Saturday, 25 February 2023 12:42

አድዋና አበበ ቢቂላ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 የፊታችን የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም 127ኛው የአድዋ ድል በመላው ዓለም እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ በሰሜን አሜሪካ፤ ካናዳና ሌሎች አገራት በየዓመቱ ከሚከበረው የጥቁር ህዝቦች የታሪክ ወርም ጋር ይገናኛል፡፡  የስፖርቱ ዓለም ከጥቁር ህዝብ ያፈራቸው  ጀግኖች በርካታ ናቸው፡፡ በአትሌቲክስ እነ ጄሲ ኦውንስ፣ አበበ ቢቂላ፣ ፣ ዩሴያን ቦልት ፤ በእግር ኳስ እነ ፔሌ፤ በቦክስ እነ መሐመድ አሊ፤ በጎልፍ እነ ታይገር ውድስ፤ በቅርጫት ኳስ እነ ማይክል ጆርዳን፤ ማይክል ጆንሰን፤ ኮቢ ብራያንት ... እያሉ ታላላቅ የስፖርቱን ባለታሪኮች  በብዛት መዘርዘር ይቻላል፡፡  የጥቁር ታሪክ ወርን ከዚያም የአድዋ ድልን ስናከብር በስፖርት ውስጥ ለጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ለመሆን የበቁትን መለስ ብለን ማስታወስና መዘከር ይጠበቅብናል፡፡ ስፖርት አድማስ ከጥቁር ህዝቦች የታሪክ ወር እና ከ127ኛው የአድዋ ድል የመታሰቢያ በዓል ጋር በማያያዝ የሚያስታውሰው አንፀባራቂ ታሪክ ሻምበል   አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ የማራቶን ውድድር በማሸነፍ ያስመዘገበው ፈርቀዳጅ ድል ነው።
አበበ በቂላ በልጅነቱ ስፓርተኛ ነበር – በትውልድ መንደሩ፡፡ በወጣትነቱ ክብረ ወሰኖችን በመስበር የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሆኗል – ዓለምን ያስደነቀ፡፡ በጎልማሳነቱ በመኪና አደጋ ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ሆኖም ስፖርተኛ ነበር – ተወዳድሮ ያሸነፈ፡፡ ደብረብርሃን አቅራቢያ ጃቶ በተባለች ቦታ የተወለደው አበበ በቂላ፤ እንደአገሬው አኗኗር በልጅነቱ የ‹ቄስ ትምህርት ቤት› ሄዷል፤ የቤተሰቡን ከብቶች አግዷል፡፡ በትውልድ አካባቢው ተወዳጅ የሆነው ግን በስፖርት ነው – የገና ጨዋታ ላይ ጎበዝ ስለሆነ፡፡
ከ1944 ዓ.ም. በኋላ፤ በሃያ አመቱ፤ ክቡር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ ሲገባም፤ ከስፖርት ጋር ይበልጥ ተቀራረበ እንጂ አልተራራቀም፡፡ ከውትድርና አገልግሎት ጎን ለጎን፤ በሠራዊቱ የስፖርት እንቅስቃሴ በተለይም በአትሌቲክስና በገና ጨዋታ ጎልቶ ለመታየት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡
ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ፤ የአበበን የህይወት አቅጣጫ የሚቀይር፤ የኋላ ኋላም የኢትዮጵያን ስም የሚያደምቅ፤ አፍሪካውያንን የሚያኮራ፤ ዓለምን የሚያባንን አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ የበአል ሰልፍ ላይ፤ ‹ኢትዮጵያ› የሚል ፅሁፍ ያረፈበት ቱታ የለበሱ ስፖርተኞችን ሲመለከት፤ በዝምታ ማለፍ አልቻለም፡፡ ‹እነዚህ ስፖርተኞች እነማን ናቸው› ብሎ ጠየቀ። ስፖርተኞቹ እነማሞ ወልዴና እነባሻዬ ፈለቀ ናቸው፤ ኢትዮጵያን በመወከል በሜልቦርን ኦሎምፒክ የተካፈሉ አትሌቶች፡፡ ከዚያች አጋጣሚ ነው፤ ውስጡ የነበረው የአትሌቲክ ፍቅር ወደ ውሳኔ የተቀየረው፡፡ ‹ኢትዮጵያ› ተብሎ የተፃፈበት ቱታ ለመልበስና በዓለም አቀፍ ውድድር አገሩን ወክሎ ለመሳተፍ ቁርጠኛ ጥረት ጀመረ፡፡ በዚሁ አመት የጦር ሠራዊት ብሄራዊ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ተካፈለ – በወቅቱ ታዋቂ ከነበሩት አትሌት ዋሚ ቢራቱና ሌሎችም ጋር ተወዳደረ፡፡
ዋሚ ቢራቱ የ5ሺና የ10ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ሪከርድ የጨበጡ ጀግና ስለነበሩ፤ በዚሁ የማራቶን ውድድር እንደሚያሸንፉ ቢጠበቅ አይገርምም፡፡ ሩጫውን በቀዳሚነት እየመሩ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ኪ.ሜትሮች በኋላ ግን ስታዲዮም የነበረው ህዝብ ያልተጠበቀ ዜና ሰማ – ውድድሩን ከሚዘግቡ ጋዜጠኞች፡፡ አበበ ቢቂላ እየመራ ነው፡፡ ‹ማን ነው አበበ፤ ይህ አዲስ ባለታሪክ ማነው› በማለት በአድናቆት ሲጠብቅ የነበረው ህዝብ መልስ አገኘ – አበበ ቢቂላ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር አሸነፈ፡፡ የጥረት እንጂ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጀግና፤ ጀግናን ያፈራል፡፡
አበበ ቢቂላ በሌሎች ውድድሮችም አሸነፈ፤ በ5ሺ ና በ10ሺ ሜትር በአትሌት ዋሚ ቢራቱ ተይዞ የቆየውን ብሔራዊ ሪኮርድ ሲሰብር፤ ኢትዮጵያ አዲስ ጀግና አትሌት ማፍራቷን ተመልክታ በተስፋ በራች፡፡ የአበበ የመጀመሪያ ህልምም እውን ሆነ – በውድድሮች ባሳየው ድንቅ ብቃት ለኦሎምፒክ ቡድን ተመረጠ፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ በምትሳተፍበት የሮም ኦሎምፒክ፤ ‹ኢትዮጵያ› ተብሎ የተፃፈበት የብሄራዊ ቡድን ትጥቅ በማድረግ ወደ ሮም አመራ፡፡
ነገር ግን፤ ከ83 አገራት የተውጣጡ ከ5ሺ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሎምፒክ ላይ፤ የዓለም ህዝብ ትኩረት በአውሮፖውያን አትሌቶች ላይ ነው፤ ስለኢትዮጵውያን አትሌቶች በተለይም ስለ አበበ በቂላ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አበበ ቢቂላ ወይም ሌላ አፍርካዊ አትሌት ሊያሸንፍ እንደሚችል አልተጠበቀም – ከዚያ በፊት አንድም አፍሪካዊ በኦሎምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ አግኝቶ አያውቅም፡፡
የሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ግን፤ የዓለምን ታሪክ ቀየረ፡፡ የውድድሩ ውጤት፤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ ለመላው አፍሪካና ለዓለም ጥቁር ህዝብ ድል ያበሰረ ችቦ አቀጣጣለ፡፡ ኢትዮጵያዊያው አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ  ሮጦ ታላቁን የኦሎምፒክ ማራቶን በአንደኝነት ከማሸነፍም በተጨማሪ፤ 2፡15፡16.2 በሆነ ሰዓት አዲስ የዓለም ሪከርድ አስመዘገበ፡፡ በኦሎምፒክ ታሪክ; የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስፖርተኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ በወርቃማ ቀለም ሰፈረ፡፡
አበበ ቢቂላ የማራቶንን ርቀት ሮጦ ያሸነፈውና ሪከርድ ያስመዘገበው፤ በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ የመላ ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስደነቀ ነበር – የአበበ በቂላን ስምና የኢትዮጵያን ዝና በመላው ዓለም ተቀርፆ እንዲቀር አድርጓል። በአድዋ ጦርነት ላይ የዘመቱ ኢትዮጵያውያን ባዶ እግራቸውን እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡  ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውታል – ዓለም ሁሉ እንዲያውቅ ፈልጌ ነው ሲል የተናገረው አበበ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ፤ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው ብሏል፡፡ የአድዋን የጦርነት ታሪክ እየጠቀሰ ይሆን…
የማራቶን ሩጫው አለወትሮው በምሽት ነው የተደረገው። የሮም ከተማን በቲቪ ለዓለም ህዝብ ለማስቃኘት ውድድሩን እንደጥሩ አጋጣሚ ስለተቆጠረ፤ የሩጫው መስመር የከተማዋን ዋና ዋና ክፍሎችና አደባባዮችን እንዲያካልል ሆኗል፡፡ ፈፅሞ ያልተጠበቀው አበበ በቂላ፤ ከጥቂት ኪ.ሜትሮች ሩጫ በኋላ ከሌሎች ሶስት አትሌቶች ጋር ይመራ ጀመር፡፡ የአበበ ሃሳብ ከሃያ ኪሎሜትር በኋላ መሪነቱን ለብቻው ለመቆጣጠር ነው። ግን ቀላል አልሆነለትም፡፡ ሞሮካዊው አትሌት ርሃዲ ወጥሮ ይዞታል፡፡ እንዲህ ጎን ለጎን እንደተናነቁ አርባ ኪሎሜትር ሮጠው፤ የአክሱም ሃውልት የተተከለበት አደባባይ ላይ ደርሰዋል፡፡ አበበ ድንገት ፍጥነቱን ሲጨምር፤ ሞሮካዊው አትሌት ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኛ የቀረበለት ጥያቄም፤ ‹ለምንድነው ሃውልቱን ስታይ ፍጥነትህን የጨመርከው;› የሚል ነበር፡፡ ሃውልቱን ሳይ ቁጣ ስለተሰማኝ ነው ብሎ መለሰ አበበ፡፡
ምሽት ነው፤ ሃውልቱን እንዳለፉ ያለው መንገድ ላይ የተተከሉት ኤሌክትሪክ አምፑሎች ግን ጠፍተዋል፡፡ ሮም ሃያል በነበረችበት በጥንት ዘመን፤ ቆፍጣና ወታደሮች አካባቢውን እያንቀጠቀጡ በሰልፍ የሚያልፉበት ታሪካዊ መንገድ ነው። ይህንን ታሪክ ለማስታወስም ነው በአምፑሎች ፋንታ፤ በጥንታዊ የወታደር አለባበስ ያሸበረቁ ሰልፈኞች ችቦ ይዘው መንገዱን ለሯጮች እንዲያበሩ የተደረገው፡፡ የሮምን ሃያልነት ያስታውሳል በተባለው የወታደሮች ሰልፍ መሃል ሰንጥቆ በመግባት ታሪክ ቀየረ – አበበ፡፡ በማግስቱ የጣሊያን ጋዜጦች በትልልቅ ፊደሎች ጎልቶ የሚታይ ርእስ በመፃፍ፤ አዲስ ስም አወጡለት፤ ‹ሮምን የወረረ ኢትዮጵያዊ› የሚል፡፡ የክብር ዘበኛ ወታደር እንደሆነ ጋዜጠኞቹ ስለሚያውቁ፤ ‹ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ግዙፍ ጦር አዝምቶ ነበር፤ ሮምን ለመውረር ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ብቻ በቂ ሆኗል› በማለት ፅፈዋል፡፡

Read 1379 times