Saturday, 25 February 2023 12:30

የልጅነት ህልማቸውን ያሳኩት ባለሃብት!

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  “በሀገራችን ጉዳይ ላይ ቀድመን ነው የምንገኘው”


          በጉራጌ  ዞን ሶዶ ወረዳ ከሱተን ከተማ ገባ ብላ በምትገኝ “ጨላ” በተሰኘች መንደር ተወለዱ። የአራት ዓመት ህጻን እያሉ አባታቸውን በሞት አጡ። የአባታቸው አክስት እሳቸውንና ወንድማቸውን ይዘው ለማሳደግ ወደ ባሌ ዶዶላ ከተማ ሄዱ። ዶዶላ ለ6 ወራት ብቻ እንደቆዩ ከአባታቸው ወንድም ጋር ወደ አዲስ አበባ መጡ። ከዚህ እድሜያቸው ጀምሮ በአዲስ አበባ ነው ያደጉትም ሆነ የኖሩት - ደግና ክፉውን ያዩት። የልጅነት ህልማቸውን እውን ያደረጉትም በዚህችው ከተማ ነው። የዛሬው እንግዳችን አቶ ሲሳይ ተስፋዬ ኢንቨስተር ናቸው፡፡ ብዙ ፈተናና ውጣ ውረዶችን አልፈው ስምንት ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው “ሲሳይ ኢንቨስት ግሩፕ” ባለቤትና ማኔጅንግ ዳይሬክተር ለመሆን በቅተዋል። ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረጉት ቆይታ ብዙ አውግተዋል። ባሳለፉት ህይወትና ዕድሜ የተጋፈጧቸውን ተግዳሮቶች ብቻ ሳይሆን ያሳኳቸውን ህልሞችም አጋርተዋታል። ቃለ-ምልልሱ እንደሚከተለው ቀርቧል። እነሆ፡-           ጨዋታችንን ከአስተዳደግዎና ከትምህርትዎ እንጀምር…
የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ ኮሜርስ ተመድቤ በዲፕሎማ ተመረቅኩ። በደርግ ጊዜ የስራ ምደባ ነበርና፣ በእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት መልካ እርሻ ምርምር ተመድቤ አራት ዓመት ካገለገልኩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተቀይሬ መጣሁ። አዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት እየሰራሁ ሳለ፣ እንደገና ወደ ክፍለሀገር ሄጄ እንድሰራ ቅያሬ ሲመጣ አሁን እንኳ አልሄድም ብዬ፣ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ በ1985 ዓ.ም ፊቴን ወደ የግል ድርጅት አዙሬ ተቀጠርኩኝ።
የት ነበር  የተቀጠሩት?
“ናትራን ፕላስቲክ ፋብሪካ” ነው የተቀጠርኩት። በዚህ ፋብሪካ ለ6 ዓመታት በስራ አስኪያጅነት ካገለገልኩ በኋላ ታዲያ ቀድሞም ቢሆን በኢንቨስትመንት ዘርፍ የመሰማራትና ባለፋብሪካ የመሆን ህልም ነበረኝና የራሴን ፋብሪካ ከፈትኩ። ትምህርቴንም ቢሆን በችግር ምክንያት ስለነበር በዲፕሎማ ደረጃ የተማርኩት፣ ስራዬን እየሰራሁ ዲግሪዬንም ማስተርሴንም ለመያዝ ችያለሁ። አሁን በማስተርስ ኦፍ ቢዝስ አድሚኒስትሬሽን (MBA) ተመርቄአለሁ።
ከስድስት ዓመት የቅጥር ሥራ በኋላ የራሴን ፋብሪካ ከፈትኩ ብለው ቀለል አድርገው ነው የነገሩኝ። ከቅጥር ወጥቶ የራስ ፋብሪካን መጀመር ግን ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። እስቲ የራስዎትን ፋብሪካ የጀመሩበትን ሂደት ይንገሩኝ?
ልክ ነው! ውጣ ውረድ አለው። የመጀመሪያው ፋብሪካችን “ቤስት ፕላስቲክ ፋብሪካ” ይባላል። ስለ “ቤስት ፕላስቲክ ፋብሪካ” ማውራት በጣም ነው የሚያስደስተኝ። ለዚህም፤ ምክንያት አለኝ። ቤስት በትክክል ስራ የጀመረው የዛሬ 24 ዓመት ነው። ናትራን ፕላስቲክ ፋብሪካ ተቀጥሬ ስሰራ መጀመሪያ በፋይናንስ ማኔጀርነት ነበር የገባሁት። ነገር ግን አንድም ቀን አልሰራሁበትም፤ ምክንያቱም ሌላ ሰው አልነበረም። እኔና ባለቤቱ ብቻ ስለነበርን ወዲያውኑ ነው ስራ አስኪያጅ  የሆንኩት። ነገር ግን ሎጂስቲክሱንም፣ ፋይናንሱንም ጀነራል ማኔጀርነቱንም… ሁሉንም ነገር እኔ ነበርኩ የምሰራው።
ገና ልጅ ሳለሁ ጀምሮ “ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?” ስባል፤ “ባለ ፋብሪካ” ነበር የምለው። አስቢው በደርግ ጊዜ እንግዲህ የግል ፋብሪካ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ያሳደገኝ አጎቴ “አንተ ሞኝ” እያለ ይመታኝ ነበር። ለምን መሰለሽ? ያን ጊዜ ባለፋብሪካ የሚሆን ግለሰብ አልነበረም። የኔ ታናሽ ወንድም ደግሞ “ኢንጂነር ነው የምሆነው” ይል ነበር። አሁን እሱ ኢንጂነር ነው፤ እኔ ደግሞ ኢንዱስትሪያሊስት ነኝ ማለት ነው።
እርስዎ ታዲያ ከምን ተነስተው ነበር ባለፋብሪካ መሆን የተመኙት?
ስለ ፋብሪካ፣ በአጠቃላይ ስለ ኢንዱስትሪ መጽሐፍ አነብ ነበር። ልጅ ሆኜ የማነባቸው መጻህፍት የሚገርምሽ ስለፋብሪካና ተያያዥ ነገሮችን የያዙ ናቸው። ስለ ኢንዱስትሪ በደንብ  አነብ ነበር። ባለኢንዱስትሪ የመሆን ፍላጎት ያደረብኝ ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነበር። ታዲያ እዚህ ፕላስቲክ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሬ ስገባ ባለፋብሪካ እንደምሆን እርግጠኛ ሆንኩኝ። በዚያ በተቀጠርኩበት ፋብሪካ ውስጥ 8 ሰራተኞች ብቻ ነበርን። ሰባቱ የፕሮዳክሽን ሰራኞች ሲሆኑ ማኔጅመንት ውስጥ እኔ ብቻ ነበርኩኝ። ስለዚህ እዚያ እያለሁ 300 ብር እቁብ መሰብሰብ ጀመርኩኝ። የመጀመሪያውን እኔ ወሰድኩና ጊዜ ሳላጠፋ ወዲያውኑ ወደ ስራ ገባሁ። ተመልከቺ የስምንታችን 300 ብር አንድ ላይ 2ሺ  አንድ መቶ ብር ብቻ ነው እቁቡ። እሱን ብር አጠራቅሜ ከምሰራበት ፋብሪካ ጀርባ “የሳሙና ፋብሪካ እንገነባለን” የሚል ማስታወቂያ አይቼ ስለነበር፣ ያንን 2 ሺህ አንድ መቶ ብር ይዤ መርካቶ የ10ሺህ ምናምን ብር እቁብ ገባሁ። እቁብ ስገባ እኔ ገንዘብ ስለሌለኝ ቅድሚያ ትሰጡኛላችሁ ብዬ ነገርኳቸው። የመጀመሪያውን እቁብ ወስጄ፣ 8ሺህ ብር የሳሙና ፋብሪካ እንገነባለን ለሚለው ድርጅት ሰጠሁት። ሰውየው ብሩን በላኝ። በቃ ተበላሁ እልሻለሁ። ከዚያ በኋላ ወለቴ አካባቢ በ10 ሺህ ብር  ከገበሬ መሬት ገዝቼ ነበር። እውቀት ስለሌለኝ እሱንም “ህገ-ወጥ” ተብዬ ተቀማሁ። ተበሳጨሁ፡፡ ፍርሃት ሁሉ ያዘኝ።
መቼም አጋጣሚው ለአንድ ወጣት ባለራዕይ ተስፋ አስቆራጭ ይመስላል?
እውነት ነው። እኔ ግን ስራዬን መስራት ቀጠልኩ። እዚያ የተቀጠርኩበት ፋብሪካ ስድስት ዓመት ስሰራ ጠዋት 12 ሰዓት እገባለሁ፤ ፋክስ ማድረግ ካለብኝም ሆነ ሌሎች የቢሮ ስራዎቼን እስከ 3 ሰዓት እሰራና ከዚያ በኋላ ጉምሩክም ሆነ ሌሎች ቦታዎች ያሉኝን ስራዎች ስሰራ ቆይቼ፣ ማታ 11 ሰዓት እገባና እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት እሰራለሁ።
የተጨማሪ ጊዜ ክፍያ ያገኙ ነበር ወይስ?...
እንኳን  የተጨማሪ ሰዓት ክፍያ  ሊኖረኝ የደሞዝ ጭማሪ እንኳን ጠይቄ አላውቅም። በቃ ለስራው ካለኝ ፍቅር ብቻ ነው ይህንን የማደርገው። በነገራችን ላይ መንግስት ቤት ስሰራም እንደዚሁ ነበር። እኔን እዚህ ደረጃ አደረሰኝ ብዬ የማምነውም ያለኝ ጠንካራ የሥራ ባህል ነው፡፡ ስራ ካለኝ ለምን አይነጋም ሳልጨርስ አልወጣም፤ በዚህ እታወቃለሁ። ብቻ ስራውን እውቀቱን ነበር የምፈልገው። የእውቀት ሀብት አከማችቼ ነው የወጣሁት። ስራ  ስቀጠር 5 መቶ ሃምሳ ብር ጠይቄ፣ ባለቤቱ 4 መቶ ሃምሳ ብር እከፍልሃሁ አለኝ። እሺ አልኩት። በኋላ ግን እኔ የጠየቅኩትን ነበር የከፈለኝ። ስድስት ዓመት ስሰራ ደሞዜ መጨረሻ ላይ 1ሺህ 300 ብር ነበር የነበረው። ያንን ፋብሪካ ትልቅ አደረግኩት። ሰራተኛውም ከ8 ወደ 300 እና 400 አደገ። እኔም በትርፍ ሰዓቴ የሂሳብ ባለሙያነት ሥራ ጀመርኩኝ። የብዙ ኩባንያዎችም ኤጀንት ሆንኩኝ፡፡ ጥሬ እቃ ማስመጣት፣ ማሽነሪ ማስመጣት ላይ እውቀቱ ስለነበረኝ ያንን እየሰራሁ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠብ ቻልኩኝ። ይህን ገንዘብ ከያዝኩ በኋላ ለምን ፕላስቲክ ፋብሪካ አልከፍትም ስል፣ ኤጀንት የሆንኳቸው ኩባንያዎች፣ “እናግዝሃለን ማሽንም በዱቤ እንሰጥሃለን” አሉኝ። ያጠራቀምኩት ገንዘብ በእርግጥ ብዙ ነው፤ ነገር ግን አይበቃም። ሆኖም  ማሽን በዱቤ አገኘሁ፤ ተበረታታሁ፡፡ ዓለም ገና ላይ የመጀመሪያውን “ቤስት ፕላስክ ፋብሪካ”ን ከ24 ዓመት በፊት ከፈትኩ።
በነገራችን ላይ ይህ ፋብሪካ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ሰበታና ዓለም ገና ላይ የመጀመሪያው ፋብሪካ ነው። ያንንም አካባቢ ከግብርናና ከወተት ልማት ወደ ኢንዱስትሪ መንደርነት ያስለወጥኩት እኔ ነኝ። ያን ጊዜ አካባቢው በአምቦ ስር ነበር የሚተዳደረው። በአሁኑ ወቅት ዓለም ገና ሰበታ ውስጥ ሲሆን፤ ወደ 1 ሺህ 600 ፋብሪካዎች አሉ። የዚያ አካባቢ አይን ገላጭ ፋብሪካ ግን “ቤስት ፕላስቲክ ፋብሪካ” ነው። ያኔ አካባቢው እርሻ ብቻ ነበር።
የዛሬ 24 ዓመት የፋብሪካው ኢንቨስትመንት ምን  ያህል ነበር? ስንት ሰራኞች ይዘው ጀመሩ? አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው?
እንግዲህ ያን ጊዜ ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት ነው የዞርኩት። በወቅቱ ሰባት ወይ ስምንት ሰዎችን ይዤ በቆርቆሮ  ቢሮ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ የመጀመሪያውን ደሞዝ ለሰራተኞች ስከፍል አልቅሻለሁ። የምሬን ነው የምልሽ፤ ለቅሶው የደስታና እግዚአብሔርን ማመስገኛ ነው። ያን ቀን ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት የተሸጋገርኩበት አዲስ ምዕራፍ እውን የሆነበት ነው። ያንን ጊዜ መቼም አልረሳወም። ለምን ብትይኝ… ሰራተኛ ቀጥሬ፣ የስራ እድል ፈጥሬ ወደ ምኞቴ ጅማሮ ስለገባሁ ነው። አብዛኞቹ ያኔ ከኔ ጋር የነበሩት አሁንም አብረውኝ አሉ። ኢንቨስትመንቱ 1.3 ሚሊዮን ብር ነበር።
ከ”ቤስት ፕላስቲክ” ቀጥሎ የትኛው ፋብሪካ ተወለደ?
እውነት ለመናገር “ቤስት ፕላስቲክ” ሁሉንም ድርጅቶች የወለደ አባት ኩባንያ ነው። ሌላው ቢቀር እኔንም የፈጠረ ነው ማለት ትችያለሽ። ለዚህ ነው ስለቤስት ተናግሬ የማልጠግበው። እንደነ ዋሊያ ብረታ ብረት ያለ ግዙፍ ኢንዱስትሪ የፈጠረ፣ እኔንም እንደ ሰው በሳልና ጠንካራ ያደረገ ድርጅት ነው ቤስት። ብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ስቃይ፣ ብዙ ድካም ያየሁበት ነው። በወቅቱ በአካባቢው ውሃ የለም፣ መብራትም አልነበረም። መብራት ዘጠኝና አስር ኪሎ ሜትር እየሳብኩ ነበር የምወስደው። ውሃ አራት አምስት ኪሎ ሜትር ሄደሽ ነው የምታገኚው። ደግነቱ ያን ጊዜ ብዙ ነገር እርካሽ ነበር። ኢንቨስትመንትም ይበረታታ ነበር። እንደዛም ሆኖ ውጣ ውረዱ ከባድ ነበር።
የራሴን ጽናትም እንዳይበት ያደረገኝ ነው፤ ቤስት ፕላስቲክ ፋብሪካ። ከዚያ በኋላ ትልቁ ዋልያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በ200 ሚሊዮን ብር ተከፈተ። ከ18 ዓመት በፊት ማለት ነው። በእኛ አቆጣጠር በ1997 ዓ.ም ነው። ይህ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በተለይ በግል ዘርፉ የመጀመሪያና ፈር ቀዳጅ ነው።  
በሀገራችን ብዙ የውጪ ምንዛሬ ከሚያስወጡን የግንባታ ግብአቶች መካከል ብረት አንዱና ዋንኛው ነው። ከዚህ አንጻር ዋልያ ብረታ ብረት ምን ያህል አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ይላሉ?
በጣም ብዙ አስተዋጽኦ ነው ያለው። ሌላው ቀርቶ በተወሰነ ደረጃ ወደ ሱዳንም ኤክስፖርት እናደርግ ነበር። የውጪ ምንዛሬን በከፍተኛ ደረጃ ከማዳኑም በላይ በኤክስፖርትም የውጪ ምንዛሬ የሚያመጣ ነው። እኛ ጥሬ እቃ ብቻ ነው ከውጭ የምናመጣው። ያለቀለት እቃ እና ጥሬ እቃ አንድ አይደለም። ሁለተኛ የሥራ እድል ፈጥረናል። በሦስተኛ ደረጃ የቴክኖሎጂ ሽግግር አድርገናል። ስለዚህ ዋልያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የገቢ ምርትን ከመተካት አልፎ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። በሌላ በኩል፤ እኛ ፈር ቀዳጅ ሆነን በዘረጋነው አርአያነት በአሁን ወቅት ከ20 እና 30 በላይ ብረታ ብረት ፋብሪካዎች ተቋቁመዋል። ከመቶና ሁለት መቶ በላይ ፕላስቲክ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል። እነዚህ ታዲያ በሚሊዮን የሚቆጠር የስራ እድል ፈጥረዋል። የውጪ ምንዛሬን አድነዋል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር አድርገዋል። ከዚያ ባለፈ ከእኛ ጋር እየሰሩ ልምድና እውቀት አዳብረው የራሳቸውን ፋብሪካ የከፈቱ አሉ። ይሄ ደስታ ይፈጥርልናል። ዋልያ እንግዲህ 800 ሺህ ቶን ብረት በዓመት የማምረት አቅም ያለው፣ በኢትዮጵያ ትልቁ ኢንዱስትሪ ነው። በምስራቅና በምዕራብ አፍሪካ ምርጥ አምስቶቹ ውስጥ ያለ ፋብሪካ ጭምር ነው። ነገር ግን በሃይል አቅርቦት እጥረት፣ በተለይ በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የአቅሙን ያህል ማምረት እየቻለ አይደለም እንጂ ቢያመርት የኢትዮጵያን ገበያ ሸፍኖ ወደ ውጭ መላክ ሁሉ ይችል ነበር። በጣም በትንሽ አቅም ነው እያመረትን ያለነው።
መንግስት በሀገር ግንባታ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና የውጪ ምንዛሬን በማዳን ትልቅ አቅም ላላቸው ኢንዱስትሪዎች በተለይ የውጪ ምንዛሬን በማቅረብ ረገድ ሃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት ይቻላል?
በኔ አረዳድ መንግስት ኢንዱስትሪውን ለማበረታታት ጥረት ያደርጋል። አሁን የፋብሪካዎች መብዛት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና ፍላጎት ያለመመጣጠን ችግር ካልሆነ በስተቀር መንግስት የራሱን ጥረት ያደርጋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስትም ባለሃብቱም ባለሙያውም በትብብር ጥናት አድርገውና ስትራቴጂ አውጥተው፣ መፍትሄ መፈለግ አለባቸው እላለሁ፡፡
ከዋሊያ ብረታ ብረት ፋብሪካ  ቀጥሎ የትኛው ፋብሪካ ተወለደ?
ቀጥሎ የተወለደው “ቤስት ፔይንት” የተሰኘው የቀለም ፋብሪካ ነው። ከዚያም ቡና የምንልክበት ኩባንያ ተፈጠረ፡፡ አሁን ላይ ሪል እስቴት መጥቷል። ወደ 300 ቪላዎች ለመስራት አቅደን አሁን ላይ 31ዱን እያጠናቀቅን ነው። ኮንስትራክሽን ኩባንያም መሥርተናል። በቅርቡ ከጄ ደብሊው ማሪዮት ጋር ተፈራርመን ካዛንቺስ ላይ ባለ5 ኮኮብ ሆቴል እየሰራን ነው። “ሊ ሜሪዲያን” ይሰኛል ሆቴሉ፡፡ በ7ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው። ማኔጅመንቱን እነሱ ናቸው የሚይዙት። ይህ ሆቴል በእቅዳችን መሰረት ጃንዋሪ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ይከፈታል ብለን እንጠብቃለን።
ትምህርት ቤቱን ስናስመርቅ እንዳየሽው፣ ቡኢ ላይም እንዲሁ ሁሉን ያካተተ የምግብ ኮምፕሌክስ ለመገንባት መሬት ወስደን፣ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠናል። ይህ ኮምፕሌክስ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ስራ ይጀምራል የሚል እምነት አለን። ሱተን ውስጥ የዶሮ እርባታና ዶሮን ፕሮሰስ አድርጎ ለገበያ የሚያቀርብ የዶሮ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ለመገንባት 5 ሄክታር መሬት ወስደን እየተንቀሳቀስን ነው። ይህን ሁሉ ለምንድነው የከፈትከው ብትይኝ፣ ገንዘብ ለእኛ ሁለተኛው ነው፤ ዋናው ግን የምንሰራው ሥራ ማህበረሰቡን ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው ነው። ለምሳሌ ቢል ጌትስን ብትመለከቺ፣ ሥራዎቹ ማህበረሰብ ተኮርና ህዝብን የሚጠቅሙ ናቸው። እኛ አንደኛና ቀዳሚ የምናደርገው፣ ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ ስራዎች መሆናቸውን ነው።  እንደምታይው የኑሮ ወድነትና የምግብ እጥረት አለ። ብዙ ሰው እየተቸገረ ነው። ቢያንስ እኛ የምንከፍተው የምግብ ኮምፕሌክስ በውስጡ የሚይዛቸውን ሰራተኞች ሳይጨምር ለበርካቶች ቁም ነገር ይሰራል ብለን እናምናለን። እኔ ሳድግ ዳቦ 10 ሳንቲም ነበር የሚሸጠው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወይ ከ20 ዓመት በፊት ጤፍ በኩንታል 200 ብር ነበር። አሁን ደግሞ 7ሺህ ብር ገብቷል። ህዝቡ ያለበት ሁኔታ በእጅጉ ያሳዝነኛል።  በጣም ነው የሚያመኝ። ይህን ስመለከት ለህብረተሰቡ አንድ ዶሮን በ50 ብር መሸጥ አለብኝ የሚል ቁጭት አድሮብኛል። ለሰው ልጅ ምግብ ችግር መሆን የለበትም።  በውጪው  ዓለም ዳቦና ዶሮ እርካሽ ነው። I want to make it in Ethiopia! ስለዚህ እነዚህ ሁለቱ ፕሮጀክቶች ማለትም የዶሮ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪውና የምግብ ኮምፕሌክሱ ዋና አላማቸው ማትረፍ ሳይሆን፤ እዳቸውን ችለው የሰራተኛ ደሞዝና መሰል ወጪ ሸፍነው ብቻ የህብረተሰቡን ችግር ማቅለል ነው። ሰው በጭራሽ መራብ የለበትምና፣ ጡረታ ከመውጣቴና ከመድከሜ በፊት እነዚህ ነገሮች እውን ሆነው ማየት እፈልጋለሁ።
እቅዴ ብዙ ነው። ለጊዜው ምስጢር ነው። እንጂ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ትልቅ ፕሮጀክትም አለኝ። የዘይት ፋብሪካው ከምግብ ኮምፕሌክሱ ጋር አብሮ ተቀናጅቶ የሚሰራ ሥራ ነው።
በእነዚህ ሁሉ ኩባንያዎች ምን ያህል ዜጎች እንጀራ ተከፈተላቸው?
የፋብሪካዎቻችን የመቅጠር አቅም ወደ ስድስት ሺህ ያህል ነው። ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በውጪ ምንዛሬ እጥረትና በጥሬ እቃ እጥረት ፋብሪካዎቻችን መስራት ከሚችሉት በታች ነው የሚሰሩት። አሁን ባሉበት ሁኔታ ግን የቀን ሰራተኞችን ጨምሮ 2ሺህ 500 ያህል ሰራተኞች አሉን።
አሁን ያለውን የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ለአገርዎ ምንድን ነው የሚመኙላት?
እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ በጣም ታሳዝናለች፤ እጅግ በጣም! እኔ እንደነገርኩሽ ከ4 ዓመቴ ጀምሮ እዚሁ አዲስ አበባ ነው ያደግኩት፤ 52 ዓመት ሙሉ እዚሁ ነኝ። የአዲስ አበባ ልጅ ነኝ። እኛ ስናድግ በኢትዮጵያ አንድነትና ፍቅር ነው ያደግነው። እኛ ስናድግ ጎረቤታችን ማን ነው? ምንድነው? ብለን ጠይቀን አናውቅም፤ ትዝም አይለንም፤ እርስ በርሳችን በጣም እንዋደድ ነበር። ስናጠናም አንዱ ቤት ተሰብስበን ነበር የምናድረው። ያን ጊዜ  ሰው መሆናችንና ኢትዮጵያዊያን እንደሆንን እንጂ ሌላ ክፍፍል አናውቅም ነበር። ስለዚህ እኔ በህይወት እያለሁ ያ የቀድሞ አንድነታችን መጥቶ ማየት እፈልጋለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ በልቶ የማያድር ህዝብ አለን። ይህ ህዝብ በልቶና ጠግቦ፣ ባይጠግብ እንኳን ቢያንስ ከረሀብ ተላቆ ምግብ እንደ ችግር የማይቆጠርበት ሀገር ሆኖ ማየት እፈልጋለሁ። እኔ ከማለፌ ወይም ከመድከሜ በፊት እነዚህን ነገሮች ነው በሀገሬ ማየት የምፈልገው። ሀገሬ ይሄ ሁሉ ምስቅልቅሏ ተወግዶ አንድነቷ ተመልሶ ማየት፣ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ ችግር የማይሆንበትና ሁሉም በልቶ የሚያድርበት ሀገር ሆኖ ማየት!!
በሌላ በኩል፤ በኢኮኖሚውም መካከለኛ ገቢና ከዚያ በላይ ያላት ሀገር ሆና በየትኛውም ቦታና ጊዜ “ኢትዮጵያ” ሲባል በኩራት አንገታችንን ቀና አድርገን የምንታይባት ሀገር ሆና ማየት እሻለሁ እመኛለሁ። መመኘት ብቻ አይደለም፤ እኔ ለዚህ የምችለውን በማድረግ አስተዋጽኦ አደርጋለሁ። ሌላውም እንግዲህ በሀብት ከኔ የሚበልጡም አሉ። ባለሀብቱም፣ ፖለቲከኛውም፣ ባለሥልጣኑም፣ ምሁሩም ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ ስራውን በአግባቡ ከሰራና ሃላፊነቱን ከተወጣ የምንፈልገው ሰላም፣ አንድነትና እድገት የማይመጣበት ምክንያት የለም። አሁን በሁሉም ቦታና ሁኔታ ሥርዓት እየጠፋ፣ ግብረገብነት እየሸሸ ነው፤ ይሄ ሁሉ ችግር የመጣው። ሀገር የምታድገው በሥራ ብቻ ሳይሆን ሥነምግባርን በማክበር ነው። እዚህ አገር ላይ ህግና ሥርዓት በአግባቡ መከበር አለበት እላለሁ።
በቅርቡ በሱተን ከተማ በ31 ሚ. ብር ለአካባቢው ማህበረሰብ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገንብተው አስመርቀዋል። ይህ እንደ አካባቢው ተወላጅም እንደ ባለሃብትም ማህበራዊ ሃላፊነትዎን ለመወጣት ከሚያከናውኗቸው ስራዎች አንዱ ነው፡፡ በዚህ በኩል ሌሎችም በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ እሰማለሁና ቢያጫውቱኝ?
በቅርቡ ያስመረቅኩትንና አንቺም ምረቃው ላይ የተገኘሽበትን ት/ቤት የማስመረቅ ምንም ፍላጎት አልነበረኝም። ት/ቤቱ አልቆ ስራ ከጀመረም ሰንበትበት ብሏል። ሲጎተጉቱኝ እምቢ ስል ቆይቼ የአካባቢው ሰው “እንረግምሃለን” ሲሉኝ ነው እንደገና ይሁን ብዬ ያስመረቅኩት። እኔ ማንኛውንም መልካም ነገር የምሰራው ለሚዲያ ፍጆታ ሳይሆን ለውስጤ እርካታ ነው። ደግሞ ሃላፊነትም አለብን፤ ግዴታችን ነው። የሰው ልጅ የመጨረሻ ስኬቱ ራሱን መለወጥ አይደለም። እንስሳ ብቻ ነው ለራሱ በልቶ የሚሞተው። ስለዚህ ስራ እየሰራሽ ስታድጊ የተፈጠርሽበትን ህዝብና አካባቢ መለስ ብለሽ ማየት አለብሽ። አሁን እኔ በንግድ ካፈራኋቸው ኩባንያዎች ይልቅ እንደ ሱተኑ ት/ቤት አይነት ንብረቶች ናቸው የሚያስደስቱኝ። እርካታም የሚሰጡኝ ጭምር። እኔ ባልፍም ስሜን የሚያስጠሩት እንደ ሲሳይ ተስፋዬ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አይነቶቹ ተቋማት እንጂ ሌላው ኩባንያ ይጠፋል። ምክንያቱም ህብረተሰቡ ከዚያ ት/ቤት ወጥቶ የሀገር መሪ፣ መምህር፣ ፖለቲከኛ ከያኒ ሌላም ሌላም እየሆነ ይቀጥላል።
እርግጥ ት/ቤቱ ብቻ አይደለም፤ በየቦታው በርካታ ነገሮች ሰርተናል። ለምሳሌ እዚህ ዋና መሥሪያ ቤታችን አካባቢ ውሃ ቆፍረን አውጥተን በቀን አራትና አምስት ሺህ ሰው ውሃ ይቀዳል። ሪል እስቴታችን አካባቢም ውሃ አውጥተን፣ ህዝቡ እንደልቡ ይጠቀማል፡፡ አለምገና ቤስት ፕላስቲክ ያለበት ቦታ ላይ ያወጣነውን ውሃ፣ 24 ሰዓት የአካባቢው ሰው እየቀዳ ይጠቀማል፤ በቀን ከ10ሺ በላይ ሰው ነው ውሃ የሚቀዳው። ይሄ ቀላል አይደለም። ሱተን አካባቢ መንገድ ሰርተን አስረክበናል፤ አለምገና ዳለቲ የሚባል ቦታ የትምህርት ቤት ብሎኮችን ሰርተን ሰጥተናል። በተለያየ ጊዜ እርዳታ እንሰጣለን። ለኮሚኒቲ ፖሊሲ ቤት ሰርተን ሰጥተናል። በገበታ ለሀገርና ገበታ ለሸገር ሲባል በፈቃደኝነት ቀዳሚ  ሆነን ከራሳችን አልፎ ሌሎችን በማስተባበር ጭምር ድጋፍ አድርገናል። በሀገራችን ጉዳይ ላይ ቀድመን ነው የምንገኘው። ይህንን ተግባር ከቢዝነሱ እኩል ሥራና ባህል አድርገን ይዘነው ነው የምንጓዘው፡፡ እንደ እኛ አይነት ሰው ሰርቶ ከተሳካለት በውዴታ ደስ ብሎት ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣት አለበት። የበለጠ በረከትና ስኬት ያመጣል እንጂ አያከስርም። ገንዘብ ካልተጠቀምሽበት ወረቀት ነው።
ከዚያ ደግሞ ነገ ጥለሽው ትሄጃለሽ። ስለዚህ ሰው ባገኘው አጋጣሚ ጥሩ ሰርቶ አሻራ አስቀምጦ ማለፍ አለበት።
በት/ቤቱ ምረቃ እለት እየጠፉ ካሉ የቀድሞ ማዕረጎች አንዱ የሆነውን የቢትወደድነት ማዕረግ፣ ከእነባለቤትዎና ከእናትዎም ጭምር ካባና ሽንጠ ረጅም ፈረስ ከነጌጣጌጡ ህዝቡ ሸልምዎታል። ምን ተሰማዎት? ለመሆኑ ፈረሱን ወደ አዲስ አበባ አመጡት?
እንግዲህ ህብረተሰቡ ያንን ያደረገው ለኔ ካለው ፍቅርና በት/ቤቱ በመደሰቱ ነው። ንግግሬ ላይ እንዳየሽው አልቅሼ ነበር። ምን መሰለሽ---እኔ የሰራሁት ለራሴ እርካታ ትንሽ ነገር ነው ብዬ ነው ያሰብኩት። ያ ት/ቤት ለህብረተሰቡ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው ያወቅኩት፣ በምርቃቱ ዕለት የሰውን ስሜት ሳይና ከልባቸው ሲመርቁኝ ስመለከት ነው። የዚያ አካባቢ ህዝብ ደግሞ እንዳየሽው፣ በጣም ትሁትና ደግ ህዝብ ነው። አሁንም ድሮም ማነሽ፣ ከየት ነሽ ብሎ የሚጠይቅ አይደለም። ባሳለፍናቸው ዓመታት ብዙ አካባቢዎች በዘር በሃይማኖት እየተከፋፈሉ ብልሽት ሲሉ፣ የዚያ አካባቢ ህዝብ እስካሁን አንድነቱና ፍቅሩ አልተለወጠም፡፡ ሁሉም የአካባቢው ሰው ክስታኒኛ፣ አማርኛና ኦሮምኛ አቀላጥፎ እኩል በሚባል ደረጃ ይናገራል። የእኔም እናት ሦስቱን በደንብ ትናገራለች፡፡ የትኛው ጉራጌ፣ የትኛው ኦሮሞ፣ የትኛው አማራ እንደሆነ መለየት አትችይም። በጣም ደስ የሚል ደግና የሚያኮራ ህዝብ ነው። በዚህ ህዝብ ቢትወደድ ሲሳይ ተስፋዬ ተብያለሁ። እንዲያውም ከዚያ በላይ ማዕረግ ስላጣን ነው ያልሰጠንህ ብለውኛል። እጅግ በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ የበለጠ ሃላፊነትም ነው የሰጡኝ።
ፈረሱን ከእነ ጌጣጌጡ እዚያው ገጠር ዘመዴ ጋር ነው ያስቀመጥኩት። ነገር ግን እንጦጦ ፓርክ እንዲቀመጥ ለመነጋገርና እዚያ ለማስገባት እቅድ አለኝ። በአጠቃላይ ማህበረሰቡን በጣም አመሰግናለሁ።


Read 2514 times