Saturday, 18 February 2023 20:11

ትምህርትን ያራቆቱ “የተማሪ ተኮር” ፍልስፍና ፈሊጦች።

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የንባብ ትምህርት፣ “ፊደል” በማሳወቅ መጀመር የለበትም የሚል ፈሊጥ፣… የተማሪ ተኮር ቅኝት ምልክት ነው። ለቃላትና ለዓረፍተነገር ቅድሚያ እሰጣለሁ ብሎ የሚያስተምር ከሆነ፣ ተማሪዎችን ለመሃይምነት መዳረጉ እንዴት ይገርማል?
እውቀትን ያንቋሽሻል። ማወቅ ከመሸምደድ አይለይም በማለት ማጥላላት፣ … የተማሪ ተኮር ቅኝት አንድ ባህሪ ነው።
የመመሪያ መፃሕፍትንም ማራቆት ሌላው ፈሊጥ ነው። የመልመጃ ጥያቄና የቤት ስራ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል፣…ተማሪዎችን ያጨናንቃል፤… በማለት ለቡድን ስራና ለቡድን ውይይት ቅድሚያ መሰጠት አለበት እያሉ መቀባጠርም፣… የተማሪ-ተኮር ቅኝት ፈሊጥ ነው።
ተማሪና አስተማሪ እኩል ናቸው የሚል ፈሊጥም ይጨምርበታል። ትምህርት በተማሪዎች አምሮት እንጂ፣ በትክክለኛ ስርዓተ ትምህርት በጥንቃቄ መመራት የለበትም ይላል- ተማሪ-ተኮር የሚሉት ፈሊጥ።
እናስ? ከ90 በመቶ በላይ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች፣ አጭር ዓረፍተነገር አንብበው መገንዘብ የማይችሉ ሆነዋል። 12ኛ ክፍል ላይ ሲደርሱም፣ ከ1000 ተማሪዎች መካከል 33 ብቻ የማለፊያ ነጥብ ያገኛሉ።
ኢትዮጵያ በመላው ዓለም “ተማሪ-ተኮር” የተሰኘውን ፈሊጥ በማስፋፋት ተጠቃሽ እንደሆነች ተዘግቧል። ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች የበዙባት አገርም ሆናለች። ዘኢኮኖሚስት ባወጣው ዘገባ ውስጥ የታተመውን መረጃ ተመልከቱ።
የ6 ዓመት ልጆች፣ በወጉ የማንበብ ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል። ከዘገየም በ7 ዓመታቸው። ተማሪ- ተኮር የተሰኘው ፍልስፍና በተስፋፋባቸው አገራትስ? ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ከ10 ዓመት ልጆች መካከል ዘጠና በመቶ ያህሉ ማንበብ አይችሉም ይላሉ- የዓለም ባንክ ጥናት። ባለፉት ሦስት ዓመታት የተገኙ ውጤቶች ናቸው መረጃዎቹ።

Read 727 times