Saturday, 25 February 2023 13:54

ሴቴው ድርሰት፤ ‹‹ሥጋ ለበስ አበባ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

  ‹‹ሥጋ ለበስ አበባ›› የደራሲ ዘማት ሥራ ነው። ድርሰቱ በአንድ በኩል የአጫጭር ታሪኮች መድበል፣ በሌላ ገጹ ደግሞ ወጥ ድርሰት ነው ብዬ አምናለሁ፤ ‹‹ሥጋ ለበስ አበባ›› በተሰኘ ድርሰት ‹‹ሥጋ የለበሰች እንስት›› እንደ እርጥብ ሌጦ ተገድግዳ እናገኛለን፤ ሃምሣ (50) በሚደርሱ ታሪኮች የተገደገደች፤ በዚያች ጽጌ መሳይ እንስት ምክንያት አንዴ እንደ አጭር - አንድ‘ዜ ወጥ ልብ-ወለድ የተተበተቡ ታሪኮች የታጨቁበት ድርሰት ነው፤ ከተነባቢነት ባሻገር የሚከተሉ ሙክርታዎች (experiments) የተስተዋሉበት ድርሰት ነው ብዬ አስባለሁ፡-
ሥነ-ውበት - ሕይወትን በሥነ-ውበት መፈከር/መተርጎም - ደራሲ የሆነን/የተከሰተን ወይም ምናባዊ ክስተትና ፈጠራን ይፈክራል/ይተረጉማል በድርሰቱ። በሕይወት ለመቆየት የደም ዝውውር ግድ ይላልና፣ አንድን ታሪክ ለመተረክ ቋንቋ አስፈላጊ ነው፤ ቋንቋ ሀሳብን መሸከም የሚችል መሆን እንዳለበት ይታመናል፤ ቋንቋ የማንም ነው፤ ግና በቋንቋ ረዳትነት የድርሰት ሀሳብ እየተፈከረ ይቀርባል።
በሥነ-ውበት ሕይወትን መፈከር የተለመደ ነው፤ ደራሲ የተለመደውን አባባል፣ ተረት፣ ምሣሌያዊ አነጋገር እና ሌላም…ለትረካው ዐውድ ባመቸ መልኩ ለውጦ በማስረግ ሕይወትን በሥነ-ውበት መፈከር ይችላል። በዚህ ድርሰት፣ ዘማት ሕይወትን በሥነ-ውበት የፈከረበትን/ የተረጎመበትን ማሳያዎች፡- በገጽ 51 ‹‹የፍቅር ክፍል ደደብ ተማሪ አድርጎ ስለሚስላት››፣ በገጽ 63 ‹‹እንደ ደረቀ ቧንቧ ብረት ብረት የምትል የፍቅር ጠብታውን የሚጥል ሰው ሆኗል›› እና ‹‹በፈጠርሁ እጄን ተነጠቅሁ›› የሚሉ ገላጭ ሐረጋትንና ዓረፍተ-ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል። ከላይ የተጠቀሱ ውበታም ቃላትን፣ ገላጭ ሐረጋትንና ዓረፍተ-ነገሮችን በትረካው ዐውድና በገጸ-ባሕርይ ምክንያት እያሠረገ፣ ከተለመደው አገባብና ቅርጽ ይወጣና ሀሳቡን ለመፈከር/ለመተርጎም ተጠቅሟል ብዬ አስባለሁ፤ ውሉ አጽንኦት ነው። በዚህ ቴክኒክ ዓለምንና እውነቷን የመፈክር ትልሙን በሠመረ መልኩ አስቃኝቶናል!
ሥነ-ልቡናዊ ሕልዮቶች /Theories - አሜሪካውዊ ፈላስፋ ጆን ደዊይ (John Dewey) እና ደቡብ አፍሪካዊው የቀመር ሊቅ (የapartheid ሥርዐት ተቃማዊ የነበረው) ሰይመር ፐፐርት (Seymour Papert) ዕውነት በግለሰቦች አዕምሮ ውስጥ እንደሚገኝ ይደነግጋሉ፤ ዕውነት ትርጉም የሚኖረውና የሰው ልጅ ዕውቀትን የሚሸምተው ከግለሰብ አኗኗሩ በመነሳት እንደሆነ ይታመናል።
ደራሲ ዘማት ይኼንን ሕልዮት በድርሰቱ ሕልው እንዲሆን ያደርጋል፤ በሳለው ገጸ-ባሕርይ እየታገዘ ዕውነት፣ ዕውቀትና ልምድ ምን እንደሆኑ ይነግረናል። በይነ-ዲስፒሊናዊነት ዕውን በሆነበት የሥነ-ጽሑፍ ዕድሜ የተለያዩ ሕልዮቶችን/ትወራዎችን (Theories) በድርሰት ውስጥ ማቀፍ ልማድ ሆኖአል። ሕልዮቶች በምንቀርጸው ገጸ-ባሕርይ ወይም በትረካው ዐውድ አስገዳጅነት ምክንያት በትረካ ውስጥ ብቅ ሊሉ ይችላሉ። ለአብነት ስንኳ ከገጽ 37 ላይ የአብርሃም ማስሎን በእርከን የመተንተን ትወራ/hierarchy of need እናስተውላለን፤ ከገጽ 40 ላይ ስሜትን ሲያብራራ እና ከገጽ 279 ላይ አፈ-ታሪክን በፈጠረው ገጸ-ባሕርይ ምክንያት ተነሳስቶ፣ በሥነ-ልቡና ትወራ ሲያስቃኘን እንመለከታለን፤ ይኼ ቴክኒክ በደራሲው ቀጣይ ሥራዎች ላይ ጎልቶ እንደሚወጣ ተስፋ አለኝ።  
ስዕላዊነት - ሥዕላዊ ድርሰት ክስተቶችን ምሥላዊ በሆነ መልኩ የሚተርክ የጽሑፍ ዓይነት ነው፤ በሥሜት ሕዋሳቶች የሚዳሰሱ ብሎም የሚንቀሳቀሱ ትዕይንቶችን መፍጠር ዓላማው ነው። ደራሲ በቴክኒካዊ እና በኪነ-ጽሑፋዊ ዘዴዎች ሥዕላዊነቱን ዕውን ማድረግ ይችላል፤ በቴክኒካዊ ዘዴ የክስተቶችን ሁኔታ (mood) ለአዕምሮአችን እንዲመቹ ያደርጋል፤ በኪነ-ጽሑፋዊ ዘዴ ደግሞ ነገሮች፣ ክስተቶች፣ ታሪኮች ስዕላዊ እንዲሆኑ ይጥራል - ደራሲ፤  
ደራሲ ዘማት ከድርሰት ዓይነቶች መካከል፣ በቴክኒክና ኪነ-ጽሑፍ ረገድ ስዕላዊ የአደራረስ ዘዴን በዚህ መጻሕፉ አካቷል ብዬ አምናለሁ። ደራሲው የክስተቶችን አጠቃላይ ወ ዝርዝር ባሕርይዎች/ዝርዝሮች ያቀርባል፤ ብሎም ክስተቶቹ ሲሆኑ በተራኪው ላይ ያደረውን/ የተፈጠረውን ሥሜትና ሁኔታ ያትታል - በዚህ ምክንያት አንባቢው ላይ ተላላፊ ሥሜት እንዲፈጠር ይተጋል፤ ማሳያ እንካችሁ፡- ገጽ 11፣ 23፣ 263 ላይ የተካተቱ ትረካዎችን ማየት ተገቢ ነው።
መልክዐ-ምድር/Geography - መልክዐ-ምድር ውህድ የአተራረክ ቴክኒክ በአንባቢ አዕምሮ ውስጥ ምስል የመከሰት ብሎም በስሜት ሕዋሶቻችን ድርጊያዎችን መዳሰስ እስኪቃጣን የማስቻል አቅም ስላለው ተመራጭ ይትባሕል እንደሆነ ይታመናል። ዘማት ከመልክዐ-ምድር ጋር ሙጥኝ ይልና በአንባቢ አዕምሮ ስዕል ይስላል፤ እንካችሁ ማሳያ፡- ከገጽ 181 ላይ ያለውን ትረካ ማየት ይቻላል።  
ግጥማዊነት - በትረካ ወቅት፣ የቃላት ምጣኔና የቃላት ቁጥብነት ሕያው እንዲሆኑ ሕገ-ደንብ አለ። የዓረፍተ-ነገር አጀማመርም እንዲሁ ማራኪ ቢሆን ይመረጣል። የደራሲ ዘማት የቃላት አጣጣልና የአተራረክ ይትባሕል ፕላቶአዊውን ቃለ-ምልልስ እምብዛም ሳያጠቃልል፤ አርስቶትላዊውን የዝርግ ዓይነት አተራረክን ተመራጭ ያደረገ ነው። በእርግጥ በቃለ-ምልልስ (ዲያሎግ) ጭምር መተረክ የገጸ-ባሕርይውን ስሜት እንድንረዳ ያስችል ይሆናል፤ ነገር ግን የአርስቶትል ዓይነት ዝርው ትረካ የንባብ ወቅት የሀሳብ መበታተንን ሊታደግ ይሆናል፤ እንዲሁም አንባቢ ስሜቱን እንዲቀላቅል ይረዳል።
በዚህ ረገድ ደራሲ ዘማት ዝርግ ግጥማዊ ቃላትን፣ ገላጭ ሐረጋትንና ዓረፍተ-ነገሮችን እንደሙክርታነት ተንተርሶ ትረካውን ውብ አድርጓል ብዬ አስባለሁ፤ ለመተማመኛ እንሆ ማሳያ፡- በገጽ 92 ‹‹ሰው ወድቆም ይመላለሳል፤ ዘላለማዊ ሞቱን እያደለበ ይንፈላሰሳል››፣ በገጽ 177 ‹‹ወይንን ዕርቃኑን መብላት የሚወዱ ሰዎች ቆዳውን ይልጡታል! ሲላጥ ውስጥ ሰውነቱ ብቅ ይላል›› እና ሌላ ማሳያዎችንም መጥቀስ ይቻላል። ከላይ የተጠቀሱ ማሳያዎች በሐረግ፣ በሐረግ ቢደረደሩ ግጥማዊ ለዛ አላቸው የሚል ዕምነት አለኝ፤ ይኼ ሙከራ የሚበረታታ ነው።
አጭር ልብ-ወለድን ከረጅም ልብ-ወለድ ማዋሃድ - ደርሰቱ የአጭር ልብ-ወለድ ስብስብ እንደሆነ መደንገግ ሕጸጽ የለውም። ሊያውም ‹‹አናሳ›› እና ‹‹የበታች›› ተደርገው የተወሰዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዕድፍ፣ ጉድፍ፤ ውጥንቅጥ፣ ትዝታ፣ እምርታ፤ ውድቀት፣ ደግነት፤ አዋዋል፣ አመል፤ ችሮታ፣ ችሎታ… አካቶ በሃምሣ ዓይነት መባዎች የቀረበ የሥነ-ጽሑፍ ቡፌ ወ ሌማት! ደራሲው በመግቢያው እንደተናገረው፣ በብዜት ሥሌት አንዳች የአበባ ሥጋ የለበስች እንስት የታሪኮቹ ማገናኛ በማድረግ አጭር ሆኖ የከረመውን ልብ-ወለድ ወጥ ልብ-ወለድ ለማድረግ ታትሯል፤ ያቺ እንስት በተለያዩ ጊዜያትና ዐውዶች መካከል በእያንዳንዱ ታሪክ ብቅ እያለች መተሳሰርን ዕውን አድርጋለች፤ በዚህ የተነሳ አጭሩን ወጥ የማድረግ ሙከራው እንደሰመረ መመልከት እንችላለን። አርክቶኛል!
ኑረታዊነት - ይኼ ነጥብ በትረካ ውስጥ ቦግ-ሕልም የሚል አንድ ቴክኒክ ነው፤ ደራሲው በትረካ ዐውድ እና በገጸ-ባሕርይ ሥሜት እየተመራ የተለያዩ ኑረታዊ፣ ፍትሐዊ፣ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን ያነሳል። ለምሳሌ፡- በገጽ 22፣ 35፣ 40፣ 47፣ 55፣ 61፣ 74፣ ላይ የተካተቱ ትረካዎችን መጥቀስ ይቻላል።  
ያልተጠበቁ ክስተቶች - ሊቃውንት እንደሚናገሩት ኪነ-ጥበብ አንድ ደረጃ ይቀድማልና፣ ከተኖረ ይልቅ ይሆናል ተብሎ የሚገመትን ክስተት መድረስ ያዋጣል ባይ ነኝ። ያልተጠበቁ ክስተቶች/unexpected incidents/ በዕውን ዓለም የሌሉ፣ ያልተጠቁ ድርጊያዎች/ክስተቶች በድርሰት ውስጥ ተተርከው እናገኛለን፤ በተለይ በፊልምና ድራማ ይዘወተራሉ። ዘማት ያልተጠበቁ ክስተቶች በትረካ ዐውድ ምክንያት እየተገደደ አካቷል፤ ለምሳሌ፡- በገጽ 28፣ 81፣ 89፣ 100 ላይ የተነሱ ሀሳቦች በዓይነታቸው ያልተጠቁ እና አዳዲስ ክስተቶች ናቸው።  
ሴቶችን ማብቃት - Post-modernism በለው Neo-Historicism የተዘነጉ፣ የተጨቆኑ፣ ትኩረት ያጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥነ-ጽሑፍ አካል እንዲሆኑ ይደነግጋሉ፤ እናም ደራሲ ታሪካቸውን ለማንጸባረቅ ይጥራል፤ ናፖሊዮን በርካታ ድሎችን የተቀዳጀው…፣ በሴት ውኃ የሴት እሳት መጥፋቱ… እሙን ነውና። ከእነዚህ መካከል እጓለምውታዎች፣ ማቲዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ወላጅ አልባ ሕጻናት፣ የቡና ቤት ሴቶች ይገኙበታል።
ደራሲ ዘማት፣ የእነዚህ ግለሰቦች ጉዳይ ይቆጠቁጠዋል ብዬ አምናለሁ። ለሴት ልጅ የሚሰጠው ዋጋ ጠንከር ያለ ነው፤ ለሴቶች ጥሩ ግምት መስጠት ከሥነ-ልቡና ጥንካሬ ጋር ይገናኛል። የመልካም እሳቤዎች ምንጭ በጠንካራ ሥነ-ልቡና መገንባት ሊሆን ይችላል፤ እናም ሴቶችን የሚያበቃ የመልካም እሳቤ ባለቤት ነው ደራሲው። ለምሳሌ፡- ከገጽ 32 ላይ የአንዲትን እጓለምውታ ታሪክ ሲያትት እናገኛለን፤ ገጽ 73 ላይ ቆፍጠን ያለች እና ጥገኛ ስላልሆነች እንስት ይተርክልናል፣ ገጽ 143 ላይ አገሯን ወዳድ ሴት ያስተዋውቀናል፣ ገጽ 267 ላይ በራሷ የምትተማመን ሴት እናገኛለን፤ እና ሌሎች ሴት አበረታች ትረካዎችን ደራሲው በቀጣይ ሥራው አበልጽጎ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።
ዘይቤአዊ ንጽጽር - ደራሲው ድንቅ የሆነ ተምሳሌት ይቀምማል። በSimulation/ፍጹም ተቃራኒ የሆኑ ሁለት ሐሳቦችን በማገናኘት ጉዳዩ ትኩረት እንዲስብ ያደርጋል። ዘይቤዎቹ በአብዛኛው አነጻጻሪ ሲሆኑ ዋናው ገጸ-ባሕርይ ቋንቋን በመጠቀም ፍትሐዊነትን፣ እውነታን፣ የሐቅ መዛባትን፣ የነገሮች አለመገጣጠምን፣ ግነትን… ወዘተ. ይመረምራል። ሌላው ደግሞ ዘይቤዎቹ ሙድ ዓይነት ትረካ መምሰላቸው ነው። ምሳሌ፡- በገጽ 63 ‹‹ቡና ጠጥቶ ከጊዜአዊ እንቅልፉ እንጂ ከዘለዓለም ንዴቱ የነቃ ማንም የለም››፣ ገጽ 64 ‹‹እዚም የተቆረጠን ተስፋ ከተቆረጠ ራሱ ጋር ለማመሳሰል ሲል››፣ ገጽ 106 ‹‹የተነገሠባቸው ከሌሉ የሚነግሡ አይኖሩም›› እና ገጽ 267 ‹‹ነጻነትን ያጣነው ነጻነትን በመፈለግ ውስጥ ነው፤ ብናገኘው ማስፈለጉን እንኳን ርግጠኛ ላንሆን እንችላለን›› እና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል።
ቁስ አካላዊ መሣሪያዎች/Mechanical Device - ቁስ አካላዊ መሣሪያዎች በኢታሊክስ የተጻፉ ዓረፍተ-ነገሮች፣ የተሠመረባቸው ሐረጋት፣ በቃለ-አጋኖ የሚያልቁ ገለጻዎችን ያካትታል። የዚህ ቴክኒክ ጠቀሜታ በትረካ ወቅት የሚስተዋሉ የአቅጣጫ፣ የሂደትና የጊዜ መለዋወጦች እና የገጸ-ባሕርይውን ትኩረት መጠቆም ነው፤ በታሪኩ ውስጥ ምን እየሆነ እንደሆነ አመላካች ናቸው። ለማሳያነት በደማቅ ተጽፈው እና በItalics የተተረኩ ሀሳቦችን ማየት ቀላል ነው፤ በዚህ ዓይነት ቴክኒክ ደራሲው ትኩረት የሚሹ ብሎም ወሳኝ ክስተቶችንና የገጸ-ባሕርይውን ግብረ-መልስ በጥንቃቄ እንድንመረምር ያደርጋል።
የአጭር-አጭር ታሪኮች/Short-short story/ Post-card story - ‹‹ለምን በ20 ዓመቱ ሞተ?›› እያልን ማንጓጠጠጥ ተገቢ አይመስለኝም። የአጭር-አጭር ታሪኮች ከዕድሜአቸው አንጻር አጭር ናቸው፤ በሕዋ ጊዜ ኮንቲነማቸው ለመገባደድ እጅግ በጣም የፈጠነ ሲሆኑ፣ በአንድ መቀመጫ የመነበብ፣ በአንድ አፍታ የመጠናቀቅ ዕድል አላቸው። የአጭር-አጭር በመሆናቸው አላባዊያንን ሙሉ በሙሉ ላያጠቃልሉ ይችላሉ - በዋናነት ከገጸ-ባሕርይ ይልቅ ለክስተቶች ትልቁን ስፍራ ይሰጣሉ - ገጸ-ባሕርይው በመሀል ብቅ እያለ ግብረ-መልስ ይሰጣል። ጊዜ ከመቆጠብ፣ መሰላቸትን ከመቀነስና ከውስብስብነት የጸዱ በመሆናቸው ተመራጭ ናቸው - የአጭር አጭር ትረካዎች! ደራሲ ዘማት በበኩሉ በአጠቃላይ በሚመስል ሁኔታ መጻሕፉን በአጭር አጭር ትረካዎች ደርሷልና ከላይ የተጠቀሱ ጥቅማ-ጥቅሞችን አንባቢ ያገኛል ብዬ አስባለሁ።
ምልክት/Symbolism - ምልክት የድርሰት ማኅበረሰብን ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወግ ይወክላል። እውነት የሚመነጨው ከምልክትና ከማኅበረሰብ ፎክሎር እንደሆነ ይታመናል። ዘማት የተረሱ እና ትኩረት ያጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በትረካዎቹ አካቷል የሚል እምነት አለኝ፤ ለዚህም በሥነ-ልቡና ጠንካራ መሆኑ ጠቅሞታል ብዬ አምናለሁ!!
አፈ-ታሪክ - የነበረን ከርክሞ አዲስ ታሪክ የማምጣት ሂደት ነው ይኼ ነጥብ - de-constructivism፤ ዘማት ነባሩን ይትባሕል ከርክሞ አዲስ ያበጃጃል፤ ማሳያ እንጥቀስ፡- በገጽ 173 ላይ ጥንት የምናውቀውን የማክዳንና የሠሎሞንን አፈ-ታሪክ የአሁን ጊዜ አድርጎ ቀይሮት እናገኛለን፤ ሊያውም ወንድን በሴት ሥም ‹‹ማክዳ›› ብሎ እስከመሠየም የበቃ ጥንካሬ።
ማጠቃለያ - ‹‹ሥጋ ለበስ አበባ›› የድርሰት ሀሳብን መሸከም የሚችልና የመመራመር አቅም ባለው ቋንቋ የተከሸነ ድንቅ ልብ-ወለድ ድርሰት ነው። ሕጸጻቸው ያልጎላ ሙክርታዎች እንደልብ ናቸው! አጭር ልብ-ወለድ ከረጅም ልብ-ወለድ ጋር እየተዋሃደ የተደረሰበት መጻሕፍ ነው፤ ወዲህ ሲል ደራሲው የሴቶች ጉዳይ ይቆጠቁጠዋልና፣ ሚናቸውን፣ አስተዋጽኦዋቸውን፣ ደካማና ጠንካራ ገጻቸውን፣ አበክሮአቸውን… በሚገባ ያስቃኛል::





_________________

Read 858 times