Saturday, 04 March 2023 11:07

አድርያና ሊማ የደጋፊዎች ዓለም አቀፍ አምባሳደር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   ከ3.5 ቢሊዮን በላይ የእግር ኳስ ደጋፊዎች አሉ

          ብራዚላዊቷ ሱፐር ሞዴል አድሪያና ፍራንቼስካ ሊማ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ  የደጋፊዎች ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆኗ እንደተሾመች ታውቋል፡፡ በዓለማችን የፋሽንና የኮስመቲክስ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ሱፕር ሞዴሎች አንዷ ስትሆን፤ በተዋናይትና በንግድ ስራዎቿ ስኬታማ ናት፡፡
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ሹመቱን በሰጡበት ወቅት በሰጡት አስተያየት “አድሪያና እግር ኳስን ትኖራለች ፤ትተነፍሳለች፡፡ ከሁሉም ሰው ስትገናኝ የምትሰጠው ሞቅ ያለ ወዳጅነት፣ ደግነቷን ስንመለከት እግር ኳስን ምን ያህል እንደምትቀርብና እንምትወደው እንደሆነ ይሰማናል” ብለዋል። አድሪያና ሊማ በበኩሏ በሹመቱ ዙርያ ስትናገር “ለተሰጠኝ ሃላፊነት አመሰግናለሁ፡፡ ክብርም  ይሰማኛል... በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር የመጀመሪያዋ የደጋፊዎች አምባሳደር በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፡፡  የእግር ኳስ ደጋፊዎቸ ወደ ጨዋታው ይበልጥ እንዲቀርቡ ለመርዳት እሰራላሁ” የሚለውን አስተያየት ሰጥታለች፡፡ አድርያና  በፊፋ በተሰጣት ሃላፊነት በዓለም ዙሪያ ባሉ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር የምትሰራ ይሆናል፡፡ እግር ኳስን በተለያዩ አጀንዳዎች በዓለም ዙርያ በሚያንቀሳቀሱ ዘመቻዎች ላይ ደጋፊዎችን በመወከል አምባሳደር ሆና ትሰራለች፤ ታስተዋውቃለች፤ ትሳተፋለች፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በሰራው ጥናት በዓለም ዙርያ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መኖራቸው ይገመታል፡፡
41ኛ ዓመቷን የያዘችው ሱፕር ሞዴል አድርያና ሊማ በአዲሱ ሹመቷ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፓሪስ ላይ ባዘጋጀው የ2002 የእግር ኳስ ምርጦች ሽልማት ስነስርዓት ተሳታፊ ነበረች። በሞዴልነት ከ26 ዓመታት የሰራችው ብራዚላዊቷ በታዋቂው ቪክቶርያ ሴክሬት ኩባንያ ኤንጅል የተባሉ ምርቶችን ከ15 ዓመታት በላይ አስታውቃለች፡፡ በአሜሪካው ሱፕር ቦል እና በኪያ የመከኒና ምርቶች ማስተዋወቅ ከፍተኛ ልምድ ያላት ሲሆን የሃብት መጠኗ ከ45 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመትና በዓመት እስከ 11 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ታውቋል፡፡


Read 597 times