Saturday, 04 March 2023 11:02

“…ከሁሉም ከሁሉም አሳ ሙልጭልጭ ነው!”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

  ሁለት ጓደኛሞች ጥንብዝ ብለው ሰክረው መኪና ይዘው ወደ ሀገራቸው ይሄዳሉ። ክረምት ነው። ዝናብ ያካፋል። ድንገት በሹፌሩም መስታወት በኩል አንድ ጥቁር ጥላ የመሰለ ሰው መጥቶ በልመና መልክ እጁን ይዘረጋል። ሹፌሩ በዚህ  ዓይን ቢወጉ በማይtaይበት ጨለማ እንዲህ ያለ ቀጭንና በጣም ረዥም ጥላ የመሰለ ጥቁር ሰው በማየቱ ደንግጦ, ወደ ጓደኛው ዞሮ ያየውን በምልክት ያሳየዋል።
ጓደኛውም ´ምናልባት ሰይጣን ሊሆን ይችላል´ በሚል, ´ቶሎ መገላገል ይሻላል´ ብሎ አንድ ብር አውጥቶ ይሰጣል። ያም ጥቁር ጥላ አንድ ብሩን ተቀብሎ ወደመጣበት ይሄዳል። በግምት ከአዲስ አበባ አቃቂ የሚሆን ርቀት እንደነዱ ያ ጥቁር ጥላ ድንገት በመስታወቱ ታክኮ ይመጣና እጁን ይዘረጋል። ሹፌሩ ከቅድሙ የበለጠ በመደንገጥ ፈጠን ብሎ አንድ ብር ያወጣና ይሰጠዋል። ጥቁሩ ጥላ ይሰወራል። እፎይ ብለው ከድንጋጤያቸው ተላቅቀው ከአቃቂ ደብረዘይት ያህል መንገድ ሄዱ። ያ ጥቁር ጥላ እንደገና ተከሰተ። መስታወቱንም እየታከከ ተጠጋ። ጓደኛሞቹ በጣም ተደናገጡ። የሚነጋገሩትን ሊሰማ እንደሚችል በመጠራጠር በሹክሹክታ ያወሩ ጀመር።
አንደኛው፡- ይሄ ሰይጣን በጭራሽ የሚለቀን አልሆነም። ምን ብናደርግ ይሻለናል?
ሁለተኛው፡- እኔም በጣም ግራ ገብቶኛል። እንደመሰለኝ ከሁለት አንዳችን መስዋዕት እንድንሆንለት አስቦ ነው።
አንደኛው፡- እንደዘማ በጭራሽ መሆን የለበትም። ሁለታችንም ከዚህ መኪና ተፈናጥረን እንውጣና ለሁለት እንጋፈጠው። ከፊትና ከኋላው ሆነን ብናጣድፈው በጭራሽ አያቅተንም። ስለዚህ አንተ የክሪክ ብረት ያዝ። እኔ የመፍቻ ብረት እይዛለሁ። ከዚያ ፈጥነን እንቀጠቅጠዋለን።
ሁለተኛው፡- እስቲ ግን ድንገት አማርኛ ይናገር እንደሆን “ምንድን ነህ? ምንስ ነው የምትፈልገው?” እንበላለው።
አንደኛው፡- አዎ እግረ-መንገዳችንን እንዴት ሊተናኮሰን እንደሚፈልግ ለማወቅ እንችላለን።
ጓደኛሞቹ ጥቁር ጥላ በሌለበት በኩል ተስፈንጥረው ወጡ። አንደኛው የክሪን ብረት እንደያዘ ተጠግቶ፡-
“ምንድን ነህ ተናገር?” ይለዋል።
ጥቁሩ ጥላ፡- እስካሁን ልረዳችሁ ሞከርኩ። አሁን ግን ደከመኝ። ስለዚህ ጥያችሁ መሄዴ ነው።
አንደኛው ምንድን ነው የምትረዳን?
ጥቁሩ ጥላ መኪናችሁን ልገፋላችሁ ነዋ። ጎማው ከቅድም ጀምሮ ጭቃው ውስጥ እየተሽከረከረ ነው። እናንተ የሄዳችሁ ሳይመስላችሁ አልቀረም። ነገር ግን ብገፋው ብገፋው ከጭቃው ሊወጣ አልቻለም። እስካሁን ለገፋሁበት ስለከፈላችሁት ሁለት ብር አመሰግናለሁ።
ጥቁሩ ጥላ በዚያ በድቅድቅ ጨለማ ቀስ እያለ ጭቃ ያልሆነውን መንገድ እየመረጠ ወደቤቱ ሄደ። ጓደኛሞቹ መኪናዋን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት ልፋታቸውን ቀጠሉ።
***
ሀገራችን ማጥ ውስጥ በገባችበት ሰዓት ከችግሯ ሊያላቅቋት የሚጥሩ እውነተኛ ዜጎችን ትሻለች። ጭቃ ውስጥ እንደሚሽከረከር ጎማ፣ ከችግር ወደ ችግር ስትሽከረከር ብዙ ዘመን ሆኗታል።
ለአያሌ ዘመናት፣ ከጦርነት ባለመላቀቋ በሺዎች የሚቆጠሩ ውድ ልጆቿ ለህልውናዋ ሲሉ ተሰውተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠር ጥሪቷንም አጥታለች። ካዝናዋን ለጦር መሳሪያ ግዥ አራግፋለች። ኢትዮጵያ  በጦርነት ወላፈን ውስጥ በነበረችበት ወቅት አንድ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ ቃለመጠይቅ ሲቀርብለት፡-  “Ethiopia is not a country, It is a war” (ኢትዮጵያ እኮ አገር አይደለችም ጦርነት ናት) ብሎ ነበር። ዘበቱም እንደ ጦርነቱ ተፈራርቆብናል። ያም ሆኖ ህዝቧ ዳር እስከ ዳር እየተንቀሳቀሰ፣ የክት ወኔውን እንደቋያ እሳት እያቀጣጠለ በየዘመኑ የተነሳበትን ጠላትን ሁሉ እንደየ አመጣጡ መልሷል። የቁርጥ ቀን ልጆቿም ለህልውናዋ ሲል ገብሯል። ጦርነቱ ካስከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ባልተናነሰ መልኩ ኢኮኖሚው ክፉኛ ደቅቆበታል። ድርቅ ተፈራርቆበታል። የየአይነቱ በሽታ ዘምቶበታል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በየዘመኑ ያጋጠሙት ሹማምንት ሁሉም “ለእኔ” እያሉ የራሳቸውን ጥቅምና ምቾት ለማደላደል ሲሉ ያላወጁበት አዋጅ፣ ያልላኩበት ቀላጤ፣ ያልወሰኑበት ውሳኔ የለም። ከሁሉ በስተጀርባ ጥቅማቸውን ማጋበስ፣ ፍትሁንም ፍትፍቱንም ለዘመድ አዝማዳቸው ማዋል ዋና ስራቸው አድርገውታል።  አዲስ መንገድ ከመቀየስ ይልቅ አሮጌው አረንቋ ውስጥ መሽከርከር እንደ ባህል ተወስዷል። ቢያንስ ጭቃ የሌለበትን መምረጥ እንኳ የአባት ነበር።
ህዝቡ “ዜጋና ሹም ተሟግቶ ደንጊያና ቅል ተላግቶ አይሆንም” እያለ ነባሩን የድህነቱን ሰንኮፍ ከመንቀል ይልቅ አዳዲስ ምርጥ ሹማምንት የሚፈጠሩበትን አዲስ ድህነት እየለመደ መኖርም እንደ ተፈጥሮ ክስተት ተቀብሎታል። ከነግ-ሰርግ ህይወቱን ማጥ ውስጥ እየዘቀጠ አስተዳደራዊ አድልኦን፣ ቢሮክራሲያዊ ጥልፍልፉንና ከገዛ ማእዱ መገፋቱን ችሎ “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው” እያለ አንጀቱን አስሮ እንዲቀመጥ ተገድዷል። በስሙ የማይነሳ አጀንዳ፣ የማይበጠስ ቅጠል የለም። ኑሮው ግን ፈቀቅ አላለም። የማይወሳ አይነት የፖለቲካ ርዕስ የለም ለእሱ ግን። አንዳችም የዲሞክራሲ ሀቅ  ጠብ አላለለትም። ይልቁንም ትላንት “ዲሞክራሲያዊ” የነበረ ዛሬ “ጸረ-ዲሞክራሲ” ሲሆን፣ ትላንት “ታጋይ” የነበረ ዛሬ “ኢ-ታጋይ” ሲሆን፣ ትላንት ህዝባዊ የነበረ ዛሬ “ጸረ-ህዝብ” ሲሆን የማያቋርጠውን የለውጥ መኪና “Perpetual machine of change” በትዝብት ያስተውላል።
ጭራሽ ህዝቡን በአንድነት መምራት የሚገባው ገዢው ፓርቲ-ብልጽግና አመራሮች፤ የለየላቸው ጽንፈኛ ብሄርተኞች ሆነው አገርን ለማፍረስ ሲጣደፉ ማየት ያስደነግጣል። ምኒልክንና የኢትዮጵያን ባንዲራ ጠልቶ፣ አድዋን ለማክበር መሞከር የማይመስል ነገር ነው የሚሆነው።
የማይወራ አይነት የኢኮኖሚ ስርዓት የለም። ለሱ ግን አንዲት ተጨማሪ ድንቡሎ ኪል አላለችለትም። ይልቁንም ደረሰኝ ቀረሽ ሙስና ሲካሄደበት፣ የሙስናው መጠቅለያ ፖለቲካ ነውና የግዱን ባኮውን ተቀብሎ ጭጭ ይላል።
ወጥተን ወርደን፣ ከችግር ችግር ተዟዙረን አንድ መመለስ የሚገባው ጥያቄ ላይ ደርሰናል። ተገቢውን ባለሙያ በተገቢው ወንበር ላይ ማስቀመጥ። ሀገራችን የህዝቧን ኑሮ ለማስተካከል የባለሙያ ዜጎቿን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም አልቻለችም። በየስራ መስኩ የፖለቲካ ተሿሚ ሳይሆን የሙያው ባለቤት መቀመጥ ይኖርበታል። በደም- በስጋ መተሳሰር ተመልምሎ ስርዓት ያቆያል። እምነት ይሰብካል የሚባል ሰው/ እንደተባለውም “አብዮታዊ” ዲያቆን አሊያም “የተሞላ ጠበቃ” ሳይሆን በእውቀቱ አገር የሚያበለጽግ፣ በሰለጠነበት ሙያ ለትውልድ የሚበቃ አገልግሎት የሚሰጥ ዜጋ ነው የሚያስፈልገው።
 ሁሉ በሙያው ለመታገል ዝግጁ ከሆነ ድል ቅርብ ይሆናል። ሀገራችን ከገባችበት የኢኮኖሚ ማጥ የምትወጣው፣ የተሰራውን ጥፋትና ስህተት አምኖ የፖለቲካ ንሰሃ በመግባት እንጂ “የበላችው አቅሯታል በላይ በላዩ ያጎርሷታል” እንደሚባለው አይነት፣ አንዱን ጉድፍ በሌላ ጉድፍ ልሸፍንህ ሲሉት፤ A point of no return እንዲል መጽሐፈ-መርከበኛ፤ የመጣነው መንገድ ረዥም ነውና ወደፊት እንቀጥል በሚል ወደማይመለሱበት አዘቅት መግባት ይከተላል። ከቶውንም አንድ ችግርና በዚያም ሳቢያ ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ ምላሽ መስጠት ችግርን ከማባባስ በቀር ፋይዳ አይሆንም። ለማናቸውም ወቅታዊ ችግር፣ አግባብ ያለው ምላሽ በወቅቱ መስጠት ምንጊዜም ወሳኝ ነው። ማውገርገርም፣ ማድበስበስም፣ ለጥያቄ በር መዝጋትም ለእድገት ጸር ነው። አለበለዚያ የዱር አራዊቶች ሁሉ በተሰበሰቡበት፣ በተለይም ደግሞ አስፈሪዎቹ ዝሆንና አንበሳም ባሉበት፤ “ከአንበሳና ከዝሆን የቱ ይበልጣል?” ተብሎ ቢጠየቅ “ከሁሉም ከሁሉም አሳ ሙልጭልጭ ነው” አለ እንደተባለው ሰው ብንመልስ፣ ለዛሬ እንጂ ለነገ የሚበጅ ቤት አልሰራንም።

Read 2923 times