Print this page
Saturday, 18 February 2023 20:31

የሥራ ቀላል የለውም!

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

 “--ምናልባት የሀገሩን ፖለቲካ ለአለፉት አርባና ሀምሳ አመታት ቀረብ ብሎ ላስተዋለው «ባለህበት መርገጥ»ም የሥራ አይነት እንደሆነ ሊገለጽለት ይችላል፡፡ የፖለቲካ «ውሃ ቅዳ ውሃ መልስነት» ለውጥ እየተባለ ሲጠራ በተደጋጋሚ ያደምጣል፡፡ የታሪክን «ቆብ ቀዶ መስፋቱ»፣ የእነ ማኪያቬሊን የተንኮል ፖለቲካ  መፅሐፍ ደጋግሞ ማጠብ፣ ‘አወቅህ አወቅህ’ የሚያስብል የመሰላቸው፣ ትልቅ ስራ እንዳከናወኑ አምነው ደፋ ቀና ብለዋል፡፡ በተሳሳተ ሃሳብ ትክክለኛ ሥራ ፈጽሞ እንደማይሳካ ሳይገባቸው ተቸግረው አስቸግረውናል፡፡ የሥራ ቀላል የለውም፡፡ --”
     
      ሥራ አይናቅም፡፡ አዎን፣ እኔም አልንቅም፡፡ ግን ወደድኩም ጠላሁም፣ አንዱን ሥራ ከሌላው ሆነ ብዬም ባይሆን ማነጻጸሬ አይቀርም። ከባድ የሚመስል ሥራ አለ፤ ቀላል መሳይም እንደዚሁ፡፡ ‘ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ’ በመሆኑ እንጂ፣ ‘እስቲ ሞክረው’ ብለው ቢያስጨብጡህ ማንኛውም ስራ ቀላል አይደለም፡፡
በቀላሉ ገንዘብ የሚያስገኝ የመሰለህ ሥራ ራሱ፣ በቀላሉ ከራስህ ጋር የሚያጣላህ፣ ከነብስህ ጋር ያለውን መከባበር በመናናቅ የሚለውጥ ይሆንብሃል፡፡ ኪስህ በገንዘብ ቢሞላ እንኳን፣ መንፈሳዊ ደስታህ በዛው መጠን የጎደለ ይሆናል። ይህ የሚሆነው ግን ከኪስህ በተጨማሪ መንፈስም ያለህ እንደሆነ ነው፡፡ የመንፈስ እርካታህ በኪስህ በኩል የማይሞላ ሲሆን ምድርና ሰማይ እውነትም ስለመራራቃቸው ትገነዘባለህ፡፡
ኦስካር ዋይልድ:- «በነብስ እና በስጋቸው መሃል ልዩነት የሚታያቸው ሁለቱም የሌላቸው ናቸው» ብሎ በመናገር እንደሳተ ባስታወስኩ ጊዜ አዝናለሁኝ፣ ነገሩ ግን ተገላቢጦሽ ነው። እኔ የምለው ደግሞ:- በነብስ እና ስጋ መሃል የማይታረቅ ሆድ እና ጀርባነት የማይታያቸው፣ ጀርባቸው ቢጠና አንድም ሆድ ብቻ አልያም ደግሞ ኪስ ብቻ ሆነው መገኘታቸው አይቀርም።
ለማንኛውም፣ ማንኛውም ስራ መናቅ የለበትም፡፡ በተለይ ደግሞ በሩቁ ተሞክሮ ባልታየበት፡፡ ለምሳሌ እኔ፣ የዘበኝነትን ስራ ሳላስበው ስንቅ ብዙ ጊዜ ራሴን እጅ ከፍንጅ ይዣለሁኝ፡፡ ግን ዘበኛ ዘራፊ ከመጣ ያስጥላል፤ ሌባ ከመጣ ያስፈልጋል፡፡ ‘ፈጣሪ ብቻ ነው የማይተኛ ጠባቂዬ’ የሚሉት እንኳን ዘበኛ ቀጥረው በራቸውን ያስጠብቃሉ፡፡ ስራው ግን ፈጽሞ ቀላል አይደለም፡፡ አንድ ቦታ ተቀምጦ እንደማይመጣ የሚያውቁትን ነገር ሲጠብቁ መዋል፣ እዛው ቦታ ተቀምጦ ውሎ ተቀምጦ ማደር፣ በፀሐይም ሆነ በውርጭ። የምትጠብቀው ነገር ደግሞ እንደማይመጣ እያወቅህ ተግተህ መጠበቅህ፡፡ የምትጠብቀው ነገር ከመጣ፣ ስራህ እንደሚጀምር እያወቅህ፣ ስራህ እንዳይጀምር ፈጣሪህን እየተማጸንክ ውለህ ማደርህ፡፡ መስሪያ ቤት ወይንም መኖሪያ ቤት ደጃፍ ላይ ዱላ ወይንም መሳሪያ ይዞ መዋል ከባድ ስራ ነው፡፡ የቀጠረው ሰው ለአስር ደቂቃ ሲዘገይበት እንኳን ሰው ስንት ጊዜ ስልክ ይደውላል፡፡ ስንት ሻይ እና ቡና ያጋታል፡፡ ስንት ጊዜ ጫማውን ያስጠርጋል፡፡
ግን ደግሞ መለስ ብዬ ሳስበው፣ ወይንም ሰፋ አድርጌ ስመለከተው፣ ለካ ሁላችንም ዘበኞች ነን፡፡ ሞት የሚባል ሌባ መጥቶ ህይወታችንን ሳናስበው እንዳይሰርቀን ስንጠብቅ ውለን የምናድር ምስኪን ዘበኞች ነን ለካ፡፡ ግን ያስፈለገ ያህል ህይወታችን እንዳይሰረቅብን ተግተን ብንጠብቀውም አንድ ቀን የፈራነው ሌባ መምጣቱ አይቀርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው የግለሰብ ስራ እንዲያውም በራሱ ህልውና ላይ ዘበኛ ሆኖ ሲጠብቅ መኖር ነው፡፡ የስራ ቀላል የለውም፡፡
የነጋዴም ስራ ከባድ ነው፡፡ ድሮ ድሮ የሱቅ ነጋዴ ስራ በጣም ቀላል ይመስለኝ ነበር፡፡ ሌላ ሰው በሌላ ሀገር ያመረተውን እቃ ደርድሮ ዋጋ እየጨመረ መሸጥ ይመስለኝ ነበር፡፡ እሱም ግን ከባድ መሆኑን ተረዳሁኝ፡፡ በተለይ ደግሞ ከባድ የሚሆንበት እንደኔ አይነት የጨፈገገ ፊት ላለው ሰው ነው፡፡ ለካ ይኼ ሁሉ የሱቅ ነጋዴ፣ደንበኛን የማያሸሽ፣ ያልተቆጣ ፊት እስከተላበሰ ድረስ ነው ሱቁ የማይከስረው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ድሮ ሰፈሬ የማውቀው ባለሱቅ ትዝ ሊለኝ ይችላል። ባለ ሱቁ ልጅ እግር ነበር ያኔ፡፡ ከሱቁ ውጭ ይኼንን ልጅ ሳገኘው አፉ ይለጎማል፡፡ ቀና ብሎ ሰው ማየትም አይችልም። ከባህር የወጣ ዓሳ ይመስላል፡፡ ሱቁ ውስጥ ገብቶ ሲቆም ግን ጤናማ ይሆናል፡፡ በመንገድ ላይ የሚያልፍ ሰውን እየተጣራ ሰላም ይላል። ሱቁ ደጃፍ የሚመጡትን ሁሉ ሲያማክር፣ ሲመክር እና ሲያስቅ ይውላል፡፡ ከሱቅ አለሙ ሲነጠል ግን ግራ ይጋባል፡፡ በሱቁ መስኮት በኩል ካልሆነ አለምን አያውቃትም፤ ወይንም እንዲያውቃት አይፈልግም፡፡ እቃ ከሱቁ እየተገዛ በካልኩሌተር ሲደመር ብቻ ነው የአለም ነገር ትርጉም የሚሰጠው፡፡ እኔም በእሱ ሱቅ ውስጥ እሱም በእኔ መኮሳተር ውስጥ መሆን አንችልም። ስለዚህ እሱን መሆንም ቀላል አይደለም ማለት ነው፡፡ የስራ ቀላል የለውም፡፡
ክህሎት የማያስፈልገውን ስራ በቀላሉ ለመናቅ ይዳዳኛል፡፡ በአፌ እንደምንቀው ባልገልጽ እንኳን፣ እንደማያስፈልግ ግን በሙሉ ድምጽ እውስጤ አጸድቃለሁኝ፡፡ ለምሳሌ :- ተዋናይ ሆኖ በፊልምም ሆነ በማስታወቂያ ላይ የሚጫወት ሰው ክህሎት እንዳለው ለማወቅ፣ ቢያንስ፣ በሞያ ዘመኑ (አንዴ እንኳን) ከራሱ የተፈጥሮ ባህሪ ውጭ የሆነ ገጸ ባህሪን ተላብሶ መጫወት መቻል አለበት ብዬ አስባለሁኝ። ዘወትር በፊልምም ሆነ በድራማው ላይ ወይንም በሳሙና እና የፓስታ ማስታወቂያው ላይ ራሱን ሆኖ የሚመጣብኝ ከሆነ፣ ከጥሩ ተዋናይ ይልቅ ጥሩ ‘ኮኔክሽን’ ያለው መሆኑን ነው የሚያስገነዝበኝ፡፡ ስለዚህ፣ በፊለፊት ባልገልጸውም እንቀዋለሁኝ፡፡ ክህሎቱ ራሱን ማብዛት ላይ ነው እንጂ ሌላ ገጸ ባህሪን ወክሎ መተወን ላይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ራስን ማብዛት እና ከካቦ የጠነከረ ‘ኮኔክሽን’ መፍጠርም የክህሎት አይነት ነው፡፡ አራድነትም የክህሎት አይነት ነው፡፡ ብዙ አራዳ ነን የሚሉ አይን አውጦች በበዙበት ዘመን፣ የበሰለ አራድነትም የማይናቅ ስራ ሊሆን እንደሚችል ወደህ ሳይሆን በግድህ ትቀበላለህ፡፡ የስራ ቀላል የለውም፡፡
የስራ ቀላል ባይኖረውም… አንድ አይነት እንቅስቃሴ ከHobby እርከን ወደ ስራነት ደረጃ መመንደጉን እንዴት ማወቅ ይቻላል? የሚለው ያከራክራል፡፡ ብዙዎች ስራን ስራ የሚያደርገው የገቢ መጠኑ ነው ይላሉ፡፡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ ቢሆኑ እንኳን፣ ስራ የሚባሉት ግን ገቢ ማስገኘት እስካልተሳናቸው ድረስ ነው ማለታቸው ነው በቀላልኛ፡፡ ልመና ስራ ነው፤ መጽዋች እስካለ ድረስ፡፡ ሰባኪነት ስራ ነው፤ አስራት እስከተቆረጠ ድረስ፡፡ ነገር ግን በትጋት እና በክህሎት፣ ያውም መስዋዕትነት ተከፍሎባቸው በዝንባሌ እና በውስጥ ግፊት የሚከናወኑ ግን ገቢ የማያስገኙ ተግባሮችስ? የዕድሜ ዘመናቸውን ብዕር ሲገፉ እና ስንኝ ሲያረቁ… በማይገለጽ የውበት ዛር ሲናጡ የሚኖሩ ደራሲያን እና አርቲስቶችስ? ውበትን ከገንዘብ ጋር በፍጹም መመዘን ወይንም አዳብለው መገንዘብ የማይፈልጉትስ? ስራ ፈት ናቸው ብለን እንጠቅልላቸው?
ጥበብ የገበያው ዑደት ማሟሻ አይደለችም፤ የራሷን ምህዋር ይዛ የምትዞር ናት የሚሉትስ? ምርጥ ስጦታዎች እና ተሰጥኦዎች በነጻ የሚገኙ ስለሆኑ፣ ተመልሰው በነጻ ሲሰጡ ብቻ ነው ከሃቅ ጋር ያላቸው ቁርኝት የሚበረታው የሚሉትስ? ጥበብ ለጥበብነቱ፣ እውነት ለእውነትነቱ፣ እውቀት ለእውቀትነቱ፣ መንፈሳዊ እምነት ለመንፈሳዊ ዋጋው የሚሉቱስ? ወደ ስራነት ደረጃ ስላላደጉ፣ የስኬት አልቦነት መገለጫ አድርገን እንደው በደፈናው እንውሰዳቸው? እንንቀፋቸው? አኖማሊ ብለን የጎሪጥ እንያቸው?
ጉልበት የወጣበት፣ ግፊት አርፎበት የሆነ ርቀት የተጓዘ፣ ለውጥ ያስመዘገበ ሁሉ የስራ አሻራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እንግዲህ ቢዋጥልንም ባይዋጥልንም እነ :- «የቄሱን መፅሐፍ ማጠብ» ፣ «ቆብን ቀዶ መስፋት» ፣ እነ «ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ» በሙሉ የስራ አይነቶች ናቸው፡፡ የስራው አይነት በልዩ መገለጫው «ስራ ፈትነት» ተብሎ ቢታወቅም፣ እሱም የስራ አይነት ነው፡፡ «ስራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ»ም የስራ አይነት ነው፡፡ የአሻጥር ፖለቲካም ስራ ተብሎ ቢሮ ተከፍቶ ይዋልበታል፡፡ መግለጫም ይሰጥበታል፡፡ የስራ ቀላል የለውም፡፡
ምናልባት የሀገሩን ፖለቲካ ለአለፉት አርባና ሀምሳ አመታት ቀረብ ብሎ ላስተዋለው፤ «ባለህበት መርገጥ»ም የሥራ አይነት እንደሆነ ሊገለጽለት ይችላል፡፡ የፖለቲካ «ውሃ ቅዳ ውሃ መልስነት» ለውጥ እየተባለ ሲጠራ በተደጋጋሚ ያደምጣል፡፡ የታሪክን «ቆብ ቀዶ መስፋቱ»፣ የእነ ማኪያቬሊን የተንኮል ፖለቲካ  መፅሐፍ ደጋግሞ ማጠብ፣ ‘አወቅህ አወቅህ’ የሚያስብል የመሰላቸው፣ ትልቅ ሥራ እንዳከናወኑ አምነው ደፋ ቀና ብለዋል፡፡ በተሳሳተ ሃሳብ ትክክለኛ ሥራ ፈጽሞ እንደማይሳካ ሳይገባቸው ተቸግረው አስቸግረውናል፡፡ የሥራ ቀላል የለውም፡፡
ትልቁ ጥያቄ ግን፣ ሥራን ሥራ ያደረገው ዋናው ንጥረ ነገር ምንድነው? የሚለው ነው።  ቀላል አለመሆኑ (ክብደቱ) ነው ወይንስ ውጤቱ?  በጣም ከባዱ ሥራ፣ የሥራን ትክክለኛ ትርጉም ማወቁ ላይ ነው፡፡


Read 865 times