Sunday, 12 March 2023 10:41

እነቢንያም 100 ጎዳና ላይ የወደቁ ሲያነሱ፤ የዘር ፖለቲከኞች 1ሺ ያፈናቅላሉ

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(0 votes)

- ፖለቲከኞች ለቦረና እርዳታ ያሰባስቡ ሲባል ሸጠውት አረፉ
           - ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተዓምር የሰሩበት 3 ቀንና ሌሊት
              
          “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን  ብቻ በቂ ነው…” በሚል መሪ ቃሉ ነው የሚታወቀው-
የመቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ድርጅት መሥራች (የክብር ዶ/ር) ቢኒያም በለጠ። (የክብር ዶክተር ሲያንሰው ነው!) ቢኒያም መቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ማዕከልን የዛሬ 23 ዓመት ገደማ ነው የከፈተው-20 ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያንን በወላጆቹ ቤት በማኖር። ዛሬ መቄዶንያ ከ7ሺ በላይ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውንና የአካል ጉዳት ያለባቸውን አረጋውያን ሰብስቦ ይረዳል ይደግፋል-መጠለያ፣ ምግብና ህክምና አሟልቶ በማቅረብ።
የማዕከሉ መሥራች ቢኒያም በለጠ፤ የመቄዶንያ የቀን ወጪ 1ሚ. ብር መሆኑን ደጋሞ ሲናገር ይደመጣል- አግዙኝ እያለ መሆኑን መርሳት የለብንም። እንዲያም ሆኖ መቄዶንያ አድማሱን በማስፋት በሁሉም ክልሎች ማዕከሉን ከፍቷል። ህንፃዎችንም በቅጡ እየገነባ ነው፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ላይ የገነባው ግዙፍ ዘመናዊ ህንፃ ሲጠናቀቅ፣ ለሆስፒታልና ለአረጋውያን መኖሪያ የሚያገለግል ነው ብሏል-ቢኒያም።
የዚህ ማስታወሻ ዓላማ ስለ መቄዶንያም ሆነ ስለ መስራቹ ቢንያም ለማስተዋወቅ አይደለም። ይልቁንም ባለፈው ሳምንት ዝነኞችና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው የሰሩትን ተዓምር  ለማውሳትና ለመዘከር ነው። ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን፤ የማይቻል የሚመስለውን እንደሚቻል አሳይተውናል- በፍቅር!
የዶንኪቲዩብ  መሥራች ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ፤ መቄዶንያ ለሚያሰራው ግዙፍ ህንፃ በርና መስኮቶችን ለመግጠም የሚያስፈልገውን 1 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ ስርጭት የማሰባሰብ መርሃ ግብር የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚያካሂድ በተደጋጋሚ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል።  ማስተዋወቅ ብቻ ግን አይደለም። ከወር በፊት  መስኮትና በር  በሌለው ህንጻ ውስጥ በብርድና በውርጭ እየተገረፉ ለአንዲት ቀን ማደር ምን እንደሚመስል በቪዲዮ በመቅረፅ አሳይቶናል- እሱ ራሱ ከአረጋውያኑ ጋር ብርድ እየፎደፎደው ለአንድ ቀን በማደር።
ቀኑ ደርሶ ባለፈው እሁድ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም 1 ሚሊዮን ዶላር የማሰባሰብ መርሃ ግብሩ በዶንኪቲዩብ በቀጥታ ስርጭት (LIve) ሲካሄድ ዓለም አይቶታል። መርሃ ግብሩ በባላገሩ ቴሌቪዥንና በማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሲተላለፍም ነበር። እርግጥ ነው 1 ሚሊዮን ዶላር  በ24 ሰዓት ውስጥ የማሰባሰብ ዕቅዱ አልተሳካም።  A blessing in disguise እንዲሉ፣ አለመሳካቱ ለበጎ ነው ብያለሁ ለ3 ቀን በመራዘሙ ብዙ ፍቅር፣ ብዙ ጽናት፣ ብዙ አንድት አሳይቶናል። የመርሃ ግብሩ ፊታውራሪ “ተርቡ” ኮሜዲያን እሸቱ፤ ቀሪውን ገንዘብ ለሌላ ለሌላ መርሃ ግብር የማስተላለፍ ምርጫ ነበረው። ኮሜዲያኑ ግን የመረጠው የሚፈለገው ገንዘብ እስኪሞላ ድረስ እዚያው ስቱዲዮ ውስጥ ማደርን ነበር- “በሮችና መስኮቶቹን እስክንገጥም ድረስ  ከላይቭ አንወጣም” በሚል ጽናትና ቁርጠኝነት! በዚህ ሁኔታ ነው 1 ሚሊዮን ዶላር የማሰባሰብ መርሃ ግብሩ ለ3 ቀናት ቀጥሎ፣ የማታ የማታ ከ1.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማሰባሰብ የተቻለው።  (ከታቀደው በላይ ማለት ነው!) ይሄ ታዲያ ተዓምር አይደለም!?
ይህ የገንዘብ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር፤ ተራ የገቢ ማሰባሰቢያ አይደለም። “ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በፍቅር ተዓምር የሰሩበት፤ ታላቅ ታሪክ የፃፉበት፤ ዕፁብ ድንቅ ክስተት” ነው። እኔን በግሌ የማረከኝና የመሰጠኝ ከተሰበሰበውም ገቢ በላይ የ3 ቀናት ሂደቱ ነው- ፅናት፤ ቁርጠኝነት፤ ሰብአዊነትና አንድነት ጎልቶ የተንፀባረቀበት!!
እንግዲህ እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን ኢትዮጵያ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ  ከግጭት ወጥታ አታውቅም። ማንነት ተኮር ግድያውና ማፈናቀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን እያስተዋልን ነው። ዜጎች በታጣቂ ሃይሎች ዕድሜ ዘመናቸውን ከኖሩበትና ሃብት ንብረት ካፈሩበት ቀዬ ይፈናቀላሉ- የመፈናቀልም ዕድል የማያገኙ ግን አሉ። ያለ ጥፋታቸው በጭካኔ የሚገደሉ። በሰሜኑ የ2 ዓመት ጦርነት ቢያንስ 500ሺ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል- ጦርነቱን ጨምሮ በረሃብና በበሽታ ሳቢያ። ባለፈው ሰሞን በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ለ15 ዓመታት መሬት ገዝተውና ጎጆ ቀልሰው የኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች “ህገ-ወጥ” በሚል ቤታቸው በመንግሥት ፈርሶባቸው  የተፈናቃዮች ቁጥር እንዲያሻቅብ ሆኗል በራስ አገር ስደት በሉት! በዚያ ላይ በቦረና ድርቅ ከ4 ሚሊዮን በላይ ከብቶች አልቀው፣ አሁን ደግሞ የረሃብና ሞት አደጋው በወገኖቻን ላይ እያንዣበበ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ የዘር ፖለቲካው ከምንጊዜውም በላይ እየጦዘ ነው- ዕድሜ ለግጭትና ሁከት ጠማቂ ፅንፈኞች!!ቢቢሲ ኦሮምኛ ሰሞኑን እንደዘገበው ደግሞ “የቦረና እርዳታ በሹመኞች እየተሸጠ ነው” ባለስልጣናትን አስተባብለዋል ቢባልም፡፡(ሊያምኑ ነው እንዴ ታዲያ!)
ኢትዮጵያችን እንዲህ እንቆቅልሽ ናት፡፡ እነ ቢንያም (የመቄዶንያው) 100 ጎዳና ላይ የወደቁ ሲያነሱ፤ ጽንፈኛ ብሄርተኞች (በዘር ፖለቲካ ናላቸው የዞረ) 1ሺ ዜጎችን ያፈናቅላሉ። የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች በህዝቦች መካከል ቂምና ቁርሾ ለመፍጠር ተግተው ሲሰሩ እየታዘንባቸው ነው- እንቅልፍ አጥተው። የማጣያ  ሰበብ እንኳን ቢያጡ ዝም ብለው አይቀመጡም- ወደ ኋላ 100 ዓመት  ተጉዘው የግፍና የበደል ትርክት ይፈበርካሉ፡፡ ዋና ዓላማው የጥላቻ ስሜትን አጋግሎ ህዝብን  ከህዝብ  ማጋጨት ነው- እርስ በርስ ማፋጀት።
የመቄዶንያ መሥራች ቢኒያም በለጠ የሚረዳቸውን አረጋውያን ቁጥር ከ7ሺ ወደ 20ሺ ለማሳደግ ነው፤ ግዙፍ  የማዕከሉ ህንፃ በሮችና መስኮቶች በአፋጣኝ እንዲገጠሙለት የፈለገው፡፡ ጧሪ ቀባሪ አጥተው ሜዳ ላይ የወደቁ  አያሌ  አረጋውያን ከጎዳና ላይ ለማንሳት ማለት ነው። ከእሁድ ጀምሮ ለ3 ቀናት ያለ እንቅልፍ የዘለቀው የዶንኪቲዩብ live የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር፤ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ይመስላል፡፡ ለሰው ልጅ ህይወት ዋጋና ክብር የሚሰጡ አያሌ ደጋግ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ማወቅ የመኖር ተስፋ ያለመልማል፡፡
በሦስት ቀናቱ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ በዶንኪቲዩብ ስቱዲዮ ያልተገኘ ታዋቂና ዝነኛ አርቲስት፣ ድምፃዊ፣ አነቃቂ፣ የሀይማኖት አባት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወዘተ አልነበረም ማለት ይቻላል። መርሃ ግብሩ ሚሊዮን ዶላሮች ብቻ አይደሉም የተሰባሰቡበት፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ ደግነት፣ ፍቅር፣ ሰብዓዊነት፣ አንድነት፣ በጎነት የፈጣሪ ፀጋ ወዘተ ተሰብኮበታል፤ ተዘምሮበታል፡፡ ተቀንቅኖበታል። ተወዳጅ ድምፃውያን በጥዑመ ዜማቸው አዝናንተዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ምክር ለግሰዋል። የደግነትና ልግስና ትሩፋትን በምሳሌ እያጣቀሱ አስተምረዋል፡፡ በዩቲዩብ ስክሪን ላይ በጉልህ ይነበብ የነበረው፤ ”የፅድቅ በር እና የፅድቅ መስኮት እነሆ!” የሚል መልዕክትም ልብን የሚያራራና እጅን የሚፈታ ነው- በተለይ ለሀይማኖተኞች። እንደ እውነቱ ከሆነ በዶንኪቲዩብ ስቱዲያ የታዩት ዝነኞችና ታዋቂዎች እንዴትና ከየት ተሰባሰቡ ያስብላል። ልዩ መንፈስና ልዩ ውበት አጎናጽፈውታል- ለመርሃ ግብሩ! ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል… መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ፣ ኡስታዝ አቡበክር አህመዲ፣ አንጋፋው ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱ፣ አርቲስት ያሬድ ሹመቴ፣ አርቲስት ሚካኤል፣ ገጣሚ ምሥራቅ፣ ድምፃዊ ሳሚ ዳን፣ ቴዲዮ፣ ተወዳጁ  እንስፍስፍ አቀንቃኝ አቡሽ ዘለቀ ወዘተ ዝርዝሩ አያልቅም፡፡ እኒህ ሁሉ  ታዋቂዎችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ተሰባስበው፤ ዝናቸውንና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ተጠቅመው፤ በፍቅር ተዓምር የሰሩበት ክስተት ነው-የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ!
በነገራችን ላይ ኮሜድያን እሸቱ ለቦረና ድርቅና ረሃብ ተጎጂዎች 10 ሚሊዮን ብር በስኬት አሰባስቧል- በዶንኪቲዩብ!! ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአሜሪካ ለገዛው ሰፊ መሬት በአንድ ቀን ብቻ 1ሚ.ዶላር በማሰባሰብ ረከርድ ሰብሯል ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን በአጭር ሰዓት በማሰባሰብ ለገዳም መነኮሳት የቧንቧ ውሃ አስገብቷል- ገንዘብ አሰባስቦ!! በአማራ ክልል የተጀመረ መስጊድ ለማጠናቀቅም የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ በመርሃ ግብሩ ማጠናቀቂያ ላይም ለቅሶና ሳግ እየተናነቀው እንዲህ ነበር ያለው፤ “ጨርሰናል።
እግዚአብሔር ይመስገን፤ በሩም መስኮቱም ተሳክቷል! አመሰግናለሁ”
እርግጥ ነው፤ በዶንኪቲዩብ ስቱዲዮ የነበሩት ሁሉ በተመሳሳይ ስሜት ውስጥ ነበሩ፤ በደስታ አንብተዋል። በመጨረሻ በፈጣሪ ፈቃድና ቸርነት ከታቀደው በላይ ገንዘብ መሰባሰብ በመቻሉ-  ነው ያ ዓይነት ስሜት የተፈጠረው ቀልድ እኮ አይደለም። ከ1.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው የተሰበሰበው ይኼ!! ዕፁብ ድንቅ ነው- ተዓምር!!
በዚህ ስኬት ከፕሮጀክቱ ባለቤትና ከማዕከሉ መሥራች ቢንያም በለጠ በላይ የሚደሰትና የሚፈነድቅ አይኖርም ብሎ ይታመናል። ቢንያም ግን የራሱን ስሜት ከመግለጽ ይልቅ ስለ እሸቱ ነው የተናገረው። እንዲህ ሲል፡-
“…የዛሬ 5 ዓመት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነው፤ መቄዶንያ መጥቶ… ወደ ማታ አካባቢ ነው የመጣው…. እና የዚያን ጊዜ በጣም የገረመኝ መልካም ባህርያቱ… ብዙ ሰው መቄዶንያ ይጣል፤ ይጎበኛል፤ ይረዳል።  ግን ሁሉም ሰው አንድ አይደለም። እሱን በጣም ትልቅ ቦታ ከምሰጣቸው ውስጥ ሆኖ እንዲገኝ ያደረገው፣ አንደኛ ትህትናው ነው። ራሱን ዝቅ ያደርጋል… በጣም። (የዚያን ቀን ማታ ያየሁትን ብቻ ነው የምነግራችሁ) በእግዚአብሔር ከፍተኛ እምነት አለው። ትጋት አለው። ሦስቱን ነገሮች አይቻለሁ። ይህንንም ፕሮግራም እንዲሳካ ያደረጉትም እነዚህ ሶስቱ ናቸው”
በመጨረሻ፤ በዚህ የመቄዶንያን የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር፣ የአቅማቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉና በመላው ዓለም የሚገኙ  ኢትዮጵያውያን ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል- ባለፉት ዓመታት ለመከላከያ፣ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወዘተ ገንዘብ እንዲያዋጡ መወትወታቸው ሳያታክታቸው በፍቅርና በደስተኛነት በማዋጣታቸው። ያለ እነሱ የሚፃፍ ታሪክም ሆነ የሚሰራ ተዓምር… አይኖርም ነበር። ከበረከቱ ይድረሰን ብለውም ይሁን አጋርነታቸውን ለማሳየት በዶንኪቲዩብ ስቱዲዮ ውስጥ ለተገኙና ውለውም ላደሩ ምስጋናና ክብር ሲያንሳቸው ነው- አርአያነታቸው የትየለሌ ነውና!
የመርሃ ግብሩ ፊታውራሪ የሆነው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰም ምስጋናና አክብሮት ይገባዋል። “የዓመቱ በጎ አድራጊ” (“Man of the Year” ዓይነት)  ተብሎ ቢሸለም (ዕውቅና ቢሰጠው) ቢያንሰው እንጂ አይዛበትም።
የመቄዶንያ መሥራች ቢንያም በለጠ፤ ለበጎ ሥራና ለሰብአዊነት ሙሉ ህይወቱን የሰጠ፣ የመንግስትንና የሃይማኖት ተቋማትን ስራና ሃላፊነት የተሸከም ዕፁብ ድንቅ ሰው ነው። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰሞኑን ስለ እሱ እንዲህ ተፅፎ አንብቤአለሁ፡-
 “ይህ ሰው ዘመናዊ ህይወቱን ትቶ ለተጎዱና አጋዥ ለሌላቸው እንዲሁም የአካል ጉዳት ላለባቸው አረጋውያን ድጋፍ እየሰጠ ነው።… በሱ መኖር የብዙዎች ህይወት ተቃንቷል… በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በዘመናቸው  ማምሻ ላይ ከማልቀስ ድነዋል፤ በክብር ከኖሩበት ዓለም ከማፈር ተርፈዋል…”
እውነት ነው። ቢኒያም በግሩም ሁኔታ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ብዙ የቢንያም ዓይነት ልብ ያላቸውን በጎ ሰዎች ትሻለች። ርህሩህና ቸር ልብ ያላቸውን ያብዛልን።
ከመሰናበታችን በፊት… የቅዠት ሃሳብ እነሆ፡-
በመጨረሻ ግን እንዲህ የሚል የቅዠት  ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ መጣብኝ፡-
ኢትዮጵያ ሰላሟን የምታገኘው ፖለቲከኞች እንደ አርቲስቶች ሁሉ በመሰል የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ መሳተፍ ሲጀምሩ ነው። ለምሳሌ ለቦረና የድርቅና ረሃብ ተጎጂዎች የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በራሳቸው ሲያዘጋጁና በመሰል መርሃ ግብሮችም ተገኝተው (እንደሰሞኑ አርቲስቶች) መርሃ ግብሩን በመደገፍና በማስተባበር ሲሳተፉ ማየት አልናፈቃችሁም? (ሲያምራችሁ ይቅር!) ለጊዜው ባለን መረጃ መሰረት ለቦረና እርዳታን የሚያሰባስቡ ሳይሆን የሚሸጡ መኖራቸውን ነው የሰማነው። ፖለቲከኞቹ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” የሚለውን መሪ የሰብአዊነት ቃል ሲያቀነቅኑ አልታያችሁም? ህዝብን በጎሳና በመንደር ከመከፋፈልና ከማጋጨት ለአፍታ ወጥተው።
ይታያችሁ… ወደዚህ ሃሳብና ተግባር ገቡ ማለት እኮ  ሰብአዊ ሆኑ ማለት  ነው- ሰው!! ከስልጣንና የግል ጥቅም ይልቅ ህዝባቸውን (ዜጎችን) ያስቀድማሉ ማለትም ነው። ክፋቱ ግን እንዲህ ያለው ነገር በዚህ በእኛ ዘመን እውን የሚሆን አይደለም።
ከፖለቲከኞች በተለይም ከአፍሪካ ዘረኛ ፖለቲከኞች ሰብአዊነትን፣ ርህራሄን፣ በጎነትን፣ ቸርነትን መጠበቅ በራሱ ቅዠት ነው። ከገሃዱ ዓለም የራቀ- የማይጨበጥና የማይዳሰስ!! ወደድንም ጠላንም ከዘረኛ ፖለቲከኞች መጠበቅ ያለብን ጠባብነት፣ ስግብግብነት፣ ሙሰኝነት፣ ከፋፋይነት፣ ወዘተ ብቻ ነው።

Read 1044 times