Saturday, 25 February 2023 13:46

ፍዳ የኪነት ማኅፀን፡ “ሰዉነትን” የሚነቅሱ የከበደች ተክለአብ ቅኔዎች

Written by  መኮንን ማንደፍሮ
Rate this item
(0 votes)

   ፩. መግቢያ
ፋይዳ ቢሱ የሰዉ ልጅ በመልከ ብዙ ስንክሳሳሮች ዳክሮ ሊያልፍ፣ መራራ ፅዋን ተጎንጭቶ አልያም የደስታን ጣዝማ አጣጥሞ በሞት ትቢያ ሊሆን የተኮነነ (doomed to be perish) ፍጡር ነዉ፡፡ በድንገቴ (randomness) ወደ ህልዉና ስለመጣም ባይተዋር (solitary) ነዉ፤ ከእሱ ሌላ የነፍሱን ሰቆቃና አሳር ሰምቶ አይዞህ የሚለዉ ሰሚ ጆሮ ያለዉ ሌላ አጋዥ አካል በሚኖርበት ሁለንታ (universe) ባለመኖሩ፡፡ ሰዉ እርስ በእርሱ በፍቅርና በመተሳሰብ ካልኖረ በቀር ከተጨካከነ እንባ ያለ ጡር ተዘርቶ ይቀራል እንጂ አባሽ የለዉም፡፡ የሰዉ ደምም በከንቱ ፈሶ ይቀራል እንጂ ተበቃይ የለዉም፡፡ ከገደል ማሚቶ ሌላ የዋይታና ጩኸት ደራሽም የለም፡፡ ሁሉም ሰዉ ባይተዋር ነዉ፡፡ ይህ ሐቅ ለመዋጥ የሚያቅር ሐቅ ነዉ፡፡ ሁለንታም ግዑዝ በመሆኑና ከሰዉ ልጅ ጋር ህብር (harmony) ፈጥሮ የሚኖር ባለመሆኑ ፍትህን መስጠት አይችልም፡፡
*  *  *
ከበደች ተክለአብ በማትታገለዉ ዕጣ ፈንታዋ አሉታዊዉን የሕይወት ገፅ ገፈት እንድትቋደስ ተገዳ የሰዉ ኅሊና ሊቋቋመዉና ሊያስታምመዉ የሚከብድና ፅናትን የሚገዳደር መራርና አሰቃቂ የረጅም ዘመን የእስር መከራን ያሳለፈች ታላቅ ከያኒ ናት፤ የሰዉ ልጅ ፅናትና የጥንካሬ አብነት፡፡ እስራትን ከሌሎች ሰብአዊ የህልዉና ተግዳሮቶች እጅግ የከፋ የሚያደርገዉ የግለሰቦች ዐቢይ የኑሮ ትርጉም መሠረት የሆነዉን ነፃነትን ስለሚገፍ ነዉ፡፡ ሰዉን ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ ከሚከዉነዉ ተግባሩ (labor) መገደብ ወደር የሌለዉ ቅጣት ነዉ፡፡ ሕይወት ያለ ነፃነት አስከፊ ቀንበር ነዉ፡፡ በነፍስ ምሬት ወቅት የፈቃድ ሞት እንኳ ሩቅ ምኞት ነዉ፡፡ እስር እጅግ አስከፊዉና ደዌን ተስተካካዩ የሰዉ ልጅ መከራ (human tragedy) ነዉ፡፡ እስር የአካልና የኅሊና ጉስቁልና ሰበብ ነዉ፡፡ እስር እጅግ ፈታኝ የሕይወት ፍዳዎች ርሀብ፣ ናፍቆት፣ ባይተዋርነት፣ ብሶት፣ እርዛት፣ ጥማት እና ህማም የሚፈራረቁበት እኩይ ገፅታ ነዉ፡፡
ሕይወት ልዩ ጣዕምና ጌጥ የሚኖረዉ የተለያየ ቀለም ባላቸዉ የአክርማ አለላዎች ሲሠራና የተለያየ ገፅታ ባለዉ ድር ሲሸመን (ደስታ-ሐዘን፣ ክብር-ዉርደት፣ ስቃይ-ሐሴት፣ ሲሳይ-ዕጦት፣ ግዞት-አርነት እና ፍቅር-ጥላቻ) ነዉ፡፡ ሠዓሊና ባለቅኔ ከበደች ተክለአብ በብሩሁ የሕይወት ገጽ ብቻ ሳይሆን በፀሊሙ ዳክራ አፋራወትሪንን 38904879                ልፋ የታዘበችዉን እና የተገነዘበችዉን በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ ዳክራ ካለፈችበት ሕይወት የተቀዳ እዉነተኛ ኪነትን (ያልኖሩት ኪነት ሐሰተኛ ነዉና) በብዕሯ እና በብሩሿ አማካኝነት ገልጣ ያስቃኘችን ታላቅ ከያኒ ናት፡፡ ምንም እንኳ ከበደች በመጥፎ የሕይወት አጋጣሚ ሰበብ ወህኒ የአበባነት ዘመኗንተ (ess partment of)  መብላቱ ቢያሳዝንም፣ በከያኒ የሕይወት ጉዞ ባከነ፣ ተቃጠለ፣ መና ቀረ ተብሎ በቁጭት የሚንገበገቡበት የታሪክ ምዕራፍ የለምና (ሁሉም የሕይወት ጎኖች ብሩሁም ፀሊሙም ኪናዊ ፈጠራን እንዲሰራ ዋና ልምዶቹና ስንቆቹ (wisdom) በመሆናቸዉ) ከያኒዋ ከእዚሁ ሕይወቷ የተቀዱ፣ የሰዉ ልጅን የመከራ ጥግ ያስቃኙ ታላቅ ጥበባዊ ሥራዎቿን ማበርከት በመቻሏ ነፍሳችን በጥበብ እርካታ ደስታን ሊገበይ ችሏል፡፡
*  *  *
የት ነዉ? (1983) ባለቅኔ ከበደች ከአስራ አንድ ዓመታት የእስር ቆይታዋ በኋላ ለህትመት ያበቃችዉ የበኩር የግጥም መድበሏ ነዉ፡፡ ይህ ሥራ ያለጥርጥር ከ20ኛዉ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሸጋ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል አንዱ የሆነና የባለቅኔዋን የነፍስ ቅኝትና ስሜት በርቀትና በጥልቀት የሚያስቃኘን ነዉ፡፡
ይህ መጣጥፍ በእዚህ መድበል ዉስጥ የቀረቡ ሦስት ሥራዎችን የሚተነትን (critical analysis) ነዉ፡፡ መጣጥፉ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጣጥፉ የመጀመሪያዉ ክፍል ከበደች የት ነዉ? በሚለዉ መድበሏ ዉስጥ ያቀረበቻቸዉን መዴራ እና ተስፋ የተሰኙ ሥራዎችን ማዕከላዊ ጭብጥ (central theme) የሚዳስስ ነዉ፡፡ የእዚህ መጣጥፍ ሁለተኛዉ ክፍል ከበደች በመድበሏ ባካተተችዉ መድኃኒት በተሰኘዉ ሥራዋ ያቀረበችዉን ንፅረተ ዓለም (out look) የሚዳስስ ነዉ፡፡
    ፩. ፅናት፡ “የሰዉነት” ልዕልና ሚዛን
     የት ነዉ? በተሰኘዉ የከበደች የግጥም መድበል ዉስጥ ከቀረቡ እጅግ ሸጋ ሥራዎች መካከል አንዱ መንዴራ ነዉ፡፡ መንዴራ እንባና ፈገግታ፣ የሁለት ዓለም ሰዎች፣ የዝናብ ጠብታ፣ ተስፋ፣ወርቅ ነዉ፣ ረስታዬ፣ ሞትም አይነት አለዉ፣ የት ነዉ?፣ እንግዳሽ፣ ቢሆንማ፣ ቀሰቀሰኝ፣ ይብላኝ! እና መድኃኒት እንደተሰኙት ሥራዎቿ ሁሉ የቋንቋ ዉበት የተንፀባረቀበት (high diction) እና ገጣሚዋ የሚሰማት ሰቆቃና ተስፋ የእኛን ቆዳና አጥንት ሰርስሮ ዘልቆ ህመሙ እንዲሰማን (thone) ተደርጎ የተሠራ ሸጋ ሥራ ነዉ፡፡ የጎምቱ ከያኒ ክህሎት ዐቢይ ሚዛኑና ማሳያዉም ይህ ነዉ፡፡ መንዴራ ከበደችና ሌሎች ኢትዮጵያዉያን በግፍ ታስረዉበት የነበረ በርበራ የሚገኝ አሰቃቂ የሶማሊያ እስር ቤት ነዉ፡፡ በእዚህ ሥራዋ ከበደች የሰዉ ልጅ ከሞት በስተቀር ጫንቃዉ ሊሸከመዉ የማይችለዉ የመከራ ቀንበር እንደሌለ አሳይታናለች፡፡ ሰዉ ከሌሎች ፍጡራን ተለይቶ ልዕለ ኃያል ፍጡር የሆነዉም አካላዊና ኅሊናዊ መከራንና ጣዕርን በፅናት ማለፍ በመቻሉ ነዉ፡፡ ግርፋትም ቢሆን ርሀብ፣ እርዛትም ቢሆን ህማም፣ ዉርደትም ቢሆን ጥማት፣ ሐሩርም ቢሆን አመዳይ፣ ድካምም ቢሆን ባርነት ሰዉ በፅናት ተቋቁሞ የሚያልፋቸዉ ፍዳዎች ናቸዉ ትለናለች ከበደች፡፡ የሰዉ ልጅ ገጸ ብዙ የህልዉና ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ማለፍ የሚችል ፅኑ ፍጡር መሆኑንያሳየችበት መንዴራ የተሰኘዉ የከበደች ሥራ ከእዚህ ቀጥሎ የቀረበዉ ነዉ፦     
መንዴራ!      
             የእኩይ ገጽታ ጣምራ
              መቅሰፍት አንጸባራቂ ጮራ
              የሥቃይ መናኸሪያ ጎተራ!
ምን ይሆን ሟርትሽ መንዴራ
በደጅሽ ብርሃን የማይበራ
ምን ይሆን ከቶ ምስጢርሽ
የጨለመበት እንግዳሽን
በጨለማ ቤት መቀበልሽ
በሰናስልት ግጭት ጩኸት
በቁልፍ ቅጭልጭል ማሸበርሽ
ለመግባት እንጂ ለመዉጫ
እማይከፈት ይመስል
በሩን በቁጣ መዝጋትሽ
ጸጥ ባለዉ ጨለማ ቤትሽ
ድምፅ ሥቃያት ማብዛትሽ
 ምን ይሆን እኩይ ጥበብሽ
 የሲኦል ተቀጽላ ሟርትሽ!
 መንዴራ!
                 አንቀጽሽ ምንኛ ይከፋል
                ጨለማሽ ምንኛ ይዉጣል
                በርሽ ምን ያህል ይጫናል
                የሰናሰልትሽ እኩይ ድምፅ
                ለስንት ጊዜ ይደዉላል?!
መልከ ጥፉዋ መንዴራ
ቆረቆር እንደ ቦዳደሰዉ ራስ
የተላላጠዉ ተራራ
እጅ ለእጅ ተቆላልፎ
አንቺን ከሌላዉ ለይቶ
አብራኩ መሐል ከቶ
እንደ ቅዱስ ኅቡዕ ዕቃ
ራሱን ላንቺ መክቶ
አካል ለአካል ተላልሶ
ጎን ለጎን ተነካክቶ
የበረሃ ገነት ሳይሆን
የበረሃ ሲኦል ሠርቶ
አድማስሽን በራሱ ልክ
ትዕይንትሽን ሰማይ አርጐ
እንደ ባቤል ግንብ ሕንፃ
ራሱን ሰማይ ጥግ አሳድጐ
የርዕዮት መብትሽን ነፍጐ
ሙቅ አየርሽን አፍሞ
ሙቅ መሬትሽን አግሞ
              መንዴራ መርዕድ መደንግፅ
              የበቀለብሽ የግፍ ዕፅ
              አንቺ ፀረ ሕያዋን
              ምግብሽ ለብርታት ላይሆን
              ዉሃሽ ላያርስ ላንቃን
              የረገመሽ ተፈጥሮ እንኳን
              መንዴራ ቤተ እሱራን
                       ትዕይንተ ሥቃይ መንዴራ
                       የቅጣት ቤትሽ ሲያስፈራ
                       የሞት ልሳንሽ ሲጣራ
                       የእልቂት ጨረርሽ ሲያበራ
                       እንደ አልተራቫዮሌት ጨረር
                       ከያንዳንዱ ሕዋስ ዘልቆ
                        ሥጋዉን አክስሎ ገብቶ
                        ዐፅሙን እንዳይሆን አድቆ
                         ተስፋ እንዳይገባዉ ሕሊና
                         በሥጋት ጉሙ አምቆ
                         አእምሮን የኋሊት አስሮ
ሕዋስ ለሕዋስ አጨማምቆ
ፍርደኞችሽ በዝግ ቤቶች
አካለ ገላቸዉ አልቆ
የሞት ፍርዳቸዉ ዕለት
ከፍፃሜዉ ቀን ተራርቆ
አካላቸዉ በሞት ፍርሃት
በሞት ሥጋት ተሳቆ
ርቀቱን ሳይሆን ቅርበቱን
መገላገሉን ናፍቆ
ሞትን በገሃድ ለመዳሰስ
ረቂቁን ፍርሃት ለመግሠሥ
ይህን ሥዉሩን አምሳል
ሐሳባዊ የጠር ሲኦል
መግዘፍቱን ለመታገል
ከህልዉና ለመገለል
ትዕግሥታቸዉ ተሟጦ
አእምሯቸዉም ተናዉጦ
የሰዉ ወዛቸዉ ተለዉጦ
አዉሬ መስለዉ
ጸጉር ለብሰዉ
ቀለም አጥተዉ
ወይቦ
               እራሳቸዉን በራሳቸዉ
               በዉስጥ ማንነት መስጠዉ
               በእጅ እግሮቻቸዉ ሰንሰለት
               በጩኸታቸዉ ተዉጠዉ
               ዐይኖቻቸዉ ዉስጥ እያዩ
               ለዉጭዉ ግንዛቤ አጥተዉ
መንዴራ
       ሰዎችሽ ያሳዝናሉ
       የዓለም ብያኔን ሲሹ
       ሰብአዊ ፍርድን ሲማለሉ
መንዴራ!
          የግፍ የሥቃይ ጐራ
          አንቺዉ በፈጠርሽዉ ገጽ
          አቤት መልክሽ ሲያስፈራ
መንዲራ!
            የእኩይ ገጽታ ጣምራ
            መቅሠፍት አንጸባራቂ ጮራ
            የሥቃይ መናኸሪያ ጐተራ
መንዴራ!
ከበደች እንደምትነግረን፣ የሰዉ ልጅ ፅናት መሠረቱ ተስፋ ነዉ፡፡ ተስፋ ለኤግዚስቴንሻሊስቱ ፈላስፋ ዣን-ፖል ሳርተር፣ ሰዉ ነባራዊ ሕይወቱን መሠረት አድርጎ በወኔ የተሞሉ ገቢሮችን እንዳይከዉን (quetism)፣ ሕይወቱንም በምልዓት አንዳይኖር የሚያደርግ ደንቃራ ቢሆንም፣ ለከበደች ሰዉ ዕድል ፈንታዉ የሚጭንበትን የመከራ ቋጥኝ ትከሻዉን አደንድኖ እንዲሸከም የሚረዳዉ ዐቢይ ኃይል ነዉ፡፡ ለሳርተር ጠቃሚዉ የሕይወት መርህ ተስፋ (hope) ሳይሆን ቀቢፀ-ተስፋ (despair) ነዉ፡፡ ሳርተር ከከበደች በተቃራኒዉ ኤግዚስቴንሻሊዝም ኢዝ ኤ ሂዩማኒዝም በተሰኘ የፍልስፍና ሥራዉ የሚከተለዉን ብሏል፦
As for “despair,” it has a very simple meaning. It means that we must limit ourselves to reckoning only with those things that depend on our will, or on the set of probabilities that enable action. Whenever we desire something, there are always elements of probability. If I am counting on a visit from a friend who is traveling by train or trolley, then I assume that the train will arrive on time, or that the trolley will not derail. I operate within a realm of possibilities. But we credit such possibilities only to the strict extent that our action encompasses them. From the moment that the possibilities I am considering cease to he rigorously engaged by my action, I must no longer take interest in them, for no God or greater design can bend the world and its possibilities to my will. In the final analysis, when Descartes said “Conquer yourself rather than the world” he actually meant the same thing: we should act without hope (Sartre, 35).
     ተስፋ ከበደች እንደምትነግረን፣ በድቅድቅ ጨለማ የወደቀ ግለሰብ ከሩቅ ያለ የብርሃን ዉጋጋንን እንዲመለከት ያደርጋል፡፡ የከበደች የተስፋ እሳቤ አንድምታዉ፣ ሰዉ ተስፋዉ ከልቡ ከነጠፈ ሙት ነዉ የሚል ነዉ፡፡ ከበደች ተስፋ የሰዉ ልጅ ፅናት ካስማ መሆኑን ያተተችበት ተስፋ የተሰኘዉ ሸጋ ሥራዋ የሚከተለዉ ነዉ፦
ከነባራዊዉ አደጋ ከተጨባጩ ፈተና
ከምዝብር ህላዌ ጭንቀት ከምስቅልቅሉ መዲና
እንደ ለጋ ሸንበቆ ዐፅም ፅናት ካጣበት  
አካል ከዳሸቀበት
አንደበት ከደከመበት
መኖር መብረር መምጠቅ ቀርቶ
ዳዴ ርምጃ በሆነበት  
ከመከራዉ አዉታር አልፎ ከጭንቀት ክልል
ባሻገር
መልካሙን ጸጋ ለማጤን ተስፋ ብቻ ነዉ
የሚሻገር  
      በመተሳሰብ እልባት
      በፍቅር ሰናስልት ዉሕደት
      የተሳሰረዉ ቤተሰብ የጠበቀዉም አንድነት
             ፍቅሩን በፍቅር ላይመልሰዉ
             ምን ሊበጀዉ?
                    ብቻ አይቀርም መመኘቱ
                    ርኅራኄንም መሻቱ
                    ዐይኑ ፍቅሩን መቃኘቱ
                    ገላዉም አለምድ እያለዉ
                    ወገኑን ባዕድ ሲያደርገዉ
የባዳ ሞኝ እንደሚሉት “አስቀድሙኝን”
ሲያስመኘዉ
ግና ጭራሽ ላያገኘዉ
በኃዘን ጭጋግ ተጋርዶ ሕሊናዉ ሊጨልምበት
እንዳልጸና ለጋ ችግኝ አብራኩ ጽናት ሲያጣበት
 አቤት ጽልመት
ሆኖም—ከዚህ ጨለማ ባሻገር ያለዉን ፋና
የሚያየዉ
         ትዕግስትን የሚላበሰዉ
         ሐሳብን ሰፋ የሚያደርገዉ
         መሪሩን ጣፋጭ አድራጊዉ
         የሕይወት ጣዕም ተስፋ ነዉ
ከዕለት ዕለት የሚዘለዉ የሰዎች የሕይወት ድርሻ
የአዕምሯቸዉ አብሳይ ኃይል የአካላቸዉ
መጐልመሻ
የጉልበታቸዉ ምንዳ
የድካማቸዉ ፋይዳ
ለኑሯቸዉ ለዋጭ ሆኖ ችግራቸዉን ሊያጸዳ
        ሲገባዉ እንዳዛ ሊሆን   
        ሆኖም መሆን ያለበት ሳይሆን
        በወጉ ሳያድግ አካልም  
        በቁስ አካላት እጦት ሳይበለጽግ አንጎልም
        ላብም ጥሪት ሳያፈራ
        እጅም ጭብጡን ሲዘራ
        ድካም ብቻ ለፍቶ መና
የሕይወት ቀንበር ክብደቱ እማይለቀቅ ይመስልና
መልካም ገጷ ጭራሽ ዞሮ ሲኦል ለበስ ትሆንና
             አዬ ሕይወት ምንሽ ቀና?   
             የሚለዉን የሲቃ ቃል
             ተስፋ ዳሩ ይለዉጣል
 የሕይወት መራሩ ፍሬ ዛሬ ለኛ ቢታደልም
ይህን የሰጠዉ እጅዋ ጣፋጩንም አይነፍገንም
       ይላል ተስፋ
       ዐይነ—ሕሊናን ሊያሰፋ
       ምዕራፍ የለሽ ጉዞ የለም
       ግብ—አልባ እቅድም አይኖርም
 መነሻዉና መድረሻዉ በሒደቶች ቢራራቅም
ወጣኙ ትልሙን ሲመጥን ከጊዜ ጋር ያያይዛል
በያንዳንዷ ሰኮንድ እልፈት ያችን ታህል ያቃልላል
ሥራና ጊዜ ሊጣመር የግብን ልደት ያቀርባል
የወጣኙም ልብ ይጓጓል
ዳሩ ግን በዚህ ጉዞ መሐል ድንገት
አዲስ ክስተት ይመጣና
ጅምሩ ዉጥን ተቀምጦ ሌላ የሕይወት ጫና
           ሌላ የኑሮ ዕዳ
           እማይደፍን ቀደዳ
           ለማያዉቁት አዲስ ዉጥን
           ግንቡንም ለማይተምኑት
           ባለቤትም ለማይሆኑት
           አዲስ ዕቅድ
           ታዲያ ራስን ሲዳርጉት?
           ሰማይ እንዴት አይደፋ?
           ኑሮስ እንዴት አይከፋ?
          በጠበበዉ ምድርና በተደፋዉ ሰማይ ማዶ
ዐይነ—ሕሊና አሻግሮ ሐቅን ከሒደት አዋህዶ
ተስፋ ብቻ ይሻገራል ጥቁሩን ሕዋ ቀዳዶ፡፡
፪. አብሮነት እና ባይተዋርነት
መንዴራ ከተሰኘዉ ሥራ ሌላ የት ነዉ? በተሰኘዉ የግጥም መድበል ዉስጥ የቀረበዉ የከበደች ሸጋ ሥራ መድኃኒት ነዉ፡፡ ከበደች በእዚህ ሥራ እንደምትነግረን፣ በየትኛዉም የሕይወት ገፅታ ዉስጥ ቢገኝ ለሰዉ መድኃኒቱ ሰዉ ነዉ፡፡ እናም፣ ለእሷ እጅግ አስከፊዉ አንገሽጋሽ መከራ ከሌሎች ተገልሎ በባይተዋርነት ግዞት መማቀቅ ነዉ፡፡ ሰዉ በአብሮነት ከተጋመደ ሥጋዊ ፍዳዎች የሚያሳርፉበትን ብርቱ በትር ተቋቁሞ ፈተናን ማለፍ ይችላል፡፡ ከበደች የአብሮነትን ፀጋና ትሩፋት መድኃኒት በተሰኘዉ ሥራዋ እንደሚከተለዉ ፈክራለች፦   
      ሰዉ እንጂ መድኃኒት
      ለሰዉ ሕመምማ
      ለሰዉነት ደዌዉ
      ለመንፈሱ ፃማ
      ለዐይንም መድኃኒቱ
      አድማስ ነዉ ፈዋሹ
      ገደብ የለሽ ትዕይንት
      ሰማይ ጥግ ግርዶሹ
      ለእግርም እርምጃ
      ወሰን የለሽ ጉዞ
      ጣመን እስኪይዘዉ
      ዉስጡ ዉሃ አርግዞ
      ለርኃብም እህል
      ለጥማትም ዉሃ
      ለአእምሮም ፍስሐ . . .
      ዐይንም አድማስ ይጣ
      እግርም ይታሰር
      አንጀትም ይጠበቅ
      ላመል ታህል በልቶ
      ሁሌ መርካት ቀርቶ
      ላንቃም በጥም ይረር
      ዉስብስብ አዕምሮም
      በሐዘን ይቦርቦር . . .
      ግን ከንፍገት ሁሉ
      ሰዉ መንፈግ ይከፋል
      ለሰዉ ህመም ደዌ
      ሰዉን ምን ይተካል?
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያዊቷ ሠዓሊ፣ ቀራጺ እና ባለቅኔ ከበደች ተክለአብ ከረጅም ዘመናት በፊት ያሳለፈችዉን ፈታኝ የሰዉ ልጅ ፍዳ፣ በእስር ሕይወቷ የታዘበችዉን የሕይወት ገፅ በሠመረ ኪነት ስለ ሰዉነት እና ህልዉና ጥልቅ አረዳድ እንዲኖረን ያደረገች ታላቅ ከያኒ ናት፡፡ ግለ ታሪኳና ሰብዕናዋ የሰዉ ልጅ ፅናት፣ ጀግንነት፣ ፍቅርና ርህራሄ አብነት ነዉ፡፡ ሥራዎቿ በእሳት የተፈተነ ኪነት ምን እንደሚመስል፣ ኃይሉ የት ድረስ እንደሆነ፣ ፋይዳዉ ምን እንደሆነ ግንዛቤ እንዲኖረን ረድተዉናል፡፡ የግጥም ሥራዎቿ  የሰዉ ዘር እኩይነቱንና ኢ-ፍትሃዊነቱን ነቅሶ የመልካምነት ሸማን እንዲጎናፀፍ የሚያሳስቡ ናቸዉ፤ ኅሊና ማሳ ላይ ብርቱ  ቁም ነገር የሚዘሩ፡፡


Read 1107 times