Sunday, 12 March 2023 10:21

በባጃጅ ትራንስፖርት ላይ የተሠጠው ውሣኔ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

• ክልከላውን በሰላማዊ ሰልፍ ባወገዙ ወጣቶች ላይ ፖሊስ ጥይት በመተኮሱ የቆሰሉና የተጎዱ ወጣቶች አሉ
    • በመቶዎች የሚቆጠሩ ባጃጆች በክሬን እየተጫኑ ተወስደዋል ተብሏል
    • ከ95% በላይ አሽከርካሪዎች የአማራ ተወላጆች በሆኑበት የሥራ ዘርፍ ላይ የተደረገው ክልከላ አማራውን ለማዳከም ከአዲስ    አበባ  ለማስወጣት ታስቦ በጥናት የተደረገ እንደሆነ ተነግሯል።
     
       የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን (በተለምዶ አጠራር ባጃጆች) ከየካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም  ጀምሮ  ላልተወሰነ ጊዜ ሥራ መስራት እንደማይችሉ ያሣለፈውን ውሣኔ ተከትሎ   ክልከላውን በሰላማዊ ሰልፍ ለማውገዝና   ለተቃውሞ በወጡ የባጃጅ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ  2 ባለ ባጃጆች መቁሰላቸውና በርካቶች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
‹‹የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን በተሻለ መልክ ለመምራት የሚያስችል የአሰራር  ማሻሻያ ስራዎችን ለመዘርጋት በሚል ምክንያት የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትን ላልተወሰነ ጊዜ ያገደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ፤ የባጃጅ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎቹ ላቀረቡት "የምን ሰርተን እንብላ" ጥያቄ የሠጠው ምላሽ የለም።
በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ  ጋርመንት አካባቢ ክልከላውን በሰላማዊ ሰልፍ ለማውገዝና ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ በወጡ ወጣቶች ላይ አድማ በታኝ ፖሊስ ጥይት በመተኮሱ፣ ሁለት ወጣቶች እንደ ቆሰሉና  በርካቶችም ለእስርና ለድብደባ እንደተዳረጉ  ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ  ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ14 ውስጥ ነዋሪና በባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ  የሚተዳደረው ወጣት መስፍን አማረ እንደሚናገረው፣   
በአካባቢው በባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ከ5 አመታት በላይ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነታቸው በግልፅ በማይታወቁና  በመንግስት ኃይሎች ድጋፍ በሚደረግላቸው ወገኖች የተለያዩ ችግሮች ሲደርስብን ቆይቷል  ብሏል። ከ3 ወራት  በፊት ባጃጅ  በአስፋልት ላይ ማለፍ አይችልም ተብለን ስለተከለከልን ለተወሰኑ ቀናት አስፋልቱ ትተን በኮብልስቶን መንገዶች አገልግሎት መስጠታችንን እንድንቀጥል ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ከቀናት በኋላ ወደ መደበኛው አገልግሎታችን እንድንገባ ተደርጎ፣ ሥራችንን ስንሰራ ቆይተናል ብሏል። አሁን ቢሮው ያሳለፈው ውሣኔ ግን ለሁላችንም ዱብ እዳና ኃላፊነት የማይሰማው ውሣኔ ነው ሲል ተናግሯል።
በህጋዊ ማህበር ተደራጅተው ከጆሞ ወደ መብራት ኃይል፣ ከመብራት ወደ ኃይሌ ጋርመንት፣ ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ሰፈራ፣ ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ሀናማርያም፣ እና ከኃይሌ ጋርመንት ወደ ጋራ በአዲሱ መንገድ ላይ ለአመታት የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን የሚገልፁት የባጃጅ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች  ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ አሁን በድንገትና ምንም ዝግጅት ሳናደረግ ድንገት ስራችሁን መስራት አትችሉም መባላችን እጅግ አስደንግጦናል ብለዋል። "እንዳንሰራ ልንከለከል አይገባንም፣ ምን ሰርተን እንብላ፣ የትእንሂድ!" ያሉት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች እያንዳንዳችን መተዳደሪያችን በሆነው በዚሁ ስራ አምስትና ስድስት ቤተሰቦች ይዘን በዚህ የኑሮ ውድነት የትውደቁ ልንባል ነው።  መንግስት እኛንም እንደዜጋ አይቶን በገዛ አገራችን ሰርተን መኖር እንዳንችል የሚያደርግ ውሣኔውን ዳግም  ሊያጤን ይገባል ብለዋል።
የአሠራር ማሻሻያዎች ለማድረግ በሚል ከትራንስፖርት ቢሮው የተሠጠው ምክንያት  እውነተኛ አለመሆኑንና መንግስት ከእኛ አውቅና ውጪ በራሱ መንገድ የአካባቢው ነዋሪዎች ያልሆኑና የማይታወቁ ሠዎችን በላያችን ላይ  ለማደራጀትና ሌላ  ማህበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ለማቋቋም ታስቦ  ነው  ሲሉ ግምትና ጥርጣሬአቸውን   ተናግረዋል።
ይህ ባጃጆችን ከስራ የማስቆም ተግባር የተፈጸመው  ሰፊ ጥናት ተድርጎ ማንነትን ከለዩ በኋላ ነው የሚሉት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች  በዚህ የሥራ ዘርፍ በስፋት ተሠማርቶ የሚገኘው የአንድ ብሔር ተወላጆች በመሆናቸው እነሱን  ለማዳከም እና ከአዲስ አበባ ለማስወጣት ሆን ተብሎ የተወሰደ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
አሁን በአዲስ አበባ የትኛውም አካባቢ ላይ እንዳይሠሩ የተከለከሉት ባጃጆች በተለይ በከተማ ዳርቻ ላይ ባሉ መኖሪያ ሠፈሮችና የጋራ መኖሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሠጡ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት  ቢሮ በተሽከርካሪዎቹ ላይ የጣለው ክልከላ እስከመቼ እንደሚቆይ ትክክለኛ ቀኑን አላስቀመጠም።   በጉዳዩ ላይ ከቢሮው ምላሽ ለማግኘትና ክልከላው እስከ መቼ ድረስ እንደሚቆይ ለመጠየቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ የጸጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል በሰጠው መግለጫ፣  ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውስጥ 100 ያህል ባጃጆች ባልተፈቀደላቸው አካባቢ አገልግሎት እንሰጣለን በሚል ሁከት ፈጥረው ነበር ብሏል።



Read 2388 times