Print this page
Saturday, 25 February 2023 12:04

ሰሜን ሸዋ ዞን ተጨማሪ ተፈናቃዮችን መቀበል እንደማይችል ገለፀ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(4 votes)

   - ባለፉት 2 ዓመታት 72 ሺህ ተፈናቃዮችን ተቀብለናል
     -ባለፉት 10 ቀናት ብቻ ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ ብቻ 9 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ዞኑ መጥተዋል
        
       የተፈናቃይ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱና በሀብት እጥረት ሳቢያ ተጨማሪ ተፈናቃዮችን መቀበል እንደማይችል የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ\ቤት አስታወቀ፡፡
ጽ\ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ በዞኑ በተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶችና ጦርነቶች እንዲሁም ከኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ብቻ የመጡ ከ77 ሺህ በላይ ተፈናቃዮችን በብዙ ተግዳሮት እስከዛሬ ይዞ መቆየቱን ጠቁሞ፤ ከፌደራል መንግስት የሚመጣው ድጋፍ በቂና የተሟላ ፓኬጅ ካለመሆኑ በተጨማሪ በየወሩ ስለማይመጣ የዞኑ አመራርና የፅ\ቤቱ ሰራተኞች ህብረተሰቡን በማስቸገር በግል ውስን ለጋሶችን በመለመን ተፈናቃዮችን እንዳይሞቱ እንዳይድኑ ሆነው እንዲኖሩ ሲታገል መቆየቱን አመልክቷል።
የዞኑ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ፅ\ቤት ሀላፊ አቶ አበባው መሰለ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት ባለፉት አስር ቀናት ብቻ ከአዲስ አበባና ከምስራቅ ወለጋ ከባኮ ዞን አኖ አካባቢ የመጡ ወደ 3ሺህ ተፈናቃዮችን፣ የተቀበሉ ሲሆን ሰሞኑን ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተካሄደ ባለው የቤት ፈረሳ ምክንያት ወደ 6 ሺህ በድምሩ 9 ሺህ ተፈናቃዮች ተቀብለዋል፡፡
“እኛ ተፈናቃይ ስንቀበል ሁሉን አቀፍ የሆነ ድጋፍ ነው የሚጠበቅብን” ያሉት ሀላፊው፤ እስካሁን መጠለያ፣ አልባሳት ቀለብ፣ ህክምናና መድሀኒት እያቀረብንና ብዙ ተግዳሮቶችን ተጋፍጠን ብንቆይም ለተጨማሪ ተፈናቃዮች ግን ይህን ሁሉ የማሟላት አቅም የለንም ብለዋል።
የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ደብረ ብርሃን ከተማን ጨምሮ በዞኑ ያሉ 31 ወረዳዎችን እንደማስተዳደሩ፣  በተለይ በሰሜን ሸዋ አጣዬና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በተደጋጋሚ በሚፈጠር ችግር ብዙ ተፈናቃይ ስላለ፣ የመጠለያ ችግር ከመከሰቱ የተነሳ በደብረ ብርሃንም ተፈናቃዮች በባለሃብቶች ፋብሪካዎች ውስጥ ነው የተጠለሉት ያሉት ሃላፊው፤ ይህ ቁጥር ይቀንሳል ብለን ስንጠብቅ እያደር መጨመሩ በእጅጉ አስጨንቆናል ብለዋል፤ ለአዲስ አድማስ።
“እኛ ተጨማሪ ተፈናቃይ አንቀበልም ያልነው ወገኖቻችንን ጠልተን ሳይሆን ከፍተኛ የሀብት ችግር ስላለብን ነው” ያሉት አቶ አበባው፤ “እዚህ መጥተው አይናችን እያየ በረሀብ እንዲሞቱ አንፈልግም” ብለዋል።
እስካሁንም ያሉት ሁሉ ተሟልቶላቸው እየኖሩ እንዳልሆነ የተናገሩት ሃላፊው፤ የዞኑና የደብረ ብርሃን አመራር እየተሯሯጠ ህብረተሰቡም ከልጆቹ ጉሮሮ እየነጠቀና እየሰጠ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውንና ባለሃብቶች ፋብሪካዎቻቸውን ለመጠለያነት ሰጥተው ባለፉት ሁለት ዓመታት ስራ ፈትተው መቀመጣቸውን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ችግር ሲፈጠርና ህዝብ ሲፈናቀል መፍትሄ እስኪመጣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ሰብስቦ በመያዝና አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መቆየት እንዳለበት የገለጹት ሃላፊው፤ “እየመጣ ባለው የተፈናቃይ ቁጥር በእጅጉ ተጨናንቀናል፤  እስከመቼስ ነው የምንቀበለው፤ ምን ያህል ተፈናቃይ ስንቀበል ነው የሚቆመው” ሲሉ ጠይቀዋል።
“ሀገር በተለያየ ችግር በተወጠረችበት በዚህ ሰዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10 እና 15 ዓመት የኖሩ ዜጎችን ቤት እያፈረሰ ማፈናቀል የፈለገው ለምንድን ነው?” ሲሉ የጠየቁት አቶ አበባው፤ ቤት ማፍረሱ አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነም ከተማ አስተዳደሩ ላፈናቀላቸው ዜጎች መፍትሄ መፈለግ አለበት ብለዋል።
እንደ አቶ አበባው ገለጻ፤ በዞኑ የተለያየ ችግር ደርሶባቸው እርዳታ የሚፈልጉ 546 ሺህ ሰዎች መኖራቸውንና 135ሺህ ህዝብ ደግሞ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ ከክልሉ ውጪ ማለትም ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ የተቀበልናቸው ተፈናቃዮች ግን 85 ሺህ ደርሰዋል፤ እስካሁን ተፈናቃዮቹ በደብረብርሃን፣ በምንጃር ሸንኮራ፣ በሚዳወረሞ፣ በመርሃቤቴ፣ በእንሳሮ፣ በመንዝ ማማ፣ በመንዝ ላሎ እና በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው እንደሚገኙ በመጠቆም፣ “በዚህ የተነሳ ነው ሌሎች ተፈናቃዮችን መቀበል ያልቻልነው” ሲሉ አቶ አበባው አስረድተዋል።


Read 2055 times