Print this page
Saturday, 18 March 2023 20:14

«ሰው ለአገሩ የሚዋጋው መንደሩን እያለመ ነው»

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(4 votes)

  «በር»
አለማየሁ ገላጋይ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ (በነፍስ መቆየት) ጉልህ ሚና ካላቸው፣ ከሚኖራቸውም ደራሲያን መካከል አንዱ ነው። ቃላት ይታዘዙታል፣ አንደበተ-ርቱዕ መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው። ከዐሥራ ምናምን ዕንቁ  ሥራዎቹ መካከል ለዛሬ የበኩር ሥራው በሆነችው “አጥቢያ” ላይ ላትት ወደድኩ።
ሰው በሰው ላይ ያለው ጭካኔ ቢከብደኝ አልያም የGeorge Orwell Animal Farm [Above all, no animal must even tyrannize over his own king weak or strong ,clever or simple ,we are all brothers. No animal must ever kill any other animal. All animal are equal] መልዕክቱ ቢገዝፍብኝ ልመርጣት ወደድኩ።
አጥቢያ ልብ-ወለድ ወይስ ኢ-ልብ ወለድ?
 አጥቢያ ኹለቱንም መሆን ችላለች እላለሁ። ለምን? የሚለኝ ቢኖር  ዐራት-ኪሎ ከመፍረሱ በፊት ያነበቧትን ሰዎች ማስታወስ እፈልጋለኹ። ለዚህም ከመፍረሱ በፊት በጭብጧ የምናብ ውጤት (ልብ-ወለድ) ነበረች። ዐራት ኪሎ ከፈረሰ በኋላ ላነበቧት ሰዎች ግን ኢ-ልብ ወለድ (በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘች)  መስላ ነው የምትታየው።
አጥቢያ ሟርት፣ ትንቢት ወይስ ግምት?
አለማየሁ ገላጋይ «በፍቅር ስም» መጽሐፍ ምርቃት ላይ ጋዜጠኛ በፍቃዱ ዓባይ መድረኩን እያጋፈረ... ሳለ የተናገረውን ንግግር አብላላሁት። እሱም «አንዳንድ ሰዎች ከፍ ሲያደርጉኝ ትንቢት ተናገረ ይሉኛል፤ ዝቅ ሲያደርጉኝ አሟረተ ይሉኛል.. እኔ ግን መሐል ላይ ነኝ...» የሚለውን...
ሟርቱን ትተን (ብቻውን ስለማይቆም)...አጥቢያ በፕሪዲክሽን እንጂ በፕሮፌሲ የተሰራች አይደለችም እላለኹ። ለምን? የሚለኝ ቢኖር፣ ኹለቱም ስለ ወደፊት መናገራቸው ቢያመሳስላቸውም፣ ጉልህ ልዩነታቸውን  ደግሞ እንይ። በዕውቀት (knowledge)፣ በልምድ (experience)፣ በታ’ዝቦ (observation) ስለወደፊት የሚነገረንን ነው ፕሪዲክሽን የምንለው። አለማየሁ ከደራሲነቱ ባሻገር ጋዜጠኛ ነው። ለመንግሥት ተግዳሮቶች፣ ለዕቅዶች ሙያዊ ቅርብነት ነበረው፤ ለዚህም የመንግሥቱን አዝማሚያ በሚገባ ታዝቦ ፕሪዲክት አደረገ የሚል ድምዳሜ ነው ያለኝ በግሌ።
ትንቢት ከእምነት ጋር ነው ቁርኝቱ (The term prophecy is often used in the context of religion and mythology). ወደፊት ስለሚፈጸሙ ተለቅ ያሉ ሁነቶች (የዐራት ኪሎ መፍረስ ቀላል ነበር የሚል አተያይ የለኝም) በነቢይ አማካኝነት የሚነገር ነው ይሉታል ትንቢትን፡፡ (prophecy usually predicts a relatively greater phenomenon than a prediction. (ex: the end of the world, death of a king, rise of a hero, etc)
አጥቢያ የማህበረሰብ ኅልውና ላይ ያጠነጠነ ሥራ ነው። የሕይወት ኩርባዎችን፣ የመኖር እጥፋቶችን ሰካክቶ ነፍስ ዘርቶበታል። የከተማ መስፋፋት (urbanization) በዐራት ኪሎ ነዋሪዎች ላይ ሊያደርሰው ስለወጠነው ጠባሳ አስቀድሞ የለፈፈ ደራሲ ነው። ምናልባትም ከአፉ ማረጋገጫ «ታለ»ን ሊያስተዋውቅ ሰይፉ ጋር ቀርቦ «ሰዎች ዝም በአሉበት ተናግሬያለሁ፤አሁን አድማጭ ነኝ »ማለቱን እናስታውሳለን።
አጥቢያ እና 4KRI
፩.Keep Reader Interested
[አጀማመርን ማሳመር፣ ያልተለመዱ ሁነቶችን ማካተት፣ የሚስብ ገፀ-ባሕርይ መቅረጽ (intriguing character)፣ ቆንጆ ግጭት፣ እና ጠንከር ያለ ትልም ቢኖሩ አንባቢ ይሳባል።]
አለማየሁ ገላጋይ እርጥባንን ሆኖ የኼደበት እርቀት፣ የሴት ንግግር፣ ስሜትንና እና ሁኔታን የተረዳበት ጥልቀት ያስገርማል። ምንም እንኳ  የሙሉ ጌታ ማስታወሻዎች በየመሐሉ ቢዶሉም የአጥቢያ ነገራ በሴት ነው።
ደራሲው ጠንካራ  ሆኖ ጀምሮ ወደ መለስለስ ቢንደረደርም አንባቢን መያዣ አያጣም። ጋሽ ማርቆስ ቢቆጡ አባ ገሬ ያስቁናል። ሙሉ-ጌታ በል ብሎት ቢቆዝም ኮምሬድ ሊያነቃው ይመጣል። ቅምቅምን እና አድባሯን፣ የአባይነሽ ዲናሞ ጨዋታ፣ የአቡንደጅ ኹናቴ፣ በየመሐሉ የሚሰነቀሩ ሳቅም ኀፍረትም የሚቸሩን ገለጻዎቹ ከንባብ እንዳንቆም ያደርጉናል። የገፀ-ባሕርያት ነፃነት (ዲሞክራሲያዊ መብት ልበል? ሃሃ) ተከብሯል። አባገሬ ስለ ወሲቡ፣ጋሽ ማርቆስ  ተንኳሽነቱን፣ሙሉጌታ ታፈሰ ቤት ኼዶ እስከ መናገር ድፍረቱን፣ የአዝማሪዎች metaphorical ነገር፣ የደሃውም የሀብታሙም ገፀ-ባሕርይ ስለሚያምኑበት ነገር አትተዋል። «ዕውቀቴን ልሽጥ» የሚለውን ቀሽት ገፀ-ባሕሪ ኮምሬድ ጨምሮ።
አጥቢያ በትራያንግላዊ ቅርጽ ላይ ትጎላለች። በታፈሰ ሀብታምነት፣ በሙሉ-ጌታ ድህነት፣ በእርጥባን ኹለቱን አገናኝነት ጸንታለች። ብዙዎቹ ፍዝ ገፀ-ባሕርይ ለመሆን የተገደዱ ናቸው። ስለ ሀብት እና ሀብታምነት የሚሟገት ታፈሰ ብቻ ነበር። ዙሪያውን የከበቡት ተቃራኒዎቹ ናቸው (ለምን? ምናልባት ወደፊት ጠንካራ በትር የሚያርፍባቸውን ሰዎች ለማጉላት አስቦ ይሆን? ወይስ ሀብትን ተቃውሞ ድህነትን ለማንቆለጳጰስ?)
አጥቢያን ለማንበብ የሚያሳሱ ገለጻዎች አሉ። የሙሉጌታን ማስታወሻ ያነበበ እንዴት የእርጥባንን ገለጻ ሊቀበል ይችላል? (በእርግጥ መጻፍ አለመቻሏን ቀድማ «በመጀመሪያ ደራሲ አለመሆኔን መናዘዝ እፈልጋለሁ» የሚል disclaimer ሰጥታለች)። በዚህም የእርጥባን የፍቅር ታሪክ፣ የታፈሰ የክፉ ሀብታምነት መገለጫን እንደ ምርጊት አየዋለኹ ፤ማለትም በሙሉ-ጌታ ሸጋ የትረካ ግድግዳ ላይ መጥቶ እንደተለጠፈ ዓይነት።
፪.keep Reader informed
[አንብቦ መረዳት የአንባቢ ፋንታ (ውስጡ ለቄስ) ቢሆንም የታሪክ መደላድሉን (Exposition)፣ የተለዋዋጭ እና ጽኑ ገፀ-ባሕርያትን፣ የዋና እና የንዑስ ገፀ-ባሕርያትን ድርጊት ፍንትው አድርጎ ማሳየት]
አለማየሁ ገላጋይ የዐራት ኪሎ ልጅ ነው። የአጥቢያም ትኩረቷ/”መደላድሏ እዛው ነው። አንባቢ ዐራት ኪሎ ምን ትመስላለች? ብሎ ቢጠይቅ መኼድ ሳይጠበቅበት «ዐራት ኪሎ ብሎ ገዳም አለ ወይ?» ከሚለው ገለጻው ላይ ብቻ የሚያገኘው እውነት አለ (ሌላ ጎኗ ሳይካድ)። አራት ኪሎን ፖለቲከኞች ሲሳሱላት እናውቃታለን፤ በአጥቢያ በኩል ደግሞ አንባቢዎች ይሳሱላታል (ለእነ ኮምሬድ፣ ለእነ አባ ገሬ፣ ለእነ ቅምቅም፣ ለእነ ሙሉ-ጌታ...)።
አጥቢያ የዐራት ኪሎን መጻዒ ዕድል ከማተት ባለፈ የዕለት አኗኗራቸውን ትነግረናለች። «ዐራት ኪሎ የሚንጠባጠበው ብዙ ነው» እንዲለን። የህብረተሰቡን አኗኗር ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል። ወደር የለሽ የማድመጥ ክህሎቱም ተንጸባርቆበታል። ለምን? በደንብ ያላደመጠ በደንብ አይጽፍም አይናገርምና...
፫.Keep Reader involved
[ትረካዎችን በድርጊት ማስጀመር፣ የአተራረክ ለዛን ማሳመር (ጋሼ ስብሐትን አስታውሱ)፣ አንባቢ ምን እንደሚያደርግ ባለመንገር፣ እንደ ወኃ ፍስስ እያደረጉ አንባቢን ወደ ሌላ ዓለም የማጓጓዝ ኺደት ነው።]
አለማየሁ ገላጋይ አንባቢን እያዋዛ ይዞ መጓዝ ይችላል። እንደ ጋሼ ስብሐት ወሲቧን ጠቆም አድርጎ አሳስቶ የሚፈልገውን መረጃ ያስከትላል (እነዚህ ስንቃረዎች ሊያስፈልጉም ላያስፈልጉም ይችሉ ይሆናል። ግን ተጠቅሟቸውም ይነበባሉ..)። ወደ ሐይማኖት ተቋማት ጣቱን ሲቀስር ያስቀስራል፣ ወደ አድባር ሲኼድ ይወስዳል፣ ወደ ሀብት እና ድህነት ሲመጣም ያመጣል። አንባቢን ከገፀ-ባሕርያት ጋር የማሽከርከር አቅም ከአንድ ደራሲ የሚጠበቅ ነው። ስሜቱን ካላጋባ፣ እልሁን፣ ትህትናውን ካላጋባ ድርሰቱ ብሽቅ ይሆናል።
አጥቢያን ያነበበ ሰው ዐራት ኪሎን ሰፈሬ ብትሆን ምን ይውጠኝ? ብሎ ሳያስብ አይቀርም። እትብታችን የተቀበረባት ቦታ ሁሌም ከልብ አትጠፋም። «ወደ ፊት ሕመም አይደለም፣ አለመታየት ነው የሚገድለን» እያለ ሲያብሰለስለን፣ «ዕድሜአችን እንደተሸጠ በሬ ከገበያ እስከ ቄራ ነው»ን ስንሰማ ሲያሳዝነን፣ «መንደራችን በብዙ ወጣቶች ውልብታ የተሞላች ነች» ብሎ ሲያስተክዘን፣ «ሚዳቋ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለነብርም ነው የተፈጠረችው» እያለ ሲያሳምመን፣ «ተሸናፊነትን መቀበል ለመኖር አለመፍቀድ  ነው፤ በእነሱ አስተሳሰብ» እያለ ሲያነቃን፣ «ሰው ለአገሩ የሚሞተው መንደሩን እያለመ ነው» (የመንደር መፍረስ የሚሞቱለት አገር ማጣት ነው) እያለ ከሐሳቡ ጋር ያዋሕደናል።
፬.Keep Reader inspired
[Reading inspires writing. Writing inspires living]
አለማየሁ ገላጋይ የአንባቢን ቀልብ በመግዛት፣ ስለ ዋና ሐሳብ ለመንገር፣ አንባቢን ከንባቡ ለማዋሃድ የሚቸገር ጸሃፊ  አይደለም። የአጥቢያ ታናናሽ ወንድም እኀት (ከእርሷ በኋላ በመታተማቸው) የሆኑትን ሥራዎቹን ስናነብ አጥቢያን እንንቃለን። እየጨመረ የሚኼድ ደራሲ  ነው።
በአጥቢያ በኩል የተገለጸው የህንዱ መንደር የካልካታ የፈንጥዚያ ከተማ (The city of joy) ውክሉና ስያሜው አራምባ እና ቆቦ መሆኑን (ድሆቹ የሥጋ ደዌ ተጠቂ፤ ፈረስን ተክተው ጋሪ የሚጎትቱ መሆናቸውን)። ኤቭሊን ሪድ ስለጻፈችው woman evolution (እማዊ ሥርዓት) ለሕብረተሰብ ያለውን እምርታ ጣል ያደርጋል። ይህም አንባቢን ያበረታል_ ለቀጣይ ንባብ። የመጽሐፉ አጨራረስ cliffhanger (left the reader hanging or wanting more)ነው፤ «የደሃዋ እና የሴተኛ አዳሪዋ የአቡንደጅ ልጅ ነህ» ብሎት አለቀ። ሌላ አልፈለግንም፣ ቢደባደቡ፣ ይቅርታ ቢጠያየቁ... ሌላም ሌላም እንድናስብ ከፍቶ ለቀቀን። በዚህም ሊደነቅ የሚገባው ነው። ሌላኛው የኢትዮጵያ literary figure የሆነው አዳም ረታ ይህን ሰቀላ በየመሐሉ ያደርጋል።
«ኖር ...»
1.አጥቢያ እንደ ግብዓት
ስለ ዓራት ኪሎ የመፍረስ መጻዒ-ዕድል ቀድሞ አለማየሁ በአጥቢያ በኩል ለፍፏል።  በ2011, [THE LIVELIHOODS OF DISPLACED PEOPLE IN ADDIS ABABA: THE CASE OF PEOPLE RELOCATED FROM ARAT KILO AREA]   በሚል ርእስ  በሀብታሙ አጥላው የተሰራ መመረቂያ ጽሁፍ  ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቀርቧል:: (peripheral,  places  with  inadequate  access  to  urban  infrastructure  and  services.  They  were relocated  with  no  consideration  of  the  social  and  economic  consequences  of  displacement. This  further  made  their  livelihood  worse  thereby  threatening  their  livelihood  activities  and various  assets,  such  as,  financial,  social  and  human  dimensions  (Gebre, 2008;  Berhanu, 2006)). ይኼን ጥናት አንብቤ የአለማየሁን የአጥቢያ ስሜት ስቸልስበት ጉዳዩ ኃያል ሆነበኝ። ደራሲው የፈራው ደርሶ የጠላው ወርሶ አይተናል። ወደፊትስ በዚች ከተማ ምን ይኖር? ለሚለው ግብዓት ናት። ከሥነ-ጽሑፍ መልኳ ባሻገር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መስሎ ታይቶኛል።
2.ምሰላ
አለማየሁ ገላጋይ በአጥቢያ ውስጥ የጽሕፈት ዘይቤው ወደ ምሰላ ያደላል ። «እንደ» እና «ይመስላል» ያጀቡት ሐሳብ ለማግኘት ‘ሩቅ መኼድ አይጠበቅብንም። በመጀመሪያ ገፁ ብቻ በእንደ የተገለፁትን እንይ ...
[አዲስ አበባ ላይ «እንደ» ጭጋግ የምንሳፈፍ መሰለኝ፣ አዲስ አበባ «እንደ» ብረት ቁና ዓይን...፣ የተራራ አጥሮቿ «እንደ» ሲዖል አጋፋሪ፣ «እንደ» አዛባ ማከማቻ ጉድጓድ፣ ከተማዋ «እንደ» ተበተነ ልም መስታዎት፣ ሰደድ አዝረክርኮ «እንደ» ተወው መስክ፣ «እንደ» ባለጌ ምላስ ሰማይ ላይ ያግጣሉ። የፓርላማው ሰዓት «እንደ»ማጥ ..እና መሰል ነገሮች በአንድ ገፅ ያውም መጀመሪያው ላይ መታጨቃቸውን፤ አልፎም በገጽ (53) ከአቅም በላይ መወጣጠሯን አልወደድኩትም፤ የምሰላውን ጥልቅነት አለማድነቅ ግን ንፉግነት ነው።
3.በአንድነት ውስጥ ያለ ልዩነት
[ኹለት ነገሮች ተቀላቅለው ግን መለያየት የሚችሉ ከሆነ ኬሚስትሪው ልይ-ዘር ይለዋል።] የዚህን ቅልቅል በእጅ መልቀም (Handpicking)፣ በመውቃት (Threshing)፣ በማጣራት (Sieving)፣ በማትነን (Evaporation)፣ በማቅረር እና በሌሎቹም ዘዴዎች  በቀላሉ የተደበላለቀውን መለየት ይቻላል። ለስሙ ቅልቅል ናቸው ግን መለያየትም ግብራቸው ነው። እነዚህ ኹነቶች በአለማየሁ ገላጋይ አጥቢያ የቀረቡትን «ላይዋሃዱ የተቀላቀሉ» የሚሰኙትን በደንብ ይወክሉልኛል (ይህም የከፋው ከተደሰተው፣ የሞላለት ካልሞላለት፣ የራበው ቁንጣን ከያዘው የነበሩበት ኹኔታ ነው)። ተወዳጁ አቀንቃኝ ዘሩባቤል ሞላ «ውኃ እና ዘይት»ን ለዚህ አባሪ አደርጋለሁ። ልንለያይ የተደባለቅን መሆናችን አይገርምም?
4. የገፀ -ባሕርይ አሰያየም
አለማየሁ በአጥቢያ ገፀ-ባሕርያቱ ስም ዙሪያ በተደጋጋሚ ሲያደርገው ያስተዋልኩት ስም ግብርን ሲወክል ነው፤ አንዳንዴም metaphorical የሆነ ሐሳብ ለማስረጽ። ምሣሌ፦
ከዋና ገፀ-ባሕርያቱ የሐብታሙ (የታፈሰ ሀብቱ) ልጅ ሆና ስሟ እርጥባን፣የደሃ ልጅ ሆኖ ስሙ ምሉዑ-ጌታ፣
ከፍዝ  ገፀ-ባሕርያቱ አልማዝ - ሚንቄ (በድሮ ሂል መመናቀሯን)፣ ማሜ-ባሊ (ባሊ መስረቋን)፣ ሮማን-ሲ (ሲለዩ አቃጣሪነቷን)፣ አባይነሽ-ዲናሞ (ምናልባት የፊት ጥርስ የሌላት ስትናገር  ምራቅ የምትረጭ መሆኗን አልያም ረባሽነቷን)፣ ከአዝማሪዎቹ አንዷ አሰለፈች/ቅምቅም (አፏ የተቀመቀመ ጠይም ጨርቅ ስለሚመስል)፣ ፍቃዱ/እንቅላሊት (እንቁራሪት ማለት ፈልጎ በተናገረው) ለመጠቆም ቃትቷል። ብዙ የሰፈር ስሞችም (ምናልባት እውነታ ይሆናሉ) በዚሁ መልኩ ተቀምጠው ይታያሉ።
5.የትውስታ ማዕከሎቹ እና ማሕበራዊ እሴቶቹ
መስፍን (ከንቱው)፣ አባይነሽ ዲናሞ፣ የቅምቅም አዝማሪዋ ሁኔታ እና የአድባርት ትዝታ፣ (ስለ አድባር መብዛት የፈረደው ነገር የለም። ደራሲ ያለመፍረድ መብት ስላለው..)፣ የልጅ አገራረፍ ዘዴ (በእርጥብ የመግረፍ ብሂል (ገጽ 84)፣ ሴቶች የራሳቸውን መብት ለማስከበር የሌሎችን ሴቶች በማስጠበቅ ረገድ፣ የሴተኛ አዳሪዎች ሕይወት ተመሳሳይ ቀለም የተቀባ መሆኑን፣ የድሃ እና የሃብታም ንጽጽሮሽ (ሰፋ ባለ ሐሳብ)፣ ሴት ትምታህ? ይሉትን፣ የገሬ አስቂኝ ቀልዶች፣ ወንድ በሚስቱ ላይ ሲደርብ ላዩን ቢጠላም በድብቅ «ወንድ እሱ እንደሚባልለት»፤ሲጠቃለልም ማህበረሰቡ ያልተተኮሰ ጥይት አለው። እኛ ከሸፍን ማለት እነሱ ከሸፉ ማለት አይደለም እንዳለው...ይሁን።
«መውጫ»
አጥቢያ በአርትዖት በኩል ብዙ ጎደሎዎች አሏት። በንግግር ወቅት የምንጠቀማቸው ወደ ጽሕፈት ወርደው ይታያሉ። «ያዛሉ» «ያዝዛሉ» ለማለት፤ «ማሪያም» «ማርያም» ለማለት፣ «ጉስቋም» «ቁስቋም» ለማለት ..ወዘተ። አለማየሁ ገላጋይ አሁን በአለበት በራሱ የጽሑፍ ብቃት ስለካት አጥቢያ ደካማ ናት (ግን የዐራት ኪሎን እውነታ እና አሁንም በአገሪቷ እየተደረጉ ያሉ ሁነቶችን ገልጣ በመያዟ ከሁሉም ሥራዎቹ በላይ ናት)። በጥቅሉ የትልም ልልነት ይታይባታል።
ደራሲው ኪነትን ይመኛታል ከልቡ፤ የምግብ አበላል ላይም ሳይቀር። የገለፃው ለዛ አጃኢብ ነው። «ያልደመቀ ሪዝ»፣ «ዓይኖቼን አሸራምሜ ልጁ ጋር አነቃኋቸው» («ከወደቀው ፍሬ ዛፍ ይነቃል” እንዲል ሮፍናን)። story with in story የሚሉት አተገባበር ላይ ለስላሳ ደራሲ ነው። የእርጥባንን ታሪክ፣ የመጽሐፉ አጽመ ታሪክ ከሆነው ሐሳብ ጋር የሰፋበት መንገድ አሪፍ/ለስላሳ ነው (ግን የሙሉ-ጌታ ማስታወሻ ብቻ ልቤን እንደያዘው /እሱን በይበልጥ እንደወደድኩት አልክድም)።
አጥቢያ «ተሻጋሪ ባሕርያት» ብለን ልናስባቸው ለምንችላቸው ነገሮች ጥንስስ ናት። ከአጥቢያ መጽሐፍ ጀምሮ በሌሎች መጽሐፍቶቹ በኩል የምናገኛቸው የድምፅ፣ እና የአንዳንድ ባሕርያት ሽግግር አለ። የሙሉጌታ አውራጣት እና ጺም፣ የቡቹ መቅበጥ፣ ግድግዳው ላይ የተሳለች ወፍ (ስዘምርላችሁ ዱቤ ይጀምራል የምትለዋ፤ ግን የማትዘምረዋ)፣ የኃ/ሚካኤል ሳቦሬ (የጋሽ እፉፉ) «ዮቭ ሁሁ» (የሬብ ሁሉ ድምጸት)፣ የገረመው”ቺ” ድምጽ (ይኽ ገፀ ባሕርይ ኑሮ የቀልድ ምንጭ ነው፣ ምን እውነት አለበትና በምሥጢር የሚጠበቅ? የሚል የአልበርት ካሙ በThe myth of sisyphus መጽሐፉ የወከለውን The absurd man Don Juan መሰል seducer ባሕርይ ይታይበታል።Albert (Don Juan, He moves from woman to woman) እንዲል..የአለማየሁ አባገሬም «ከፍተኛ የሴት ባሕርይ አምሮት አለብኝ» እንዲል...
እርጥባን በቀዛፊ ታንኳ ውክል (አጋባሽ ሐብታሞች ወደፊት ለመጓዝ ወደ ኋላ ያሽቀነጠሯቸውን ድሆችን መረዳቷን)፣ «መልኬ ከአባቴ ተቃራኒ ነው ስትል» በሐሳቧም እንደምትቃረነው፤ ዓይኖቹ የክልስ ናቸው ስትል ካፒታሊዝምንም ድህነትንም ያውቃል ማለቷ እንደሆነ መረዳት ነበረብን። በኮምሬድ አንደበት፦ቤተ ክርስቲያን የከሸፈች የአብዮት ቦታ መሆኑን፣ እምነት የመጨቆኛ መሣሪያ መሆኑን፣ የኢየሱስ ውልደት ከግብፃዊያን «ኦሲሪስ» ትንግርታዊ ውልደት የተኮረጀ መሆኑን፣ ለአቃቤ ንዋይ ይሁዳን ወክሎ «ገንዘብ አያስፈልግም» ሲል መስበኩን የፈጣሪንና የሰይጣን ልዩነት ሲያትት፣ እግዚአብሔር በሐሳቡ ጠንቋይ በሆዱ ስለሚያስቡ ነው ማለቱን ስናይ፤ በፍቅር ስም ምርቃት ላይ የነበረው ስሜት «አጥቢያን ስጽፍ እግዚአብሔር የለም» በሚለው እያጠነጠንኩ ነው የሚለውን ያጎላልናል፤ ሙግቱ ጠንካራ የነበረው አጥቢያ ላይ ነው። «በፍቅር ስም»ላይ ሲደርስ የእግዚአብሔርን ታጋሽነት መስክሯል።
በመጨረሻም፦ መንደር እየታሰበ አገርን ከጠላት መከላከል እንደሚቻል አጥቢያ ትናገራለች። ከገለጻዎቹ ኹሉ የወደድኩት ነው (time and space) እንድወደው ስለፈቀደ። የዐራት ኪሎ ማህበረሰብም፣ የአንዳንድ መንደሮች አኗኗር ነፀ-ብራቅ፣ እውነታውንም ናትና።


Read 885 times