Sunday, 12 March 2023 11:48

የማይክል ጆርዳን 3.3. ቢሊዮን ዶላር…

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 በዓለም የስፖርት ታሪክ  የምንግዜም ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኞች የደረጃ ሠንጠረዥን አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ማይክል ጆርዳን በ3.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚመራ ታውቋል። ማይክል ጆርዳን ቅርጫት ኳስ ስፖርትን ካቆመ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል። በዓለም የቅርጫት ኳስ ስፖርት በፈጠረው ተፅዕኖ ተስተካካይ የለውም። በስፖርት ትጥቅ በኢንዱስትሪው ስሙ የንግድ ምልክት ሆኖ ቆይቷል።  የዓለማችን 50 ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኞችን የደረጃ ዝርዝር ያወጣው ስፖርቲኮ (Sportico) የተባለ ተቋም ነው። በስፖርት ዘመናቸው ከደሞዝ፤ ከተለያዩ  የቦነስ ክፍያዎች፤ ከማስታወቂያ ከስፖንሰርሺፕና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የሰበሰቡት ተሰልቷል። ታዋቂው የቢዝነስ መጽሔት ፎርብስ እና ስፖርት ኢለስትሬትድ የሰሩ ጥናታዊ ዘገባዎች ተዳሰዋል። 50ዎቹ ታላላቅ ስፖርተኞች  ባለፋት 40 ዓመታት በድምሩ ያገኙት ገቢ ከ45.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። ከ1-50 በወጣው ደረጃ ላይ ከሰፈሩት ስፖርተኞች 62 በመቶው አሜሪካዊ ዜግነት ቢኖራቸውም 17 የተለያዩ አገራትን የሚወክሉና በ9 የስፖርት አይነቶች ስኬታማ የሆኑ ስፖርተኞች ተወክለዋል።  በደረጃ ዝርዝሩ ላይ 13  የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ተጨዋቾች የገቡ ሲሆን ከሴት ስፖርተኞች በብቸኛነት የተጠቀሰችው በ600 ሚሊዮን ዶላር ገቢ 38ኛ ደረጃ የተሰጣት የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቿ ሴሪና ዊልያምስ ናት።
በምንግዜም ከፍተኛ ተከፋይ  ስፖርተኞች የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ከማይክል ጆርዳን በመከተል 3 አሜሪካዊ የጎልፍ ስፖርተኞች የተቀመጡ ሲሆን ታይገር ውድስ በ2.5 ቢሊየን ዶላር፤ አርኖልድ ፓልመር በ1.7 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም ጃክ ኒኮላስ በ1.63 ቢሊየን ዶላር ገቢያቸው ነው። ፖርቱጋላዊው የእግርኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ1.58 ቢሊዮን ዶላር፤ አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ተጨዋች ሌብሮን ጀምሥ  በ1.53 ቢሊየን ዶላር ፤ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በ1.48 ቢሊየን ዶላር፤ አሜሪካዊው ቦክሰኛ ፍሎይድ ሜይዌዘር በ1.41 ቢሊዮን ዶላር፤ ስዊዘርላንዳዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሮጀር ፌደረር በ1.38 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም አሜሪካዊው ጎልፈኛ ፊል ሚክሊሰን በ1.36 ቢሊየን ዶላር ገቢያቸው እስከ 10ኛ ደረጃ አከታትለው ይዘዋል።
ማይክል ጄፍሪ ጆርዳን ወይንም በአጭሩ MJ በሚለው ስሙ ይታወቃል። የአሜሪካን ቅርጫት ኳስ ከ1980ዎቹ አጋማሽ አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተወዳጅነት እንዲያተርፍ በተጫወተው ሚና ከበሬታ አግኝቷል። በተጨዋችነት  ዘመኑ በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ላይ ለ15 የውድድር ዘመናት ሲሳተፍ ከቺካጎ ቡልስ ጋር 6 የሻምፒዮንነት ክብሮችን ተጎናጽፏል። የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ማህበሩ በድረገፁ ስለሱ የህይወት ታሪክ ባሰፈረው ማስታወሻ የምንግዜም ምርጥ ቅርጫት ኳስ ተጨዋች በሚል  አድንቆታል።
ከሁለት ሳምንት በፊት 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከበረው ማይክል ጆርዳን MAKE-A-WISH ለተባለ የበጎ አድረሰጎት እንቅስቃሴ 10 ሚሊዮን ዶላር የለገሰ ሲሆን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ  በአንዴ የተሰጠ ከፍተኛ ድጋፍ ሆኖ ተመስግኖበታል። በሰሜን ካሮሊና በሚገኝ ዮኒቨርስቲ በካልቸራል ጂዮግራፊ ዲግሪ ያገኘ ሲሆን በፕሮፌሽናል ቅርጫት ኳስ ባይሳካለት ኖሮ የአየር ትንበያ  ባለሙያ ሆኖ የመሥራት እድል እንደነበረው በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለምልልሱ ተናግሯል።
በስፖርት ታሪክ በንግድና ስፖንሰርሺፕ በከፍተኛ ደረጃ የተሰራበት ታላቅ ስፖርተኛ ሆኖ ይጠቀሳል። በስፖርቱ በቆየባቸው 38 ዓመታት ከታላላቅ ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት ችሏል። ናይኪ፤ ኮካኮላ፤ ቼቭሮሌት፤ ጋቶርዴና ማክዶናልድ የሚጠቀሱ ናቸው።
በ1984 እ.ኤ.አ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከናይኪ ኩባንያ ጋር የስፖንሰርሽፕ ውል ሲፈራረም በዓመት 500ሺ ዶላር ክፍያ ለ5 ዓመታት ያገኘ ነበር። በ2022 እ.ኤ.አ ላይ ከታላቁ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ጋር ያለው የስንሰርሽፕ ውል ዓመታዊ ገቢው 150 ሚሊዮን ዶላር ሆኗል። በናይኪ በስሙ “Air Jordan” ብሎ በሚያመርተው ስኒከርና ተያያዥ ንግዶች ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ አግኝቷል።
ከቅርጫት ኳስ ስፖርት ደመወዝ፣ ከቦነስ ክፍያዎችና ሌሎች ሽልማቶች ከሚያገኛቸው ገቢዎች ባሻገር በሌሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችም ተሳክቶለታል። በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ቻርሌቴ የተባለ የቅርጫት ኳስ ክለብ በ150 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ባለቤት ሆኗል። በአሁኑ ወቅት የክለቡ ዋጋ ተመን ከ1.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። ጆርዳን በሚለው ስሙ የንግድ ምልክትነት ከ4.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ እያንቀሳቀሰ ይገኛል። በሞተር ስፖርትና በሜጀር ቤዝ ቦል ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች የባለቤትነት ድርሻ ያለው ሲሆን በመኪና ሽያጭ ዘርፍና  በመላው አሜሪካ ከ5 በላይ ግዙፍ ሬስቶራንቶችን እያስተዳደረ ነው። በበጎ አድራጎት  ስራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ በሰሜን ካሎሪና ከትምህርትና ከጤና ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ፤ ክሊኒኮችን  በመገንባትና ለተለያዩ ግብረ-ሰናይ ተቋማት በመገንባትና በማቋቋም እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ ምስጋናን አትርፏል።


Read 870 times