Saturday, 25 February 2023 12:07

ከ800 ሺ በላይ ሰዎች ለአስከፊ ረሃብ ተጋልጠዋል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(10 votes)

  “ረሃቡ ከቀጠለ ቦረና ምድረ በዳ ትሆናለች”
     
         በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን   የተከሰተው ድርቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮችን ለአስከፊ ረሃብ ማጋለጡ ተጠቁሟል። በዞኑ ከሚገኙ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን ነዋሪዎች መካከል  ከስምንት መቶ ሺ በላይ የሚሆኑት የድርቁ ሰለባ ሆነዋል።   ድርቁ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ  የቀንድና የጋማ ከብቶችን የገደለ ሲሆን በዚህም ወደ 30  ቢሊየን ብር የሚገመት ሃብትን አሣጥቷል ተብሏል።
በዞኑ የገጠር መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች መንደራቸውን ለቀው ወደ ከተሞች በመሰደድ ላይ ሲሆኑ፤ ድርቁ እጅግ ያዳከማቸውና በእድሜ የገፉ ሰዎች ግን ረሃቡን  መቋቋም አቅቷቸው  እየሞቱ መሆኑ ታውቋል። የቦረና ዞን የተልተሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጎንጎ ዋሪዮ  ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በወረዳው በተከሰተው ረሃብ እስካሁን የሁለት ወር ህጻንን ጨምሮ የ7 ሰዎች ህይወት አልፏል።
መንግሥት   በዞኑ በድርቅ ሣቢያ  ለረሀብ የተጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ አላስፈላጊ የፖለቲካ ሽኩቻዎችና መጠላለፎችን  ወደ ጎን ትቶ፤ ለረሀብ ለተጋለጡ ወገኖቻችን ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሠራ  ኢዜማ ጠይቋል። 
ከተጋረጠው ሰብዓዊ ቀውስ አንፃር መንግስት  አስቸኳይ ብሔራዊ የዕርዳታ ኮሚቴ አቋቁሞና   መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተባብሮ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ሊደርስላቸው እንደሚገባም ኢዜማ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በዞኑ በታልታሌ ወረዳ ቡሌደንቢ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አርብቶ አደር ማሌኖ ታራ  ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በዞኑ ላለፉት አምስት የዝናብ ወቅት በጠፋው ዝናብ ሣቢያ   መሬቱ ዘር ለማብቀል የሚችል ባይሆንም፣ አርብቶ አደሩ ባለው መሬት ላይ ዘር እየበተነ ሲጠባበቅ  ጠብ የሚል ነገር በማጣቱ ለከፋ ረሃብ ተዳርጓል። “አርብቶ አደሩ ለአመታት በዘለቀው ድርቅ ሣቢያ ጥሪቱን አሟጦ ጨርሶ ባዶ እጁን ቀርቷል።  መሬቱ ደርቋል፤ እህል አያበቅልም። ከብቶቻችን በረሃብና ጥም አልቀዋል። ቀረን የምንለው ነገር የለም፡፡  ያልተራበ ማንም የለም። በርካታ ሰዎች ቀናትን ያለ ምግብና ውሃ በማሳለፍ ላይ ናቸው፤ ረሃቡ ከብቶቻችንን ጨርሶ ፊቱን ወደ እኛ አዙሯል። መንግስት ረስቶናል ወገኖቻችንም ጨክነውብናል ፈጣሪም ፊቱን አዙሮብናል።” ብለዋል፤ አርብቶ አደሩ።
ትንሽ አቅም ያለውና ረሃቡ ክፉኛ ያልጎዳው እግሩ ወደመራው ተሰዷል። ቀደም ያሉት እንደውም ከሞት የተራረፉ ከብቶቻቸውን ይዘው ነው የተሰደዱት። አሁን ሰዉም ከብቱም መንከላወስ አቅቶታል መንግስትና ወገን እንዲደርስልን ከመማጸን በስተቀር ምንም ማድረግ አንችልም” ብለዋል።
አርብቶአደር  ማሊኖን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የቦረና ነዋሪዎችና አርብቶ አደሮች  በተራዘመው ድርቅ ሳቢያ አሁን አቅማቸው ተንኮታኩቷል፡፡ በዞኑ ከፍቶ በቀጠለው ድርቅ የተፈተነው አርብቶአደር ለከፋ ረሃብ ተጋልጧል። አስራ ሶስቱም የዞኑ ወረዳዎች የድርቁ ሰለባዎች ሆነዋል። በዞኑ ከሚገኙ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊየን ነዋሪዎች ስምንት መቶ ሺ ያህሉ የድርቁ ሰለባ መሆናቸው ተገልጿል።
የቦረና አርብቶአደር  የኑሮ መሠረት  ከሆኑት ከብቶች 3 ሚሊዮን የሚሆኑት በዚሁ ድርቅ ሣቢያ አልቀዋል።
ከዚህ በፊት በዞኑ ከፊል ወረዳዎች በድርቅ ሲመቱ አርብቶ አደሩ የራሱንና የከብቶቹን ህይወት ለማትረፍ ወደ አጎራባች ወረዳዎች ይሰደድ እንደነበር የሚገልጹት በዞኑ የአሬሮ ነዋሪና የመንግስት ሠራተኛ  የሆኑት አቶ ታምሩ ጉልማ፤ አሁን ግን ሁሉም የዞኑ ወረዳዎች በድርቁ ክፉኛ በመጠቃታቸው ማህበረሰቡ  የሚሰደድበት ስፍራ አጥቷል  ብለዋል፡፡ ከወራት በፊት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የቦረና አርብቶ አደሮች ድርቁንና አስከፊውን ረሃብ በመሸሽ   ወደ አርሲ ና ጂንካ   ከብቶቻቸውን ይዘው መሠደዳቸውንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ለቀናት ከእህልና ውሃ ተነጥሎ በመክረሙ አቅሙ ከድቶታል።  ከብቶቹን ትቶ ህይወቱን ለማትረፍ እየተጣጣረ ነው  ያሉት አቶ ታምሩ፤  “ከራሱ በፊት ለከብቶቹ ህይወት ቅድሚያ ይሰጥ የነበረው የቦረና አርብቶ አደር፣ የጎጆውን መሸፈኛ ሣር ሣይቀር ለከብቶቹ ሰጥቶ  ሊያተርፋቸው ባለመቻሉ  አይኑ እያየ ከብቶቹን ረሃቡ ነጥቆታል። አሁን የራሱንም ህይወት ለማትረፍ የሚያስችል አቅም አጥቷል። 
“በዚህች ደቂቃ እንኳን በሺዎች የሚቆጠሩ  የአካባቢው ማህበረሰብ  በረሃብና ረሃቡን ተከትሎ በሚመጡ በሽታዎቸ እየሞቱ ነው።  በቦረና ታሪክ እንዲህ አይነት አስከፊ ረሃብ ታይቶ አያውቅም።  መንግስት በቸልተኝነቱ ከቀጠለና ህዝቡን ከረሃብና ሞት መታደግ ካልተቻለ አካባቢው በጥቂት ጊዜ ምድረበዳ መሆኑ አይቀሬ ነው” ሲሉ መጪውን አስከፊ ሁኔታ ገልጸውታል። በቤት አንስሳቱና በቀንድ ከብቶቹ ላይ የከፋ እልቂትን ሲያስከትል የቆየው ረሃብ   ወደ ዱር እንስሳትም መዛመቱ አሳሳቢ ነው አስብሏል።  ድርቁ  እልቂቱን ያስከተለው በሁሉም አይነት የእንስሳት ዝርያ ላይ ነው፡፡ ድርቅና በረሃን ይቋቋማሉ የሚባሉ እንደ ግመል ያሉ እንስሳትም በዚህ ድርቅ እየረገፉ  መሆኑን ያመለከተው ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ከቤት እንስሳት በተጨማሪም አሁን አሁን የዱር እንስሳትም ድርቁን መቋቋም ተስኗቸው በስፋት እያለቁ መሆኑን አመልክቷል። በቦረና ፓርክ በጥበቃ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳትም ጭምር የረሃቡ ሰለባ እየሆኑ መሆኑን የገለጸው መረጃው   በፓርኩ የከፋ የውሃ እጥረት በማጋጠሙ  በዱር እንስሳቱም ላይ ሞት እየተከሰተ  መሆኑን አመልክቷል።
ከ40 ዓመታት ወዲህ ተከስቶ አያውቅም የተባለው በዚህ የቦረና ድርቅና  ረሃብ  ሣቢያ ለአስከፊ ሞት የተጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ ከመንግስት በተጨማሪ መንግስታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የዕርዳታ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት፣ አክቲቪስቶች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠበቅባቸውን  ኃላፊነት እንዲወጡ ኢዜማ  በመግለጫው  ጥሪ አቅርቧል።
“የፓርቲያችን አባላትም በያላችሁበት አካባቢ ኹሉ ወገኖቻችንን ለመታደግ በሚደረጉ ሰብዓዊና ወገናዊ ዘመቻዎች ላይ የተለመደውን ግንባር ቀደም ተሳትፏችሁን እንድታከናውኑ እናሳስባለን።” ብሏል  ኢዜማ፡፡
የቀጠናው የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የአየር ትንበያ ማዕከል ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፤ የአፍሪካ ቀንድ ከዚህ በፊት ከታየው የከፋ ቸነፈር ገጥሞታል ብሏል። በአፍሪካ ቀንድ  በተለይም  በሶማሊያ፣ በኢትዮጵያና ኬንያ  በአሁኑ ወቅት የሚታየው የድርቅ ሁኔታ ሩብ ሚሊዮን ሰዎችን ከገደለውና ከ 12 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ከታየው የባሰ እንደሆነም አመልክቷል።

Read 2072 times