Saturday, 18 March 2023 20:01

New Leaf …. አዲስ ቅጠል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

 በአለም አቀፍ ደረጃ ትዳር ከመሰረቱ ጥንዶች መካከል 15% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ የማግኘት ወይንም የመውለድ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡
ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት የሚለው ምርቃት ዛሬ ዛሬ የለም የለም ምድርንም የምትችለውን ያህል እንጂ ከሚገባት በላይ አታሸክሙአት ወደሚል የዞረ ይመስላል፡፡ በእርግጥ ይህ አባባል የሰው ልጅ ተፈጥሮ ልትቋቋመው በላይ ከሆነ እና የኢኮኖሚው ድጋፍ አስቸጋሪ ከሆነ የተወለደውም ማደግ አይችልም ስለዚህ ወልደን እንዲቸገር ከማድረጋችን በፊት ዶ/ር ወለላ አለሙ  እናስብለት፡፡ የመጣበትን አለም በደስታ ከመቀበል ይልቅ እንዲያማርር አናድርገው፤ በትምርቱ፤ በጤናው፤ በምጣኔ ሀብቱ በሁሉም ረገድ በደስታ የሚኖርባት እንጂ አለምን እንደተቀላቀለ ስለ ችግር እንዲያስብ እናድርገው የሚል እሳቤ ያለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ይሁን ምን የመዋለድ ተፈጥሮ ያለው ሰውም ሆነ እንስሳ ዘሩን እየተካ ካልሄደ አለም አንድ ቦታ ላይ ጉዞዋን ታቆም ይሆናል የሚል ስጋት አለ፡፡ ተፈጥሮም በየግለሰቡ ጥያቄዋን የምታቀርብ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች በትዳርም ይሁን በየትኛውም መንገድ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ልጅ እናፈራለን የሚለው ትልቁ እሳቤአቸው ነው፡፡ ይህ በተፈጥሮአዊው መንገድ ካልተሳካ በሚል የሳይንስ አዋቂዎች በተለያዩ መንገዶች ልጅ እንዲወለድ የሚያስችሉ ዘዴዎችን ፈጥረው እነሆ በስራ ላይ አውለዋል፡፡
በሳይንሳዊ መንገድ ከሚሰጡ የተለያዩ ሕክምናዎች በተጨማሪ በላቦራቶሪ የማዳቀል ስራ ተካሂዶ ልጁን ወደ እናቱ ማህጸን በማስገባት ጊዜውን ጠብቆ እንዲወለድ የማድረግ ሂደቱ እነሆ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ክሊኒኮች እየተከፈቱ በማስለመድ ላይ ናቸው፡፡ ምናልባት እስከአሁን ድረስ በሀገራችን ያልተጀመረውና ከሌሎች ሀገሮች የምንለይበት አንድ ነገር የማህጸን ኪራይና የዘር ፍሬና የእንቁላል ልገሳ የሚባለው አሰራር አለመኖሩ ነው፡፡
ለዚህ እትም በአዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ከሚገኘው ኒው ሊፍ የመካንነት ህክምና ክሊኒክ በመሄድ አንድ ሐኪም እንግዳ አድርገናል፡፡ እንግዳችን ዶ/ር ወለላ አለሙ በኒው ሊፍ የመካንነትና የስነተዋልዶ ሕክምና ማእከል ውስጥ የጽንስና ማህጸን እና የመካንነት ህክምና እስፔሻሊስት በመሆን በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ከአሰያየሙ ብንነሳ ዶ/ር ወለላ እንደገለጹት New Leaf (ኒው ሊፍ) ማለት አዲስ ቅጠል ማለት ነው። ልክ አዲስ ቡቃያ ከምድር ሲወጣ አዲስ ቅጠል እንደሚያበቅል ወይንም ደስ የሚል ነገር እንዳለው ሁሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ ልጅን ለማግኘት ሲሹ ቆይተው ነገር ግን ሳይሳካላቸው ቀርቶ ተቸግረው ከቆዩ በሁዋላ ልጅን የማርገዝ ወይንም የመውለድ እድሉ ሲገጥማቸው ሕይወታቸው እንደ አዲስ ቅጠል እንደሚለመልምና በደስታ ህይወታቸውን እንደሚቀጥሉ የሚያሳይ ትርጉዋሜ ያለው ነው፡፡
ኒው ሊፍ ከተቋቋመ ወደ ሁለት አመት ገደማ ሆኖታል፡፡ በእርግጥ የመካንነት ስራውን ጠንከር ባለ መንገድ መተግበር ከጀመረ አንድ አመት ሆኖታል። በዚህ ሂደቱም የታካሚዎችን ሁኔታ የመለየት ስራዎች ሲተገበሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም በመድሀኒት ሊታከሙ ይችላሉ ወይንስ ወደ (IVF) የላቦራቶሪ ሕክምና መመደብ አለባቸው የሚለው እየታየ ህክምናው ሲሰጥ የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡ በውጭው አቆጣጠር 2021/ ዲሴምበር ግን ወደ አይቪኤፍ ሕክምናው በቀጥታ መሸጋገር ተችሎአል፡፡
የህብረተሰቡን የመታከም ፍላጎት ለመገመት በጣም የሚከብድ ነገር ነበር ያጋጠመው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ያህል ፍላጎት ያላቸው ባለትዳሮች አሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በጣም ብዙ ጥንዶች ሕክምናውን ለመከታተል ወደክሊኒካችን ይመጣሉ። በቀን እስከ ሀምሳ እና ስድሳ ሰው ሕክምናውን ፈልጎ እንደሚመጣ እና ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት ወረፋ እየጠበቁ ይታከማሉ ብለዋል ዶ/ር ወለላ፡፡ ከሁኔታው መረዳት የቻልነው ከአሁን በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት የህክምና ተቋማት ስላልነበሩ ብዙ ባለትዳሮች ሲቸገሩ መቆየታቸውን ነው፡፡   
በአለም አቀፍ ደረጃ ትዳር ከመሰረቱ ጥንዶች መካከል 15% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ የማግኘት ወይንም የመውለድ ችግር ወይንም መካንት ይገጥማቸዋል፡፡ መካንነት ማለት በሕክምናው አገላለጽ ባልና ሚስት ለአንድ አመት ያህል ካለምንም መከላከያ በቂ የሆነ የግብረስጋ ግንኙነት እያደረጉ ልጅ መውለድ ካልቻሉ የመካንነት ችግር አለ ይባላል፡፡ ይሄ ማለት ግን ወደ ፊት በምንም አይነት ልጅ አይወልዱም ማለት ሳይሆን የህክምና እገዛ ከተደረገላቸው ልጅ መውለድ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት፡፡
ለመካንነት ሊያጋልጡ ይችላሉ ወደ ተባሉ ምክንያቶች ስንመጣ አንዱ የማህጸን ቱቦ መዘጋት ነው፡፡ ይህ ከሆነ የወንድ የዘር ፍሬን እና የሴት እንቁላልን የሚያገናኘው መስመር እንደተዘጋ ይቆጠራል፡፡ ለዚህም በጣም የተለመደው ምክንያት የማህጸን ኢንፌክሽን በቱቦው ላይ ጠባሳ ስለሚጥል ቱቦው እንዲዘጋ ያደርጋል፡፡ የእንቁላል ቁጥር ማነስ አንዱ ምክንያት ሲሆን አንዲት ሴት ስትፈጠር ይዛ የምትወለድውን የእንቁላል መጠን በየጊዜው ስለሚቀነስ እስከ ሰላሳ አምስት አመት ድረስ ለእርግዝና የሚያበቃ እንቁላል ይኖራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚያ በሁዋላ የእንቁላል ጥራቱም ብዛቱም ስለሚቀንስ ለእርግዝና መታወክ ምክንያት ይሆ ናል፡፡ ከዚህ ውጭ እርግዝናን ሊከለክል የሚችል የማህጸን እጢ ካለ እንደ አንድ እንቅፋት ይቆጠራል። ስለዚህ ሴቶች በቱቦ፤ በእንቁላል እና በማህጸን ችግር ምክንያት ልጅ ለማርገዝ ይቸገራሉ፡፡
በወንድ በኩል ደግሞ የወንድ ዘር ቁጥር ማነስ፤ እንቅስቃሴው፤ ወይም ጥራቱ ችግር ሲኖርበት ወይም ግንኙነት በተገቢው ሁኔታ መፈጸም አለመቻል የሴት እንቁላል ጋ ደርሶ እርግዝናን መፍጠር የማያስችል ትልቅ ችግር ነው፡፡ የወንዶቹ የዘር ቁጥር መቀነስ ምክንያት ብዙ ሲሆን በተለይም ከተፈጥሮ ጋር የሚያያዘው የተለመደ ነው፡፡ ዶ/ር ወለላ እንደገለጹት የወንድ ዘሩ ሳይቀንስ ከሚመረትበት  ቦታ በስነስርአት ቁጥሩም እንቅስቃሴውም ጥሩ ሆኖ በበቂ ሁኔታ ቢፈስ ነገር ግን ወደ ውጭ የሚወጣበት መስመር ከተዘጋ ፈሳሹ ላይ የወንድ ዘር አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ይህን ከሚያመጡት ምክንያቶች መካከል ልክ እንደ ሴቶቹ ወንዶቹም ኢንፌክሽን ከነበራቸው የመስመር መዘጋቱ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሌላው በወንዶች በኩል ያለው ችግር የማምረቻው ቦታ የማምረት አቅሙ ያነስ ከሆነ ወይም የሆርሞን መዛባት ጭምር ለወንዶች የዘር ፍሬ ለመቀነስ በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በወንዶች በኩል በህክምናው አለም ብዙ ጊዜ የማይታይ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥም ተፈጥሮአዊ ችግር አለ፡፡ እሱም አንድ የወንድ ልጅ በእናቱ ማህጸን ውስጥ እያለ ዘር የሚያመርቱት ሁለቱ ፍረዎች በሆዱ ውስጥ ሆነው ይፈጠሩና ከዚያ በሁዋላ ቀስ በቀስ እየወረዱ …እየወረዱ በቦታቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ ወደታች ወርደው ካልጨረሱ ወይንም በቦታቸው በተገቢው ጊዜ ካልደረሱ ወንዶች የዘር ፍሬ ማምረት አይችሉም፡፡ ይህም በሆድ እቃቸው ውስጥ ከመቆየት የተነሳ ሙቀትን የመቋቋም አቅም ስለማይኖራቸው ምንም ጥቅም ሳይሰጡ ባሉበት ሆነው ሊባክኑ ይችላሉ፡፡ በሆድ ውስጥ ያለው ሙቀት በውጭ ካለው ሙቀት እስከ ሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርስ ከፍ ይላል፡፡ ስለዚህ ለወንድ ዘር መመረት አመቺ ነው የሚባለው ውጭ ያለው ቅዝቃዜ እንጂ በሆድ ውስጥ ያለው አይደለም፡፡
የወንድ ልጅ የዘር ማምረቻ የሆኑት ሁለቱ ፍሬዎች በጽንሱ ጊዜ ሆድ ውስጥ ሆነው ሲፈጠሩ ልጁ ከመወለዱ በፊት በማህጸን እያለ ነው ወደቦታቸው ወርደው የሚጨርሱት፡፡ ስለዚህም አንድ ወንድ ልጅ በሚወለድበት ጊዜ ፍረው በቦታው አለ ወይንስ የለም የሚለውን ማረጋገጫ አዋላጆች ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ይሄ የአዋላጅ ሐኪሞችም ኃላፊነት ነው እንደ ዶ/ር ወለላ ማብራሪያ፡፡ ወላጆችም ቢሆኑ ወንድ ልጅ ሲወለድ ፍሬውን በቦታው ላይ አለ ወይንስ የለም የሚለውን በእጃቸው በመዳሰስ ማወቅ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ፍሬዎች በቦታቸው ላይ ካልሆኑ እውስጣቸው ያለው እስፐርም ከማለቁ በፊት እድሜው ከሶስት እና ከአራት አመት ሳይበልጥ በጊዜ ከሆድ ውስጥ በቀዶ ሕክምና በማውጣት ወደቦታው ማውረድ ይቻላል። ነገር ግን ይህ በአብዛኛው የሚታወቀው ወንዶቹ ትዳር ከያዙ በሁዋላ እድሜአቸውም ከሰላሳና አርባ አመት ሳያንስ ልጅ መውለድ እምቢ አለኝ በማለት ወደ መካንነት ህክምና ሲቀርቡ ነው፡፡
ዶ/ር ወለላ እንደገለጹት የወንድ ልጅ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በሚጸነስበት ወቅት የዘር ፍሬዎቹ ቦታዎቹ ከጽንሱ ሆድ እቃ ውስጥ ሲሆን ይህንን በሚወለድበት ጊዜ በትክክል ከቦታው ደርሶአል አልደረሰም የሚለውን ፈትሸው አዋላጆች ለወላጆች ማሳወቅ ይገባቸዋል፡፡ ወላጆችም ቢሆኑ ልጃቸውን ሲረከቡ ማየት ቢችሉ መፍትሔው ቀላል ነው። ከጭንቅላት የሚመጡት ሆርሞኖችም ስራው እንዲሰራ የሚያዙ ሲሆኑ መጠናቸው በሚያንስበት ጊዜ ግን ፍሬው ምንም ችግር እንኩዋን ባይኖርበት ትእዛዙን ካላገኘ ማምረት አይቸልም፡፡ እነዚህ ብዙ ጊዜ በወንዶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡

Read 885 times