Saturday, 04 March 2023 11:10

የዘመን ተልእኮ እና የትውልድ ጥያቄዎች

Written by  በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

      ሕዝብን ማን ይምራ? (ፍልስፍናዊ ምላሽ)
                              
          ይህ ጥያቄ ረዥም ታሪክ ያለው ዐቢይ ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በግሪኮቹ የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ አንዱ ወሳኝ ጥያቄ ..”ማን ይምራ? ማን ያስተዳድር?”.. የሚለው ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ ይዘን እስከ ዛሬው የዘመናዊነት አስተሳሰብ (Modernity) ድረስ መዝለቅ እንችላለን። በጥንቱ ዘመን ግሪኮቹ የራሳቸውን መልስ ሰጥተዋል፤ የመካከለኛው ዘመን (Medival period) እና ዘመናዊው አስተሳሰብም የየራሳቸውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለግሪኮቹ መሪ የሆነ ሰው በተፈጥሮው ዐዋቂ እና ዕውቅ ዜጋ መሆን አለበት፤ ስለ ሕግ (Legislator) ማወቅ አለበት፡፡ በፕሌቶ ... ”ዘ ሪፓብሊክ”.. ጽሑፍ ውስጥ ማን ይምራ ለሚለው ጥያቄ፣ መሪ የብዙ ዓመት የዜግነት እና የትምህርት ተመክሮ ያለው (እነርሱ ለዚሁ ተግባር ተብሎ የተዘጋጀ የኻያ ዓመት ሥርዐተ ትምህርት አላቸው)፣ ጠቢብ እና ብልህ ሰው ነው፡፡ የትምህርት ደረጃቸው ላነሰና ለዚሁ ተግባር ዝግጅት ላላደረጉ፣ ሀገርን ያህል ነገር የመምራት ኃላፊነት አንሰጥም ይላሉ፡፡
የመካከለኛውን ዘመን አስተሳሰብ ስንመለከት፣ ማን ይምራ ለሚለው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ከሃይማኖት ጋራ የተያያዘ ነው፡፡ መሪ ..”ሥዩመ እግዚአብሔር” መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ሥዩመ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜ በጣም ረቂቅ እና ውስብስብ ነው፤ እንዲያው ዝም ብሎ የሚሣቅበትም አይደለም፡፡ ከ1600 ዘመን በላይ ዓለምን ያስተዳደረ ዘይቤ፣ ብዙ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ያስቆመ ፍልስፍና ነው፡፡ ወደ ዘመናዊነት ስንመጣ ደግሞ መሪ “ሥዩመ ሕዝብ”. መሆን አለበት ይለናል፡፡ ሕዝብ የመረጠው ይምራ፣ ያስተዳድር ነው የሚለው፡፡
እስኪ እኒህን የአስተሳሰብ ዘውጎች በተናጠል እንፈትሻቸው፡፡ ለግሪኮቹ በትምህርት ደረጃው ያደገ፣ በክሂሉ ልምድ ያካበተ፣ በሞያው የሸመገለ፤ በተለያየ ዘርፍ ማንነቱን ያስጠራ፣ በጦርነት ወቅት ለሀገሩ በመዋጋት፣ በሰላሙ ጊዜ ሕግን በማርቀቅ፣ በመተቸት እና በማውጣት ልዕቅናውን (Excellence) ያስመሰከረ ነው፡፡
ከዚህም ጋራ ለግሪኮቹ ጥሩ መሪ ማለት፣ መምራትን ብቻ ሳይሆን መመራትንም የሚያውቅ ነው፡፡ መመራትን ማወቅ ማለት ብቻውን ወሳኝ ያልሆነ፣ በዙሪያው ካሉ ዐዋቆች ጋር የሚመካከር፣ የሚያዳምጥ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ሕዝቡ በራሱ እንደ መሪ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሕዝብ ከመሪው አቋም ጋራ አልስማማም የሚልበት፣ የማይስማማበትን ነገር የሚጠቁምበትና የሚቃወምበት ሁኔታ አለ፡፡ መመራትን የሚችል መሪ ስንል ይህን የሕዝብ ጥቆማና ተቃውሞ የሚያዳምጥ፣ አዳማጭ ሰው ሲሆን ነው፡፡
አንድ ፈላስፋ የመካከለኛው ዘመን ሥዩመ እግዚአብሔር ምንነትን ሲያብራራ፤ “..ትልቅ ሃላፊነትን የተሸከመ ማለት ነው፡፡ በእግዚአብሔር አርኣያና ምሳሌ ሆኖ በመጽሐፉ የተቀመጠውን ለማሟላት የተዘጋጀ መሪ ነው፤”.. ማለት ነው ብሏል፡፡ ሥያሜው (ሹመቱ) የሞራል ዱካ (ስታንዳርድ) ያለበት እንጂ እንዳሻ የሚኮንበት አይደለም፡፡ በስያሜው መቀባቱ ላይ የነገሥታቱ ስም የሚቀየረው ለዚህ ነው። ሓላፊነታቸውን ለማስታወስ፣ ቤተሰቦቻቸው በልደት ያወጡላቸው ስም ይለወጣል፡፡ በአስተሳሰብ (በሥነ ልቡና) ከግለሰባዊነት ወደ ማኅበረሰባዊነት የተሸጋገሩ ናቸው ማለት ነው። አሁን ሥዩመ እግዚአብሔር ስለሆኑ ቀድሞ በግል የተጣሏቸውን ሰዎች በቂም በቀል መበደል አይገባቸውም፡፡ ከመንግሥቱ በፊት መንግሥት ነበረ፤ ከመንግሥትም በኋላ መንግሥቱ ሆነ፤ ያው የተጣላውን ሰው ሁሉ ያደረገውን አደረገ፤ በአጭሩ እንዲህ ያለው ሰው መሪ እንዳይሆን ማለት ነው፡፡
በዘመናዊነት ሥዩመ ሕዝብ ሲባል ሕዝብ የመረጠው ነው፤ መምራት ያለበት ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ነው ሉዓላዊ የሚባል ሐሳብ፣ አስተያየት እና አስተሳሰብ አለ፡፡ ይህም እርምጃ ወደፊት የሄደ ነው፡፡ አሁን በደረስንበት ደረጃ ሥዩመ ሕዝብ የሚለው የመሪ አስተሳሰብ የበላይ እና ፍጹም ተደርጎ ይታያል፤ ይሁንና ሐሳቡን እንደ ሥዩመ እግዚአብሔር ሁሉ ጥያቄ ልናቀርብበት እንችላለን፤ የራሱ ውስንነቶች ሊኖሩበት ይችላል ማለት ነው፡፡
መልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ምንና ምን ናቸው?
መልካም አስተዳደር የሚለው ጥያቄ በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ መልካም አስተዳደር ግሪኮቹ ዴሞክራቲያ ብለው የጀመሩትን አስተሳሰብና ሥርዐት ሊተካ አይችልም፡፡ ለምን? መልካም አስተዳደር አንድ የዴሞክራሲ አካል ነው እንጂ ዴሞክራሲን የሚተካ አይደለም፡፡ የሁለቱን ግንኙነት (Part– Whole) ስንመለከት መልካም አስተዳደር አለ ማለት ዴሞክራሲያዊነት በተሟላ መልኩ (የግድ) አለ ማለት አይደለም፡፡ አትክልቱ በደንብ የተኮተኮተ፣ የሠራተኞች ደመወዝ በሰዓቱ የሚከፈልበት፣ መታጠቢያ ቤቱ ንጹሕ የሆነ... ወዘተ አንድ ተቋም መልካም አስተዳደር አለው ሊባል ይችላል፡፡ ዴሞክራሲ መልካም አስተዳደርን እንደ አላባ በውስጡ የያዘ ቢሆንም ከዚህ የተሻገረ እና ከዚህም የላቀ ነው፡፡
መልካም አስተዳደርን ይዘህ ኢ-ዴሞክራሲያዊ የምትሆንበትም አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጣሊያኖቹ፣ “..ሞሶሎኒ ቢኖር ኖሮ ይቺ ባቡር፣ ይቺ አውቶቡስ አትዘገይም ነበር፤.”. ይሉሃል፡፡ አሁን አስተዳደሩ ተበላሽቷል እያሉ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ግሪኮች ዴሞክራቲያ ብለው የጀመሩትንና አሁን ደግሞ ዴሞክራሲ የምንለውን ቃል አጠቃላይ ብያኔ የሚተካ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን ብንወስድ አንዱ ክልል ብቻ ኢትዮጵያን ሊገልጽ/ሊወክል አይችልም፤ ኢትዮጵያ ግን ሁሉንም ክልሎች አቅፋ የያዘች ነች፡፡ በዚህ ምሳሌ መሠረት መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ አንድ ክልል ..ገጽታ.. እንጂ ጠቅላላው ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡
የፖለቲካ እና ሞራል ፍጻሜ - በማኪያቬሌ እይታ
እንደሚታወቀው ማኪያቬሊ የዘመናዊው ፖሊቲካዊ ፍልስፍና መሠረት እና መደላድል የጣለ ሰው ነው፤ በዚህም ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። እርሱም ራሱ ቅሉ፣ “..አዲስ የፖሊቲካ ዓለም (Political Continent) ፈጠርኹ፤..” ነው የሚለው፡፡ አሁን ጥያቄው እነ ፕሮፌሰር ስታራውስ እንዳመለከቱት፣ ማኪያቬሊ በፈጠረው የፖሊቲካ ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ሊኖር ይችላል ወይ? የሚል ነው፡፡
ማኬያቬሊን እና ማኬቪያሊያኒዝምን ለያይተን መመልከት አለብን፡፡ እኔ ለማተት የምፈልገው የተወሰኑ ድርሳናትን ስለጻፈው ማኬያቬሊ ነው፡፡ ማኬያቬሊ አዲሱን መንገድ ሲጠርግ፣ መደላድሉን ሲያዘጋጅ ግሪኮቹንና የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋዎችን በመተቸት ነው፡፡ በጣም ድንቅ የሆኑ ሁለት ነጥቦችን ላንሣ፡፡
“..ፈላስፋዎች የሰውን ልጅ ከጨለማ ወደ ብርሃን መርተው ማውጣት ይፈልጋሉ፤..” ይላል ሲጀምር፡፡ መቼም ይህን ሲጽፍ በአእምሮው የፕሌቶ ሰዋስው ብርሃን አለ፡፡ ፕሌቶ ሰው በደንብ እንዲያይ፣ የጠራ ርእይ እንዲኖረው ብርሃነ ኅሊና ያሻዋል ብሏል፡፡ የማኬያቬሊ አስተምህሮ ግን፣ የሰውን ልጅ ከጨለማ ውስጥ አስቸጋሪ ወደ ሆነ ዓለም ለመውሰድ ነው፤ ነገር ግን እንዴት አድርጋችሁ ይህን ጨለማ ተቋቁማችሁ በሕይወት እንደምትቆዩ አሳያችኋለሁ ይለናል። በዚህ አባባሉ ፕሌቶንና ሌሎችንም ተችቷል፡፡ እንደ ማኬያቬሊ፣ ይህ ዓለም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም በማኬያቬሊ እምነት፣ ፈላስፋው መሲሓዊ ሳይሆን አንድ ሰው እንዴት ችግሩን ተቋቁሞ በሕይወት ለመቆየት እንደሚችል ምላሽ መስጠት ይገባዋል፡፡
ሌላው ማኬያቬሊን በፖሊቲካ ፍልስፍና ትልቅ ሥፍራ ያሰጠው በሞራሊቲ ላይ ያቀረበው ትችት ነው፡፡ ማኪያቬሊ ሞራሊቲን ሁለት ቦታ ይከፍለዋል፤ የመጀመሪያው የአደባባይ፣ ሕዝባዊ ግብረ ገባዊነት (Public Morality) የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ግለሰባዊ ግብረ ገባዊነት (Individual Morality) ነው። የአደባባይ/ሕዝባዊ ግብረ ገባዊነት ፖሊቲካዊ ግብረ ገባዊነት ነው፤ የግለሰብ ግብረ ገባዊነት ደግሞ መሠረቱ ያው ክርስቲያናዊነት ነው። ማኪያቬሊ ሁለቱን መለያየት እንዳለብን ይከራከራል፡፡ አንድ መሪ የፖሊቲካ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የሚዳኘው በፓብሊክ ሞራሊቲ እንጂ በግለሰብ ሞራሊቲ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፣ ጓደኛውን ማሰር ካለበት ማሰር አለበት፤ አለበለዚያ የሕዝቡ የወል ደገኛ እሴት(Common Good) ይጎዳል፡፡ በዚህ ምትክ፣ “..አይ፣ በርሓ አብሮኝ ጥይት ሲተኩስ የነበረውን እንዴት አድርጌ አስረዋለሁ?..” የሚለው ለማኪያቬሊ ቦታ የለውም፡፡ መሪ እና ተራ ሰው የሚጠየቅበት የሞራል ሚዛን ይለያያል፡፡ ብዙ ጫጫታ ያሥነሳው የማኪያቬሊ ትምህርት ይህ ነው፡፡
“..ብዙ ጊዜ የልሂቁ እውነታ ወደ ሰፊው ሕዝብ በወረደ ቁጥር አብዮት ይቀሰቀሳል፤ መንግሥት ይለወጣል፤ መንበሩ አይረጋም፤..” ይላል፡፡
ማኬያቬሊ አንድን ማኅበረሰብ እንደ ሕዝብ አቆራኝተው የሚያያይዙት (ሃይማኖት) እንደሚያስፈልግ ይናገራል፤ ያለ ሃይማኖት አገር አይተዳደርም፡፡ የፈረንሳይ ፈላስፎች መጥተው ሃይማኖቱን መጎንተል ሲጀምሩ የፈረንሳይ አብዮት መጣላቸው፡፡ ኅብረተሰቡ ለምእተ ዓመታት ያካበታቸው የሞራል ትምህርቶች አሉ፡፡ እኒህን የሞራል እሴቶች በይፋ፣ በአደባባይ አትቃወም፤ አትከራከር፤ አታነውር ነው የሚለው ማኪያቬሊ፡፡ እንደ መሪ ሕዝቡ የሚያምነውን ነገር አማኝ ሆነህ፣ መስለህ መቅረብ አለብህ፡፡ በሌላ በኩል፤ ‘Safe talk’ የሚለው ነገር አለ፤ ይኸውም ሕዝቡ መባል፣ መነገር የለበትም ያለውን ነገር አንተ ወጥተህ አትበል ማለቱ ነው፡፡
ለግሪኮች ፖሊቲካ አድጎ ተመንድጎ አንድን ዜጋ ደግ (ታላቅ) የሚያደርግ እና የሞራል ጸጋ የሚያላብስ፣ ጽግው/Virtuous/ ነው፡፡ ለማኪያቬሊ ደግሞ የፖሊቲካ ፍጻሜ ነጻነት ነው፤ ፖሊቲካው ሄዶ ሄዶ መደምደሚያው ሪፖብሊክ መመሥረት ነው፡፡ ማኪያቬሊ ለዘመናዊው የፖሊቲካ አስተሳሰብ በጣለው መደላድል፣ ፖሊቲካ የጥንት ግሪኮች ከሚሉት ጽግው ዜጋን /Virtuous Citizen/ ከመፍጠር ይልቅ ነጻነትን ማጎናጸፍ እንደሆነ መግለጹ አንዱ የልዩነት ጫፍ ነው፡፡ በመሆኑም ማኪያቬሊ ሰውን በጎ፣ ደገኛ/ታላቅ/ ለማድረግ የሚያስፈልገው አስተምህሮ፣ ምክር ሳይሆን የሕግ ዱላ ነው በማለት እነፕሌቶን ይተቻል፡፡ ሕግ፣ ፖሊቲካ ትልቅ አስተማሪ ነው፣ እንጠቀምበት ይላል፡፡
ነገራችንን ለመቋጨት ያህል፣ ማኪያቬሊ፣ ከሥነ ምግባር አኳያ ግብረ ገባዊ የሆነውን ነገር ግብረ ገባዊ ያልሆነው ነገር ይቀድመዋል፤ ፍትሐዊ የሆነ ነገር እንዲመጣ አስቀድሞ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ነገር መኖር አለበት፤ ይላል፡፡ ለምሳሌ፡- አገር (ሪፖብሊክ) የሚመሠረተው፣ ታላላቅ ሥልጣኔዎችም የመጡት ኢ-ሞራላዊ ነገሮች (ወንጀሎች) ከተሠሩ በኋላ እንጂ አልጋ በአልጋ ሆኖ አበባ እየተበተነ አይደለም - እንደ ማኪያቬሊ፡፡
የመንግሥት የንግሥና ተልእኮ እና የትውልድ ጥያቄ
ስለ ዘመን መንፈስ (ተልእኮ) ተጠቃሽ ድርሳን የጻፈው የታወቀው የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀርመናዊው የነባራዊ ሐሳባዊ ፈላስፋ ጊዮርግ ቬልሄልም ሄግል ነው፡፡ እያንዳንዱ መንግሥት የራሱ ተልእኮ አለው፡፡ ሄግል እንደሚያብራራው፤ “..መንፈስ ለግለሰብም ሆነ ለመንግሥታት ወይም ለአንድ የተደራጀ ኀይል ተልእኮ ታሸክመዋለች፤ ከተሰጠው ተልእኮ ውጭ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፤..” ይለናል። ስለዚህ የታሪክ ጸሐፊዎች እና ተመራማሪዎች ብዕራቸውን አሹለው በሚቀርቡበት ጊዜ፣ “..ምን ዐይነት ተልእኮ የያዘ ሥርዐት/ ሰው/ድርጅት ነበር፤..” ብለው መጠየቅ ይችላሉ፡፡
ሄግል በግለሰብ ደረጃ ሦስት ታላላቅ መሪዎችን ያነሣል፤ እነርሱም፡- ታላቁ አሌክሳንደር፤ ጁልየስ ሲዛር/ዮልዮስ ቄሣር/ እና ናፖልዮን ናቸው፡፡ ሦስቱም ሰዎች ታሪክ የሰጣቸውን ተልእኮ ጨርሰው ተፈጽመዋል ነው ያለው፡፡ ታሪክ/መንፈስ/ ተልእኮ (History assigned) ተልእኮህን በመወጣት እንደ አሌክሳንደር ታላቅ ሥራ ትሠራና በልጅነትህ ትሞታለህ፤ ወይም ደግሞ እንደ ጁልየስ ሲዛር ሴኔት ወለል ላይ በጓደኞችህ ትገደላለህ ይላል፤ አልያም እንደ ናፖልዮን (ሴይንት ሄሊና) ላይ ትታሰራለህ ነው የሚለው፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በሀገር ደረጃም እያንዳንዱ ሥርዐተ ማኅበር የራሱ ተልእኮ አለው፡፡ ያ ሥርዐት ካለፈ በኋላ ለመዘገብም ሆነ ለመመርመር በምንነሣበት ጊዜ ምን ዐይነት ተልእኮ ነበረው ብለን የተልእኮውን ገደብ ማወቅ ይገባናል፤ ይላል፡፡ አሁን ለምሳሌ የዐፄ ኀይለ ሥላሴን መንግሥት ብንወስድ በሄግል አነጋገር፣ የዐፄ ኀይለ ሥላሴ መንግሥት የመጣበት ሁለት ሦስት ተልእኮዎች ይኖሩታል። በመጀመሪያ ደረጃ፡- የውጭ ኀይል ኢትዮጵያን ቅኝ ለማድረግ ያሰፈሰፈበትና ያን መመከት የሚያስፈልግበት ሁኔታ ነበር፤ በሁለተኛ ደረጃ፡- ዐፄ ምኒልክ አቅንተው፣ አያይዘው የተዉትና መጠናከር የነበረበት ግዛት ነበር፤ በሦስተኛ ደረጃ፡- አገሪቱን ወደ ዘመናዊነት የሚያሻግሩ መደላድሎች መነጠፍ/መዘርጋት ነበረባቸው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የዐፄ ኀይለ ሥላሴ መንግሥት በሦስቱም ዘርፍ ተልእኮውን አሟልቷል፡፡
ይሁንና ከጊዜ በኋላ ዛሬም ድረስ ወደ ኋላ እየተመለስን የመብት ጥያቄዎችን እናነሣለን። ተማሪዎች ያነገቡትን የመሬት ላራሹ እና በ21ኛው መ.ክ.ዘ ጐልተው የወጡ የመብት ጥያቄዎችን እያነሣን፣ የቀዳማዊ ዐፄ ኅይለሥላሴን ሥርዐት በምንኮንንበት ጊዜ ሄግል እንዳለው፣ በዘመኑ ለሥርዐቱ ከተሰጠው ተልእኮ ውጭ ነው የሚሆነው፤ ከተልእኮው ውጭ ሊሠራ አይችልምና፡፡ የኮ/ል መንግሥቱ ደርጋዊ ሥርዐትም የተወሰነ ተልእኮ ነበረው፤ ያው እንደበረረ እንደመጣ እንደበረረ ነው የሄደው፡፡
ምን ማለቴ ነው? እነኝሀ ሰዎች ከግራ ኀይል አመራር ጋራ ሆነው አብዮት እናመጣለን፤ አብዮት እንሠራለን አሉ፡፡ አብዮቱ ፍጹም (Supreme Good) ነው፤ ለአብዮቱ ሲባል ሁሉንም ነገር ማድረግ ይቻላል፤ መንገድ ላይ ነን፤ አብዮቱ አንድ ደረጃ ላይ መድረስ አለበት፤ ለአገሪቱ ይበጃታል፤ በአብዮቱ መንገድ ላይ ቆመው ሂደቱን በሚያሰናክሉት ላይ የቅጣት ርምጃ መውሰድ ሞራላዊ ተቀባይነት አለው ነው የተባለው፡፡ የግለሰብ መብትን፣ የዴሞክራሲ ጥያቄንና የመሳሰሉትን ከሥርዐቱ ባሕርይ ውጭ አድርገውታል፡፡
ለዚህ ዐይነቱ ሥርዐት የሰብአዊ መብቶችን እና የዴሞክራሲ ጥያቄን ለሚያነሡ ሰዎች ሄግል፣ “..እንዲያው በከንቱ ነው የምትደክሙት፤ እነኝህ ሰዎችኮ ተልኳቸው ይኸው ነው፣ እናደርጋለንም ያሉት ይኸው ነው፤ ከዚያ ውጭ መጠበቁ ብዙም አያስኬድም፤..” የሚል ነገር ነው የሚነግረን ማለት ነው፡፡
አሁን ባለንበት ጊዜ አገሪቱን የሚያስተዳድረው መንግሥት ደግሞ “የልማት ተልዕኮ” አለኝ፤ እያለ ነው፡፡ ይህ ለአገሪቱ የሚበጃት ወሳኝ ነገር እንደሆነ ነው የተነገረው፡፡ ምናልባትም ከሄግሊያዊ አመለካከት አኳያ በዚህም ዙሪያ አንዳንድ የተለዩ ጥያቄዎችን ማንሣቱ ልክ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ላይ እንደተነሡት ጥያቄዎች ሁሉ ትርጉም የሚያጣበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። በጉዳዩ ላይ በቀጣይነት መወያየት ይቻላል - The Jury is still out.
***
ከአዘጋጁ፡- ውድ አንባብያን፤ ከዚህ በላይ የቀረበው የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ለንባብ የበቃ ሲሆን፤ ለ”አድማስ ትውስታ”  ይመጥናል  በሚል በድጋሚ ያወጣነው መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

Read 1772 times