Saturday, 04 March 2023 11:09

ተወዛግቦ ማወዛገብ...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

       እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ የዐቢይ ጾም ወቅትም አይደል! አንዲት ዘለሰኛ ዝማሬ ላይ ያለች ይችን ስንኝ ስሙልኝማ...
በስምንተኛው ሺህ፣ ሰው በረከሰበት
አባት ተቀምጦ፣ ልጅ በፈረደበት
እንዴት ያለው ጊዜ፣ እንዴት ያለው ወራት፣
እኛ ደረስንበት፣
በሬ አራት ሺህ ብር፣ አንድ በግ ሦስት መቶ
ዶሮ አርባ ሰባት
ሳንገናኝ ቀረን ድሀና ዱለት
ታዲያላችሁ በግ ሦስት መቶ ብር፣ ዶሮ አርባ ሰባት ብር ገብቶ ከስምንተኛው ሺህ ጋር የሚያያዝበት ዘመን ነበር ለማለት ነው፡፡ እናማ... “ሳንገናኝ ቀረን ድሀና ዱለት” የምትለዋ እኮ...አለ አይደል....ትልቅ የመረጃ ምንጭ ነች፡፡ ልክ ነዋ... ድሀና ዱለት እንደልብ ይገናኙ ነበር ማለት ነዋ!
እኔ የምለው...በስንቱ ግራ እየተጋባን ይዘለቅ ይሆን፡፡ አንዱን ሲሉት ሌላው እየሆነ፡፡ 
“በግና ዶሮ በጣም ነው እኮ የተወደደው!”
“እና ምን ይጠበስ! እንደ አቅም መኖር ነዋ!” ሲባል ቅን አመላለስ ነው ማለት ባይቻልም፣ “እንደ አቅም መኖር...” የሚል ምክር ክፉ አባባል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እንደ አቅም ለመኖር ሙከራ ማድረግ ይቻል ነበር እኮ! አሁን እኮ እንደ አቅም መኖር የሚለው አባባል አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እንደ አቅም ለመኖር የሚሸሽባቸው መሸሸጊያዎች ቀስ በቀስ እያነሱ፣ እየተመናመኑ ጭራሽ መሸሸጊያ እንዳይጠፋ ብንሰጋ ጨለምተኝነት ምናምን አይሆንም። በተለምዶ በታችኛው እርከን ወይም “ከእጅ ወደ አፍ....” በሚባል የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን ህብረተሰብ አጥብቆ ያጠቃ የነበረው የኑሮ መወደድ፣ አሁን እኮ ብዙም ጫና ያልነበረበትን ክፍል ሁሉ ያምሰው ጀምሯል፡፡
እኔ የምለው ---- ያ ሁሉ የ‘ቦተሊካ አክቲቪስት’ ‘ተጽእኖ ፈጣሪ’ ቅብጥርስዮ የሚባለው ሁሉ ምነው ድምጹን ከፍ አድርጎ ስለኑሮ በአስከፊ ሁኔታ መወደድ አያወራምሳ! ነው ወይስ ነገርዬው እዛ ሰፈር አይደርስም!
እናላችሁ... ለዓመታት በላይ በላይ ዋጋ እየተጨመረበት ህዝብ ሲያማርር የከረመው ጤፉ፤ አሁን ጭርሱን  እየራቀ፣ እየራቀ በመሄድ ላይ ነው፡፡ እንደ መኪና ብንወስደው፣ የጤፍ ዋጋ ከሁለተኛ ማርሽ ወደ ሦስተኛና አራተኛ ማርሽ የገባበትና ወደ አምስተኛ ማርሽ እየተንደረደረ ያለበት ፍጥነት፣ ከአሳሳቢ ወደ አስደንጋጭ እየተጠጋ ነው፡፡ አሁን ሰባት ሺህ፣ ስምንት ሺህ እያለ እየወጣ ያለው፣ ነገና ከነገ ወዲያ አሥራ ሦስትና አሥራ አምስት ሺህ ላለመግባቱ “አንድዬ አንተው በጥበብህ ከዚህ ጠብቀን!” ብሎ ከመማለድ ሌላ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡
በነገራችን ላይ ጤፍ እኮ ማለት የትኛውም ዜጋ ማዕድ ላይ ለሺህ ዓመታት የኖረ ነው፡፡ ምንም ያህል የማጣት ችግር እንኳን ቢከሰት፣ መሶቡ ምንም ያህል ቢራቆት ቁራሽና ቁርስራሽ በአብዛኛው ሰው ጓዳ አይጠፋም ነበር፡፡ ድስቱ ባዶ ቢሆን እንኳን “በቃ እንጀራ በበርበሬ ላቅርብልህ...” ይባል የነበረው አሁን እንደዛ ማለት ሊናፍቅ ነው፡፡ ደግሞላችሁ... ዘንድሮ በተለይ እነኚህ ወሳኝ የሚባሉ አይነት ምርቶች ላይ “እንትን ላይ ዋጋ እኮ ጨመረ...” ተወደደ፣ ሲባል ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ ወይንም እንደ ኳሱ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ ቢጫ ካርድ ምናምን ሳይኖር መጥቶ ክምር ነው!
“ስማ ቁርስ ምን በላህ?”
“ዳቦ በሻይ ነዋ፡፡”
“አንተ ዘላለምህን ከዳቦ በሻይ ቁርስ አትወጣም ማለት ነው!” እንባባል ነበር፡፡ አዎ፣ ቁራሽ ዳቦ አይጠፋም ነበር፡፡ እንዲሁ ዳቦዋ በስንዴ ዋጋ መወደድ እየተሳበበ በመጠኑዋ እያነሰች፣ በዋጋዋ እየጨመረች አሁን በመከራ ሁለት ጉርሻ የማትሞላና በፊት ከቁራሽ የምትቆጠረዋ  ስምንትና አስር ብር  ስትደርስ፣ “ጉድ! ጉድ!” ብለን ሳናበቃ፣ ጭራሽ ስንዴውም እየራቀ፣ እየራቀ መድረሻውን አንድዬ ብቻ ይወቀው፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ነው ክፋት ልክ ያጣ የሚመስለው፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ነው ሰዋችን “እፎይ!” ብሎ የተቀመጠ ይመስል በየጊዜው አዳዲስ የምንተራመስበት ነገር የሚፈጠረው፡፡
የአቤ ጉበኛ አንዲት የቀድሞ መጽሐፍ ላይ የሰፈረች “እንካ ስላንትያ” እንዲህ ትላለች...
እንካ ስላንትያ
በምንትያ
በቀበኛ
ምን አለ በቀበኛ
ከክፉ ሁሉ ይከፋል ምቀኛ፡፡
አሪፍ አይደል! ክፋቱ፣ ምቀኝነቱ፣ ትርፍ ሆድ የተፈጠረልን ይመስል ሌላን ሁሉ ረስቶ “እኔ፣ እኔ!”  “እኛ፣ እኛ!” ማለቱ ግርም ይላል፡፡ አሁንም እኮ የለየላት ድሀ ሀገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አሁንም እኮ ከዓለም በጣም የኋለኛው ረድፍ ላይ ነን! እናም በዚህ ድህነት ላይ እንደገና ክፋት ተጨምሮ፣ በዚህ ላይ ምቀኝነት ተጨምሮ! እንደው ነገራችን ሁሉ ግርም የሚል ሆኗል፡፡ ግርም አይላችሁም!
“ክፉ ጎረቤት ዶሮና ፍየል ያረባል...” የምትል አባባል አለች፣ ነገር ፍለጋ ማለት ነው፡፡ ጎረቤቱን ሰላም መንሻ ማለት ነው፡፡ ዘንድሮ እኮ ነገር ፍለጋ የሚባለው፣ ነገር የሚመጣው እንደ ቀድሞው ከጎረቤት ብቻ ሳይሆን ከየትና ከየት ሊሆን ይችላል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እዛ ማዶ ሳንድዊች እየተገመጠ፣ እዚህ ማዶ ሰዋችን ቆሎ እንኳን እንዳይቆረጥም  ነገር የሚፈለግበት ዘመን ነው፡፡
ደግሞላችሁ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ለምንድነው አሁን፣ አሁን ‘ተቋማዊ ምቀኝነት’ እያየን እየመሰለን ያለው!
እናላችሁ መግቢያው ላይ የጠቀስናት ስንኝ ያለችበት ዘለሰኛ መዝሙር ውስጥ እንዲህ የሚልም አለላችሁ...
ዶክተርም ይሞታል፣ ሀብታም ይደኸያል
ብልህ ይሳሳታል፣ ጎበዝ ይሸነፋል
የበራው ሁሉ ጠፍቶ፣ ያሠሩት ይፈርሳል
ጌጥም ሆነ ጥበብ፣ ውበት ሆነ ክብርም
ያማረበት ነገር፣ ማስቀየሙ አይቀርም፤
ዶክተርም ዋነኛ ሥራው ሰው ማዳን ቢሆንም፣ እሱም በመጨረሻ ያው ሰው ነውና፣ የሰው  እጣ ፈንታ ይደርስበታል፡፡ እግረ መንገድ ግን  ለሙያቸው ያደሩ፣ ቀና ቀናውን የተላበሱ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዳበረ ሙያቸው ላይ ሰብአዊነትን የተጎናጸፉ ዶክተሮችን ያብዛልንማ!
ሁሉም ሀብታም ሁሌ ሀብታም ሆኖ አይዘልቅም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ምናልባትም በራሱ ምክንያት ወይም ደግሞ በሌሎች መቶ አንድ ምክንያቶች፣ የወጣቶቹን አባባል ለመጠቀም ‘ደክርቶ’ ወይም አጨብጭቦ መቅረት ብቻ ሳይሆን፣ “አንድ በየአይነቱ ለሁለት...” ወደሚታዘዝበት ዓለም ይገባል፡፡ ሆኖም ዘንድሮ ሀብታምነታቸውን ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ሌላውን ወገናቸውን በተለያየ አግባብ በኦፊሴልም ሆነ ድምጻቸውን ሳያሰሙ የሚረዱ ያሉትን ያህል፣ ሀብታምነት ዘላለማዊነት የሚመስላቸውን እያየን ነው፡፡ ከተወሰኑ አንድና ሁለት ዓመታት ወዲህ፣ በዚች በየጊዜው አዳዲስ ነገሮች በማታጣው አገራችን፣ እንደ ‘ፋስት ፉድ’ ሁሉ፣ ‘ፋስት ሀብት’ በሽ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ 
አዎ ብልህም መሳሳት ብቻ ሳይሆን ከእሱ ይጠበቃል በማይባሉ ነገሮች ውስጥ መጥለቅ ብቻ ሳይሆን ‘ጎል አስቆጣሪ’ ነገር ሆኖ ማየት የለመድነው ነው፡፡ ለዚህ ነው እኮ “ያልተማሩት የገነቧትን ሀገር፣ የተማሩት እያሰቃዩዋት ነው”  የሚለው አባባል ቀልባችንን የሚስበው፡፡
እናላችሁ ሀብት ዘላለማዊ አይደለም፣ ወንበር ዘላለማዊ አይደለም፣ የተተከለው አምፖልም ይቃጠላል፤ የተገነባ ግምብም ይፈርሳል፣  ጉብዝናም ጊዜው ደርሶ ጉልበት ይልማል፣ ውበትም ይከስማል፣ ሁልጊዜ ማማር ብሎ ነገር የለም፡፡ ምነው እነዚህ አይነት እውነታዎች   አልገባ ያሉን ቁጥራችን በዛ!
አንድዬ...ዘላለማዊ ያልሆኑ ነገሮች ዘላለማዊ እየመሰሉን በሁሉም ደረጃዎች እኛም ተወዛግበን ሌሎችን ከማወዛገብ የሚጠበቅን ልቡናውን በጥቂቱም ቢሆን ስጠንማ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1101 times