Saturday, 04 March 2023 11:11

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     የመከፋፋያ አጀንዳው ሲያልቅባችሁ የአድዋንም ድል መነካካት ጀመራችሁ?
                            ጌታሁን ሄራሞ


        በጦርነቱ የተሳተፉ፣ በአንድ ሀገር ባንዲራ ሥር ዘምተው ተዋግተው ሰማዕት የሆኑ፣ የአድዋን ድል ወደየጎጣቸው ሲጎትቱ አልተስተዋሉም፤ የጦርነቱ ቀጥተኛ ገፈት ቀማሾች ለመፈፀም ቀርቶ ለማሰብ ያልደፈሩትን፣ ዛሬ በዘር ፖለቲካ ያበዱ የዘውግ አክራሪዎች (Ethnic extremists) የአድዋን ድል ወደየሰፈራቸው ለመውሰድ የሚያደርጉት መፍጨርጨር እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው።
ኢሕአዴግ በአንድ ወቅት በሐዋሳ ከተማ ባደረገው ስብሰባው፣ በ27 ዓመቱ የዘውግ ፖለቲካ ጉዞው ሚዛኑ ወደ ዘውጌ ብሔርተኝነቱ እንዳጋደለ አምኖ፣ በሀገራዊ ብሔርተኝነትና በጋራ እሴቶች ላይ በቀጣይነት ለመስራት ራሱን መገምገሙ ይታወሳል።
በሁሉም ብሔሮች ውስጥ ጀግኖች ቢወደሱ ችግር የለብኝም። የሚያመው ዋናውና ማዕከላዊው  እየተብጠለጠለ ድርጊቱ መቀጠሉ ነው... ምኒልክን አውግዞ አሉላን ወይም ባልቻ አባነፍሶን ነጥሎ ማድነቅ ምን ይባላል?  ዛሬ “ኢትዮጵያ አትፈርስም” እየተባለ በተለፈፈበት በዘመነ ብልፅግና መንግስት ማግስት፣ ከኢሕአዴግ ዘመንም በከፋ፣ የቀሩት እንጥፍጣፊ ሀገራዊ የጋራ ዕሴቶች ወደ ጎጥና ዘውግ ሰፈር መትመማቸው ለመደበኛው ተመልካች ግራ አጋቢ ክስተት ነው።  
ለዚህ ሁሉ የታሪክ ሙስና ተጠያቂዎቹ፣ በዘውጋቸው ስም እየነገዱ ኢኮኖሚውንና የፖለቲካ ሥልጣኑን ለመጨበጥ የሚቋምጡ ጥቂት የዘውግ ፖለቲከኞች ናቸው፤ እነዚህ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርና  ዘውጋቸውንም በውል የማይወክሉ የጠብና ግጭት ኤክስፐርቶች ናቸው። 30 ዓመታት ሙሉ ስለ ዘውግ የሰበኩት ዲስኩር፣ ለመደበኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በልቶ የሚያድረውን ዳቦ አላመጣላትም፤ መፈናቀልን፣ መሰደድን፣ መጨፍጨፍን እንጂ! የኢትዮጵያ ሕዝብ በየመድረኩ የሚለፈፉ ቃላትን ሳይሆን፣ በገሃዱ ዓለም ታች መሬት ላይ እየተፈፀመ ያለውን እውነታ (Real politics) መከታተል ከጀመረ ውሎ ካደረ መቆየቱን ልብ ያለው ልብ ይበል!
  በዓለም አቀፍ ታሪክ የኢትዮጵያን ስም በደማቅ ቀለም ያስቀመጠው የአድዋ ድል፤ በዘውግ ስም ለሥልጣን በሚሯሯጡ ጥቂት የዘውጌ ፖለቲከኞች ሴራ፣ ለአንድ አፍታ እንኳን አሻራው አይደበዝዝም! የአድዋ ድል በየትኛውም አመክንዮና ስሌት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ያደረገና ወደፊትም የሚያደርግ ታሪካዊ እሴት እንጂ ሀገራችንን ለመከፋፋል ጥቅም ላይ የሚውል አጀንዳ አይደለም!
_________________________________________________

                   “ምኒልክ ቅዱስ ነው፡፡ እሙት በለኝ?”
                     

        [ዘ.ጥ]
6 ማስረጃዎች!
“ባቡሩም ተጫነ፥ ስልኩም ተናገረ
ምኒልክ ነብይ ነው፥ ሆዴ ጠረጠረ”
በዘመኑ የነበረው ሰው
ምኒልክ ቅዱስ ንጉስ ነበር፡፡ እንደ እነ ቅዱስ ላሊበላ፥ ነአኩቶለአብ፥ አብርሃ ወአፅብሃ። ዘመን አልፎ ዘመን ሲመጣ፥ መታወሱ አይቀርም-በቅዱስነት፡፡ ላሊበላ እየከበሩ የሄዱት፥ የህልፈት ዘመናቸው እየጨመረ ሲሄድ ነው። ስለ አፄ ዳዊት፥ ስለ ዘርዓያዕቆብ፥ ስለ ፋሲል ንትርክ የለም፡፡ ስለ አፄ ቴዎድሮስ የጎላ ንትርክ የለም፡፡ በአመዛኙ አፄ ዮሐንስ ላይ መላጋቶች አሉ፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ የተሻለ ርህራሄ ነበራቸው - ምኒልክ፡፡
“እኒያ አፄ ቴዎድሮስ፥ አቤት ሰው ሲወዱ
የሸዋን መኳንንት፥ እጅ ነስተው ሄዱ” ተብሎላቸዋል፡፡ ምኒልክ ይሄን አላደረጉም፡፡ ከአፄ ቴዎድሮስ ራዕዩን ወረሱ፡፡ ያው ከእግሩ ስር ቁጭ ብለው፡፡ ኃይሉን ቀንሰው ብልሃትና ጥበብ ጨመሩበት፡፡ እምነትም ጨመሩበት፡፡ አፄ ዮሐንስ ጎጃም ወርደው ያደረጉት ይታወቃል። “የጎጃም ሴቶች ለምን የራስ ፀጉራቸውን አያሳድጉም?” ብሎ ጠይቆ የሚያውቅ የለም። መጠየቁም ጥቅም የለውም፡፡ ከታሪክ ላይ ተኝቶ ማልቀስ፣ ነገን ወዶ ፈቅዶ መግደል ነው። ግን ከእምዬ ምኒልክ ጋር የሚወዳደር አንጀት እንዳልነበራቸው ማሳያ ነው፡፡
“እምዬ” ያላቸው የኦሮሞ ገበሬ እንጂ ሹመት ያገኘ መኳንንት አይደለም፡፡ ደም ሳያፈሱ በጥበብ የቴዎድሮስን ራዕይ እውን ያደረጉበት መንገድ፣ 100 ዓመታትን ተሻግሮ እንኳን ያስገርመናል። ወላይታ ወርደው ምን እንዳደረጉ፥ ምን እንደሆኑ፥ አንድ ወዳጄ ቦታው ድረስ ሄዶ የጥንት ሽማግሎችን ጠይቆ ያገኘውን መረጃ በቅርብ በሰነድ ጀባ ስለሚለን አልነካካው።
የሆነው ሆኖ ምኒልክ በ’ተኮነነ ዘመን’፣ በእኛ በተኮነነ ትውልድ እጅ ደርሰው እንጂ ፃድቅ፥ ቅዱስ ናቸው፡፡እንዲያውም ያማልዳሉ፡፡ አማልደዋልም፡፡ ልባችሁን ከከፈታችሁ ማስረጃ አለኝ - ቅዱስም አማላጅም የሚያሰኛቸው፡፡ ልቀጥል?
1ኛ) በራዕይ_መወለድ
እምዬ በራዕይ የተወለዱ ሰው ናቸው፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ ይሄን እድል ያገኙ የተመረጡ ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ እናታቸው “ከብልቴ ፀሐይ ወጣች” ብለው ራዕይ አዩ፡፡ የንጉስ ሳህለስላሴ ባለቤትም ለልጃቸው ለሃይለመለኮት አጋቧት። ይህን ታሪክ የመንግስቱ ለማ አባት፣ አለቃ ለማ ፅፈውታል፡፡ ምኒልክም ተወለደ፡፡ የዓለም ፀሐይም ሆነ፡፡ ለጥቁር ህዝብ የጨለመች ዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የፀሐይ ብርሃን አበራ። ፀሐዩ ምኒልክ ጨለማውን ዓለም በብርሃን ወጋገን ሞላ፡፡ ስለ ሰው ልጅ እኩልነት ዓለምን አስተማረ፡፡ ራዕዩ ዕውን ሆነ፡፡
2ኛ) በራዕይ_ከተማን መገንባት
አፄ ሚኒሊክ በግራኝ የፈራረሰውን የአፄ ዳዊትን ከተማ ፈልገው እንደገና መገንባት ይፈልጉ ነበር፡፡ ቦታው ግን የት እንደነበር አያውቁትም፡፡ ዳዋ ከለበሰ 400 ዓመት አልፎት ነበር፡፡ የአፄ ዳዊትን ቤተመንግስት ቦታ በራዕይ አይተው፣ ቤተመንግስታቸውን ከአንኮበር ወደ አዲስ አበባ (ቀደምት በረራ) እንዳዛወሩ ምን አልባት የሚያውቅ ትንሽ ሰው ይሆናል? የአፄ ዳዊትን የንግስና ቦታ ለመፈለግ፥ አንዴ አዲስ አለም፥ ሌላ ጊዜ መናገሻ፥ ሌላ ጊዜ እንጦጦ እየዞሩ ማረፊያ ይሰሩ ነበር፡፡ መጨረሻ በራዕይ ተገለጠላቸው፡፡ እንጦጦ ላይ ፀኑ፡፡ የኢትዮጵያን መዲና ቆረቆሩ፡፡ የአሁኗን አዲስ አበባን፡፡ አፄ ዳዊትም የኢትዮጵያ ማዕከለ ምድር በሆነችው በወቅቱ ስሟ በረራ (የአሁኗ አዲስ አበባ) ላይ ትልቅ ከተማ ገንብተው ነበር፡፡
3ኛ)  ብርቱ_አማኝነት
የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ተሰርታ ስትጠናቀቅ ለምረቃው ድግስ 5395 ከብት ታርዶ ነበር፡፡ እንዲሁም እያንዳንዳቸው 40 ኩንታል ሊጥ የሚያቦኩ ዕቃዎች ተዘጋጅተው፣ ሰዎች በመሰላል እየወጡ የተቦካውን ሊጥ ያወጡ ነበር፡፡ በተጨማሪም ጠጅ በአሸንዳ እየወረደ በጉድጓድ ተጠራቅሞ፣ ሕዝቡ ከዚያ የጠጅ ጉድጓድ እንዲጠጣ ተደርጎ ነበር። ለእንጦጦ ማርያም ለቤተክርስቲያኒቱ ምረቃ የሚያስፈልገው ድግስ ከተዘጋጀ በኋላ በምረቃው ቀን ዋዜማ መስከረም 20፣ አየሩ ሁሉ ተለዋውጦ ከፍተኛ ደመና ሆኖ ነበር። ቦታውም ተራራማ ነውና ደመና መጥቶ ሳይዘንብ ስለማይመለስ፣ ሁሉም ሰው ድግሱ ሊበላሽ ነው ብሎ ተጨነቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጸሐፊያቸውን ጠርተው፤ “ዝናቡን ቤትሽ እስኪያልቅ አቁሚው” የሚል ጥቅል መልዕክት ያለው ደብዳቤ፣ ዝናቡ ይመለስ ዘንድ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አፃፉ፡፡ የተጻፈውም ደብዳቤ የእመቤታችን ታቦት ላይ ሲደረግ ደመናው ጠፍቶ ዝናቡ ተመልሶ ብሩህ ቀን ሆነ፡፡
4ኛ) የእምዬ_እምነትና_የአድዋ_ድል
የዓለም ብርሃን የሆኑት ምኒልክ እምነታቸው ለአድዋም ትልቅ ዋጋ ነበረው። የአራዳ ጊዮርጊስን ታቦት ሄደው ተሳለሙ፡፡ ለመኑት። ነጩ ጊዮርጊስ፣ ለተጨቆኑት ለጥቁሮች እንዲቆም ለመኑት፡፡ ታቦቱን በካህናት አስይዘው ወደ አድዋ ዘመቱ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርበኞች ጎን ሆኖ ለአስራት ሀገሩ ተዋጋ፡፡ አንድ በጦርነቱ የተሳተፈ ጣሊያናዊ ስለ ጦርነቱ ተጠይቆ እንዲህ አለ፤
“አንድ በነጭ ፈረስ ላይ የነበረ መልከ መልካም ወጣት በከፍተኛ ሁኔታ ተዋጋን፡፡ ብዙዎችን ጣላቸው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ አዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፣ የዚያን ወጣት ምስል ግድግዳ ላይ ከነፈረሱ ተስሎ አየሁት...” በማለት ምስክርነቱን ሰጧል፡፡ በምኒሊክ እምነትና ልመና ሰማዕቱ አድዋ ላይ ታምር ሰርቷል፡፡
5ኛ) የህግ_የበላይነትና_ርህራሄ
የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በምትሰራበት ወቅት ሰው በመግደል የተከሰሰ አንድ ወንጀለኛ በምኒልክ ችሎት ፊት ቀረበ። ተከሳሹም ወንጀሉን በመፈፀሙ የሞት ፍርድ ተላለፈበት፡፡ በዘመኑም በነበረው የፍርድ ስርዓት መሰረት በገዳይ ላይ ውሳኔው ከመፈጸሙ በፊት የተበዳይ ወገኖች፤ “ወንጀለኛው መገደሉ ቀርቶ ለተገደለው ዘመዳቸው የደም ካሳ የሚሆን ገንዘብ ትቀበላላችሁ ወይ?” ተብለው ተጠየቁ፡፡ እነርሱም፤ “አይ የወንድማችን ገዳይ ይገደልልን እንጂ ካሳ አንቀበልም” በማለት መለሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍርድ የተላለፈበት ተከሳሽ ድምጹን ከፍ አድርጎ፤ “ጃንሆይ በሥራዬ ነውና መገደሉንስ ልገደል፡፡ ግን የዚችን የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን መጨረሻ እስካይ ዕድሜ ይሰጠኝና ልገደል” ሲል ጠየቀ፡፡ ይህን የሰሙት አጼ ምኒልክ ከዙፋናቸው ተነስተው ወንጀለኞች ከሚቆሙበት ቦታ ሄደው በመቆም ከፊታቸው ላሉት መኳንንት፤ “ከሟች ወገኖች አስማሙኝ፡፡ ካሳውን እኔ ራሴ ከግምጃ ቤቴ እከፍላለሁ፤ ይህን ሰው ግን እንድታስምሩልኝ እማፀናለሁ” በማለት የንግሥና ኩራት ሳይዛቸው ከወገባቸው ጎንበስ ብለው ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ወንጀለኛው ይገደልልን ብለው የነበሩት የሟች ቤተሰቦች፣ በምኒልክ እግር ስር ወድቀው እያለቀሱ፤ “ምረነዋል ለእርስዎ ስንል ምረነዋል፤ ካሳውንም አንቀበልም” አሉ። ምኒልክም መልሰው፤ “ነፍሱን ማሩልኝ አልኩ እንጂ ካሳውንማ መተው ፍርድ ማጓደል ነው” ብለው ገንዘቡን ከፈሉ፡፡
6ኛ) ከድንግል_ማርያም ጋር የነበራቸው ቃልኪዳን
የድንግል ማርያምን ስም ጠርተው አድዋ ዘምተዋል፡፡ በማርያም ከማሉ አይመለሱም፡፡ ህዝቡም ያውቃልና ሁሉም ወደ አድዋ ተመመ። እንጦጦ ብቻ ሳይሆን የአዲስ ዓለም ማርያምን በሚያሰሩ ጊዜም በረጅም ከፍታ ላይ ይገኝ የነበረ ርብራብ ተሰብሮ ሁሉም ሰራተኞች ወደ መሬት ወድቀው በአንዳቸውም ሰውነት ላይ ግን ጭረት እንኳን ሳይገኝ በተአምራት ተርፈዋል፡፡ እሳቸውም ቃሏን ይጠብቃሉ፥ እሷም ልመናቸውን አታጎልም፡፡ በቃል ኪዳኗ ታስረዋልና!
ወዘኩሉ ዘተግብረ በእንተ ንጽሐ ልቡ ለዳግማዊ ምኒልክ እስመ ታፈቅሮ እምኩሎሙ ነገሥት፡፡
እንግዲህ ከዚህ የተሻለ ንፁህ ልብ፥ ርህራሄ፥ ቅድስና፥ እምነት፥ ድፍረት ያለው መሪ በ20ኛው ክ/ዘመን ማን አለ? ከቅዱሳን ያማለደ፥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጦር ሜዳ አብሮ የተዋደደ ፃድቅ ሰው ማን አለ?
ጠቁሙንና እናክብረው፥ ቅዱስ እንበለው?
እኔ ግን እልሃለሁ ምኒልክ ቅዱስ ነው፡፡ እሙት ስልህ፡፡ አላመንህም? ኧረ ማርያምን፡፡
____________________________________________________

                    “ከተማው በጠላት የተወረረ ይመስል ነበር--”
                          አንዳርጋቸው ጽጌ


          የአድዋን የድል ቀን፣ ወደ ውርደት ቀን የቀየሩትን የመንግሥት ባለሥልጣናት ልናወግዛቸው ይገባል። ይህ በዓል ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ተሳትፎ በከፍተኛ ድምቀት በምኒሊክ አደባባይ ይከበር ነበር። እኔም አንዱ የህዝብ አካል ሆኜ ተሳትፌበት አውቃለሁ።
በዛሬው ዕለት ግን በምኒሊክና በመስቀል አደባባይ፣ የከተማው ህዝብ ድርሽ እንዳይል ከልክለው፣ በበአሉ የታደሙት የብልጽግና ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ካድሬዎችና ብልጽግና ድህነታቸውን የታማኝነት ማሰሪያ ሰንሰለት አድርጎ በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ያደራጃቸው ምስኪኖች ብቻ ናቸው። ሌላው ህዝብ ወደ አደባባዮቹ እንዳይደርስ በወታደር፣ በፌደራል ፖሊስና በከተማው ፖሊስ እንደ ከብት ከመንገድ እየተነዳ እንዲወጣ ተድርጓል።
 በአንዳንድ ቦታዎች በድብደባ ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ መረጃው ደርሶኛል። ሁኔታውን ለተመለከተ ቀኑ የበአልና የደስታ ሳይሆን፣ ከተማው በጠላት ተወርሮ፣ የሃዘን ጥላ ያጠላበት ቀን ይምስል ነበር። ይህ በወሬ ሳይሆን በአካል ወደ መስቀል አደባባይ ከጓደኞቼ ጋር ለመሄድ ሞክሬ ከደረሰብኝ ተነስቼ ነው የምጽፈው። እንኳን ለዚህ ቀን አበቃህ የምትሉ ምጸተኞች እንዳላችሁ አውቃለሁ። በምጸታችሁ አላዝንም። የማዝነው ከታሪክ መማር ለተሳናቸው እብሪተኛ የሃገሪቱኛ ገዥዎች ነው።

__________________________________________________


                   “ቤተክርስትያን የተገኙ ምዕመናን ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ የለየለት ኢ-ሰብአዊነት ነው”
                         ሙሼ ሰሙ


          ዓለም የመሰከረለት፣ ከአፍሪካውያን እስከ አውሮፓውያን መንገድ፣ አደባባይና ተቋማት የሰየሙለት፤ የጥቁርና የነጻነት ወዳድ ሕዝቦች ኩራትና ተምሳሌት የሆነውን የአድዋ ድል በዓል ዜጎች በመረጡት አጼ ሚኒሊክ አደባባይ ላይ ለማክበር ስለወጡ የወረደባቸው ዱላ፤ ከመብት ጥሰት የላቀ አሳዛኝ ድርጊት ነው። ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላቸውን ለማክበር ቤተ ክርስትያን ቅጥር ግቢ የተገኙ አማኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ  የለየለት ኢ-ሰብአዊነት ነው።
ተወደደም ተጠላ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ፣ ሁሉም ዜጋ የድልና የሐይማኖት በዓሉን የሌላውን መብት ሳይጋፋ በፈለገው ቦታ፣ በፈቀደው ጊዜና በመረጠው መንገድ የማክበር ሕገ መንግስታዊ መብት እንዳለው አለመረዳት፣ የጋራ ውድቀትን ማፋጠን ነው።
በደሳለኝና በመሰለኝ ሳይሆን ሁሉም ልዩነቶቹ ተከብረው በእኩልነት መኖር የሚቻልባት ሪፐብሊካዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት ይልቅ አንድ ፍላጎት ብቻ የሚነግስበት ሀገር ለመፍጠር የሚደረገው ግብ ግብ ተጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ፣መጨረሻችን የሚሆነው አንድ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የጋራ ሀገርን ማስቀጠል ሳይሆን፣ ከአንድ በላይ የሆነ ሀገርን ማዋለድ  ሊያስከትል እንደሚችል መገመት ተገቢ ነው።


Read 1405 times