Sunday, 12 March 2023 11:50

ሐኬተኛው መድበል፤ ‹‹ዕውነት ማለት የእኔ ልጅ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(3 votes)

 መነሻ
መቼም በድሉ ዋቅጅራ (ፒ.ኤች.ዲ.) ይኼንን ሃቲት ሲያነብ ‹‹የሀያሲ ነፍስ በየምናምንቴው ብናኝ ካደፈ፣ የብእሩን እድፍ ከቀለሙ መለየት ያስቸግራል›› እንደማይል አምናለሁ። ከልብ ሞልቶ የሚፈስ በአፍ ይወጣልና፣ አንደበቴን ለውረፋና ለጉንተላ እያሰለጠንኩና እያሴየጠንኩ እንዳልሆነ በቅድሚያ መናዘዝ አለብኝ…
ሀሳብ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ዘይቤ፣ ተምሳሌት የማንም ነው፤ ቢሆንም ሥነ-ግጥም የመጣን ሀሳብ ሁላ አይናዘዝም፤ አይለፍፍም፤ ሥነ-ግጥም ልጬኛና ብሉይ ነው፤ ዜናነትንና ዘገባነትን ይጠየፋል። የቸከ ሂደትን ወግድ ይልና ሀሳብ እንካችሁ ይላል - ሥነ-ግጥም፤ አልባሽ አጉራሽ አይደለም፤ አንባቢ ቃር እስኪይዘው መፈትፈትና ማጉረስ የቤት ሥራው ባይሆን መልካም ነው፤ አንባቢ የምግብ አሠራር ሂደቱ ላይ የእራሱን ድርሻ እንዲያዋጣ ኃላፊነት የሚጥልበት መሆን አለበት። ያን ጊዜ ታዲያ ነቢይ መኮንን ‹‹የዕድሜ ዕቁብ›› እንዳሉት ሁሉ Poetry for poetry ቢባልለት ደግ ነው ባይ ነኝ!
አቃቂረኛ ሆኜ ሳይሆን፣ የእኔ ዘመን ገጣሚ የብዙ ጣጣዎች ተጠቂ ነው፤ በመመጻደቅና በስንፍና ጣጣዎች ውስጥ ‹‹እየገጠምኩ ነው›› ብሎ በተአብዮ ተጀቡኖ ብዕር ካነሳ ነገር ተበላሸ፤ በመጨረሻ እውነትና ሥሜት ይሳከሩበትና ሥነ-ግጥምን ያካልባታል፤ ሌላው ቀርቶ የኖርነውን፣ አለያም ተጫምተን ስለጣልነው ጫማ ታሪክ ሊነግረን ይዳዳውም ይሆናል፤ ትልቁ ነጥብ ውጥን ነው፤ ለግብ አለመቸኮል፣ ወይ የጅማሬንና የፍጻሜን ተዋረድ አለማዛነቅ፤ ገጣሚ እንደ ሰነፍ ሴት ወጥ ለ‹ይድረስ› የተድፋፋ ሀሳቡን ለንባብ ከማምጣቱ በፊት ከቁሌት እስከ መበላት ድረስ የሚኖረውን ሂደት በዓይነ ቁራኛ መከታተል አለበት። እንዲህ ያለን ድክመት ለማረም ግጥምን ደጋግሞ መፈተሽና መገምገም ተገቢ ነው፤ ቢያንስ ቢያንስ ሀሳብን ሳይሆን ንባብን የማረም ዕድል ሊፈጠር ይችላል፤ የግጥም ንባብን፣ ቋንቋን፣ የፊደል ግድፈትን፣ ዘይቤን፣ አያያዥ ቃላቶችን፣ ምትና ምጣኔን በፍተሻ ጊዜ ማረም ግጥምን ለማብላላትና ለማጎምራት ይረዳል ብዬ አስባለሁ።        
…እንሆኝ ዳሰሳው…
ውበታም ስንኞች
ገጣሚው እንኳን በዚህ ዘንድ የሚታማ አይመስለኝም። በአምሥቱም የግጥም መድበሎቹ ላይ ውበትን (aesthetic) ሳያጓድል የግጥም ሀሳቦቹን ያሰፈረ ነው ብሎ መናገር ድፍረት አይደለም። በድሉ ዋቅጅራ በውበት ረገድ እንከን አይወጣውም፤ እንደውም ደበበ ሰይፉን (ደቤ ነፍሴን) ያስታውሰኛል እንጂ። ደበበ አልሞተም የምለው በእርሱ ምኽኛት ነው። እርሱም እንደ እኔ ደቤን እንደሚወደው አልጠራጠርም፤ በግጥሞቹ ውስጥ ደበበ ሰይፉን አሻግሬ አያለሁ (ኩረጃ ማለቴ ሳይሆን) የቃላት ጠረባው፣ ቃና ቅመማው፣ ሥነ-ውበቱ፣ ገላጭ ቃላትና ሐረጋት መረጣው፣ ምጣኔው…የደበበ ሰይፉን ዓይነት ዘዬ ይላበሳል። በአጭሩ፣ በድሉ ዋቅጅራ ‹‹ከቃል መርጠው ለኪነት›› የዘለቀው ገጣሚ እንደሆነ ይሰማኛል።   
በዚህ መድበል ውስጥ የተካተቱ ውበታም ስንኞችን በጥቂቱ እንኳን እንጥቀስ ብለን ጊዜ ከምንፈጅ (ስፍር የላቸውምና - መድበሉ ይቁጠራቸው) እያልን ወደ ሌላ ጉዳይ እንሸጋገር…    
በተሃ ስንኞች
በተሃ ጠጅ (አንዳንድ አካባቢ ‹ብርዝ› ይባላል) ሆድ ከመንፋት እና ለሽንት ከመዳረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ግጥም በለብታ ተነቦ የሚታለፍ ሳይሆን ነፍስን ኮርኩሮ ለዘለዓለም ሕያውነቱ የማይስተጓጎል ጥበብ መሆን አለበት። ለአብነት ያህል፣ ከገጽ [53] ላይ ‹‹እስስታዊነት›› የተባለ በተሃ፣ ያልተብላላ፣ የደነበሸና፣ እንደዜና ተነቦ የሚታለፍ - ዘገባ ወይም ለብታ የሆነን ግጥም እናገኛለን። ግጥሙ አንዳች አዲስ ነገር ለተደራሲ ጀባታ አይልም፤ ነጮች ለጥቁሮች ጥሩ እንደማያስቡ በግጥም መናገር መባዘን ነው። ብሎም በገጽ [83] ላይ ‹‹አበሻና ትዝብት›› የተሰኘ፣ የግጥምን ልጬኛነት የሚበርዝ ግጥም እናገኛለን።
ፒላር ኦገስቲን ሊላች (2007) ባቀረበው መጣጥፍ The evocative character of poetry, its imagery, its appeal to feelings and personal experience make it very interesting and enjoyable. Poetry deviates from normal language in that it has some unusual ways of ordering words, or it attributes particular, imaginative meanings to words or combines sounds in a musical, non-ordinary way (phonological, lexical, syntactic, semantic, graphological, and style deviation ይለናል፤ ኪላንደር (2011) የተባለ ጥናት አቅራቢ ደግሞ the aesthetic function of poetry leaves room to a deeper existential one እንዲል ገጣሚ ከሥነ-ውበት በተረፈ ከግል ኑባሬአዊ ሥሜቱ ቢነሳም/ከውስጥ ወደ ውጪ ቢሰናኝም የቸከ መሆን የለበትም፤ እንደ ፈጣሪ ከአዳም ጎን ገሽልጦ ለአዳም እንደመፍጠር ዓይነት ድካም ነው ትርፉ።
አንድን ግጥም ‹በተሃ ግጥም› ነው የሚያስብለው የጭብጥ/የሀሳብ ጉዳይ ነው፤ ቋንቋ፣ ተምሳሌትና ፍካሬ በበኩላቸው ታላቅ ሚና አላቸው። ግጥም በባሕርይው ልጬኛና ብሉይ ነው። የመጣ ሀሳብ ሁላ አይጻፍም። ሥነ-ግጥም ከአላባዊያን ይዘላል፤ ከተመንና ከሕግጋት ያልፋል፤ ቋንቋ፣ ጭብጥ፣ ሥነ-ውበት፣ ፍካሬ፣ ሙዚቃዊነት፣ ስዕላዊነት፣ ምት፣ ምጣኔ… ሥነ-ግጥምን ለመግለጽም ሆነ ለመስፈር በቂ አይመስሉኝም፤ ይኼ ነው ተብሎ የተሠፈረ መለኪያ ያለውም አይመስለኝም፤ ምናልባት ከተደመጠና ከተነበበ በኋላ ለዘለ-ዓለም የማይረሳ መሆን ያለበትም ይመስለኛል፤ ነፍስን የማተራመስ አቅም ያለው ቢሆንም መልካም ነው፤ እንደ ዜና ተነቦ የማይረሳ፣ ከመዘገብ አልፎ ሕይወትና ዓለምን በሥነ-ውበት መፈከር የሚችል…‹‹ቤት ያፈራው ፍቅር›› እንዲል በረከት በላይነህ፡፡ በተደራሲ ሕዝብ ዘንድ በታሪክ፣ በተረት-ተረት፣ በቀልድና በሥነ-ቃል መልክ የሚታወቅን ሀሳብ ‹‹ግጥም ነው›› ብሎ ማቅረብ አውራነቱን ማራከስ ነው።  
በምትኩ የዚህን ግጥም ተቃራኒ በገጽ [58] ላይ ‹‹አቦ አበሽ ያውቅበታል›› በማለት የአበሻን የፍቅርና የዕውነት/የአለኝታ ጥግ አመላክቷል። በዚህ መድበል ለውልቃት ይዳርገኝና መልሶ ደግሞ በ‹‹የወይራ ሥር ጸሎት›› ወጌሻ ይይዘኛል። በገጽ [95] ‹‹አስታምምሻለሁ›› በማለት ስብራቴን ይጠግናል። ነፍሴን በተስፋ እና በእጦት መካከል ይቸነክራታል። ሲሻው ደግሞ በ‹‹የተስፋ ክትባት›› ‹‹ልጨብጠው አመመኝ›› ግጥሙ እንዳልሞት እንዳልድን አደረገኝ! በ‹‹የራስ ምስል›› ‹‹ጥፊ ልፈልግሽ›› በማለት የፍለጋንና ከማግኘት ይልቅ የማጣት/የመናፈቅ ውበትን አሳይቷል።
አልቦ-ተስፈኛ ስንኞች
ሥነ-ግጥም ሞራላዊ ልዕልናን ሰብዐዊነትን፣ ፍቅርን… ከመስበክ እስከ ብርሃንና ተስፋ ማስጨበጥ ሠርክ ትፋጭራለች። በተቃራኒው፣ የዚህ መድበል ገጣሚ ተስፋ-ቢስነትን የሰበከበት ትልቁ ግጥም ከገጽ [21] ላይ ‹‹ሚጥዬ›› በሚል ርዕስ ተቀምጧል። ግጥሙ እዚያ ላይ ለተሳለች ‹‹ሕጻን›› ገጸ-ባሕርይ ምን ዓይነት ትምህርትንና ተስፋን ይሰጣታል? ብሎ ለጠየቀኝ ‹በተስፋ አቀበት ላይ ፊቷን ወደ ኋላ አዙራ እንድትምነሸነሽ ይጋብዛታል› ባይ ነኝ። እመቀመቅ።
እንግዳውስ እስካልተሸነጋገልን Hopeless romanticism በመድበሉ ጎልቶ ይታያል፤ ግሪካዋይ እንደሚሉት missing the point ዓይነት ተፋልሶ፡ ከርዕሱ የተሳከረ መድበል ነው፤ ‹‹ዕውነት ማለት የእኔ ልጅ›› ብሎ በሠየመ ቅጽበት ለልጁ ዕውነታን የማይናገር ሆነብኝ፤ ፍቃደ አዘዘ ‹‹ጩኼት›› ብሎ በሠየመው መድበል የሚጮኹ ሀሳቦችን እንዳጨቀው፣ ደበበ ሰይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ/የብርሃን ፍቅር›› በሚል መጻሕፉ ድባቴውን፣ እርካታና ጣመኑን እንዲሁም ጨረቃንና ጸሐይን ማፍቀሩን የሚገልጹ እልፍ ግጥሞችን እንዳጨቀ ሁላ የዚህኛው መድበል ርዕስ፣ የውስጥ ግጥሞችን ቢወክል ምንኛ ደስታ በሸመትሁ፤ አልሆነም ግን!
ብዙ ሳንጓዝ የዚህን ግጥም ተጻራሪ/ተቃራኒ ከገጽ [29] ላይ ‹‹ትውልድ አለት ቢሆን›› ተብሎ እናገኘዋለን። የጭብጡ ክብደት ብሎም መልዕክቱ አንባቢ ዘንድ ደርሶ የሚፈጥረው ሚና ዘርፈ-ብዙ ነው ብዬ አምናለሁ። ገጣሚው በምናብ/በቅዠት የወለደው ቢመስልም፣ ሀሳቡን ግን ሸጋ ሆኖ አግኝቼአለሁ፡፡ ከዚህ ሌላ በገጽ [26] ላይ የሠፈረውን ግጥም ማንሳት ተገቢ ነው። ግጥሙ ከተስፋ አስቆራጭነቱ በተረፈ ዘገባነት/በተሃነትም ይጠቀልለዋል።    
ፌዘኛ ስንኞች
አንድ ገጣሚ የግድ የደበበ ሰይፉን ዓይነት ‹‹እኔና ጨረቃ››፣ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅንን ‹‹መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ›› ወይም የበዕውቀቱ ሥዩምን ‹‹የበረኸ ጠኔ›› ዓይነት ግጥም ያስነብበን ተብሎ ሕገ-ደንብ ሊጣልበት አይችልም፤ ቢሆንም ፈር ስቶ ማላገጥ የለበትም ባይ ነኝ፤ ከሆነም ሥነ-ግጥምን ያረክሳታል። ነጥቡ ጥልቅ የሥነ-ልቡና ጣጣ ነው፤ ማፌዝ ‹‹እየገጠምኩ ነው›› ብሎ በመታበይ የሚከሰት የሥነ-ልቡና ደዌ ሊሆን ይችላል። ነገሩ ከተደጋገመ እንደ too many cook spoil the broth ዓይነት የአዋቂዎች መብዛት የሚያስከትለውን መዘዝ ከተፍ የሚያደርግ መሆኑ እሙን ነው።
To love, to suffer, to think is to seek poetry ባይ ነው ኦስካር ዋይልድ፤ ሥነ-ግጥምን አስመልክቼ እቸገራለሁ በግሌ፤ A scrummy wine, my soul has ever sipped, yet yearning to sip at the vein sipping, too, is Poetry. I wondered the nature not as Poetry. Poetry has to be blooming than floras, lightening than lightening, Blanche than bright. A good poetry is not only noted with rhythm, meters, diction, but also merits poetry which praise worth its eminence. Poetry for poetry! ብዬ በልቤ ሕግ አኑሬአለሁና ይጣምነኛል።  
የዚህ መድበል ገጣሚ ፌዘኛ የሆነበትን አንድ ግጥም ልጥቀስላችሁ - ከገጽ [22] ላይ ‹‹አያችሁ ያንን ሬሳ›› ይላል። ይኼንን ለማለት ገጣሚ መሆን አያሻም፤ በዚህ ዓይነት ውስጥ የሚስተዋል ገጣሚነት ትርፉ ድካም ነው። ሌላው፣ ገጽ [79] ላይ የሠፈረውን ግጥም መጥቀስ ተገቢ ነው። በእነዚህ ግጥሞቹ ታክቶ ያታክተናል፤ ታዲያ ግጥም ሀሳብ አመንዥኮ፣ ወይም ሀሳብ ጸንሶ፣ ወዲህ ደግሞ ሀሳብ ወልዶ አሳድጎ ተማሪ ቤት የሰደደበትን ሂደት መለፍለፍ የለበትም፤ ግጥምና ገጣሚ ሀሳብ ይውለዱ፤ አንባቢ ሀሳብ ‹እንትፍ› እያለ ያሳድግ፤ እንግዳውስ ገጣሚ ተግቶ ካፌዘ የግጥምን ክብርና ንጽሕና ማግሰስ ነው ትርፉ። ለዚህም በመድበሉ ከገጽ [72] ላይ እራሱ ገጣሚው ምላሹን ያስቀመጠ ይመስለኛል። እንደዚህ…
‹‹ደፋር እንደጻፈው፣ የጋዜጣ ግጥም፣
ምስጢር አልባ - ተራ፣ ውበትሽ የማይጥም፤›› በማለት።
ከላይ የተዘረዘሩ ግጥሞች ውበታቸው ተጨምቆ የፈሰሰ፣ ብሎም ቁምነገር ያጡ ሆነው አግኝቼአለሁ።
ዘባተሎ ስንኞች  
ሰሎሞን ደሬሳ እንደሚሉት ‹የወለሎ ግጥም›፡- ግጥም የስሜት፣ የቋንቋ፣ የቃላት፣ የሐረግና የስንኝ ውቅር ሊሆን እንዲሁም ‹የመሆን/የመገኘት ግጥም› ሊሰኝ ይችላል፤ ገጣሚ ደግሞ የግሉን ድባቴ፣ ቅያሜ፣ ስጋት፣ መሻት…ሊሰናኝ ይችላል ማለት ነው/Impressionism። ከሥነ-ግጥም ጠባዮች አንዱ ቁጥብነት ነው። በቃላት አመራረጡ፣ በገላጭ ሐረጋትና ስንኝ አጠቃቀሙ ገጣሚ የተንዛዛ መሆን የለበትም። ግሪኮች የማጭበርበር ቅጥፈትን Patricio-Principe/begging the question/ በማለት ከተፋልሶዎች አንዱ እንደሆነ ይደነግጋሉ፤ መነሻ ላይ የተናገሩትን እየደጋገሙ መደስኮር ነው ይኼ ክፍተት። ገጣሚ በመግቢያ ላይ ያተተውን ሀሳብ መሀል ደርሶ፣ አለያም መጨረሻ ላይ እየደጋገመ አንባቢን ማሰልቸት የለበትም፤ ግጥም ዘባተሎ የሚሆንበት ጊዜ ሀሳብን ከመደጋገምና ግልጥልጥ አድርጎ ለአንባቢ ከማድረስ አንጻር ሊሆን ይችላል፤ ሀሳብን ግልጥልጥ አድርጎ የሚሰናኝ ገጣሚ ወደ መገሰጽና ማብራራት ሊያንጋድድ ይችላል፤ ምክርንም ሆነ ሀሳብን አንባቢ ፈትሾ ቢደርስባቸው መልካም ነው፤ ግጥም የሚያልቅበት/የሚቋጭበት ዕድሜ አለው፤ አለያ የተንዛዛ፣ የሚመክር፣ የሚያብራራና የሚሰብክ ግጥም ቅኔያዊነት ይጣላዋል፤ ከዚያ ዝብዝብ እንጂ ግጥም ላይሰኝም ይችላል፤ እንዲሁም ሀሳብ መደጋገምና ፍዝ ገለጻዎችን ማብዛት መንዛዛትን ሊያስከትል ይችላል፤ በዚህ መድበል ‹‹ዕውነት ማለት የእኔ ልጅ›› የተሰኘው ግጥም ከቅኔአዊነት ይልቅ መምከርና እግር ሥር አስቀምጦ ማስተማርን ይመስላል፤ የተንዛዛም ጭምር ነው።
የዘባተሎነት ምንጮች በሌላ መልኩ ደግሞ የአያያዥ ቃላትና የዘይቤ ድግምግሞሽ ሊሆን ይችላል፤ ገጣሚ የሀሳብ ፍሰትን እውን ለማድረግና መሰልቸትን ለመቀነስ በማለም አያያዦችን ሊጠቅስ ይችላል በስኝት ወቅት፡ እንደ፣ እና፣ ስለዚህ፣ ታዲያ፣ አንቺዬ፣ ዳሩ ግን፣ ስለሆነም…የመሳሰሉትን፤ በዚህ መድበል አያያዦች የዜማ መሸራረፍንና የምጣኔ መስተጓጎልን ሲያስከትሉ ይኖራሉ፤ አንባቢ አንዳንድ ግጥሞችን በነጻነት እንዳያዜማቸው እንቅፋት ሆነዋል ብዬ እሰጋለሁ።                
ማጠቃለያ
ገጣሚው በ‹‹ዕውነት ማለት የእኔ ልጅ›› ተስፋው ቢደበይም ብዕሩ ጮሌ ነው፤ እንደ እባብ ብልጥ፡፡ በተቀሩት፡- (ፍካት ናፋቂዎች፣ የተስፋ ክትባት፣ የወይራ ሥር ጸሎት እና የራስ ምስል) ላይ አፈር ልሶ የሚነሳ፣ የእባብ ሬሳ ሆኖ አገኘሁት።


Read 848 times