Saturday, 25 February 2023 12:16

ህይወት ያለው ፌስቡክና ኢንስታግራም...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

      “ምን መሰላችሁ...አለ አይደል...መቸስ ዘንድሮ ሀሜት የሚባለው ነገር ወደ ኢንደስትሪ ደረጃ ያደገ ይመስላል፡፡ አሀ ልከ ነዋ...እነ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክ ቶክ፤ ትዊተር...ምናምን የመሳሰሉት ሁሉ አሁን አሁን ዋነኞቹ የጎሲፕ ‘ትራንስናሽናል ኢንደስትሪ‘ ሆነው የለ እንዴ!--”
      
         እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ እንኳን እስከዚህ አኞ አልነበርሁኝ
ምነው በመላመጥ አልደቅም አልሁኝ
ግነ አሁን መታኘክ በጣም ሰለቸኝ
ወይም አድቅቁና በቶሎ ዋጡኝ
ወይንም በቅቷችሁ ካፋችሁ አውጡኝ
መረረኝ ዘወትር ስታላምጡኝ
አሪፍ አይደለች! አንዲት የቆየች የእነ አቤ ጎበኛ መጽሐፍ ላይ ያለች ስንኝ ነች፡፡
እናላችሁማ... እዚህ ሀገር በዲስኩር መልክ፣ በትንታኔ መልክ፣ በ‘ሲፕ’ አካባቢ ወሬ መልክ፣ በቃለ መጠይቅ መልክ ..ብቻ ምን አለፋችሁ በመአት ነገሮች መልክ ከሀሜታና ከአሉባልታ የማይሻሉ ከዓመት ዓመት የሚላመጡ ነገርዬዎች በዝተውብናል፡፡ የምር የሚገርም ነው እኮ! አንዳንዴም ልክ በሆነ ታይም ማሽን ምናምን በሚሉት ነገር ወደ ኋላ አስርት ዓመታት ተጎትታችሁ የሄዳችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡ ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ፣’ እንዲል ፈረንጅ ሁልጊዜ “አበበ በሶ በላ፣” ማለት  ይሰለቻላ!  በሶውን ሙሉ ለሙሉ መለወጥ ባይቻልም ባይሆን ሴኮንዶ ምናምን ይጨመርበታ! (ቂ...ቂ...ቂ) እና ግለሰባዊ ሆነም ቡድናዊ ሀሜቱ የግድ ከሆነ፣ ‘አሜንድመንት’ ምናምን ይደረግበታ! አሀ...ያ ምስኪን ሰውዬ ሳይቸግረው ለሚስቱ “ድንች እኮ በጣም ነው የምወደው!” ብሏት ሰባት ቀን በተከታታይ ድንች ስትቀልበው እንደሰነበተችው እኛ አፍ አውጥተንም ባይሆን በምልክት “የትናንት ጎሲፕ እንወዳለን!” ያልን ይመስል በተለይ በ‘ቦተሊካው’ ዝም ብላችሁ ሰባት ቀን ድንች አይነት ነገር አታድርጉብና! “የማይቀርልህን እንግዳ አጥብቀህ ሳመው” እንደሚባለው ያልተደራጀም ሆነ የተደራጀ የሚመስል ‘ጎሲፕ’ የማይቀርልን ትንሽ ‘ከለር’ ነገር ይጨመርበታ!
ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ
ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ፤
አሪፍ ነገርዬ ነበረች፡፡ ምን ያደርጋል የዘፈን ስንኝ ሆና ቀረች እንጂ! “ነግ በእኔ...” የምትለው ነገር ከሀገር ጥላ የተሰደደችበት ዘመን ሆነና እዚህ ቦታ ላይ የምንታማው ሰዎች እዛ ቦታ ላይ ዋነኞቹ ’ጎሲፕ ኢን ቺፍ’ ምናምን ሆነን ቁጭ ነው፡፡
ለወሬ የለውም ፍሬ ሲባል አልሰማህም ወይ
እከሌ አንተን ያማሀል ቢሉህም ምን ይሰማሀል፤
ይባል የለ...
ምን መሰላችሁ...አለ አይደል...መቸስ ዘንድሮ ሀሜት የሚባለው ነገር ወደ ኢንደስትሪ ደረጃ ያደገ ይመስላል፡፡ አሀ ልከ ነዋ...እነ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክ ቶክ፤ ትዊተር...ምናምን የመሳሰሉት ሁሉ አሁን አሁን ዋነኞቹ የጎሲፕ ‘ትራንስናሽናል ኢንደስትሪ‘ ሆነው የለ እንዴ! ቁም ነገር ፍለጋው በራሱኮ አዳጋች እየሆነ ነው። ስሙኝማ...ጎሲፕዬው ምን ያህል ግሎባላይዝ ምናምን እንደሆነ ለማወቅ በዩክሬይኑ ጦርነት በኩል ከምዕራባውያኑ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ሰዎች የሚነገሩትን እህ ብላችሁ ስሙ፡፡ አንድ ሰሞን “ፑቲን ደረጃ አራት ካንሰር ይዞታል፡” “የሩስያው መሪ አእምሮ መቃወስ ገጥሞታል፣ ይባል የነበረው እኮ በእንትን ሰፈር አፕሬቲቭ ቤት ሳይሆን... በባለጡንቻዎች ምዕራባውያን ሚዲያዎች ነው፡፡ እናማ... ፌክ ኒውስ ይሁን ምናምን  ያው ሀሜት ነው፡፡
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እዚች ሀገራችን ላይ አንዳንዶቻችን እንደልባችን የፈለግነውን ለመናገር፣ እንደልባችን ምስኪን ምስኪኑን  ከ“አንተ ምናምን!” በማይሻሉ ስሞች ለመጥራት የተለየ ፈቃድ አለን እንዴ! ኮሚክ እኮ ነው...በተለይ እኛ ዘንድ  ‘ጥይት ቦተሊከኝነት’ በሀሳብ ጥልቀትና ምጥቀት ሳይሆን አሪፍ፣ አሪፍ ‘ያኛውን ወገን’ ልክ ማስገቢያ ቃላትን በማወቅ ሊመስል ምንም አልቀረው፡፡ አሀ፣ ፌይር አይደለማ... “ልክ፣ ልኬን አጠጣችኝ፣ ልክ ልኳን አጣጣኋት...” እንዳለው ቲራቲረኛ ምላሽ የመስጠት ዕድል የለበትማ!  (“ዕድል! ጭራሽ መልስ የመስጠት ዕድል ትፈልጋላችሁ!” ሊሉ የሚችሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሊታሰብ ይችላል። ቂ...ቂ...ቂ...)  
“ስማ፣ ስለእንትና ሰማህ?”
“ምነው፣ ምን ሆነ?”
“እኔ እሱ ሰውዬ ግን ሥራው ምን እንደሆነ ግርም ብሎኛል፡፡”
“እኮ፣ ምን አደረገ?”
“እንደ ጉድ የምታብረቀርቅ ኤክስኪዩቲቭ አይገዛ መሰለህ!”
“አትለኝም!”
“የሚገርም እኮ ነው፣ ኑሮ ከበደኝ እያለ አንድ ድስት ሹሮ ሰባት ቀንና ማታ ሲበላ የሚሰነብት ሰውዬ በምን ተአምር ነው ኤክስኪዩቲቭ ሊገዛ የሚችለው! የሆነ ነገር ቢኖር ነው እንጂ!”
ከዛላችሁ... የፊልም ሰዎች እንደሚሉት፤ እሱዬው ወሬውን ‘ኢን ሪል ታይም’ ሲተረክልን ስናዳምጥ ቆይተን እንለያያለን፡፡ ከዛ ደግሞ እኛ በተራችን ሌላኛው ወዳጃችንን እናገኛለን፡፡
“ስማ ያ እንትና በቃ እንዲህ የለየለት ወሬኛ ሆኖ ቀረ ማለት ነው?”
“ደግሞ ስለማን አወራ?”
“ያ እንትና....ኤክስኪዩቲቭ ገዛ ብሎ አገሩን እያደረሰው ነው፡፡ እሱ ሰውዬ የሰው ስም በየቦታው እያነሳህ ካልጣልክ ደርቀህ ትቀራለህ የሚል ግዝት ምናምን አለበት እንዴ!”
“የአንዳንድ ሰው ጠባይ እንዲህ ነው፣ ምን ታደርገዋለህ፡፡”
“ስማኝማ... የእውነት ግን የእነትና ኤክሲኪዩቲቭ መግዛት ግርም አላለህም!”
ጎሽ ጎሽ! እንዲህ ነው እንጂ፡፡ እናላችሁ ...ስለ እከሌ የሆነ አሉባልታ ነገር ስንሰማ ቆይተን ስናበቃ፣ አውሪውን በወሬኛነት ኮንነነው ስናበቃ፣ እሱ ያለውን ለሌላ ደግሞ መንገር...ለምን ይዋሻል... የብዙዎቻችን ልማድ ትመስላለች፡፡ እኛው ወቃሾች፣ እኛው ተወቃሾች!
አንዱ ለወዳጁ የሆነ ነገር ”አደራ ምስጢር ነው፣” ብሎ ይነግረዋል፡፡ በስንተኛው ቀን ሲገናኙ ምስጢር የተነገረው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው... “አታስብ እኔ ምስጢርህን እንደራሴ ምስጢር ነው የምጠብው፡፡ የነገርኳቸው ሰዎች ሁሉ ለሌላ ትንፍሽ እንደማይሉ ምለውልኛል፡፡”
ይቺን ስሙኝማ....ሦስት የሆነ እምነት ሰባኪዎች ናቸው አሉ፡፡  አንድ የእረፍት ቀን አብረው ሽርሽር ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አንደኛው እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ብቻችንን ከፈጣሪ ጋር ነው ያለነው፡፡ ስለሆነም ዋነኛ ሀጢአታችንን ማንም ሰው ሳይሰማን ለፈጣሪ መንገር እንችላለን፡፡ ምናልባት ይቅርታ እናገኝ ይሆናል።”
ሁለቱም ይስማሙና፤ እሱው ይጀምራል፡፡ “እኔ ቅልጥ ያልኩ የአልኮል ሱሰኛ ነኝ፡፡ በጸሎት ቀን ሁልጊዜ ስብከቴን ቶሎ ጨርሼ ወደ መጠጥ ቤት ለመሮጥ ነው የምጣደፈው፣” ይላል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ... “እኔ የሴቶች ችግር ነው ያለብኝ፡፡ ስብከቴን በጥድፊያ ጨርሼ ወደ ቡና ቤት መሄድ ነው የምፈልገው፡፡”
የሁለቱን የሰማው ሦስተኛው ምን ቢል ጥሩ ነው... “እኔ ደግሞ ሀሜት ማውራት በጣም እወዳለሁ፡፡ አሁን መቼ ከዚህ ሄደን የነገራችሁኝን ሁሉ ለሌሎች እስክናገር አላስችል ብሎኛል፣” ብሏቸው እርፍ!
ህይወት ካለው ፌስቡክና ኢንስታግራም ይሰውራችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1327 times