Saturday, 25 February 2023 12:37

አገሪቱ ከምስቅልቅል የምትወጣው መቼ ነው?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

  መንግሥት እርምጃውን በጥሞና ይመርምር!
                         
        ወዳጆቼ፤ እንደምታወቁት…በተለይ ላለፉት አራት ዓመታት፣ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበትና ሃብት ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው እየተፈናቀሉ፣ በገዛ አገራቸው፣ እንደ አሸዋ እየተበተኑ ይገኛሉ፤ በየሜዳው፡፡ (አሳዛኝና አሳፋሪ የታሪካችን አካል ነው!)
የሚያስገርመው ደግሞ አብዛኞቹ መፈናቀሎችና ውድመቶች የሚፈፀሙት በፖለቲከኞች፣ በወረዳና ዞን አመራሮች፣ ሲከፋም በጸጥታ ሃይሎች  ድጋፍና ትብብር መሆኑ ነው። ይሄ ተራ አሉባልታ ሳይሆን በመንግስት የተከናወነ የምርመራ ውጤት ያረጋገጠው ሃቅ  ነው- በተደጋጋሚ።
በእነዚህ አፈናቃይ ፖለቲከኞችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ እስከዛሬ ስለተወሰደው ህጋዊ እርምጃ  ግን በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም- የተወሰደ እርምጃም ካለ በቂ አይደለም። ህጋዊ እርምጃው ወይም ቅጣቱ በቂ ቢሆንማ ኖሮ ዜጎችን በሰበብ አስባቡ የማፈናቀል ተግባር ይቀንስ ነበር። ነገር ግን በገሃድ እንዳስተዋልነው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ አደገኛው የዘረኝነት ፖለቲካም፣ ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ አልመጣም። (ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች ምሥጋና ይግባቸውና!)
አሁን ከሰሞኑ ደግሞ  ፖለቲካና ዘረኝነት፣ በቀጥታ ሃይማኖት ውስጥ ገብተው ሲበጠብጡና እሳት ሲያቀጣጥሉ በገሃድ አስተውለናል፡፡ አስደንጋጭና አስፈሪ ክስተት ነው፡፡  (አንድዬ መላውን ያበጅልን!)  
በነገራችን ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት፣ የተከበሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በአንድ ወቅት፣ በኦሮሚያ ክልል ከእንግዲህ የዜጎች መፈናቀል እንደማይከሰት ቃል ገብተው ነበር፤ ከተከሰተም ደግሞ የወረዳውን ወይም የዞኑን አመራር ከሥልጣን እንደሚያነሱና በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርጉም በአደባባይ ዝተው ነበር ወይም የዛቱ መስሎን ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ከተናገሩ በኋላ ግን በኦሮሚያ ክልል በዘር-ተኮር ጥቃት የተገደሉትንና የተፈናቀሉትን ዜጎች ብዛት ቤቱ ይቁጠረው። የተከበሩ አቶ ሽመልስ፣ በማፈናቀልና በግድያ የተጠረጠሩ ወይም ድርጊቱን በቅጡ ያልተከላከሉ የወረዳና የዞን አመራሮችን ከስልጣን ስለማሰናበታቸውም ሆነ ለህግ ስለመቅረባቸው የተሰማ ነገር የለም፡፡
እንደኔ አመለካከት፣ የለውጡ መንግሥት፣ ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት፣ ዜጎችን ከየትም ሥፍራ የሚያፈናቅሉና ለግጭት የሚቀሰቅሱ ፖለቲከኞችና የመንግሥት አመራሮችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ጠንካራ  ህግ  ማውጣት ነበረበት። ብዙ ሺ ዜጎችን አፈናቅሎ፣ አምስት ወይም ስድስት ዓመት ወህኒ ቤት ሲቀለብ ከርሞ የወጣ ፖለቲከኛና ባለሥልጣን ግን ከፈጸመው አስከፊ ወንጀል አንጻር ተቀጣ ለማለት አያስደፍርም። (እረፍት ወስዶ ተመለሰ እንጂ!) አሁንም  አዲስ ከበድ ያለ ህግ  ካልወጣ፣ ሰላማዊ ዜጎችን መግደልና ማፈናቀሉ መቀጠሉ አይቀርም - አሁንም የዜጎች ግድያና ማፈናቀል ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ (በባዕድ ሃይል ሳይሆን በራሳችን ወገኖች!)
እውነት ለመናገር መንግስት ለሙስና ወንጀል የሰጠውን ትኩረት ያህል፣ ዜጎችን በመግደልና በማፈናቀል ወንጀል ላይ ለተጠመዱት  አልሰጠም ማለት ይቻላል፡፡  
ይቅርታ አድርጉልኝና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ማንነት ተኮር ጥቃት መፈጸምና ሀብት ንብረታቸውን አውድሞ ማፈናቀል፣ በአገሪቱ ትልቁ ወንጀል ሆኖ መደንገግ አለበት- ከፍተኛውን የህግ ቅጣት የሚያስቀጣ! ያለበለዚያ ግን የዘረኝነት ደዌ የተጠናወታቸው አክራሪ ፖለቲከኞችና ብሔርተኞች፣ ዜጎችን ለሞትና መፈናቀል እንዲሁም ለሰቆቃ እየዳረጉ መቀጠላቸው ሳይታለም የተፈታ  ነው። ይሄ ደግሞ የማታ ማታ ህዝብን መበታተኑና  አገርን ማፍረሱ አይቀርም፡፡  
በሌላ በኩል፤ መንግስትና ፖለቲካ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ሲገቡ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከሰሞኑ በገሃድ አይተናል። (ባንድ ሳምንት እኮ አገሪቱ ምስቅልቅሏ ወጣ!) ከቤተ ክርስቲያኗ አፈንግጠው የወጡ አባቶች በጸጥታ ሃይሎች፣ በመሣሪያ ታጅበው፣ቤተ ዕምነቶችን  በሃይል ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ከምዕመናን ጋር ግጭት ተፈጥሮ፣ ዜጎች  ለሞት ተዳርገዋል፡፡ አካላቸው ጎድሏል፡፡ ተዋክበዋል፡፡ ታስረዋልም። (መንግሥት አልባ አገር ነበር የመሰልነው!)
ቤተ-ክርስቲያናቱ መቼም የምዕመናኑ ጭምር መሆናቸው  ይታወቃል፡፡ አባቶቹ ተሹመው ለማገልገልም ቢሆን እኮ የአካባቢው ምዕመናንን ይሁንታና  ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፡፡ በኃይልና በጠመንጃ መቆጣጠርም ሆነ ማስተዳደር ግን ጊዜ ያለፈበት ነው - እንኳንስ ለሰማያዊ አባቶች ለዓለማዊው መንግሥትም የማያዋጣ!  
አንዳንዶች እንደሚሉት፣ መንግሥት  የችግሩ ጠንሳሽ ነው ባልልም፣ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ግን በተለይ በኦሮሚያ ክልል የታየው ጣልቃ-ገብነት በእጅጉ አስደንጋጭ ነው። ከዚህ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብተው ላለመበጥበጣቸው ምን ዋስትና አለን?
እርግጥ ነው መንግስት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ፣ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት  በግልጽ ይደነግጋል። ባለፈው ሰሞን ግን ህገ መንግሥቱ  በግልጽ መጣሱን ታዝበናል፤ በራሱ በመንግሥት!  
በነገራችን ላይ ህገ መንግስቱ እኮ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ተዟዙረው ሰርተው የመኖርና ጥሪት የማፍራት  መብት እንዳላቸው ነው የሚደነግገው። ይሄ  የህገ መንግስቱ አንቀጽ ግን ሁሌም ሲጣስና የዜጎች መብት ሲደፈጠጥ ነው የኖረው - አሁንም ድረስ፡፡ (የህገ መንግሥት ጥሰት አዲስ አይደለም ለማለት ነው!)
አሁን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው አደገኛ ችግርና ውዝግብ የረገበና የተረጋጋ መስሏል። (ለጊዜውም ቢሆን እሳቱ ጠፍቷል!) እኔ አንዳንዶች እንደሚሉት፣ “ጠ/ሚኒስትሩ ራሳቸው የፈጠሩትን ችግር ነው አሸማጋይ መስለው ለመፍታት የሞከሩት” ብዬ አላምንም፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ ብጹዕ አባቶችም እንዲህ ሲሉ አልሰማሁም - ጠ/ሚኒስትሩን ሲያመሰግኑ እንጂ። የችግሩ ፈጣሪ ማንም ይሁን ማንም፣ ጠ/ሚኒስትሩና ሌሎች የአገር ሽማግሌዎች በቤተክርስያኒቱ አባቶች መካከል ሰላም ለማውረድ በመጣራቸው  ሊመሰገኑ ይገባል ባይ ነኝ። (ፈጣሪ ሰላሙን ያጽናልን!)
እንዲያም ሆኖ ባለፈው ሰሞን በአደባባይ የታየው የመንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባት ጉዳይ በፍጥነት ሊታረም ይገባል። ያለበለዚያ መዘዙ አደገኛ ነው፡፡ በተለይ ዘረኝነትና ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ሃይማኖት ውስጥ ከገቡ፣ የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ (በአጭሩ አገሪቱ ትፈራርሳለች!)
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዢው ፓርቲ ብልጽግና፣ ሁሉንም ነገር የመነካካትና በየጊዜው አዳዲስ አጀንዳ የመፍጠር አባዜ ክፉኛ የተጠናወተው ይመስላል፡፡ ሁሉንም ነገር በሃይልና በጥድፊያ የመፈጸም አዝማሚያም ይታይበታል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች፣ አዲሱን የብልጽግናን ባህርያት፣ ሥልጣንን ከማደላደልና ፖለቲካዊ ትርፍን ከማግኘት ጋር ያገናኙታል፡፡ ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ግን ሃገርን የማስተዳደር ሃላፊነት እንደተሰጠው መዘንጋት የለበትም። የ120 ሚሊዮን ህዝብ መንግሥት መሆኑን ደጋግሞ ማስታወስ ይኖርበታል፡፡
እርግጥ ነው የብልጽግና መንግሥት ሦስት የሥልጣን ዓመታት ይቀሩታል፡፡ አገሪቱን ለአምስት ዓመታት ለማስተዳደር ነው በህዝብ የተመረጠው፡፡ ነገር ግን ተቀዳሚ ኃላፊነቱንና ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል። ከሁሉም በፊት ራሱ ህግና ሥርዓትን አክብሮ ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ዜጎችን ከግድያና መፈናቀል መታደግ ይገባዋል፡፡ ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበርም ግዴታው ነው፡፡
መንግሥት ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በጊዜ መስጠት ይገባዋል፡፡ የተመረጠው ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ነው፡፡ ህዝብ ጥያቄውን ለማቅረብ ወይም ተቃውሞውን ለማሰማት አደባባይ ሲወጣ፣ በሃይል እርምጃ ለማዳፈን መሞከር ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አይፈታውም፡፡ (ይህን ከኢህአዴግ እንዴት አልተማረም!?) በየጊዜው ለሚፈጠሩ ችግሮች ሰበብ ከመፈለግና በውጭ ተላላኪ ሃይሎች ከማሳበብ ይልቅ ለመፍትሄው መትጋት ይኖርበታል፡፡ (እስከ መቼ አዳዲስ ጠላቶችን እየፈጠረ ይዘልቀዋል!?)
 በመጨረሻ፣ ገዢው ብልጽግናም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ሊያጤኑት የሚገባው ዋና ጉዳይ፣ ሥልጣንም ሃብትና ምቾትም የሚኖረው፣ አገርና ህዝብ ሲኖር ነው። ሰላም ሲሰፍን ነው። ይሄን መቼም ይስቱታል ብዬ አላስብም፡፡ ለሁሉም ግን ነገን እያሰቡ መራመድና ሥክነት ያስፈልጋል፡፡ (“ያዋከቡት ነገር መቅኖ አያገኝም” ተብሎ የለ!)
አንድዬ  ልብና ልቡና ይስጣቸው!




__________________________________________

Read 813 times