Sunday, 12 March 2023 11:40

ኢትዮጵያ ከ70 አመታት በፊት ለእንግሊዝ በእርዳታ ቡና መላኳን ያውቃሉ?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  • ኢትዮጵያ ለሆላንድ ከ25 ቶን በላይ ቡና በእርዳታ መላኳንም አንድ ጥንታዊ ደብዳቤ አረጋግጧል


        እ.ኤ.አ በ1953…
የካቲት 1 ቀን ንጋት ላይ…
የእንግሊዝና የስኮትላንድ ምሥራቃዊ የባህር ዳርቻ አካባቢዎች በአስከፊ የጎርፍ አደጋ ተመቱ፡፡ በእንግሊዝ 307፣ በስኮትላንድ ደግሞ 19 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው አስከፊ የጎርፍ አደጋ፣ ሃያ አራት ሺህ ቤቶችን ክፉኛ ሲያፈራርስ፣ ሰላሳ ሺህ ሰዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቀለ፡፡
ስለ አደጋውም ሆነ የአገራቱ መንግሥታት በጎርፉ አደጋ የተጎዱትንና የተፈናቀሉትን ወገኖች ለማቋቋም ስላደረጉት ጥረት መገናኛ ብዙሃን ብዙ ቢሉም፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ለእንግሊዝ መንግሥት በእርዳታ መልክ ስለላከችው ታላቅ ስጦታ በጥቂቱም ቢሆን መወራት የተጀመረው ግን አደጋው ከተከሰተ ከ60 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2012፣ ጥር 18 ቀን፤ ጎልዲንግ ያንግ የተባለው የእንግሊዝ አጫራች ኩባንያ፣ በሊንከን የሽያጭ ማዕከሉ ለእለቱ ቀጠሮ የያዘለትን ጨረታ ደወል አስደውሎ በይፋ አስከፈተ፡፡ ኩባንያው በዕለቱ ለጨረታ ካቀረባቸው ነገሮች መካከል፣ በጨረታ መለያ ቁጥር 345 ለሽያጭ የቀረበው ለዘመናት ታሽጎ የኖረ አንድ ታሪካዊ ጣሳ ይገኝበታል፡፡
“እ.ኤ.አ በ1953 በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የተጎዱትን ለማቋቋም፣ ከግርማዊ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት፣ ለግርማዊት ንግሥት በስጦታ መልክ የተበረከተ፣ እሽግ የቡና ጣሳ” የሚል አጭር የጽሁፍ መግለጫ ሰፍሮበታል ጣሳው፡፡
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ ወደ እንግሊዝ የላኩት ይህ መጠነኛ የቡና ጣሳ፣ በዕለቱ በተከናወነው ጨረታ፣ በ22 የእንግሊዝ ፓውንድ መሸጡን በአንግሎ ኢትዮጵያን ሶሳይቲ ድረ-ገጽ ለንባብ የበቃ አንድ ጽሁፍ ያስታውሳል፡፡
አና ፓርሰንስ የተባለች እንግሊዛዊት የጻፈችው ይህ ማስታወሻ፣ ማርክ ሰርጃንት የተባለ አንድ እንግሊዛዊ እ.ኤ.አ በ2007 ታይም ኤንድ ታይድ በተባለው ሙዚየም በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ላይ በጨረታ ከተሸጠው ጣሳ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሌላ የኢትዮጵያ ቡና ጣሳ ለእይታ ቀርቦ ማየቱንም ይጠቅሳል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ2013 ጥር ወር ላይ ሜልቪን ኢን ዘ ሞርኒንግ በተባለው የሬዲዮ ፕሮግራሙ፣ የጎርፍ አደጋውን 60ኛ አመት ማስታወሻ በተመለከተ በሰራው ዘገባ፣ ኢትዮጵያ ለእንግሊዝ የአደጋው ተጎጂዎች ማቋቋሚያ የላከችውን ቡና ጉዳይ በአጭሩ ጠቅሶታል፡፡
በአንግሎ ኢትዮጵያን ሶሳይቲ ድረ-ገጽ ስለጉዳዩ የጻፈችው አና ፓርሰንስ፣ ኢትዮጵያ ለእንግሊዝ የላከችውን የቡና እርዳታ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ባደረገችው ጥረት፣ ሱዛን ኒኮላስ የተባለች አንዲት እንግሊዛዊት፣ እ.ኤ.አ በ2013 በአባቷ ጋራዥ ውስጥ ስላገኘችው ተመሳሳይ በርሜል መስማቷንም ትጠቅሳለች፡፡
የዚህ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ከላይ የጠቀስናቸውን መረጃዎች ይዞ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ፍንጮችን ለማግኘት ባደረገው ጥረት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከጥቂት ጊዜያት በፊት፣ በሊንክዲን ድረገጹ ይፋ ያደረገውን አስገራሚ መረጃ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ጥንታዊ ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ በ1947 ዓ.ም የጎርፍ አደጋ ደርሶባት ለነበረችው ሆላንድ (ኔዘርላድ)፣ 25 ቶን ከ500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቡና በእርዳታ መልክ መላኳን ያረጋግጣል፡፡
ሚያዝያ 26ቀን 1947 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለጠቅላይ ግምጃ ቤት የጻፈው ይህ ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ለሆላንድ በእርዳታ መልክ የላከው ቡና፣ ከእነ መላኪያውና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ጋር፣ በወቅቱ የገበያ ዋጋ፣ 67,656.30 ብር (ስድሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ሃምሳ ስድስት ብር ከ30 ሳንቲም) እንደሚገመትም ያመለክታል፡፡
 በዚህ ደብዳቤ የተገለጸው የቡና እርዳታ ወደ ሆላንድ የተላከበት ጊዜ፣ ቀደም ብለው የተጠቀሱት የቡና እርዳታዎች ወደ እንግሊዝ ከተላኩበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፣ እንዲሁም የተለያዩ የመረጃ ምንጮች በዚያ ጊዜ በእንግሊዝም በሆላንድም ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋዎች ተከስተው እንደነበር ማረጋገጣቸውን በማጤን፤ በሁለቱ የቡና ስጦታዎች መካከል ግንኙነት ሊኖር እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡
(የኢትዮጵያ ቡና ማህበር 50ኛ ዓመት ልዩ መጽሔት፤ የካቲት 2015)Read 1648 times