Saturday, 18 February 2023 20:15

አማርኛን ለአማርኛ ቋንቋ የሚያስተምር ድርሰት ‹‹ወሪሳ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

 መነሻ
ዓለማየሁ ገላጋይን መላመድ ንፋስ እንደመግራት ነው፤ አቅጣጫው በየት እንደሆነ በውል ለመገመት ያዳግታል። 15 መጻሕፍት ጀባ ቢለንም መነጣጠል እንጂ ድግግሞሽ አይስተዋልም በሥራዎቹ ላይ፤ ሌላው ቀርቶ ‹‹በፍቅር ሥም››፣ ‹‹ታለ፤ በዕምነት ሥም››፣ ‹‹ሐሰተኛው በዕምነት ሥም›› እና ‹‹የተጠላው እንዳልተጠላ›› ወጥ/ተያያዥ ሥራዎች ቢሆኑም ድግግሞሽ አይስተዋልባቸውም። ምናልባት ቋንቋውን አይቶ ‹‹ይኼ የዓለማየሁ ገላጋይ ድርሰት ነው›› ማለት ይቀል ይሆናል፤ ነገር ግን ታሪኩ/ጭብጡ ከመርኀ-ግብሩ በፊት ውጤቱ እንደሚታወቅ የአገራችን ምርጫ ዓይነት ሳይሆን ከተነበበ በኋላ እየተገለጠና እያላለቀ የሚሄድ ይሆንብኛል፤ ‹‹የተሰጠኝ ብዙ ስለሆነ አልደጋግምም›› ማለቱን መዝግቤአለሁ…
…ደራሲው ብዙ ነጥብ ይገደዋል፤ የምናባዊና የዕውናዊ ታሪኮች ባለቤት ነው፤ ምናባዊ መርቀቅን ከእራሱ ንጡልነት፣ ቁዘማ፣ መታከት፣ ድባቴ…ወዘተ. ጋር በመለወስ ይደርሳል፤ ከሮማንቲስም መገለጫዎች መካከል ንጡልነት/Isolation እና ድባቴ/Melancholy/depression ተጠቃሾች ናቸው፤ Romanticism focuses on emotions and the inner life of the writer, and often uses autobiographical material to inform the work or even provide a template for it እንዲል ዓለማየሁ ገላጋይ በንጡልነት ውስጥ (የራሱ የእግር ዳና እንኳን የሚረብሸው) ሰጥሞ የእሳቤውን ዳና የሚያሳርፍ ደራሲ ነው፤ የሚረብሸውን ሳይሆን የሚበጀውን ዳና ነው የሚያኖረው ታዲያ - በሽሙጥና በጥምዝ ሥነ-ልቡና (reverse psychology) እያስታከከ ነው…
‹‹ወሪሳ››
ደራሲው ኮስታራ ርዕሰ-ጉዳይ ሊነግረን ይተልማል፤ አንድ ከልታማ አስተማሪ በማሕበረሰብ፣ በፖለቲካ፣ በሥነ-ልቡና፣ በምጣኔ-ሀብት እና በሌሎች ጉዳዮች ሰርክ ተጨብጦ እንደ መወርወሪያ ከወዲህ ወዲያ ሲንገላታ እናስተውላለን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነበው እንደ ማንኛውም አንባቢ በዓለማየሁ ጨዋታ አዋቂነት ነፍሴን እስክስት መሳቄን እናዘዛለሁ፤ ግና ጨዋታ አዋቂነቱ ጨዋታ መስሎ የታየው በአንባቢ በኩል እንጂ ደራሲው ያለምክንያት የዶለው አይደለም፤ ዐውዱን ያማከለ እና የገጸ-ባሕርይውን ሥሜት የታከከ ነው፤ ቢሆንም ዓለማየሁ አማርኛን እንዳሻው በማዘዝ ከኀሊነቱ ከድርሰቱ ጭብጥ በመጠኑም ቢሆን አናጥቦኛል፤ ‹‹ወሪሳ›› ሲነበብ/እየተነበበ መስፋቱ እሙን ነው…
…በዚህ ድርሰት አማርኛን ለአማርኛ ቋንቋ ያስተምራል፤ ዓለማየሁ ገላጋይ ኪናዊ ወጆ ከቀፈቀፈ በኋላ በተቆረረለት ቋንቋ ብቻ እንዲምነሸነሽ ደንብ የተጣለበት ደራሲ አይደለም፤ መሪር ጉዳዮችን (ገጸ-ባሕርይው ወይም ተራኪው የተሰማውን) እየነገረን በቋንቋው ጣት ይኮረኩረናል፤ ከዚያ አንዳች ተድላ ትሰርጽና ሳቅ ይሆናል…
…‹‹ራሴን ተቆጣሁ››….
…አማርኛን አሟጦ በመጠቀም አማርኛ ቋንቋን በስፋት ጥቅም ላይ ያውላል፤ በዚህ ድርሰት። የአማርኛ ቋንቋ ወጆ/የይለፍ-ቃል/pass-code የተለገሰው ደራሲ ነው ዓለማየሁ፤ በማሕበረሰብ ባሕል፣ ተረት፣ ምሳሌ፣ ተምሳሌት… ስርቻ ውስጥ ተደብቀው የኖሩ ቃላትን አነፍንፎ እያወጣ ይገለገላል፤ እግረ-መንገዱን ለአማርኛ አማርኛ ያስተምራል - Commensalism!
በዚህ መልኩ ነው ታዲያ፡-    
የዓረፍተ-ነገር አጀማመር /beginning sentence/topic sentence      
በትረካ ወቅት የዓረፍተ-ነገር አጀማመር ፈታኝ እንደሆነ ይነገራል፤ ደራሲ ከ5-7 ጊዜ በላይ እየሠረዘና እየደለዘ ሊከርም ይችላል፤ የመጀመሪያ ዓረፍተ-ነገር የድርሰቱን ታሪክ፣ ሀሳብና ዐውድ የመሸከም አቅም ሊኖረው ግድ ይላል፤ ሃቲቱና አጀማመሩ መሳከር የለባቸውም፤ beginning sentence/topic sentence, also called hooking sentence, announces about the story, theme, mode of character…etc., and it should discuss only those. Then, the body part expands the points raised in the beginning sentence; it should not mess the story discussing something else different ነውና እውነቱ፣ ዓለማየሁ ገላጋይ ይኼንን አይስትም…
‹‹እንደ ኢየሱስ በወንበዴዎች መካከል ተቸንክሬአለሁ›› ገጽ (7)
ብሎ ይጀምራል፤ በዚህ ዓረፍተ-ነገር ሊነግረን የተለመው የበዳዮቹን ክፋት ብቻ ሳይሆን የበደሉንም ግዝፈት ነው። በአስተምህሮ የምናውቀውን እውነት ወደ ዐውዱ በመሳብ ተክቶ ተጠቅሟል፤ ይኼ የሚያሳየው የምሰላ ክኅሎቱን ብቻ ሳይሆን የተነሳበትን ታሪክና ሀሳብ በሥሜትና በሥጋ እየለወሰ ባማረ ቋንቋ ማቅረብ መካኑንም ጨምሮ ነው፤ ስለ አስተማሪው ውጥንቅጥ ሊነግረን ተልሞ ለንፋስ አይሰጠንም ደግሞ!
መቼት/Setting (When is what? Vs. Where is what?)
መርቀቅ ገጸ-ባሕርይ መሳል፣ ተውላጠ-ሥም መቅረጽ፣ ምሰላ፣ ፍካሬ፣ ሥነ-ውበት፣ ኑባሬያዊነት… ወዘተ. ላይ ማተኮረ ብቻ እንዳልሆነ ‹‹ወሪሳ›› እማኝ ነው፤ ለዚህም ቋንቋ ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፤ ቋንቋ ሀሳብን፣ እውነትን፣ እውቀትን፣ ኑባሬን፣ ፍትሐዊነትን ሲናኝ ሳይሆን ሲፈትሽና ሲፈክር ይገኛል እዚህ፤ ዓለማየሁ ‹‹ወሪሳ›› የተሰኘ ምዕናባዊ መቼት የቆረቆረ ሲሆን፣ የመቼቱን ነዋሪዎች (ወይም የውልድ መቼት ውልድ ገጸ-ባሕርይዎች) ውልድ አኗኗር፣ ይትባሃል፣ ሥነ-ልቡና…ወዘተ. እንግዳ በሆነ መልኩ ይታዘባል፤ ከይትባህላቸው ግርንቢጦሽነት አንጻር መቼቱን ሆነ ብሎ ውልድ እንዳደረገው መናገር ይቻላል፤ ሽሽት ነው፤ ከሒስና ከሕግ አንጻር ራስን የመከላከል ብልሃት ታክሎበታል ብዬ አምናለሁ። ሌለው ቀርቶ የዘነበ ወላንና የመሐመድ ሰልማንን ንትርክ መርሳት እንዴት ይቻላል?
ከዚህ ሳንርቅ፣ ታሪኩ የተከናወነበት ጊዜ በሰዓት፣ በዓመተ-ምሕረት፣ ቁርጥ ባለ ዘመን የተገደበ አይደለም፤ ድርሰቱ ማንኛውንም ዘመን የሚወክልና ጊዜ የማይሽረው ወረተኛ እንዳይሆን ረድቶታል! አሁንም ከዘመኑ ነዋሪ ቅያሜ ለመሸሽ ይረዳዋል! በአጠቃላይ የታሪኩን ክብደት የሚመጥን መቼት የፈጠረ ይመስለኛል።
የገጸ-ባሕርይ ቤተ-ሙከራ፤ ‹‹ወሪሳ››
ሥምና ርዕስ ወካይ ናቸው - ሥራን/ተግባርን! ደራሲው ከቀጥተኛ ሥም/Proper noun ይልቅ ተውላጠ-ሥምን ተጠቅሟል፤ ገጸ-ባሕርያቱ ሥማቸውን የሚወክል ሥራ ሲያከናውኑ እናገኛለን፤ ለዚህ ነጥብ ሁነኛ ማስረጃ ‹‹አምጰርጵር›› እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፤ የ‹‹ወሪሳ›› መንደርተኞችንና ንጡሉን አስተማሪ በነገር ሲያንጰረጵሩ ይኖራሉ፤ ሸር መቀመም ቀላል ነው ለእሳቸው! ያቺ…
‹‹ሲጠሩህ ዝም በል
ሳይጠሩህ አቤት በል
ነገሩ እንዲዘናበል›› ብሒላቸው ለነገር ማቆብቆባቸውን ታመላክታለች።
‹‹ሽኮኮ›› ሾካካ ነው፤ ዓሳ እንደ ላሰው ድንጋይ የሚያሟልጭ ሸርታታ ፍጡር፤ ዓይኑን ከድኖ እስኪከፍት ሱሪውን ልፎት አልነበር?
‹‹ወሪሳ››ን የገጸ-ባሕርይ ቤተ-ሙከራ ነው ለማለት ያስደፈረኝ ሕያው የሚመስሉ ገጸ-ባሕርያትን በውስጡ ስላጨቀ ነው፤ በአካል የምናውቃቸው እስኪመስለን እንደመማለን፤ የዓለማየሁ ገላጋይ ውልድ ሰው ‹‹አምጰርጵር›› ሲንቀሳቀሱ የሚያሳይ ስዕላዊ ትረካ ከዓይነ-ሕሊናችን ይጋረጣል፤ አስተማሪውን ሲንጨረጭሩት ዕኩል እንንጨረጨራለን፤ ለነገር ማንገርገባቸውን፣ ድምጸታቸውን፣ አረቄ አጠጣጣቸውን፣ ሽመል አሰናዘራቸውን ከአስተማሪው ጎን ቆመን የምንታደም ያስመስላል ዓሌክስ! ከመላመዳችን አንጻር ምናልባት የሽመላቸውን ትክክለኛ ርዝማኔና የድምጻቸውን ዘይቤ መለየት ላይከብደን ይችላል። ሽመል ሲነዝሩ ደንብረናል፤ ዝም ሲሉ ነገር እያምሰለሰሉ እንደሆነ ቀልባችን ነግሮናል፤ ዓለማየሁ ገላጋይ በስዕላዊ እንቅስቃሴ በማስደገፍ የአንባቢን ሥሜት መቀስቀስ ችሏል።
ብዙ ጊዜ የዓለማየሁ ገላጋይ ገጸ-ባሕርያት protagonist እና አሸናፊ ብቻ አይደሉም፤ ይኼንን የቸከ ልምድ አይፈቅድም ዓሌክስ፤ ከውድቀት መማርንም ያምናል። ድርሰቱ በአማርኛ ልብ-ወለድ ታሪክ የገጸ-ባሕርይ ዕድገትን፣ ቀረጻን፣ ስሜትን፣ ስዕላዊ እንቅስቃሴን በአግባቡ በማሟላት ረገድ ግንባር ቀደም ስፍራ የሚሰጠው ነው ብዬ አምናለሁ!    
 ጨዋታ-አዋቂነት
ዓለማየሁ ገላጋይ ጨዋታ አዋቂ ነው፤ በ‹‹ወሪሳ›› ሊያመለክት የተለመውን ጽንሰ-ሀሳብ በግሩም ቋንቋ እየታገዘ ለአንባቢ አቅርቧል፤ ቋንቋው፡- የቃላት አጣጣሉ፣ የገላጭ ሐረጋት፣ የዓረፍተ-ነገርና ሰዋሰዋዊ አወቃቀሩ እና ዘይቤአዊነቱ ሰዓቢና ከተቀመጡበት ሳይነሱ መጻሕፉን ለማገባደድ የሚያስገድድ ነው፤ ሆኖም ለሳቅ ፍጆታ ብቻ የታለሙ አይደሉም፤ ታሪኩን፣ ዐውዱን(context)፣ ሀሳቡንና የገጸ-ባሕርይውን ሥሜት መሠረት ያደረጉ ናቸው፤ ምሳሌ እንጥቀስ፡-  
‹‹እራሴን በተራቡ ድመቶች አንፃር እንደተንጠለጠለ ቋንጣ ቆጥሬዋለሁ። ዕድሜ የሆነኝ ድመቶቹ ከተሰቀልኩበት ለማውረድ እስኪዘይዱ ድረስ ማሰላሰላቸው ብቻ ነው›› ገጽ (7)
‹‹ጤናማ አንተ ስጠኝ እንጂ ለማን ‹ሪፈር› ትልከኛለህ?...›› ገጽ (12)
በገጽ (22) የጫት ቃሚው ስኳድ ስለ አስተማሪው ቤት ሰርሳሪ መግባቱን የሚተርክበት ክፍል፤ አስተማሪው እንዲመች አድርጎ ይተርካል (‹‹ለዚህም መምህርነቴ ጠቅሞኛል››ይላል)
‹‹…ነገ በጠዋት ኩይሳው በሬን ይቆረቁራል። እከፍታለሁ። የእንጨት ገበቴ እጁን ፊቴ ላይ ይደቅናል። ብሩን አስቀምጣለሁ። የእንጨት ገበቴውን ይጨብጣል፤ ጣቶቹን ሲሰበስብ ቡጢው ጉቶ ይመስላል። እንግዲህ በዚያ ጉቶው ነው ፊቴ ላይ የሚለኝ። ሊደግመኝ የኮቴን ክሳድ ይዞ ከወደኩበት ሲያነሳኝ የለሁም። በባሕላችን አስክሬን ክቡር ነው። በእርጋታ አስቀምጦኝ ካማተበ በኋላ ይሄዳል። ፍትሐቴም በኩይሳ ማማተብ ይጠናቀቃል።›› ገጽ (37)
‹‹ለመተኛት ጀርባ ብቻ በቂ ነው፤ ከሰውነት አካል ኩላሊት፣ እግር፣ ሳንባ፣ ጉበት ምን ጥቅም አላቸው? ጀርባ ብቻ። ሌላው ትርፍ ነው።››
‹‹ሳጂን መርጌ ካሁን አሁን በጥፊ መረገብኝ ስል ‹ጎሽ ጀግና እወዳለሁ› አለኝ…››
‹‹ትንቢት ማለት ሌላ ሳይሆን አንድ ሰው የእግዚሐር ራዲዮ መሆኑ ነው›› ገጽ (283)…
እያለ አስተማሪው የገባበትን የመንፈስ ውርክብ ያሳያል። ዐውዱን ያልሳቱ ማጣፈጫዎች ተካተዋል። ዓለማየሁ ከራራና ኮስታራ ጉዳይ እየነገረን በውብ ቋንቋውና በጨዋታ አዋቂነቱ ያስፈግገናል!
ፈጠራ
በ‹‹ወሪሳ›› የተመለከትነው የመቼትና የገጸ-ባሕርይ ፈጠራ የሚደነቅ ሙከራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዓለማየሁ ገላጋይ ዐውዱን መሠረት በማድረግ ቃላት፣ ምሣሌያዊ አነጋገር፣ ተረት፣ ታሪክና ጭውውት እየፈጠረ - በዋናነት ተውላጠ-ታሪክ በመፍጠር ትረካውን አስውቧል፤ ለምሳሌ ‹‹አባ ጆቢር›› እና ‹‹እማማ ጉዶ›› ስለ ወሪሳ አመሠራረት የሚነግሩን ታሪካዊ ዳራ ሁነኛ ፈጠራ ነው፤ የ‹‹አምጰርጵር›› ራዕይ ማየትና የሳቫስታፖል የመሥራት ቅዠት፣ የ‹‹ጭፍን›› ‹‹ፍቅር እስከ ቅብሮ›› ድርሰትና ሌሎች በርካታ ነጥቦችን መጥቀስ ይቻላል።      
ሽሙጥ  
‹‹ወሪሳ›› ፖለቲካዊ ሽሙጥ የተጫነው ድርሰት ነው፤ የአስተማሪን ውጥንቅጥ አኗኗር፣ የምጣኔ-ሀብት ጥገኝነት፣ የሥነ-ልቡና ጥቃት፣ የአለቆች ጣልቃ-ገብነት፣ የሥራ ነጻነት ማጣትና ሌሎች ፖለቲካዊ ጣጣዎች በጥምዝ/reverse የተተረኩበት ድርሰት ነው፤ ከዚህ ባለፈ በአስተማሪ ላይ የሚደርሰውን ማሕበረሰባዊ በደል ሊያንጸባርቅ ሞክሯል።   
ንጡልነት/Isolation  
በድርሰቱ እንደተመለከትነው አስተማሪው ለሚደርስበት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ፣ ማሕበረሰባዊና የትዳር ጫና ግብረ-መልስ የሚሰጠው በመሸሽ ሲሆን ስልቱም ንጡልነት ነው፤ ከሀሳባቸው ይሸሻል፣ የሚያደርጉትን አብሮ አያደርግም፣ ድርጊያቸው ያውከዋል፣ የዘቀጠ ሥነ-ልቡናቸውን ያበራየዋል፤ ግና ንጡል ቢሆንም ኅልዮ ይምሳል፤ ሀሳብ ያሰርጻል።
ማስረጽ/Canonization
የአጀብ እውነታን ነቅፎም ሆነ ንቆ የራሱን እውነታ ይከተላል፤ እውነታ ለእሱ ኑባሬ/existentialism መር ነው። መሬት ረግጦ ለውጥ ማምጣት አለበት ቢያንስ። በሽሽት ውስጥ አዟዙሮ መናገር የሚሻው እውነታ አለ፤ ማሕበረሰባዊ ነውራችን፣ አስተማሪን የማሳነስ ሕጸጻችን፣ ግብ አልባ አኗኗራችን የተተቸበት ድርሰት ነው።   
ዕንቁ ቃላት፣ ምሳሌና ተረት/Precious pen
ያልተለመዱ ውብ ቃላት በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል፡- ‹‹ጎፈሉ››፣ ‹‹ተንጠረበቡ››፣ ‹‹አንገረበበ››፣ ‹‹ቆጭባራ››፣ ‹‹አንቆራባጭ››…የመሳሰሉ፤
እንዲሁም ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮችም፡-
የዝንጀሮ መነኩሴ፣ የሰንበሌጥ አንካሴ
ድመት መንኩሳ፣ አመሏን አትረሳ
እኔው ሞቼ፣ እኔው ቄስ ጠርቼ
ባቄላ እንደማይተርፍ ውኃ ተፈላ
እና ሌሎች በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ቃላት፣ ሐረጋትና ምሣሌያዊ አነጋገሮችን በስፋት አስርጓል፤ ዓለማየሁ ገላጋይ ተወዳጅ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት የቋንቋ ሀብቱ ነው፤ የድርሰት ሀሳቡን ለአንባቢ የሚያቀርብበትን ቋንቋ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ለዛው ያማረ ነው!
ድበ-ልቦለዳዊነት/Sur-realism
ዘመናዊነት/modernism ተገባዶ ድኅረ-ዘመን/post-modernism እውን ሲሆን ሌጣ እውነት ይሉት ነገር ‹ወግድ› ተባለ። Neo-historicists እነ ሚሼል ፉኮ (Michael Foucault) ደግሞ በታሪክና በልብወለድ ድርሰት መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ፣ የቦታና የተደራሽነት ጉዳይ እንደሆነ ይደነግጋሉ። ዓለማየሁ ገላጋይ በንጡልነቱ ሮማንቲስም ሲጠቀልለው፣ በብዝኀ-እውነት ጥቁምታው ድኅረ-ዘመናዊነት ይጎላበታል። በ‹‹ወሪሳ›› የእውኑንና የቅዠቱን ዓለም ኬላ እየጣሰ፣ እውኑን ከምዕናብ እያዳቀለ…. ንጡል እውነት የለም/There is no single reality/plurality of reality እንዲል Fredrick Nietzsche ‹‹ወሪሳ›› በብድር ወ በምዕናብ ዓለም ውስጥ እውናዊ ትዕይንቶችና ኩነቶች የሚከናወኑበት ድርሰት ነው።
ዓለማየሁ ገላጋይ በልብ-ወለድ ውስጥ ሌላ ልብ-ወለድ(Meta-fiction - another fiction fused in a fiction) ይፈጥራል፤ የልብ-ወለዱ ታሪክ/ሀሳብ/ጭብጥ ለእውኑ ዓለም ቅርብ ቢሆንም መቼቱ ከእውናዊ ዓለም ይልቅ ለምናባዊ ዓለም ያደላ ነው።   
ድኅረ-ዘመን/post-modernism
ድርሰቱ ድኅረ-ዘመናዊነት ጎልቶ የታየበት ሲሆን ከመገለጫዎቹ መካከል ውስን እውነታን፣ እውቀትን፣ ልምድን፣ ይትባሕልን ይክዳል፤ ገጸ-ባሕርይውም ተራኪውም/ደራሲውም ናቸው በእውነት ብዝኀነት የሚያምኑት ብዬ አምናለሁ! ደራሲው ከልምዱ፣ ከድባቴውና ከሚቸከው እውናዊ ዓለም ለመሸሽ ሲወጥን ወደ ቅዠቱ ዓለም ዋሻ ቱር ብሎ ይገባል፤ እናም የእውኑንና የምናቡን ዓለም አድማስ ያወዳጃል፤ ከመንጋው ተነጥሎ ይምሰለሰላል፤ እውነታን ይክዳል፤ እኒያ ከይሲና ጉዳቸው የማያልቅ ‹‹አምጰርጵር›› ራዕይ ያያሉ!
መውጫ
‹ማጠቃለያ› ለማለት አልፈቀድሁም፤ መውጫ ያልኩበት ምክንያት እንደምመለስ ለመጠቆም ነው፤ ‹‹ወሪሳ›› የሚያልቅ/የሚጠቃለል ድርሰት አይደለም፤ እያደር ማማርና መጣፈጥ ግብሩ ነው፤ እና የሚጣፍን ነገር መሸሽ ጤነኝነት ነውን? ‹‹ወሪሳ›› የድርሰት ቁንጮዬ ነው!




Read 893 times