Saturday, 11 March 2023 00:00

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የላከው ግልጽ ደብዳቤ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የአገዛዝዎ ብልሹ አሰራርን ማስተካከያ እድሉ አሁን ነው”


        አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም
ለተከበሩ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤
ለኢትዮጵያ ሀገራችን ትውልድና ታሪክ ተሻጋሪ የሆነ ለውጥ ያመጣሉ በሚል ተስፋ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ፣ እርስዎንና መንግሥትዎን እስከዛሬ ድረስ በሙሉ ልብ ድጋፉን በመስጠት፤ ወደ እናት ሀገሩ የእርዳታ ገንዘብ በመላክ፤ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ፤ በድርቅና በግጭት በመፈናቀል ብዙ ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎቻችንን በመርዳትና መልሶ በማቋቋም፤ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በሞያ የተደገፈ ምክር በመስጠትና በቁሳቁስ በማገዝ ዳያስፖራው ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከእነዚህ በተረፈ፣ ለዐባይ የህዳሴ ግድብ ስኬት ገንዘብ በማዋጣትና በዲፕሎማሲው መስክ ድጋፍ በመስጠት ሰፊ የሆነ ያልተቋረጠ እገዛ አድርጓል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ የትግራይ ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅትም ዳያስፖራው ከእርስዎ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከመከላከያና የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም፣ ሀገራችንን ለማዳን በተደረገው ከፍተኛ እርብርብ፣ በተለይም በዓለም አቀፉ መስክ ግንባር ቀደም በመሆን በዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ዙሪያ  ያደረገውን ታላቅ ተጋድሎና አስተዋጽኦ ምንግዜም ታሪክ አይረሳዉም።
በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (Nov 4, 2020) ህወሐት በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት፣ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሀንን በተኙበት ሳይቀር ጨፍጭፎ፣ በአማራና አፋር ክልሎችም በዘመተበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የዲፕሎማቲክ ዘመቻ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና ከምዕራባውያን እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ጫና ገጥሟት ነበር። ይህን ለመቋቋም በዓለም ዙሪያ ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳትና በየሲቪክ ማህበሮቻችን በመደራጀት፣ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ አድርገን፣ የጥብቅና ዘመቻዎችን በማደራጀት፣ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በመስጠት፣ በተለይም የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እና ሌሎች አለም አቀፍ አካላትን ሎቢ በማድረግ ታላላቅ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን አስመዝግበናል። በተጨማሪም ከሰላም ደጋፊ “ፓን-አፍሪካን” አጋሮቻችን ጋር በመተባበርና፤ ትግላችንን በማቀናጀት የ“#በቃ” (#NOMORE) ሰፊና ሕዝባዊ ንቅናቄ በዓለም ዙሪያ የህወሓትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ፤ የኢትዮጵያ ችግር የአፍሪካ ሁሉ ችግሩ ሆኖ እንዲታይ፤ የምዕራብ አለም ዜጎች አብረውን እንዲቆሙና ድምጽ እንዲሆኑ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገናል። በአምስት አህጉራትና ከሰላሳ ሁለት በላይ አገሮች ውስጥ ታሪካዊ ታላላቅ ሰለማዊ ሰልፎችን በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ የተነፈገችውን ትኩረት ድምጽ ልንሆንላት ችለናል።
እኛ፥ ከእዚህ ደብዳቤ በታች የፈረምነው ዓለም አቀፍ የዳያስፖራ ድርጅቶች፣ ግንባር ቀደም መሪ በመሆን ሌትና ቀን ያለእረፍት በመታገል፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በምንችለው ሁሉ አቅም፣ በእውቀት፣ በሞያ፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በጊዜ ከፍተኛ መስዋእትነትን የከፈልን ነን። በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትም ተነሳስተን ይህን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመቻላችን ልዩ ኩራት ይሰማናል። ይሁን እንጂ፣ ይህን ስናደርግ የእርስዎን “የብልጽግና ፓርቲ” አጠራጣሪ ታሪክ ማለትም፤ የህወሓትን (ኢህአዴግ) ጠባብ የብሄር፣ የዘረኝነትና ከፋፋይ የፖለቲካ መስመርና፣ በሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና ደባ ለአፍታም ቢሆን በመርሳት አይደለም። ያንን ሁሉ በሆዳችን ይዘን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ፤ ለሕዝባችን ነጻነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ብልጽግና የሰፈነበት ስርአት እንዲገነባ “እናሻግራታለን” ያሉንን ቃል ኪዳን ተስፋ በማድረግና በማመን ነበር ከጎንዎ የቆምነው። ይሄም በብዙዎች ዘንድ መደገፍ የማይገባውን ሥርአት እንደደገፍን አስቆጥሮን ነበር። አሁን እርስዎና መንግሥትዎ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደልና ግፍ ስናስተውል ግን፤ እኛም ከሕዝባችን ጋር አብረን የተከዳን አይነት ስሜትና ቁጭት ነው የሚሰማን።
በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ገብተው ባፈረሱት ቃል ኪዳን የተነሳ፣ በእርስዎ አመራር ላይ ያለን እምነት ከምንጊዜውም በበለጠ አዘቅት ወርዷል። ሀቁ እንደሚያሳየው፣ እርስዎ ከአምስት አመት በላይ በመንግሥት ሥልጣን መሪነት በቆዩባቸው አመታት ውስጥ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ላይ ትገኛለች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፤ የሕዝቡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከምንጊዜውም በበለጠ ተጥሰዋል፤ መንግሥት እራሱ ህገ መንግሥቱን አያከብርም፤ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሚባሉት በሀገሪቱ ስማቸውም ተረስቷል፤ ሌብነትና  ሙስና እንዲሁም  የኑሮ ውድነት ሕዝቡን አስመርሮታል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ለረሀብና ለስደት ተጋልጠዋል፤ ችግሩ ተዘርዝሮ አያልቅም!
ከእዚህ በታች ዋና ዋና የሚያሳስቡንን፤ ለሀገራችን ሠላም፣ ለሕዝባችን ደህንነትና ለህልውናዋ የሚያስጨንቁንንና፤ ሌትና ቀን ቁጭት የሚያሳድሩብንን ክስተቶች ለመዘርዘር እንሞክራለን፥
በሚዘገንን ሁኔታ እያየን ያለነውና መግታት ያቃተዎት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት  እጅግ አድርጎ ያሳስበናል፤ በእርስዎ አመራር ስር በዘር እየተለየ የሕዝባችን በገፍ መታሰርና መንገላታት፤ በጠራራ ጸሀይ መገደል፤ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፤ የማምለክ ነጻነት መገፈፍ፤ በነጻ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ወዘተ መቆም፤ ከባድ የሆኑ በሰው ልጅ ላይ  እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች፤ ከመጠን በላይ ብቻ ሳይሆኑ፣ መንግስትዎ እያወቀ መሆናቸው፤
ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ወይም የአገዛዙን ፖሊሲዎች የሚቃወሙ ታስረዋል። በመላው ኢትዮጵያ በግፍ የታሰሩ የህሊና እስረኞች ቁጥር፣ ከመብዛታችው የተነሳ፣ ይህ ነው ለማለት አዳጋች ነው፤
ሕዝቡ በእርስዎ አስተዳደር ላይ ተስፋ እየቆረጠ ነው፤ ሌላዉ ቀርቶ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ወደ ጎን በመተው፣ ተቃዋሚ የሚባሉትን ጥቂት ድምጾች፥ ለስሙ እንኳን ሳያዳምጡ በአንገብጋቢ የሀገር ጉዳዮች ላይ እንደፈለጉ በግልዎ ውሳኔ ይሰጣሉ፤
ህወሓት የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በግልፅ እየጣሰ፣ የእርስዎ አስተዳደር የህወኃትን ወንጀለኛ ድርጅት መልሶ ለማቋቋም በትጋት ሲሰራ በከፍተኛ ስጋት እየተመለከትን ነው፤
ይህን ሁሉ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሕዝብ፤ በተለይም ዘራቸው እየተለየ በአማራ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ጭፍጨፋ ለማስቆም ባለመቻልዎ፤ እንዲሁም የኦሮሞ ብልጽግና አባላትና የመንግስት ባለሥልጣኖች በሀገሪቱ ፓርላማ “አሸባሪ” ተብሎ ከተሰየመው የ“ኦነግ ሠራዊት” ጋር መነካካታቸውን እያወቁ ባለማስቆምዎ እጅጉን አዝነናል፤
በሰው ልጆች ላይ አሰቃቂ ወንጀል ሲፈጸም፤ በደቦ ድብደባና ግድያ፤ ሴቶችን እናቶችንና ህጻኖችን መድፈር፤ ከእርጉዞች ጽንስ በሳንጃ እያወጡ ማረድ፤ ወንዶችን አንገታቸውን መቅላት፣በአንድ ቤት ውስጥ በማጎር በእሳት በማጋየትና ሌሎችንም ለጆሮ የሚዘገንኑ ወንጀሎች እያዩ፣ ይህን ያህል ዓመት ድንግጥ ብለው በማዘን፤ የመንግሥትዎን ኃይል ከሕዝብ ጋር አስተባብሮ በጋራ በመጠቀም እንዳይቀጥል ማስቆም አለመቻልዎ፤
በተለይም በአማራ ኢትዮጵያውያንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፤ እንዲሁም በሌሎች ብሄረሰቦች በጉራጌና ጌዲኦ፣ እንዲሁም በሻሸመኔ ኗሪዎችና በመሳሰሉት የደረሰውን ግፍ አለማስቆምዎና፤ ወንጀለኞችንም ለፍርድ ማቅረብ አለመቻልዎ፤
በምእራብ ኦሮሚያ (ወለጋ) በተለይ በደርግ ዘመን፣ በ1970ዎቹ  በተደረገው የድርቅ ሰፈራ ከሰሜን የመጡ አማራ ዜጎች ላይ እየተካሄደ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀልና ጭፍጨፋ ማንንም በህግ ተጠያቂ በማያደርግ መልኩ አሁንም እየቀጠለ በመሆኑ፤
በተለይም የክልሉ አስተዳደርና ፖሊስ፤ ወንጀለኞች ይህን የተደራጀ የዘር-ማጥፋት ግፍ ሲፈጽሙ ድንገት እንደተቀሰቀሰ የጎሳ ግጭት አድርጎ፣ አይቶ እንዳላየ ማለፍ፣ ወይንም ለሚያደርጉት ትብብር በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኃይሎችን እጅግ አስቆጥቷል፤
ህገ መንግሥቱን በመጣስ፤ የእርስዎ መንግሥት በተደጋጋሚ በኃይማኖት ጣልቃ እየገባና ፖለቲካ እየሰነቀረ፤ ብዙ ጉዳት እያደረሰና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት በማናጋት ለህልውናዋም አስጊ እየሆነ በመምጣትና የኃይማኖት አባቶችንም መናቅና ማሰቃየት፤
በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእርስዎ መንግሥት ኢላማ ለመሆኑ፤ በቅርቡ መንግሥት በኃይማኖት ላይ ጣልቃ በመግባቱ ሳቢያ ሲኖዶሱን ለሁለት በመክፈል፣ በሀገሪቱ አንዣቦ የነበረው  አደጋና፤ በሕገወጥ በተሾሙ ጳጳሳት ምክንያት በሻሸመኔ የኦርቶዶክስ ምእመናን ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፤ እንዲሁም በቅርቡ የአድዋን ድልንና የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓላት ለማክበር በወጡት ምእመናን ላይ የደረሰው ድብደባና ግድያ፤ በአስለቃሽ ጭስ መታፈን በቂ ምስክሮች ናቸው፤
ገና ውጤቱ ያልታየውንና ስኬቱ የሚያጠራጥረውን “የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን” ከማቋቋም ባለፈ፣ መንግሥትዎ እስካሁን ድረስ በቅንነትና በቆራጥነት ተነሳስቶ፣ በህወሓት-ኢህአዴግ የተመሠረተውንና በብሄር ፖለቲካ ላይ የቆመውን የዘረኝነት ሥርአትና፣ ህገ መንግሥቱን ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ይህ ነው የሚባል እርምጃ ሲወስድ አይታይም፤
ከ3.6 ሚሊዮን ዜጎች በላይ ከቀያቸው መፈናቀል፣ ኢትዮጵያን በሀገራቸው-ዉስጥ በተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከዓለም አንደኛ አድርጓታል፤
የከተሞች ልማት በሚል ሰበብ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለአመታት የኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮምኛ የማይናገሩ ዜጎችን፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ በማንነታቸው እየተለዩ ቤታቸውን በሌሊት በላያቸው ላይ በቡልዶዘር እያስፈረሱ፣ ህጻናትን፣ ሴቶችንና አዛውንትን ለረሀብ፤ ለስደትና ለአውሬ ሳይቀር መዳረግ ከፍተኛ የሆነ ኢ-ሰብአዊ ግፍና ወንጀል ነው፤
አስተዳደርዎ ህገ መንግሥቱን ኢ-ፍትሐዊ በሆነና በዘፈቀደ መንገድ እንደሚተገብር በበርካታ ምሳሌዎች ማስረዳት ይቻላል፤ ከእነዚህም በቅርቡ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ለአንድ ብሄረሰብ (ሲዳማ) አዲስ ብሄርን መሰረት ያደረገ ክልል ሲፈጠር፣ በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎች ብሄረሰቦች፤ ለምሳሌ እንደ ጉራጌ እና ወላይታ ያሉት ግን መከልከል ብቻ ሳይሆን መብታቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን እንዳያደርጉና ድምጻቸውን እንዳያሰሙ እየታፈኑ፤ ለእስር ለድብደባና ለእንግልት ተዳርገዋል፤
ሌላው ቀርቶ የመጠጥ ውሀ ለወራት በማጣት ጉዳት ደርሶብናል በሚል ድምጻቸውን ለማሰማት በወልቂጤ ባዶ ጀሪካን በትከሻቸው ይዘው ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡትን ንጹሀን ዜጎችና በሻሸመኔ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት የሄዱትን ዜጎች የጸጥታ ኃይሎች በግፍ ገድለዋል፤ እንደተለመደው ለጥያቄና ለፍርድም አልቀረቡም፤
እርስዎ የሚመሩት መንግሥት፤ ዓለም የሚያደንቃቸውን የሀገራችንን የረዥም ጊዜ ታሪኮችና ቅርሳቅርሶች እንደፈለገው እየበረዘ ደብዛቸዉን ማጥፋት፤ ብሄራዊ አርማዎችን፣ የባህል ተቋሞችንና፣ የጥንት ቅርሶችን ማፍረስ፤ በኅብረ ብሔራዊነት የሚታወቁ ትልልቅ ከተሞችን ወደ አንድ ብሔር የበላይነት መቀየር፣ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ዘርና ጎሳ ደረጃ ማውረድን ተያይዞታል፤
ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ታላቅ ኩራት የሆነው የአድዋ ድል በዓል እየደረሰበት ያለው ፈተና ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፤
አስተዳደርዎ ከመድብለ ባህላዊነት ይልቅ በአንድ የጎሳ የባህል-አብዮት ላይ አተኩሯል። የኢትዮጵያ መዲና እና የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል የሆነችውን የአዲስ አበባ ባለቤትነት ከአህጉራዊ እና አገራዊ ቦታዎ ዘቅጦ የአንድ ጎሳ የበላይነት ለመውሰድ የሚደረገው ጥረት አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን፣ ማለቂያ ወደሌለው ደም መፋሰስና እልቂት ሀገራችንን እንድታመራ እያደረጋት ነው፤
አባቶቻችን ምንም አይነት የዘርና ሀይማኖት፣ የጎጥ ልዩነት ሳያግዳቸው፤ ሀገራቸውን ከጠላት ለማዳን ለነጻነቷ ሲዋደቁና በህይወታቸው መስዋእትነትን ሲከፍሉ፤ የአፍሪካ ሀገራትም ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ሲታገሉ በኩራት ያነገቡትን አርማ፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብር የተላበሰውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አታሳዩን እያሉ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ዜጎችን ሲያስሩና ሲደበድቡ ምንም ሳይባሉ ሲቀሩ፤ አሁን ጭራሽ የአድዋን ድልም በምኒልክ አደባባይ ልታከብሩ አትችሉም መባሉ እጅግ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ሆኖአል፤
በየካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የአድዋ የድል በዓል በሚከበርበት እለት፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታሪካዊውን የቅዱስ ጊዮርጊስ - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግቢ በጉልበት ገፍተው ገብተው፤ በዓሉን በጸሎትና በወረብ በሚያከብሩት ካህናትና ምእመናን ላይ በድንገት አስለቃሽ ጭስ ተኩስ ከፍተው፣ በብዙዎች ላይ ከባድ የመቁሰል ጉዳት ማድረሳቸው፤ በዚህም ዕለት ለበዓሉ የወጡ ንጹሐን ዜጎች በጥይት ተኩሶ በመግደል፣ በጭካኔ እንደ አራዊት በመደብደብ፤ ይህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተደረገው ግፍ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ምን ያህል ፍትሕና የህግ የበላይነት እንደጠፋና፤ የፖሊስ አምባገነን አስተዳደር እየገነነ እንደመጣ በግልጽ የሚያሳይ ነው፤
ባለፉት አምስት አመታት፣ በእርስዎና የመንግሥትዎ አገዛዝ ወቅት የሀገራችን ወሰንና ዳር ድንበር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተደፈረ ነው። በተለይም በሱዳንና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ቦታዎች የመንግሥትና የሌሎች ኃይሎች ከጎረቤት ሀገር እየገቡ፤ ኢትዮጵያውያንን ማጥቃት እየተለመደ ሄዷል። በዚህም በርካታ ዜጎቻችን በየጊዜው ህይወታቸው ያልፋል፤ ንብረታቸው ይዘረፋል፤ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉም ይደረጋል፤ የሀገራችን መሬትም እየተቀማ ለባዕድ ሀገራት መጠቀሚያ ሲሆን መንግስትዎ ዝም ብሎ ማየትን መርጧል፤
ልክ ከእርስዎ በፊት እንደነበሩት መንግሥታት፣ የእርስዎም አስተዳደር ለዜጎቹ የምግብ ዋስትና ለማምጣት እስከዛሬ አልቻለም፤ እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ (OCHA) መረጃ ከሆነ፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በህይወት ለመኖር ዛሬ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፤ የቅርቡ በረሀብ ተጎጂዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቦረና የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህ ሁሉ ከባድ የረሀብ አደጋ በሀገራችን እያንዣበበ እያለ፤ እርስዎ ግን የአስተዳደርዎን “መልካም ገጽታ” ለመገንባት ሲሉ የስንዴ ምርት ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ፣ አንድን ጎሳ በዋስትና ለመሸንገል፣ ሽር ጉድ ይላሉ፤
በመንግስት ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና፤ የዋጋ ግሽበት እና ወገንተኝነት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ሲሆን፤ የእርስዎ መንግሥት ምን ያህል ማስተዳደር እንዳቃተው ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፤
ለእነዚህና ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶች ከቀን ወደ ቀን እያደጉ ለመጡ የሀገሪቱ ውስብስብ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ቁርጠኝነት ባለማሳየትዎ፤ በተለይም የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል የጸጥታና አስተዳደር አካሎች ግፍ ሲፈጽሙ እያዩ እንዳላዩ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ በማሳየትዎ፤ በኢትዮጵያ የስርአት አልበኝነት ባህል እንዲነግስና፤ የህግ የበላይነትና ፍትሕ እንዲጠፉ በሩን ከፍቷል። ለምን እና በማን ስልጣን እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ፖሊሲዎች አገሪቱ ተከተለች ለሚለው ጥያቄ፣ ሃላፊነት በእርስዎ ላይ ነው – የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመንግስት ርዕሰ መስተዳድር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እርስዎ ስለሆኑ።
አሁንም በቆራጥነትና በቅንነት ተነሳስተው፤ በማስተዋል ወሳኝ የሆኑ መፍትሄዎችን መውሰድና በቶሎ በሥራ ላይ ማዋል ካልቻሉ፤ በዓለም ላይ እራሷን ለማጥፋት የምትጓዝ ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ትሆናለች። ያኔ እርስዎና መንግሥትዎ በታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ድምፅ ለሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ የመሆን ግዴታ አለበት። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል የገቡትን ለማክበር፣ የአገዛዝዎ ብልሹ አሰራርን ማስተካከያ እድሉ አሁን ነው።
ይህንን አደገኛ አካሄድ በአስቸኳይ ለመቀየር እና ጥፋቶችን ለማረም፣ ዜጎችን ለመጠበቅ እና ቅሬታዎችን ለመፍታት ቆራጥ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ እንጠይቃለን። ዛሬ የመንግሥት መቀጠል ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውና አደጋ ላይ ነው ያለው። አስተዳደርዎ ኢትዮጵያን ከአስገባት ከዚህ አጣብቂኝ ጨለማ ለማውጣት እድሉ በእጅዎ ነው። በሰከነና በእውነት መንፈስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባለድርሻ አካላት አሳትፎ ሀገራችንን ለማዳን በአስቸኳይ ስራ እንዲጀመር አጥብቀን እናሳስባለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ!!!
(ማስታወሻ፡- ከላይ የቀረበውን ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፈርመው የላኩት በአሜሪካ የሚገኙ 15 የኢትዮጵያ የሲቪክና ምሁራን ድርጅቶች ሲሆኑ ብዙዎቹ የጠ/ሚኒስትሩ መንግሥት የሪፎርም አጀንዳ ደጋፊዎች የነበሩ ናቸው፡፡)

Read 869 times