Sunday, 12 March 2023 11:38

‘አሸወይና’ ለሰርግ ብቻ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “--ሚሊዮኖች ወገኖቻችን የስድሳዎቹን አ ጋማሽ በምሬት በሚያስታውስ ሁኔታ በድርቅና በረሃብ እየተሰቃዩ “የሰው ያለህ! የወገን ያለህ!” እያሉ ባለበት፣ እንዴት ብሎ ነው “ሁሉም ነገር ኖርማል ነው!” ሊባል እሚችለው! --”    
      
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ኡጋንዳዎች ወደ እኛ እየፈለሱ ነው አሉ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩት እኚሁ አማኞች፣ ዓለም ስትጠፋ የምትተርፍው ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗ ተነግሯቸው ነው አሉ፣ ጊዜ ሳይቀድማቸው ሊቀድሙት ፈጥነው የመጡት፡፡
አዎ፣ አብዛኛው ዓለማችን ጊዜ ቀድሞት ወደ ኋላ እንዳይቀር እየለፋ እየተጋ ነው፡፡ ይብላን ለእኛ እንጂ ውሎ ሲያድር በእኛና በጊዜ መኻል ያለው ክፍተት እየሰፋ፣ እየሰፋ ለሄደብን! የሆነ ቦታ ላይ ፊት ለፊታችን ቀድሞን የነበረውን ጊዜ ማየት እንኳን የማንችልበት ደረጃ የማንደርስበት ምክንያት የለም፡፡ የምር እኮ... አለ አይደል... ቀድሞን ልንደርስበት እየተከተልን ያለነውን ማየት ካቃተን፣ በየትኛውስ አቅጣጫ እንደሄደ አውቀን ነው ልንከተለው የምንችለው! ያኔ በቃ አጨብጭቦ ቁጭ ነው፡፡
ስሙኝማ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎች ጠበቅ አድርገው ሰላምታ ሲያቀርቡላችሁ፤ “ሁሉም ነገር ኖርማል ነው፣ አይደል” ይሏችኋል፡፡ የቋጥኝ ያህል የሚከብድ ጥያቄ፣ አይደል! በተለይ ደግሞ ዘንድሮ፡፡ እናንተም አብሮ መኖር የሚለው ለስንትና ስንት ዘመን የኖረ ታላቅ እሴት እየሳሳ እየተመናመነ የሄደ ቢሆንም፣... አለ አይደል... “አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ...” የሚለውን ተረት ሳትረሱ “አዎ፣ አሸወይና ነው፣” ትላላችሁ፡፡  እናንተ  ያልተመቻችሁን ነገሮች በተናገራችሁ ጊዜ በምክንያት ከመሞገት ይልቅ “ተረት ነው የምታወሩት...” የሚሉ ሰዎች ግርም አይሏችሁም! ጥያቄ አለን፤ ተረት የሚለው ቃል ከ‘ቦተሊካው’ መዝገበ ቃላት ይውጣልን፡፡ ልክ ነዋ! ወይም ተረት የሚለውን ቃል ስንጠቀም “የግርጌ ማስታወሻ” ምናምን የሚል ነገር ይካተትልንማ!
“ተረት የሚለው ቃል በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተካተተው በ‘ቦተሊካዊ’ ትርጉሙ ነው፣” ምናምን ይባልልን፡፡
“ኢትዮጵያ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ የወሰደች ጊዜ...”
“እባክህ ሦስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ የሚባለው ተረት ተረት ነው፡፡”
እናላችሁ እንዲህ እንዲህ በተለይ የሀገርን ስም በበጎ የሚያነሱ፤ ትውልዶችና መልካም ሥራዎች የሚተርኩ፣ የቆየ የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን የሚጠቅሱ ነገሮችን፣ “እባክህ ተረት ተረት ነው...” የሚሉት አባባል፤ የ‘ፍሬሽማን’ ቦተሊከኞች ብቻ ሳይሆን በቦተሊካው ጥርሳቸውን የነቀሉ (በቅንፍ “የሌላውንም ጥርስ ያረገፉና ያስረገፉ...”) የሚባሉት ሁሉ ሲጠቀሙት ስትሰሙ፤ “እንኳን ተንታኝ አላደረገኝ!” (ቂ...ቂ...ቂ...) ትላላችሁ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በሚደረግ ምርምር ይደረስበት ይሆናል ብለን የምንጠረጥረው  ነገር ቢኖር... “የሀገርና የህዝብን የትናንት ወዲያ፣ የትናንትና የዛሬ በጎ ነገሮችን ሁሉ እድሜ ልካቸውን ተረት ነው ሲሉ ከኖሩ የቦተሊካው ሰፈር ሰዎች መሀል፣ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት ራሳቸው ተረት ሆነው እንደቀሩ በጥናት ተደርሶበታል፡፡” አሪፍ አይደል!
እናላችሁ፣ እኛ ደግሞ...
“ተረት፣ ተረት፣”
“የላም በረት (የመሰረት)”
“ከዕለታት አንድ ቀን ሩቅ በሆነ ሀገር...” ምናምን ተረቶቻችንን፣
“በካብ ላይ ብሠራ እባቡ መከራ፣ በዛፍ ላይ ብሠራ አሞራው መከራ፣ በምድር ላይ ብሠራ እረኛው መከራ፣ የት ውዬ፣ የት አድር ብዬ...” ምሳሌያዊ አባባሎቻችንን..
ወይ አላሳጨደው. ወይ ከብት አልበላው
ከቶ መቼ ይሆን ያ ሣር ማለቂያው፣
ቅኔዎቻችንን ያለፉትን ትውልዶች፤ “እንኳንም እኛ ዘንድ ድረስ እንዲደርስ ጠብቃችሁ አቆያችሁልን...” እንላቸዋለን፡፡ በአንዲት “ተረት፣ ተረት...” ውስጥ አንድ ሺህ ገጽ የማይገልጿቸው የሞራልና የስነምግባር መልእክቶች ማስተላለፍ ይቻላልና፡፡ በአንዲት ምሳሌያዊ አባባል  አምስት ወርክሾፖች ላይ የሚቀርቡ የጥናትም ሆኑ ሌሎች ጽሁፎች መግለጽ የማይችሏቸውን የህይወት እውነተኛ ገጽታዎች መግለጽ ይቻላልና! በአንዲት የሁለት መስመር ቅኔ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የፊት ለፊትና ጥልቅ የአእምሮ ሥራ የሚጠይቁ ቅኔያዊ መልእክቶች ማስተላላፍ ይቻላልና!
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል፤ ቀደም ሲል ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚል ጠቅሰን አልነበር!  አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ...እሱዬው አንጋፋ የሚባል የስፖርት ጋዜጠኛ ነበር፡፡ እናም በአንድ ወቅት በሆነ ሚዲያ ላይ ከሚሠራ ወጣት ጋዜጠኛ ጋር ስለ አፍሪካ ዋንጫ እየተወያዩ ሳለ፣ ወጣቱ የስፖርት ጋዜጠኛ ምን አለ መሰላችሁ... “ሦስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ወሰደች የሚባለው ውሸት ነው!” ብሎላችሁ እርፍ! ይህኛው እንኳን ግልጽ የሆነ በጉዳዩ ላይ የእውቀት እጥረት ነው፡፡
ለነገሩ እንደዛም ቢሆን ኮሚክ ነገር መምሰሉ አይቀርም፡፡ አለ አይደል...ልክ እኮ የቀዶ ጥገና ሀኪሙ፤ “በቀዶ ጥገና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ይካሄዳል የሚባለው ሀሰት ነው...” አለ እንደማለት ነው፡፡ እናማ... ሰዋችን “ይህች አገር እኮ የጉድ ሀገር ሆና መቅረቷ ነው!” ቢል ምን ይፈረድበታል! ታዲያማ...አለ አይደል... ምን ለማለት ነው፣ እኛም የስፖርት ትንታኔዎችንም ሆነ ዜናዎችን ማድመጥ ስንፈልግ የየራሳችን ምርጫዎች ያሉን በምክንያት ነው ለማለት ነው። 
 እናላችሁ...ወጣቱ ሦስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ መውሰዳችን “ውሸት ነው...” እንዳለው ሁሉ የሆኑ ቦተሊከኞች ደግሞ ስለ አገራችን በጎ በጎውን ሁሉ “ሀሰት ነው...”፤ “የፈጠራ ወሬ ነው...”፤ “ተረት፣ ተረት ነው...” የሚሉት ነገር የእውቀት እጥረት ከመሆኑ ባሻገር የአእምሮ መቀንጨር የሚሉት ነገር መሆኑን ለማወቅ የየትኛውም አገር ተሞክሮ አያስፈልገንም፡፡
የሚገርም ነው እኮ... ስለምንም ነገር የምታወሩት ለእነሱ ካልተመቻቸው፣ በእነሱ ትርክት ውስጥ ቢገባ ነገሮችን በአፍጢማቸው የሚደፋባቸው ሲሆን፤ “ተረት ነው! ሀሰት ነው! የሆነ ምናምን ነገር ነው፡፡” ለነገሩ የሚይዝ ይዞን እንጂ “እሰይ፣ ደግ አደረግን! እንኳንም ተረት ሆነ!” ብንል ምንኛ በወደድን፡፡ እሰይ!
ስሙኝማ...እንግዲህ ይህን ሁሉ ጨዋታ ያነሳነው “ሁሉም ነገር ኖርማል ነው...” ስለሚለው ማውራት ጀምረን ገባንበትና ነው፡፡ እናላችሁ...አሁን አሁን የሚሆነው፣ እየሆነ የሚመስለንና የማይሆነው ወይም እንዳይሆን የተፈለገው ግራ ባጋባንና ባወዛገበን ሰዓት፤ “ሁሉም ነገር አሸወይና ነው፣ ኖርማል ነው!” የምንለው ነገር፣ ከአባባሉ ጀርባ ቅንነትና የጨለሙ ነገሮችን የበለጠ ላለማጨለም ፍላጎት ቢኖርበትም ልክ አይደለም፡፡ ከታላላቅ ደራሲዎቻችን አንዱ እንዲህ የምትል ስንኝ አለችው፡-
ታናሹንም አየሁ በልቼ፣ በልቼ
ታላቁንም አየሁ በልቼ፣ በልቼ
ከኮሶ በስተቀር ሌላ ምን አይቼ፤
እንዲህ ነው ነገሩ፡፡ ብዙ ነገር ከኮሶ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር እየተጣባበት (ያውም ‘የሚበላው’ ከተገኘ!) መልካምነታቸው ከማረጋጋት ይልቅ ይበልጡኑ ሆድ የሚያስብሱ ነገሮች ይኖራሉ፡፡
ኪሎ ጤፍ ሰማንያ ብርና ከዛ በላይ ገብቶ እንዴት ነው ሁሉ ነገር ኖርማል የሚሆነው! አሁን እኮ እንደ ቀድሞው “ኩንታል፣ ግማሽ ኩንታል፣ እሩብ ኩንታል” እያሉ ማዘዙ ቀርቶ ሰዋችን ጤፍን እንደ ስኳርና እንደ ቡና በኪሎ እየገዛ በትንሽዬ ፌስታል እየቋጠረ ነው ተብሎ በሚወራበት ዘመን ውስጥ ነን፡፡
ሚሊዮኖች ወገኖቻችን የስድሳዎቹን አጋማሽ በምሬት በሚያስታውስ ሁኔታ በድርቅና በረሃብ እየተሰቃዩ “የሰው ያለህ! የወገን ያለህ!” እያሉ ባለበት፣ እንዴት ብሎ ነው “ሁሉም ነገር ኖርማል ነው!” ሊባል እሚችለው!  
 “አይችሉት ድንጋይ ቢሸከሙት ከፍ ብሎ ደረት ይመታል፤ ዝቅ ብሎ እግር ይቆርጣል፣” የምትል ምሳሌያዊ አባባል አለች፡፡ እናም ለአብዛኛው ሰው ኑሮው አይችሉት ድንጋይ ከሆነ በከራረመበት እንዴት ተብሎ ነው፣ ሁሉም ነገር አሸወይና የሚሆነው! እና በዚህ ሁሉ መሀል ዝምታ በማያስፈልግበት ቦታ ‘ዝምታ’ ሲበዛ አሳዛኝ ነው፡፡
ይቺን እዩልኝማ...
ምነው አይመጣልኝ
የፈረሱ ምስል፣
ምነው አይመጣልኝ
የጎራዴው ምስል፣
ምናው አይመጣልኝ
የጠብመንዣው ምስል
የዚህ ቤት ከዚያ ቤት የሚቀር ይመስል!
ግዴላችሁም፤ ዛሬ እነኛን ቤቶች እያመሱ ያሉ መከራዎች፣ ስቃዮች---እኒህኞቹን ቤቶች መጎብኘታቸው የመሆን ወይም ያለመሆን ጉዳይ ሳይሆን የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን መገንዘብ አቅቶን እኮ  ነው፣ ነገራችን ሁሉ ለያዥ ለገራዥ አስቸጋሪ የሆነው!
እናማ..አሸወይና የምትለው ቃል እዛው ሰርግ ዘፈን ውስጥ ትቆይልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1398 times