Saturday, 25 February 2023 13:47

መስቀል ተሰላጢን

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በዛሬው ቀን የልጆቼ የቤት ውስጥ መምህርት፣ ደሞዟን ለመተሳሰብ ወደ ንባብ ክፍሌ እንድትመጣ ባዘዝኩት መሠረት ደፋ ቀና እያለች ደረሰች። ለጥቂት ሰኮንዶች ከተመለከትኳት በኋላ…
“ወ/ት እንከን የለሽ ኃይሉ እንደምን አደርሽ?... እሱ ጋ ተቀመጭ!” አልኳት የፊት ለፊቱን ወንበር እያመለከትኩ… እንደታዘዘችው አደረገች።
“ያስጠራሁሽ እኔ ዘንድ ያለሽን ሂሳብ ለመተሳሰብ ነው። ስጠኝ ብለሽ ባትጠይቂኝም ለአንዳንድ ጉዳዮች ገንዘብ እንደሚያስፈልግሽ ዕሙን ነው። አስበው ካልሰጡሽ በቀር ጠይቀሽ መቀበል ፍላጎት አይቼብሽ አላውቅም። ሆነም ቀረም ወደ ሂሳቡ እንግባ! አይሻልም?” አልኩ።
አንገቷን “ተስማምቻለሁ” በሚል ዓይነት ነቀነቀች።
“እሺ እንግዲህ ስትቀጠሪ እንደተነጋገርነው የወር ደሞዝሽ ዘጠና ብር ነው” ስላት፣ በጣም ዝግ ባለና በሚጎተት ድምጽ፤ “መቶ!” አለች።
“መቶ አይደለም፤ ይኸው ማስታወሻዬ ላይ ጽፌዋለሁ’ኮ ዘጠና ነው። ከዚህ በፊት ለቀጠርኳቸው ሁሉ ዘጠና ብር ነው ስከፍላቸው የቆየሁት” ንግግሬ ውስጥ የቁጣ ድምፅ አለበት። በአንገቷ “እሺ-ይሁን” የማለት ምልክት ስላሳየችኝ ቀጠልኩ።
“እሺ… ዛሬ ስራ ከጀመርሽ ልክ ሁለተኛ ወርሽ ነው-አይደል?”
“አይደለም-ሁለት ወር ከአምስት ቀኔ ነው” አለች፤ ዓይኖቿን ወደምታደርግበት ጠፍቷት እያርበተበተቻቸው።
“በጭራሽ! ይኸው ጽፌዋለሁ’ኮ ወደፊት ወደኋላ የለም፤ ዛሬ ልክ ሁለተኛ ወርሽ ነው” አልኳት፤ አልተቃወመችም።
“ጥሩ! በወር ዘጠና ብር አለሽ ማለት ነው።”
አሁንም በአንገት መወዝወዝ ብቻ ስምምነቷን ገለጠች።
“እሺ! ከ60ው ቀናት ዘጠኝ እሑዶችን እንቀንሳለን። ምክንያቱም በእሑድ ቀን ልጆቼን አስተምረሻቸው አታውቂምና ነው። እሑድ እሑድ ወይ ሽርሽር ወይም ቤተክርስቲያን ለመሳም እያልሽ መሄድሽን ማስታወሻዬ ያሳየኛል።… አዎ! ሌላም አለ። ያልሰራሽባቸው ሦስት ያመት በዓል ቀናት አሉ። ስለዚህ በወር ዘጠና ብር ማለት በቀን ሶስት ብር ማለት ሲሆን፣ ዘጠኝ እሑዶች ሲደመሩ ሦስት የበዓል ቀኖች ማለት አስራ ሁለት ቀናት አልሰራሽም። ከጠቅላላው ደሞዝሽ ሠላሣ ስድስት ብር ይቀነሳል ማለት ነው። ግልፅ ሆነልሽ?” አልኩና ፊት ለፊት አፈጠጥኩባት።
ግንባሯ ከመቅጽበት ፍም መሰለ። ጌጣጌጦች የተደረደሩበት ብልጭልጭ ቀሚሷ ብቻውን “እስክስታ” ይመታ ጀምሯል (ተንቀጠቀጠች ላለማለት ነው።) በጆሮ ግንዷ ስር የወረደው ላብ፣ ቦይ ሰርቶ በአንገቷ በኩል በማለፍ፣ መንጋጭላዋ ዘንድ ደርሶ እየተንጠባጠበ በጡቶቿ መሃል ዘለቀ።
“ሰላሳ ስድስት ብር ከደመወዝሽ ተመላሽ ይሆናል ማለት ነው። አዎ! ማስታወሻዬ እንደሚጠቁመው ወንዱ ልጄ አዶናይ ለአራት ቀናት ያህል በታመመ ጊዜም እረፍት አድርገሻል። በእርግጥ ሴቷን ልጄን ሶስናን ማስተማርሽ አይካድም። ሌላም አለ፤ ጥርስሽን ለሶስት ቀናት በመታመምሽ ከነምልክቱ ባለቤቴ ከእራት መልስ እንድትሄጂ የፈቀደልሽን ማለቴ ነው።… እና አስራ ሁለት ቀናት ሲደመር አዶናይ ያልተማረባቸው አራት ቀናት ጥርስሽን የታመምሽባቸው ሶስት ቀናት ሲደመሩ በጠቅላላ አስራ ዘጠኝ ቀናት ሆኑ ማለት ነው። እንግዲህ ከሰላሳ ቀናት አስራ ዘጠኝ ሲቀነስ የአርባ አንድ ቀን ደመወዝ እኔ ዘንድ አለሽ ማለት ነው። ትክክል ነኝ?”
ቀደም ሲል እንደጠቆምኩት የወ/ሪት እንከን የለሽ አይኖች መቅላታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአገጯ መንቀጥቀጥ ሳይታወቅ በጥርሶቿ ረግጣ ልትይዘው ብትሞክርም፣ አልቻለችበትምና የባሰውኑ ሞጥሟጣ መሰለች።
“ምነው ዝም አልሽ?...ሂሳቡ  ልክ አይደለም እንዴ?” አልኩ።
መሃረብ አወጣችና እንባዋንም አፍንጫዋንም አደራረቀች። ቃል አልተነፈሰችም፤ ዝም ብላ ማየት ብቻ!
ማስታወሻዬን ገለጥኩና በቀይ ቀለም እያሰመርኩ “አዲሱ ዓመት በተለወጠበት ቀን ግብዣ ላይ ስታስተናግጂ የሆነው ነገር ትዝ ይልሻል?” አልኩ።
አፍንጫና አይኖቿን እያባበሰች በዝምታ “ይሁን” ማለቱን ቀጥላለች።
“ከረሳሺው ላስታውስሽ… የዚያን እለት አንድ የሻይ ሲኒ ከነማስቀመጫው መስበርሽ ትዝ አለሽ? እሱን ማለቴ ነው። በተለይ ሲኒው የቤተሰባችን ማስታወሻ ቅርስ ነበር። አይ እሱ ሲኒ!... ሲኒው ከነማስቀመጫው ስድስት ብር ታስቦልሻል፤ ይህም በአስተያየት ነው። ቅርስ ነው ብዬሻለሁ።”
አጅሪት በዝምታ ሸለቆ ተውጣ ዓይኖቿ ግን “አቤት የዚህች አለም አበሳ” የሚሉ ይመስላሉ።
“እሺ! በአንቺ የጥንቃቄ ጉድለት ልጄ አዶናይ አጥር ሾልኮ በሚያልፍበት ጊዜ ጃኬቱ ስለተቀደደ የሰላሳ ብር ኪሳራ ደርሶብኛል። በተመሳሳይ ሁኔታ በአግባቡ መጠበቅ ሲገባሽ፣ የወጥ ቤት ሰራተኛችን የሴት ልጄን የሶስናን ጫማ ሰረቀች። የልጆቻችንን ሃላፊነት ሙሉ በሙሉ ስንሰጥሽ ተገቢውን ጥበቃ ታደርጊላቸዋለሽ በሚል እምነት ነው። ደመወዝ የሚከፈለው ለተጠናቀቀ ግዳጅ ብቻ ነው። ነጠላ ጫማ በመሆኑም አስራ አምስት ብር ብቻ እንድትከፍይ ወስነናል። ባለፈው ጥር አስር ቀን ብድር እንድሰጥሽ በጠየቅሽኝ መሰረት ሰላሳ ብር መበደርሽን ማስታወሻዬ ያመለክታል። ልክ አይደለም?”
ባለታሪካችን ሦስት ቃላትን ብቻ በሹክሹክታ ተነፈሰች።
“ብድር አልጠየቅኩዎትም፤ አልወሰድኩምም” አለችና ወደተለመደው የዓይን ግርምታ ተመለሰች።
“እንዴዴዴ! ይኸውልሽ የተጻፈው፤ በእለቱ መዝግቤዋለሁ። ማስታወሻ የመያዝ ልማድ ሊኖርሽ ይገባል” አልኩና ማስታወሻዬ ላይ በቀይ ያሰመርኩበትን አሳየኋት።
አምላክ ምስጋና ይግባውና፣ በዚህ ጊዜም ሁለት ተጨማሪ ቃላትን አንሾካሾከች።
“ይሁና መቼስ”
“እሺ ቅድም ስንተሳሰብ የአርባ አንድ ቀን ደመወዝ እኔ ዘንድ እንዳለሽ ተስማምተናል። ከዚያ በኋላ የሲኒ ማስቀመጫ ስድስት ብር፣ የአዶናይ ጃኬት ሰላሳ ብር፣ የሶስና ጫማ አስራ አምስት ብር እና የተበደርሽው ሰላሳ ብር ሲደመሩ ሰማኒያ አንድ ብር ይሆናል። ከቀረሽ የአርባ አንድ ቀን ደመወዝ (41 በቀን የምታገንው 3 ብር) ማለትም ከ123 ብር 81 ብር ሲቀነስ 42 ብር እኔ ዘንድ አለሽ ማለት ነው፤ ልክ ነኝ?” አልኩ።
ምስኪን ልጃገረድ! ዓይኖቿ ውስጥ እንባ ተጎዝጉዟል። በእርሳስ የተሰመረ ከሚመስለው አፍንጫዋ ላይ የላብ ጎርፍ ይኩረፈረፋል፤ ስትጠርገው መልሶ እየተካ፡፡ ጆሮዋ፣ ማጅራቷ፣ ማጅር ግንዷ ላብ እየተብሰከሰከባቸው መንተክተክ ያዘች። እንደምንም አምጣና ቃጥታ በሚርገበገብ የድምጽ ቃና…
“ብድር አሉኝ? ብድር አንድ ጊዜ ብቻ ነው የወሰድኩት። ዘጠኝ ብር ብቻ… እሱንም ከእርስዎ ሳይሆን ከእትዬ ነው የተበደርኩት… ሌላ ብድር ግን አልወሰድኩም” በማለት በእለቱ ውይይታችን የተመዘገበውን ረጅሙን ንግግር አጠናቀቀች።
“አሃ! ለካስ ያልመዘገብኩትን ሌላም ብድር ወስደሻል ማለት ነው? ጥሩ ስላስታወስሽኝ ምስጋና እያቀረብኩ፤ ይህንንም… ቆይ… አዎ… ባጠቃላይ ከቀረሽ 42 ብር የአሁኑ ዘጠኝ ብር ሲቀነስ 33 ብር እኔ ዘንድ አለሽ ማለት ነው… እንግዲህ ይኸውልሽ ደሞዝሽ” አልኩና 33ቱን ብር ደጋግሜ ቆጥሬ ሰጠኋት።
በሚንቀጠቀጡት እጆቿ ተቀብላ ሳትቆጥር ጥቅልል  አድርጋ ከጡቶቿ መሃል ሸጎጠችና ሙትት ባለ ድምጽ፤ “አመሰግናለሁ” በማለት እጅ ነስታ ልትወጣ ስትል… “እንዲህማ አንላቀቅም” በማለት ድንገት እምር አልኩና በክፍሉ ውስጥ መንጎራደድ ያዝኩ። ግልፍ አለኝ። ፊት ለፊቴ እያየኋት…
“ምን ስላደረኩልሽ ነው ምስጋናው?” አልኳት።
“ለገንዘቡ ነው፤ ደመወዜን ስለሰጡኝ”
“እኔ የማውቀው እያጭበረበርኩሽ መሆኑን ነው። የደከምሽበትን ላብሽን ሰበብ እየቆለልኩ ማታለሌን ነው። እየዘረፍኩሽ መሆኑን ነው። እና ምስጋናው ለዚህ ተግባሬ ነው?” በሷ ፋንታ መርበትበትና ላብ ማንዠቅዠቁ ወደእኔ ተዛወረ። “አይደለም” አለች በጣም ተረጋግታ። “በሌላ በሰራሁባቸው ቦታዎች ሁሉ… ማንም ሰው “ደሞዝሽ ይህ ነው” ብሎ እንደርስዎ ሰጥቶኝ ስለማያውቅ ነው…”
“ማንም ከፍሎኝ አያውቅም አልሽ?! ይገርማል… እኔ ግን ዝም ስለምትይና ስለማትጠይቂ እስኪ በዚህ ሰበብ ላነጋግራትና በድንገትም የሚያስቅ አጋጣሚ ልፍጠር በማለት ልቀልድብሽ እንጂ የምሬን አይደለም። ደመወዝሽን በሙሉ ይኸው በፖስታ አዘጋጅቼልሻለሁ፤ አምጭው እሱን የሰጠሁሽን… ይኸውልሽ” አልኩና ፖስታውን ካቀበልኳት በኋላ…
“ግን እንደ አንቺ አይነት አፍላ ወጣት ዝምተኛ ሆና በደል ስትሸከም ማየት ያስገርማል። ያልሰራሽውን ሰርተሻል፣ ያልወሰድሽውን ወስደሻል፣ ያላጠፋሽውን አጥፍተሸል ስትባይ እንዴት አትከላከይም? ወይም ባትቃወሚ እንኳን አስተያየት ቢጤም ቢሆን ለምን አትሰነዝሪም? በደልንም፣ ጥቃትንም፣ ዘረፋንም… ሁሉንም “ እሺ ይሁን” በማለት የዚችን ዓለም ጭካኔ እንደምን ትቋቋሚያለሽ?... ለምንም አላማና በምንም ምክንያት ይሁን በዚች ጥርሳም አለም ውስጥ “የማይቻል” ነገር ነው ስላት፣ እጅ እየነሳችኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አለች። በፈገግታዋ ውጥ ዘልቆ በዐይኖቿ ውስጥ ግን “እሱን እንኳን ተወው፤ የሚቻል ነው” የሚል መልዕክት ያነበብኩ መሰለኝ።
ላሳየችኝ ትዕግስትና ትህትና አክብሮቴን ከመግለጽ ጋር ለአቀራረቤም ይቅርታ ጠይቄ ሳሰናብታት ደጋግማ “አመሰግናለሁ” እያለች ወጣች። ስትወጣ ከጀርባዋ እየተመለከትኳት በሀሳብ ሰገርኩ።
በዚህች ዓለም ትዕግስተኛና ጠንካራ ስለመሆን ከዚህ የተሻለ ምን ቀላል ምሳሌ ይኖራል? እንግዲያውስ ናዝራውያን “መስቀል ተሰላጢ” ይዘው የሚዘዋወሩት ለምንድን ነው? ሩሲያውያን ለካንስ “ድመትን በጨለማ መፈለግ በጣም አስቸጋሪ ነው-በተለይማ ድመቷ ጥቁር ከሆነች” ያሉት በከንቱ አይደለምና!
ማስታወሻ፡- “መስቀል ተሰላጢን” ማለት ባህታውያን የሚይዙት ከብረት የተሠራ፣ ከላይ መስቀል (መባረኪያ) ከሥር የሾለ የጦር ቅርጽ (መውጊያ) ያለው ዘንግ ነው፡፡
(ምንጭ፡- “አባቶችና ልጆች እና ሌሎች ታሪኮች” ከሚለውና ጋዜጠኛና ደራሲ አብርሃም ረታ ዓለሙ ከተረጎመው መድበል የተወሰደ፤በ2007 ዓ.ም የታተመ)


Read 1176 times