረው ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ፤ 10 የበጎ አድራጎት ስራዎችን ሰርቷል። ጥቂቶቹን እንዘረዝራለን። በነገራችን ላይ...
ታሪክ ቀመስ መረጃዎች እንደሚጠቁሙን ከሆነ፤ “በጎ አድራጎት” ይሉት ቃል የተፈጠረው በ363 ዓመት፣ በሮማ ግዛት ንጉሠ ነገስት፣ በፍላቪዮ ክላውዲዮ ጁሊያኖ ነበር። ከዚያን ግዜ ጀምሮ ቃሉን ብንጠቀመውም፣ በጎ ምግባር ግን የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ማንነቱ ነው። የጥንት እብራዊያን ምስኪኖችን የሚረዱበት “Tithe” የሚባል የታክስ አከፋፈል ስርአት ነበራቸው። የሚሰበሰበው የታክስ ገቢ ድሆችን ለመደገፍ ይውል ነበር።
እማሆይ ትሬዛ፣ ካርል ሀይንስ፣ ካትሪን ሀምሊን፣ አበበች ጎበና እና ቢኒያም በለጠን ማንሳት እንችላለን። ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ለበጎ አድራጎት ስራ ያዋሉ ናቸው። እንደዚህ አይነት ሰዎች  Philanthropist ይባላሉ። እኛስ? “እምዬ” እንበላቸው ይሆን?
ወደ “ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የimo group”ልመልሳችሁ። መስራቹ በimo ስማቸው Mack ይባላሉ። አቶ ምህረተዓብ ጌታቸው። የሚኖሩት በሀገረ እስራኤል ነው።
የመሐል ካዛንቺስ ሰው ናቸው። በተለያዩ ሀገራት በስደት ሲኖሩ 17 ዓመት አስቆጥረዋል። ከ 10 ወር በፊት ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ ብለው የimo group ሲመሰርቱ፣ ጥቂት ልበ ቀናዎች ተከትለዋቸዋል። አሁን ላይ ከ4000 በላይ ተከታዮችን  አፍርተዋል።
አቶ ምህረተአብ ጌታቸው (Mack) እንዴት ይሄንን ሰናይ ተግባር ማድረግ እንደፈለጉ ሲያስረዱም፤ “ከአካል መቀራረብ ይልቅ የልብ መቀራረብ... ለልብ ይደርሳል፤ ካንጀት ጠብ ይላል” ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ ተደራሽነቱ ለማን ነው? የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው ሲመልሱ… “አያ ችግር ሆዬ  ጾታ፣ ብሄር፣  ሀይማኖትና እድሜ ብሎ አይመርጥም። ለቸገረው ሁሉ መድረስ ብንችል ደስ ይለናል። ጋሽ ስብሀት ‘ጊዜን እንቅደመው’ እንዳለ ሁሉ፣ እኛም ጊዜን እየቀደምን ለተቸገሩ መድረስ ህልማችን ነው” ነበር ያሉት።
አንድ ብለው በብሩህ ተስፋ የተሰሩ ስራዎችን ሲዘረዝሩም...
* አንዲት ዐይኗ አካባቢ ፍየል ወግቷት በህክምና የተሰፋላት ሴት በህገወጥ መንገድ ሳውዲ አረቢያ ገብታ ትኖራለች። ይቺ ሴት የተሰጣት ህክምና አልጠቀማት ኖሮ እያደር ትሰቃያለች። በቃኝ አትል አትወጣ ነገር ፤ አገባቧ ወንጀል ለበስ ነው። ችላ አትኖር ነገር ፤ ህመም አሰቃያት።” ካገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ ፤ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ”ን እያዜመች ስትኖር ፣ ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብን በ imo ትተዋወቃለች።  ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብም በጎ ልብ ያላቸው አባላቱን አሰባስቦ፣ ኤምባሲ አካባቢ ያሉ ሰዎችን አስተባብሮ፣ ኢትዮጵያ እንድትገባ እና ለህክምና እንድትበቃ አደረገ።
* እስኪ ደግሞ መካነ ሰላም አካባቢ እንጓዝ። ገጠራማው ስፍራ ይኖሩ የነበሩ ቤተሰቦች ዘንድ እናምራ። አንድ አዛውን አባት ናቸው። ሴት ልጃቸውን ለአንድ ወጣት ይድራሉ። የተጋቡት ጥንዶች በፍቅር እየኖሩ አንድ ልጅ ይወልዳሉ። አዛውንቱም አያት ሆነው ደስታ ይጎናፀፋሉ። ውሎ አድሮ የሴት ልጃቸው ባል በድንገት በተነሳ ጠብ የሚስቱን ወንድም ይገድላል። ሟች የአዛውንቱ የበኸር ልጅ ነበርና አባት ሆዬ ገዳዩን የሴት ልጃቸውን ባል ሊገድሉ ይነሳሉ። አያት ያደረገቸው የሴት ልጃቸው ባል ወንዝ ተሻግሮ፣ አገር ጥሎ ይጠፋል። አዛውንቱም አጠገባቸው ያለው እና አያት የሆኑበት የገዳይ ህፃን አይናቸው ይገባል። አይገድሉት ነገር የልጅ ልጃቸው፣ አይተዉት ደሞ የገዳይ ልጅ ይሆንባቸዋል። እርቅ እንዲያወርዱ ባገር ሽማግሌ፣ በንስሀ አባት ተመከሩ። ቂማቸው አልጠፋ፣ ንዴታቸው አልከስም፣ ቁጣቸውም አልበርድ ይላል።  
የዚህን ቤተሰብ መበጥበጥ የሰማው ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ፤ “የእርቅ መአድ” በተሰኘው የimo መሰናዶ ላይ አዛውንቱን ጋብዞ ያናግራል። በፈጣሪ እርዳታ፣ በልባም አባላቱ ጥረት እርቅ እንዲፈፀም፣ ሰላም እንዲወርድ ይጥራል። ልፋቱ ፍሬ አላጣም። እንዳይገድሉት የእድሜው ለጋነት አሳስቷቸው ከፍ እስኪል የሚጠብቁትን የልጃቸውን ልጅ፤ “ልጄ” ብለው ተቀበሉ። ለብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብም እልል በቅምጤ የሚያሰኝ የማይዘነጋ ተግባር ሆኖ አለፈ።
* እስኪ ወደ ድሬዳዋ ልውሰዳችሁ። ጥንታዊቷ የንግድና የኢንዱስትሪ ከተማ። በዚህ መንደር አንድ የ96 ዓመት አዛውንት ይኖራሉ። እድሜ አካላቸውን፣ ጎጇቸውን አቅም አሳጥቷል። ድህነት ሰቅዞ ይዟቸዋል። ባለቤታቸው ካረፉ ጀምሮ አጉራሽ አልባሽ የሆናቸው የጎረቤት እጅ ነበር። ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ ከአባላቱ እና ከልበ ቀናዎች አሰባስቦ ባገኘው ብር ቤታቸውን አፍርሶ በአዲስ መልክ ገነባ። ጎረቤቱም እልል አለ። የከተማዋ ባለስልጣናትም ተደሰቱ። ተደስተውም የምስክር ወረቀት አበረከቱ። እድሜ ጠገቡ አዛውንትም መረቁ። “ካንጀት ካለቀሱ እምባ አይገድም”  እንዲሉ ፣ በየወሩ ቀለብ የሚሰፍርላቸው የብሩህ ተስፋ አባል ከወደ ካናዳ ተገኘ።
* ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ እንምጣ። በቀናት ልዩነት ወደ ሌላ የቤት ጉዳይ እናምራ። ኮዬ አካባቢ የሚኖሩ ሁለት ህፃናት ዘንድ። ወንድምና እህት ናቸው። አባታቸውን በልጅነታቸው አጥተዋል። ብሩህ ተስፋ ሲያገኛቸው እናታቸው ካረፈች አንድ ወሯ ነበር። የ19 እና የ 20 ዓመት ልጆች የሆኑት ሁለቱ ወንድምና እህት፤ ውሏቸው በጠበል ስም ገዳም ለገዳም ሆኗል። የሚላስ የሚቀመስ ከቤታቸው መጥፋቱ፣ አለሁ የሚል ዘመድ ማጣት ጋር ተዛምዶ አስመንኗቸዋል። ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የ imo group  አፈላልጎ ሲያገኛቸው “ ቸገረን”  ያሉትን ተናገሩ። እናቷ ክንዷ ላይ እያለች በደረቅ ለሊት ያረፈችባት የ20 ዓመቷ ታዳጊ እምባ እየቀደማት ታስረዳለች።
የሚኖሩበት የኮንዶሚኒየም ቤት የባንክ እዳ እንዳለበትና በየወሩ 800 ብር መክፈል እንዳለባቸው ተናገረች። ብሩህ ተስፋም የቤቱን ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ፈፀመላቸው። ለእናቷ መድሀኒት መግዣ በማጣት ያቋረጠችውን የኮሌጅ ትምህርት፣ ብሩህ ተስፋ በየወሩ እየሸፈነ ዳግም ቀጠለች። ወንድሟም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን ወሰደ። በየወሩም ቀለባቸውን የምትሸፍን የብሩህ ተስፋ አባል፣ ደግ እህት ተገኘች።
* የብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ አባላት በክረምት፣ በደረቅ ለሊት ጎዳና ላይ ለተኙ ሰዎች ብርድ ልብስ ለግሰው ከጉለሌ ክ/ከ ወረዳ 6 የምስክር ወረቀት አግኝተዋል። ለመቄዶንያ የአረጋውያን ማህበር 100,000 ብር ለግሰው ከክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ እጅ የምስጋና ደብዳቤ ተቸሯቸዋል። የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሂሩት ካሳው በተገኙበት የስዕል አውደ ርዕይ ላይ  ለበጎ አድራጎት ስራቸው እውቅና እንዲሆን ከሰዓሊ ራስ በረከት አንዳርጌ የምስክር ወረቀት ተረክበዋል። በቅርቡ ወደ ሀላባ ሄደው ለአንድ አዛውንትና ለአንዲት ማየት ለተሳናት የሁለት ሴት ልጆች እናት፣ ከሀላባ ቁሊቶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በተረከበው መሬት ላይ 2 ቤት ገንብቶ አረስክቧል።  የሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት እና ከከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት 2 የእውቅና ሰርተፍኬቶች ተበርክቶለታል።
የሀላባውን በተለየ እናውሳ። ከሁለቱ የቤት እድለኞች መሀከል የሴቷን። ሁለት ሴት ልጆች አሏት። የ7 እና የ9 ዓመት እድሜ አላቸው። “ጎዳና ነው ቤቴን “እየዘፈነች ትኖር ነበር። አንድ ቀን ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ ያገኛታል። ምን ቸገረሽ ሲሏት፤ “ጎዳና ላይ ልጆቼን ቢወስዱብኝ ማንን እጠይቃለሁ፣ ምን አንስቼ ምን አሸታለሁ” ብላ መለሰች። ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የimo group ከከተማ መስተዳደሩ መሬት ተረክቦ፣ ቤት ሰርቶ አስረከባት። ዛሬ እፎይ ብላ ተኝታ ታድራለች። ውላ ቤቷ ትገባለች።   
* ወደ ሀረር እንጓዝ። ከሰው ቤት- ሰው ቤት እየተንከራተተች፣ እንጀራ እየጋገረች፣ ልብስ እያጠበች ትኖር የነበረችን ሴት እናገኛለን። የአንድ ልጅ እናት ነች። የራሷን ችግር በጉያዋ ደብቃ ብሩህ ተስፋ በሚሰራቸው የእርዳታ ስራዎች ላይ ተሳትፋለች። ከሌላት ላይ ሰጥታ እረድታለች። ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የኢሞ ግሩፕ ችግሯን ይደርስበታል። ከአባላቶቹና ከመልካም ልብ ባለቤቶች ባሰባሰበው 150,000 ብር ምግብ ቤት ከፍቶ ንግድ ያስጀምራታል። ዛሬ ተረጂዋ ሴት ከራሷ ተርፋ ለሰዎች ደርሳለች። እንባዋ ታብሶ ስቃ ታስቃለች።
* ደሞ ሌላ ጉዳይ እናንሳ። ከወደ ደሴ ለ6 ዓመት አልጋ ላይ የተኛን አንድ ወጣት እናገኛለን። ለሰርግ ብሎ ወጥቶ የመኪና አደጋ የደረሰበትን ወጣት፣ ብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የimo group ከ2,000,000 ብር በላይ አሰባስቦ በዚህ ወቅት የወጣቱንና የሁለት ቤተሰቡን የትኬት ወጪ ሸፍኖ ታይላንድ ድረስ ልኮ እያሳከመው ይገኛል።
ይሄን መሰል ሌሎች ሥራዎችም በብሩህ ተስፋ የመልካሞች ስብስብ የimo group ተከናውኗል። የማይተዋወቁ በአካል ያልተያዩ ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያን እንዲህ ለበጎ ነገር መጠቀም ችለዋል። ከአካል መቀራረብ ይልቅ የሀሳብ መቀራረባቸው የአላማ አንድነት እንዲላበሱ አድርጓቸዋል።
የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዳቸው ደረቅ አይደለም። ሳቅ ጨዋታን፣ ግጥም ዜማን የተንተራሰ ነው። በአንድ ወቅት ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ) እና ሙዚቀኛ እዮብ በላይን እንግዳ አድርገው ጋብዘው፣ በአንድ ምሽት ከ 100,000 ብር በላይ አሰባስበው ለበጎ አድራጎት ስራ አውለዋል። የሙዚቃ አቀናባሪው ጊልዶ ካሳ፣ ሙዚቀኛ ሳንቾ እና ሌሎች ጓደኞቻቸው የብሩህ ተስፋ አላማ ማርኳቸው፣ የአቅማቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። የብሬ ማን ፕሮዳክሽን ባለቤት ብርሃኔ ጌታቸውም፣ የብሩህ ተስፋ የበጎ አድራጎት ስራን በተደጋጋሚ አግዟል። ይሄ ሁሉ የሆነው በአካል ተገናኝተው አይደለም። ዓለም ላይ ተበትነው፣ በአካል ሳይሆን በመልካምነት መንፈስ ተቀራርበው እንጂ።
ጥያቄና መልስ፣ ድንቅ ዓለም፣ እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት እና ሌሎችም መርሐግብሮች ሳምንቱን ጠብቀው ይከናወናሉ። የሙዚቀኞች የተሰጥዖ ውድድርም ያደርጋሉ። ይሄ ሁሉ የሚሆነው በኢሞ መተግበሪያ ነው።
አንዳንዴ በዋልድባም ይጨፈራል። ከእህል ዘር መሀልም ምርጥ ዘር ይገኛል። ከእሾህ መሀል ደግሞ አበባ። ጥፋት እና ቅጥፈት፣ ጩኸት እና ሁከት ከሞላው የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን መንደር ደግሞ የምስራች የሚሆን ነገር አይጠፋም።
የማኅበራዊ ድረ ገጽ ትስስርን  ከአመፅ ይልቅ ለመማማሪያ፣ ከጥፋት ይልቅ ለበጎ አላማ ማዋል እንደሚቻል ምሳሌ የሚሆን ስራ ነው። ለብዙዎቻችንም መነቃቃትን እንደሚፈጥር እሙን ነው፡፡  Read 2060 times