Saturday, 04 March 2023 11:09

ሊዮኔል ሜሲ ከአውሮፓ እግር ኳስ የመልቀቅ ፍላጎት የለውም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በ2022 የፊፋ ምርጥ ሽልማት ላይ በኮከብ ተጨዋችነት ተሸልሟል፡፡ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ተመሳሳይ ሽልማት ሲቀበል ለሰባተኛ ግዜ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ ለመመረጥ  በተለይ ለአርጀንቲና ለተጎናፀፈችው የዓለም ዋንጫ ድል  ያበረከተው አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ ገብቶለታል፡፡ በኮከብ ተጨዋች ምርጫው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አባል አገራት በሙሉ ይሳተፋሉ፡፡ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች፤ ዋና አምበሎች እንዲሁም አለም አቀፍ ጋዜጠኞችና ደጋፊዎች ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ ሊዮኔል ሜሲ አናፊ ለመሆን የበቃው ከተሰጠው ድምጭ 52 ነጥቦች በማስመዝገብ ሲሆን  ፈረንሳዊያኑ በ44 ነጥብ ኪሊያን ምባፔና በ35 ነጥብ ካሪም ቤንዜማ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር  The Best Fifa Football Awards 2022 በሚል ስያሜ የሽልማት ስነስርዓቱን ባለፈው ሰሞን  በፓሪስ ከተማ ማከናወኑ ይታወቃል፡፡ በሴቶች የ2022 ምርጥ ተጨዋች ሆና የተሸለመችው የስፔኗ አሌክስያ ፑቴላስ ስትሆን፤  በምርጥ አሰልጣኝነት የአርጀንቲናው ሊኔል ስካሎኒ በወንዶች የፈረንሳይ ሳሪና ዊይግማን በሴቶች፤ በምርጥ በረኝነት አርጀንቲናዊው ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ በወንዶች  እንግሊዛዊቷ ማሪ ኢርፕስ አሸናፊዎች ሆነዋል። የፖላንዱ ማርሲን ኦሌክሲ የፊፋ ፑሽካሽ አዋርድን ሲጎናፀፍ በፊፋ የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ሉካ ሎቾሂቪሊ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ ኳታር አስተናግዳ በነበረው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ አርጀንቲናን  ከ44 ዓመታት በኋላ ለሶስተኛው የዓለም ዋንጫ  ድል ማብቃቱ ከፍተኛ ከበሬታን አስገኝቶለታል። የዓለም ዋንጫውን ድል ከማጣጣም ባሻገር በኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ መሸለሙና በማይረሳው የዋንጫ ጨዋታ  ፈረንሳይን ያሸነፉበትን ሁለት ጎሎች ጨምሮ ሰባት ግቦችን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡  በዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጨዋችነት የወርቅ ኳስ ሽልማትን ሁለት ጊዜ በመውሰድ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ብራዚል በ2014 እኤአ ላይ ባካሄደችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ኮከብ ተጨዋች ነበር፡፡
 ሊዮኔል ሜሲ በአሁኑ ወቅት በክለብ ደረጃ በኳታር ቱጃሮች በሚተዳደረው የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንትዠርመን እየተጫወተ ይገኛል።  ከ2021 እኤአ አጋማሽ ወዲህ የስፔኑን ባርሴሎናን በመልቀቅ በርካታ ክዋክብት በተሰባሰቡበት የፈረንሳይ ክለብን ተቀላቅሏል፡፡ በአንድ የውድድር ዘመን እስከ 42 ሚሊዮን ዶላር  በፒኤስጂ የሚከፈለው ሲሆን  በመጀመርያው  የውድድር ዘመን የሊግ 1 ዋንጫን ማንሳት ችሏል። በሊግ 1 46 ጨዋታዎችን አድርጎ  18 ጎሎችን ያስመዘገበ ሲሆን በአውሮፐቀ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ 13 ጨዋታዎችን በመሰለፍ 9 ጎሎችን ከመረብ አዋህዷል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን  የዓለም ዋንጫ ድል በ36ኛ ዓመቱ ላይ ካስመዘገበ በኋላ በእግር ኳስ ታሪክ የምንግዜም ምርጥ ተጨዋች ተብሎ መጠራቱን አጠናክሮለታል። ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ በፊት ሊዮኔል ሜሲ በስፔኑ ክለብ ባርሴሎና 15 ዓመታት ሲጫወት ከ600 በላይ ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ከ34 በላይ ዋንጫዎችን ተቀዳጅቷል፡፡ በእግር ኳስ ከ125 በላይ የተለያዩ ሪከርዶች ማስመዘገቡና  ከ111 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ገቢ ያገኝ እንደነበርም ይታወቃል፡፡፡
ታላላቅ ተጨዋቾች በፓሪስ ሴንትዠርመን መገኘታቸው የፈረንሳዩን ክለብ በዋንጫ ድሎች ያንበሻበሸው ባይሆንም በአውሮፓ በብዛት ስሙ የሚጠቀስ ክለብ አድርጎታል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ የፊፋን የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማት ካገኘ በኋላ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው በፒኤስጂ ይቀጥላል አይቀጥልም  የሚለው አጀንዳ ነው። በአውሮፓ ሚዲያዎች የያዝነው የውድድር ዘመን ሲያበቃ ወደ ውድ ክለቡ ባርሴሎና ሊሄድ  እንደሚችል ሲነገር ቆይቶ ከዚያም ወደ ትውልድ አገሩ አርጀንቲና መመለስ እንደሚፈልግ በስፋት ተወስቷል፡፡ ወደ ስፔኑ ባርሴሎና ከመዛወሩ በፊት ለአምስት አመታት በወጣት ቡድን የተጫወተበት የአርጀንቲናው ኔውኤል ኦልድቦይስ መድረሻው እንደሚሆን አንዳንድ ዘገባዎች አውስተው ነበር፡፡ ወደ አሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግና ወደ ጣሊያኑ ክለብ ኢንተርሚላን ሊዛወር እንደሚችልም የተናፈሱ መረጃዎች ነበሩ፡፡   ፒኤስጂ ከተጨዋቹ ጋር የፈረመው ውል በጥቂት ወራት ውስጥ የሚያበቃ ሲሆን አንጋፋው የፈረንሳይ ክለብ ተጨዋቹን በፓሪስ ለማቆየት አዲስ ኮንትራት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ሊዮኔል ሜሲም  በቅርብ ዓመት ውስጥ  ከአውሮፓ እግር ኳስ የመልቀቅ ፍላጎት የለውም፡፡Read 257 times