Saturday, 04 March 2023 10:38

በኢትዮጵያ ከትንባሆ ጋር በተያያዘ በዓመት 17 ሺህ ሰዎች ገደማ ይሞታሉ ተባለ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  የምግብና መድሀኒት ባለሥልጣን አዲስ ድረ-ገፅ ይፋ አደረገ
                       
         በኢትዮጵያ የትንባሆ አጠቃቀም ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሳምንት 259 ወንዶችና 65 ሴቶች እንዲሁም በዓመት 16 ሺህ 800 ሰዎች እንደሚሞቱ ተገለፀ፡፡
ይህንን የገለፀው የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል አዲስ ድረ-ገፅ ባስተዋወቀበት ወቅት ነው፡፡
ባለስልጣኑ መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔን ለማጠናከር ከዴቨሎፕመንት ጌትዌይ ጋር በመተባበር፣ የኢትዮጵያ ትንባሆ ቁጥጥር ድረ-ገፅን (Ethiopia.tobaccontroldata.org) እ.ኤ.አ ከ2021 ዓ.ም ጀምሮ ሲያዘጋጅ መቆየቱን የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና  የዳይሬክተር ሔራ ገርባ ተናግረዋል።
ድረ-ገፁ በዋናነት ህግ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላት ትንባሆ ቁጥጥርን በሚመለከት የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም አይነት መረጃዎች በአመቺ ሁኔታ እንዲያገኙ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ድረ-ገጹ ውጪ የደቡብ አፍሪካ፣ የዛምቢያና የናይጀሪያ ድረገጾች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ውለዋል። በቀጣይ የኬንያና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድረ-ገጾች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ የተባለ ሲሆን፣ እነዚህ ድረ-ገጾች የተዘጋጁት ዴቨሎፕመንት ጌትዌይ ሚለንዳጌትስ ፋውንዴሽን ባደረገለት የገንዘብ ድጋፍ በሚያስፈጽመው የትምባሆ ቁጥጥር ዳታ ኢኒሼቲቭ (TCDI) ፕሮግራም አማካኝነት ነው ተብሏል።
ዋና ዳይሬክተሯ ጥናቶችን ጠቅሰው እንደተናገሩት፤ በዓለም ዙሪያ የትምባሆ ፍጆታ እየቀነሰ ቢሆንም በአፍሪካ ግን ከፍተኛ የአጫሾች ቁጥር ጭማሪ ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ እስካሁንም ድረስ ሲጋራዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኙ በመሆናቸው ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው በአጽንኦት ገልጸዋል።
በሀገራችን ብዙ ወጣቶች መኖራቸውና የገቢ መጠናቸው እየጨመረ መሄድ፣ በትምባሆ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በተመለከተ የግንዛቤ ውስንነት፣ የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎች እንዳይጸድቁና ተግባራዊ እንዳይሆኑ የትምባሆ ኢንዱስትሪው ጣልቃ ገብነትና ተያያዥ ጉዳዮች ለአጫሾች ቁጥር መጨመር በምክንያትነትና በስጋትነት ተጠቅሰዋል።
በዚህም ምክንያት ከ15 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው 3.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የትምባሆ ምርቶችን ይጠቀማሉ የተባሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የህግ ማዕቀፍ በአፍሪካ ውስጥ ካሉትና በጣም ጠንካራ ከሚባሉት የቁጥጥር ህጐች የሚመደብ ቢሆንም፣ አተገባበሩ ግን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል።

Read 1545 times