Saturday, 18 February 2023 19:56

የእውቀት ልምሻ የመጣው ከየት ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ዘኢኮኖሚስት መፅሔት ያወጣው ሰፊ ዘገባ፣ ከአዲስ አድማስ ዘገባዎች ጋር ይመሳሰላል፡፡
                    
          “ተማሪ-ተኮር”፣ “ተማሪ-መር” ተሰኘው የትምህርት ፍልስፍና ጠማማ ነው? የአገራችን ትምህርት የተራቆተው፣ ማንበብና መጻፍ፣ መደመርና ማባዛት ለተማሪዎች እንቆቅልሽ የሆነባቸው በዚህ ምክንያት ነው? በአዲስ አድማስ የወጣው ዘገባ እንደዚያ ይላል።
የዘኢኮኖሚስት ሕትመት ከሳንምት በፊት ያሰራጨው ዓለማቀፋዊ ዘገባስ ምን ይላል? ከኢትዮጵያ እስከ ቤኒን፣ ከኬንያ እስከ ናይጀሪያ፣ ዓለማችንን ከሚመሩ ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች እስከ ዓለም ባንክ ድረስ፣ ብዙ ጥናቶችንና መረጃዎችን የዳሰሰ ነው- የመጽሔት ዘገባ። እናስ ምን ይላል?
“ተማሪ-ተኮር” የተሰኘው የትምህርት አሰጣጥ ቅኝት በኢትዮጵያ መስፋፋቱ እውነት ነው። በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ፣ ብዙ አሞጋሾች ታጥቀው የተሰለፉለት በዩኒስኮ ጭምር  ተቀባይት አግኝቶ እየተደገፈ፣ በተለይ በአፍሪካ አገራት የተስፋፋ የትምህርት አሰጣጥ ቅኝት ነው። በእርግጥ፣ የአዲስ አድማስ ዘገባም ይህን ይገልጻል።
በዓለማቀፍ ደረጃ የተደገፈና የተስፋፋ የትምህርት ቅኝት፣ እንዴት ጠማማ ቅኝት ሊሆን ይችላል? ተማሪዎችን መሃይም የሚደርግ የትምህርት ቅኝ እንዴት በሰፊው ተቀባይነት ያገኛል?
ካሁን በፊት በጋዜጣው በታተሙ ዘገባዎች ላይ፣ ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ በርካታ ጥናቶችንና የመስኩ ታዋቂ ምሁራንን፣ አገራዊና አለማቀፋዊ መረጃዎችን በማካተት በርካታ ትንታኔዎች መቅረባቸው አይካድም።
ቢሆንም ግን፣ ዓለማቀፋዊውንና ገናናውን የትምህርት አሰጣጥ ቅኝት ላይ መፍረድ አያስቸግርም? የአዲስ አድማስ ዘገባዎች ትክክለኛ ከሆኑስ እንዴት ሰሚ አያገኙም? ለምን በስፋት መነጋገሪያ አይሆኑም? እንዲህ አይነት ሃሳብና ጥርጣሬ ቢፈጠርብን አፈረድብንም። ይፈረድብናል?
በእርግጥ፣ ተማሪ-ተኮር ወይም ተማሪ-መር የተሰኘው የትምህርት ፍልስፍና ለተወሰኑ ዓመታት በእንግሊዝና በአሜሪካ ከተሞከረ በኋላ፣… አላዋጣም ተብሎ ተትቷል።
ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎች ሲበረከቱ፣ ጉዳቱ በጥናቶች ሲረጋገጥ፣ የወላጆች ቁጣና ግፊት ሲበረታ፣ ተማሪ ተኮር ተብሎ የመጣው ቅኝት ገሸሽ ተደርጓል።
ቢሆንም፣ በዓለማቀፍ ደረጃ በብዛት የሚዘመርለት ገናና የትምህርት ቅኝት መሆኑ ግን አልቀረም። በጀማሪዎቹ አገራት በአሜሪካና በእንግሊዝ ገሸሽ ቢደረግም፣ በአፍሪካ እንዲሁም በሌሎች ድሃና ተረጂ አገራት ውስጥ  እየተስፋፋ መጥቷል።
እንደማያወጣና ተማሪዎችን እንደሚጎዳ በተግባር ከታየ፣ ከሁሉም ቀድመው የሞከሩት አገራት ውስጥ “ይቅርብን” ተብሎ ከተተወ፣ ለምን ዓለማቀፍ ተቀባይነቱን አላጣም? ለምን ገነነ? ለምንስ በአፍሪካና በሌሎች ድሃ አገራት ውስጥ ተስፋፋ?
ለነገሩ፤በአሜሪካና በእንግሊዝም ቢሆን፣ መጥፎ ነው ተብሎ ሙሉ ለሙሉ አልተመዘገበም። በተግባር ስላላዋጣና የወላጆች ቁጣ ስለበረታ እንጂ፣ “ሀሳብ ደረጃ” አሁንም እንደተመራጭ የትምህርት ዘይቤ የሚሞገስ ነው፤ ተማሪ ተኮር የተሰኘው ቅኝት።
ለድሃ አገራት እርዳታ ሲሰጡም፣ ይህንኑ፣ “በሃሳብ ደረጃ የተሞገሰውን” የትምህርት ቅኝት በተከተለ መንገድ ነው። ደግሞስ በሃሳብ እየተሞገሰ እንዴት በገንዘብ አይደግፉትም? ጉዳቱና መዘዙ፣ የተማሪዎች ውድቀትና የወላጆች ቁጣ በቀጥታ አይመጣባቸውም። ለሩቅ አገር ነው እርዳታ የሚሰጡት።
በተግባር እንደማያዋጣ ቢታይም፣ በሃሳብ ደረጃ ያምኑበታል። የኮሙኒዝም አፍቃሪዎች ወይም የሶሻሊዝም ወዳጆች፣ ከአገር አገር በተግባር አሳዛኝ ጥፋትና መዘዝ ቢያዩም እንኳ፣ የአብዛኞቹ ፍቅር አልደበዘዘም። መጥፎ አስተሳሰብ ቢሆኑም፤ ከመቶ ዓመታት በላይ የዓለማችን ገናና የፖለቲካ ቅኝት ሆነው ዘልቀዋል።
የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም ሃሳቦች የተጠነሰሱትና የተፈለፈሉት፣ የተዛመቱትም በምዕራብ አውሮፓ አገራት ከዚያ በአሜሪካ እንደሆነ አትርሱ። ግን የምዕራብ አገራት ጠቅልለው ምርኮኛ አልሆኑም። ይልቅስ እነ ሶሻሊዝም በተግባርና በሰፊው የነገሱት በአፍሪካና በሌሎች ድሃ አገራት፣ እንዲሁ ወደኋላ ቀርተው በነበሩ በራሺያ፣ በሌሎች የምስራቅ አውሮፓ አገራት እንዲሁም ቻይናን በመሳሰሉ አገራት ነው።  አሜሪካና እንግሊዝ ውስጥ በሃሳብ ደረጃ ባይሆንም በተግባር ገሽሽ የተደረገ አጥፊ የፖለቲካ ቅኝት ወይም ጠማማ የትምህርት ዘይቤ፣ ባሕር ተሻግሮ አፍሪካንና ብጤዎቿን ማጥለቅለቁ አይገርምም። የሶሻሊዝም ፖለቲካና፣ ተማሪ ተኮር የተሰኘው የትምህርት ቅኝት በዚህ በዚህ ይመሳሰላሉ።
በሰፊው እየታመነባቸው በዓለማቀፍ ደረጃ መግነናቸው፣ አጥፊና ጎጂ እንደሆኑ በተግባር መታየታቸው፣ በሃሳብ ደረጃ ግን እየተሞገሱ ወደ ድሃ አገራት መዛመታቸውና መንገሳቸው ሲታይ አያመሳስላቸውም?
በዚህ ንጽጽር ከተሰላ፣ ነገሩ ከባድም የሚያስጨንቅም ይሆናል። አጥፊው ሃሳብ እንደ አልሚ ከተቆጠረ፣ የእርግማን ሙሾ የምርቃት  ዜማ ነው ተብሎ ከተሞገሰ፣ የመርዶ ኡኡታ ደግሞ የምስራች እልልታ መስሎ ከታየ ገና ከተሰማን፣… ምን ይባላል? እያዩ የማለቅ፣ እየሰሙ የመጥፋት አበሳ ነው ቢባል ይበዛበታል? ከዚህም ይብሳልም እንጂ። ጥፋትን እንደ መጋበዝ፣  በችኮላ ለአደጋ እንደ መሽቀዳደም ነው።
ቢሆንም ግን፣ ስህተትና ጥፋት የዚህን ያህል እየተሞገሰ፣ ያተከላካይ እንደልብ በየአገሩ መግነንና መስፋፋት ይችላል? ለዚያው በድብቅ ሳይሆን በግላጭ፤ ለዚያውም በጠላት ሴራ ሳይሆን በወዳጆች እርዳታ፣… ለዚያውም ሳይወዱ በግዴታ ሳይሆን በጭብጨባ በእልልታ ክፉ የጥፋት ሃሳብ ይዛመታል?
የአዲስ አድማስ ተከታታይ ዘገባዎች፣… ከ10 ዓመታት በፊትም አምናም ዘንድሮም ይህንን አሳዛኝ እውነታ በመረጃዎች ለማሳየት በትንታኔ ለማብራራት የሚሞክሩ ናቸው።
ቢሆንም ግን ለማመን ያስቸግራል። አስደንጋጩ ነገር ለዓመታት በአዲስ አድማስ ተዘገቡትን ቁምነገሮች የያዘ ሰፊ ዘገባ ከሳምንት በፊት ዘኢኮኖሚስት መፅሄት ላይ ታትሞ ለንባብ መቅረቡ  ነው።
“ተማሪ-ተኮር”፣ “ተማሪ-መር” የተሰኘው የትምህርት ቅኝት፣ የበርካታ አገራትን ትምህርት እንዳራቆተ  የመጽሔቱ ዘገባ ይገልጻል።
በአንድ በኩል፣ በዚሁ የትምህርት ቅኝት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱና በምሳሌነት ከሚሞገሱ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች ዘኢኮኖሚስት ጠቅሷል።
ከዚህ ጎን ለጎንስ?
 ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች በብዛት ከሚገኙባቸው ቀዳሚ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ሆናለች።
እየተሞገሰና እየተስፋፋ በመጣው የትምህርት ቅኝት ነው፣ ተማሪዎች ለመሃይምነት የተዳረጉት? የተወደሱ አገራት ናቸው ቀልጠው የቀሩት።


Read 979 times