Print this page
Saturday, 04 March 2023 11:40

“ሁሉም እስር ቤቶች አንድ አይደሉም”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  • የኦሮሚያና የፌደራል ወህኒ ቤቶች ለየቅል ናቸው
       • ፍ/ቤት ሥልጣን የለውም፤ ትዕዛዙ እየተፈጸመ አይደለም

          “አዲስ ስታንዳርድ” የተሰኘው የእንግሊዝኛ ድረገጽ፣ ሰሞኑን የኦነግ ከፍተኛ አመራር ከሆኑትና ለሁለት ዓመት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ታስረው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከተፈቱት ከኮሎኔል ገመቹ አያና ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ ቃለ ምልልሱ በዋነኝነት በኦሮሚያ ክልል ተባብሶ በቀጠለው ጦርነትና ባስከተለው ሰብአዊ ቀውስ እንዲሁም በመፍትሄው ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ እኛ ለጊዜው በኮሎኔሉ የእስር ጉዳይ ላይ ማተኮርን ወድደናል። ሁሉም እስር ቤቶች ሁሉ አንድ አይደለም የሚሉት የኦነጉ ከፍተኛ አመራር፤ የኦሮሚያና የፌደራል ወህኒ ቤቶች ለየቅል ናቸው ይላሉ፡፡ የፖሊስና የወህኒ ቤቶች የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን እንደሚመስልም በዝርዝር ይነግሩናል። ለግንዛቤ ይጠቅማል በሚል ግምት የሁለት ዓመት የእስር ሁኔታቸውን የሚመለከተውን የቃለ ምልልሱን ክፍል መርጠን ወደ አማርኛ በመመለስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
***
“ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ሥር የዋልኩት እ.ኤ.አ በ2019 ዓ.ም ሲሆን፤  ለአንድ ዓመት ታስሬ ተፈታሁኝ፡፡  ከዚያም በጁን 2020 ዓ.ም  የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ፣ ጃዋር መሃመድ፣ በቀለ ገርባና ሃምዛ ቦራናን ጨምሮ ሌሎች በርካቶች ተይዘው ታሰሩ፡፡ ያኔ እኛ አብረናቸው አልነበርንም፤ ነገር ግን በድጋሚ ከታሰሩ የኦነግ መሪዎች ውስጥ አንዱ ነበርኩኝ። እኛ የታሰርነው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሲሆን፤ እነዚህ የጠቀስኳቸው ጓዶች የታሰሩት በፌደራሉ መንግሥት ነበር፡፡
“እኔ የታሰርኩት ከኦነግ ጓዶቼ ጋር ነበር -አብዲ ረጋሳ፣ ማይክል ቦራና፣ ቀናሳ አያንን ጨምሮ ከሌሎች በርካቶች ጋር፡፡ እዚህ የጠቀስኩት የአመራሮቹን ስም ብቻ ነው፤ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ የኦነግ አባላትም የታሰሩ ሲሆን፤ ገሚስ ያህሉ እኔም የማላውቃቸው ነበሩ፡፡ ከአራት ወይም አምስት ወራት በኋላ ፍ/ቤት የቀረብን ሲሆን አቃቤ ህግ በእኛ ላይ የሚመሰርተው ክስ እንደሌለው ተናገረ፡፡ ፍ/ቤቱም ከእስር እንድንፈታ ብያኔ ሰጠ፡፡ ይሄ ብያኔ የተሰጠው ሁለት ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን ሁለቴም ከወህኒ ቤት በር ላይ ተይዘን ወደ እስር ተመለስን፡፡
“በኋላም  እኔ ከጓዶቼ ተነጥዬ ወደ ፌደራል ወህኒ ቤት ተወሰድኩና፣ በመጀመሪያ እስሬ ወቅት (እ.ኤ.አ 2019) ውድቅ በተደረገ ጉዳይ ክስ ተመሰረተብኝ፡፡ በኦሮሚያ እስር ቤት መከራ ነው፡፡  የታሰርነው 6 ኪሎ በሚገኘውና አሁን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ በሆነው ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ በጠበቃህ ወይም ቤተሰብህ  መጎብኘት አትችልም፤ ምግብ አይቀርብልህም፤ በቀን 20 ብር ብቻ ነው የሚሰጥህ፡፡ 300 ወይም 400 ገደማ እስረኞች ነበሩ፤ ነገር ግን እኛ የኦነግ አመራሮች ለብቻችን ነበር የታሰርነው፡፡ አሁን በጀርመን የሚገኘው ዶ/ር ሽጉጥ ገለታ ከእኔ ጋር ነበር፡፡ ቀጥሎ ሳንሱሲ ወደሚባል ቦታ  ተወሰድን፡፡ በሳንሱሲ ወህኒ ቤት የምንተኛው ተራ በተራ ነበር፤ በጣም ብዙ እስረኞች ነበርንና ሁላችንም በአንድ ጊዜ መተኛት አንችልም። ከዚያም ሰበታ ወደሚገኘው ዳላቲ ወህኒ ቤት ተወሰድን፡፡ ከዳላቲም ሁለት ጊዜ ከእስር እንድንፈታ ተወስኖ፣ ሁለቴም በሩ ላይ በፖሊስ ተይዘን እንድንመለስ ተደረገ፡፡
“በኋላም  እኔን ወደ 6 ኪሎ መልሰው አመጡኝና፣ ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወስድኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ ወደ አባ ሳሙኤል ወህኒ ቤት- ቀጥሎም  ወደ ቂሊንጦና ቃሊቲ እስር ቤት ተወሰድኩ፡፡ ቃሊቲ በአንድ ሳምንት ብቻ፣ በሦስት ዞኖች ውስጥ ታስሬአለሁ፡፡ አንዳንዴ፣ አደገኛ እስረኞች በሚገኙበትና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንድቆይ ይደረግ  ነበር፡፡ ለፍርድ ቤት ይግባኝ አልኩና፣ ፍርድ ቤቱ ወደ ቂሊንጦ እንድመለስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ቂሊንጦ ሳለሁ ከሌሎች 20 እስረኞች ጋር ፍርድ ቤት ቀረብኩ፡፡ አቃቤ ህግ በርካታ ምስክሮችን የጠራ ቢሆንም፣ በእኛ ላይ ሊመሰክር የተገኘ ማንም አልነበረም። በዚህ ምክንያት ፍ/ቤቱ እኔን ጨምሮ 12 ሰዎች የቀረበብንን ክስ መከላከል ሳያስፈልገን፣ በነጻ ከእስር እንድንፈታ ብይን ሰጠ፡፡
“ይህ የሆነው በድምሩ ለ2 ዓመታት ከታሰርኩ በኋላ ነበር፡፡ በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረትም፣ ከቂሊንጦ እስር ቤት ልወጣ ስል እንደተለመደው ወህኒ ቤቱ በር ላይ ተያዝኩኝ። የፊንፊኔ ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ አባላት፤ ከባድ መሣሪያዎች በደገኑ 12 ተሽከርካሪዎች መንገዱን ዘግተው፣ ወደ ገላን ዲሬ ሶሎያ ወህኒ ቤት ወሰዱኝ፡፡  ከሳምንት በኋላ ወደ አዋሽ መልካሳ የተወሰድኩ ሲሆን፤ እዚያም የቀድሞውን የኦነግ ቃል አቀባይ ጓድ ባቴ ኡርጌሳንና ሌሎች ከ400 በላይ እስረኞችን ተቀላቀልኩ፡፡ ይሄ ቦታ ሲኦል ነበር ማለት ይቻላል፡፡
“ከአዋሽ መልካ ወደ ገላን ተመልሼ ተወሰድኩኝ፡፡ በገላን እስር ቤት ሳለሁም፣ ፍ/ቤት ከቂሊንጦ ወህኒ ቤት እንድለቀቅ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቃወም ፌደራል ፖሊስ ይግባኝ አለ፡፡ እናም ሜክሲኮ ወደ ሚገኘው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተመልሼ ተወሰድኩ። ይግባኙ ከእስር መለቀቄን በመቃወም ነበር። የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከእስር እንድፈታ መበየኑን፣ በተጨባጭ ግን አለመፈታቴን ያውቃል። ፍ/ቤቱ የእኔን ጉዳይ አላይም ብሎ፣ ወደ ወህኒ ቤት መመለስ አለበት አለ፡፡ ምንም አይነት ክስ ስላልተመሰረተብኝ፣ ወዲያውኑ መፈታት ነበረብኝ፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ፣ አቃቢያኑ ጉዳዬን ወደ ፌደራል ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰዱት ሲሆን እዚያም ነፃ ወጣሁ፡፡
“በኦሮሚያ እጅግ የከፋ ነገር እየተፈጸመ ነው። አንተ ባትጠይቀኝ ኖሮ ስለ እስሬ ሁኔታ መናገር አልፈልግም ነበር፡፡ ልነግርህ የምፈልገው ግን እስር ቤቶች ሁሉ አንድ አለመሆናቸውን ነው፡፡ በኦሮሚያ ወህኒ ቤቶች ረሃብ አለ፤ የጸሃይ ብርሃን ማየት አትችልም፤ ገንዘብ ከሌለህ በቀር ህክምና አታገኝም፤ ዘመዶችህን ወይም ጠበቆችህን ማግኘት አይፈቀድልህም፤ ፓስተርህን ማግኘት አትችልም፤ የት እንዳለህ ማንም አያውቅም፡፡ ፖሊሶች  (ባያዝኑልህ ኖሮ) አንተን የመግደል መብት እንዳላቸው በቀጥታ  ይነግሩሃል -  በምስጢር ሳይሆን በግልጽ ስብሰባ ላይ፡፡  “በአንድ ወቅት አተት በእስር ቤቱ ተከስቶ ነበር፡፡  አንድ ሃኪም መጣና መድሃኒቱ ውሃ አለመጠጣት ነው አለን፡፡ ውሃ መጠጣት እንድናቆምም ነገረን፡፡ “እንኳን ለናንተ ለጠላቶቻችን ቀርቶ በትግራይ ለሚዋጉት ወታደሮቻችንም መድሃኒት የለንም፡፡” ስለዚህ ውሃ መጠጣት አቁሙ አለን፡፡
“በኦሮሚያ የተሻለ ሁኔታ ያለበት ብቸኛው የእስር ሥፍራ፣ በሰበታ የሚገኘው  ዳላቲ ወህኒ ቤት ነበር፡፡ እዚያ ፖሊሶች አብረውን የተለያዩ ጨዋታዎችን ይጫወቱ ነበር፡፡ ኢሬቻን ሁሉ ከኛ ጋር ያከብራሉ፡፡ ከፖሊስና ከወህኒ ቤቱ አስተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት ነው የነበረን።
“ሌላው ገላን ፖሊስ ጣቢያ ነው። እዚያ ፖሊሶች አያስፈራሩንም፤ ምግብ አይከለክሉንም። ቤተሰቦቻችንና ጠበቆቻችን እንዳያገኙን አያደርጉም። ፖሊሶች እንደሰው ልጅ ነበር የሚይዙን። ይህን ቦታ ማመስገን እፈልጋለሁ።
“በጠቅላላ በ18 ቦታዎች ታስሬአለሁ። በሁሉም ፌደራል ወህኒ ቤቶችና ሜክሲኮ በሚገኘው የማቆያ ማዕከል (የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ)፤ በአባ ሳሙኤል፣ በቃሊቲና በቂሊንጦ እስር ቤቶች ፖሊሶች አይነኩንም ነበር። ትግራይ ሆንክ አማራ አሊያም ከምባታ….. በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የምትያዘው። ፖሊሶቹ በትክክለኛ የፖሊስ ሰብዕና ነው የሰለጠኑት። በጣም ትህትና የተመላባቸው ነው፡፡
“የፍ/ቤት ቀጠሮ ሲኖረኝ፣ ፍ/ቤት ወስደው ይመልሱኛል። ለምን በካቴና እንደሚያስሩንና የሚፈትሹን ለደህንነታችን ሲሉ እንደሆነ አስቀድመው ይነግሩናል። እኒህ ፖሊሶች በጣም ወጣት ሲሆኑ  በመሳደብ፣ በማንኳሰስ ወይም በማጥቃት መብታችንን የሚጥስ የለም። አንዳንድ ቁጣ ቁጣ የሚላቸው የፖሊስ መኮንኖች ቢኖሩም፤ የቂሊንጦ፣ አባ ሳሙኤልና ቃሊቲ ወህኒ ቤቶች አስተዳደሮችን በተመለከተ ምንም ቅሬታ የለኝም። በእውነቱ መመስገን ይገባቸዋል። በዚሁ ሁኔታ እንዲቀጥሉና ለሌሎቹ አርአያ እንዲሆኑ መበረታታት አለባቸው።
“ፍትህ መስጠት ግን የእነሱ ሃላፊነት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቀጠሮ ሲኖር በሰዓቱ ፍ/ቤት ይወስዱሃል፡፡ ፍ/ቤትንም በተመለከተ ብዙ ቅሬታ የለኝም፡፡ ፖሊስም አቃቤ ህግም በእኔ ላይ የሚመሰረተው ክስ ባልነበረበት ሁኔታ፣ ፍ/ቤቱ ከእስር ሊለቀኝ ሲገባ ወደ ወህኒ ቤት እንድመለስ ከማድረጉ በስተቀር፡፡ በተረፈ እኔ የህግ ባለሞያ ባልሆንም፣ የፌደራል ፍ/ቤት በእኔ ላይ ያደረገው ነገር  የለም፡፡
“በተቃራኒው በኦሮሚያ ነገሮች አስከፊ ናቸው፡፡ ፍ/ቤት ሥልጣን የለውም፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ጓዶቻችን እዚያ ነው ታስረው የሚገኙት፡፡ አቃቤ ህግ በሁሉም ላይ ክስ እንደሌለው ተናግሯል፡፡ እኔ በግል የማውቃቸውን ለመጥቀስ ያህል፡- አብዲ ረጋሳ፣ ሚካኤል ቦራን፣ቀናሳ አያና፣ ዳዊት አብደታ፣ለሚ ቤኛ፣ጋዳ ገቢሳ፣ ገዳ ኦሊጀራ…ናቸው፡፡ ፍ/ቤት እንዲፈቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፤ ነገር ግን አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የኦሮሚያ እና የፌደራል እስር ቤቶች ለየቅል ናቸው፤ በጣም ይለያያሉ፡፡---”
(ከአዘጋጁ፡- የእንግሊዝኛ ሙሉ ቃለ ምልልሱን በ”አዲስ ስታንዳርድ” ድረገጽ (ፌቡራሪ 21, 2023) ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 1997 times
Administrator

Latest from Administrator