Saturday, 04 March 2023 10:54

የዘንድሮው የአድዋ በዓልን በምኒልክ አደባባይ ማክበር አለመቻሉ ነዋሪውን አስቆጣ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(6 votes)

  • በዓሉን ለማክበር የወጣ አንድ መምህር በጥይት ተመቶ ህይወቱ አልፏል
    • በርካቶች በፀጥታ ሀይሎች በተተኮሰባቸው ጥይት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል
    • የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ንግስ በአስለቃሽ ጭስ ተስተጓጉሏል
    • በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በርካታ ህጻናትና አቅመ ደካሞች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል
    • ቤተክርስቲያኗ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ታወጣለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
        
          ላለፉት 127 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ምኒሊክ አደባባይ በታላቅ ድምቀት ሲከበር የኖረው የአድዋ ድል በዓል፤ ዘንድሮ ከፍተኛ ችግር ገጥሞታል፡፡ በዓሉን ለማክበር በስፍራው በተሰባሰበው ነዋሪ ላይ የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት የሃይል እርምጃ፣ የሰው ህይወት ማለፉንና በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል፡፡
በየዓመቱ የካቲት 23 የሚከበረው የአድዋ ድል በዓል ቀድም ሲልም ሲከበርበት በቆየው የሚኒሊክ  አደባባይ ላይ ለማክበር የሚሄዱ ሰዎችን የፀጥታ  ሃይሎች ወደ ስፍራው የሚወስዱትን አምስት መግቢያ መንገዶች በመዝጋት፣ በዓሉን ለማክበር ወደ አደባባዩ የሚሄደውንም ሆነ ዓመታዊውን የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ንግስ ለማክበር ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄደውን ምዕመን በመኪናም ሆነ በእግር እንዳያልፍ ሲከለክሉ ቆይተዋል። ከጎጃም በረንዳ ወደ ሚኒሊክ አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብቻ ነበር ለእግረኛ ክፍት የተደረገው።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ማለዳ ላይ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ተገኝተው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠው ከሄዱ በኋላ ወደ አደባባዩ በመጠጋት ፎቶግራፍ ለመነሳትና በተለያዩ መንገዶች በዓሉን ለማክበር የሚፈልጉ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች በስፍራው ተሰብስበው ነበር፡፡ የፀጥታ ሀያሎች በስፍራው በዓሉን ማክበር እንደማይቻል በመግለጽ የተሰበሰበውን ሰው ለመበተን በተኮሱት አስለቃሽ ጭስ፣ የላስቲክ ጥይትና እውነተኛ ጥይት በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው የታወቀ ሲሆን በዓሉን ለመታደም ከስፍራው የነበረ አንድ መምህር ከፀጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉም ተነግሯል፡፡
የዳግማዊ ሚኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሲቪክ መምህር እንደነበር የተነገረው መምህር ሚሊዮን ወዳጅ፤ ሚኒሊክ አደባባይ አካባቢ ከፀጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት ተመቶ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉ ተናግሯል፡፡ ሚሊዮን በጥይት በተመታበት ቅፅበት ሕይወቱ ያለፈ ቢሆንም፤ ወደ አብንት ሆስፒታል እንዲሄድ ተደርጓል፡፡
በሆስፒታሉ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች እንደገለፁትም ሚሊዮን የተመታበት ጥይት በአንድ ጎኑ ገብቶ በሌላኛው እንደወጣና ህይወቱም ወዲያውኑ እንዳለፈ ተናግረዋል፡፡
የፀጥታ ሃይሎች በአደባባዩ ላይ የነበረውን ህዝብ በአስለቃሽ ጭስና ጥይት ለመበተን ከሞከሩም በኋላ በመናገሻ ገነተ ፅጌ ቅዱስ  ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አመታዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል በማክበር ላይ የሚገኙ ምዕመናን ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱንና በዚህ ሳቢያም የንግስ ክብረ በዓሉ መቋረጡን በርካታ ህፃናትና አቅመ ደካማ ምዕመናን ከፍተኛ ጉዳት  እንደደረሰባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስታውቋል፡፡ በምዕመናኑ ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ሳቢያ ወደ ሆስፒታል እንዲወሰዱ መደረጉንም ሀገረ ስብከቱ አስታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ቤተክርስቲያኒቷ ወቅታዊ መግለጫ ትሰጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ የአድዋ በዓልን በሚሊኒክ አደባባይ ለማክበር ወጥቶ ከፀጥታ ሀይሎች በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ማለፉ የተነገረውን ወጣት መምህር ሚሊዮን ወዳጅን አሟሟት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ወጣቱ የፓርቲው አባል እንደነበር አስታውሶ፤ በሰላማዊ መንገድ የአድዋ በዓልን ለማክበር በወጣበት ሁኔታ በሚሊኒክ አደባባይ በፀጥታ ሀይሎች በግፍ ተገድሏል ብሏል፡፡
የፀጥታ ሀይሎች በበዓሉ አክባሪዎች ላይ ከፈፀሙት ድርጊት ጋር በተያያዘ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ አብን በመግለጫው ጠይቋል፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በዓሉ በታሰበው ሁኔታ መከበሩን አመልክቶ፤ አንዳንድ ሰዎች በሚኒሊክ አደባባይና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቀጽር ግቢ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ ረብሻ ለመቀስቀስ መሞከራቸውንና ይህንን ለመቆጣጠር መንግስት በወሰደው እርምጃም በምዕመናን ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
በሚኒሊክ አደባባይ የነበረውን ግርግርና የጸጥታ ሃይሎች በዓሉን ለማክበር በተሰባሰበው ህዝብ ላይ የወሰዱትን የብተና እርምጃ በስፍራው ተገኝተን ለመመልከት እንደቻልነው፣ የጸጥታ ሃይሎች በሚኒልክ አደባባይ ላይ በመሰባሰብ በዓሉን ለማክበርና በመቀጠልም ወደ አድዋ ድልድይ ለመሄድ የሞከሩ በርካታ የበዓል አክባሪዎችን አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ በትነዋል። በዚህ ሳቢያም በተፈጠረ ረብሻና ግርግር በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ተጎጂዎችም በአቅራቢያ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት ተወስደዋል። የፀጥታ ሃይሎች በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አመታዊውን ክብረ በዓል በማክበር ላይ በነበሩ ምዕመናንና በርካታ ህፃናትና አቅመደካማ ምዕመናን ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል። በጉዳቱ ራሳቸውን የሳቱ ምእመናን በአንቡላንስ ወደተለያዩ የህክምና ተቋማት ተወስደዋል።  በሌላ በኩል 127ኛው አድዋ በዓል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶችና ዝግጅቶች በመስቀል አደባባይ ተከብሯል።

Read 2185 times