Print this page
Sunday, 12 March 2023 10:21

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጠየቁ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

መንግስት ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን ካገደ አንድ ወር ሆኖታል
                   
         መንግስት ከየካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም  ጀምሮ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የጣለውን  ገደብ እንዲያነሳ   አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት  ተሟጋች  አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ጠይቀዋል።
ህብረተሰቡ በስፋት በሚጠቀምባቸውና  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሆኑት ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክ ቶክ እና ዩቲዩብ ላይ መንግስት  ክልከላና ገደብ ከጣለ   ድፍን አንድ ወር እንደ ሞላው የገለጸው አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል፤ ይህ ድርጊት የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃን የማግኘት መብቶችን በግልጽ የሚጥስ እንደሆነም አመልክቷል።
  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ህገ ወጥ ነው ካለችውና የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖናና ስርዓት የጣሰ ነው በሚል ከእምነቱ ተከታዮች ታላቅ  ተቃውሞ ከገጠመው   የጵጵስና ሹመትና የሲኖዶስ ምሥረታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ፣ በመንግሥት የተወሰደው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን የማገድ እርምጃ ህገ ወጥ መሆኑን ያመለከተው የአሚኒሲቲ መግለጫ፤ ድርጊቱ  የአገሪቱን  ሕገመንግሥትና   የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች የተቃረነ ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ ለዓመታት መጠነ ሰፊ ተቃውሞዎች በሚያጋጥሙበትና በተለያዩ ምክንያቶች   ግጭት   በሚኖርባቸው አካባቢዎች  ኢንተርኔት የማቋረጥና የመዝጋት ተግባር በተደጋጋሚ እንደሚከናወን  የተለያዩ ድርጅቶች ሪፖርት አድርገዋል ያለው  አምነስቲ፤ ይህ እርምጃም አገሪቱ በሚዲያ ነጻነት ላይ ያላትን አያያዝ የበለጠ የሚያጠለሽ መሆኑን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በበኩሉ ፤ መንግስት በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ የጣለው ገደብ   “የሰዎችን መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ገደብ የሚጥል እና የሚጋፋ ስለሆነ”  ሊነሳ ይገባል ብሏል። ድርጊቱ  በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ  ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ያመለከተው ኢሰመጉ፤   የመገናኛ ብዙሃን ሥራቸውን በአግባቡ   ለሕዝብ እንዳያቀርቡ ችግር በመፍጠር ላይ እንደሆነ አመልክቷል።    ገደቡ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠሩ   ሳቢያ መንግስት ገደቡን እንዲያነሣ ከዚህ ቀደም በመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የተጠየቀ መሆኑንም  ኢሰመጉ አስታውሷል።
በአገሪቱ   በማኅበራዊ  ትስስር ገጾች  ላይ በተጣለው እገዳ ሳቢያ  ተገልጋዮች የትስስር መድረኮቹን ለማግኘት ቪፒኤን የተባሉትን መተግበሪያዎች ለመጠቀም መገደዳቸውን ያመለከተው የሰብአዊ መብቶች ጉባዔ መግለጫ፤  የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እነዚህን ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በሚያገኙዋቸው ቨርችዋል ፕራይቬት ኔትወርክ ለመጠቀም በመገደዳቸው “የመረጃዎችን የደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል” ብሏል።
ሁለቱ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማቱ በመግለጫቸው መንግስት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የጣለውን    ገደብ   በአስቸኳይ   እንዲያነሳ   እና በቀጣይም   በሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ እንዲሁም መረጃዎችን የማግኘትና የመቀበል መብት ላይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠብ  አሳስበዋል።
የስታቲስቲክ መረጃ እንደሚያመለክተው፤  እስከ ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ድረስ በኢትዮጵያ በጣም ታዋቂው የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ የሆነው ፌስቡክ ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎች  የነበሩት ሲሆን ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የኢትዮጵያ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች  ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን ታውቋል።

Read 1618 times