Print this page
Saturday, 18 March 2023 20:14

የማይታየው ከሌለ - የሚታየው አይዘልቅም “The unseen is proved by the seen”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

ሁሉም ሰው የሚስማማበት ነገር አለ። ወይም ደፍሮ ቀና ብሎ የማያነሳው ጥያቄ። ውስጡ አጥንት ያለውን የአሳ ስጋ በጥንቃቄ እንዳይወጋው አላምጦ እንደሚውጠው፣ እንደዛ ነው ውሸትን ከእውነት ሳይነጣጥል የሚመገበው፡፡
የአለም አጥንትና ስጋ እንደዛ ነው የተመሰረተው። የተገለጸው ውሸት ከሆነ፣ የተደበቀው አጥንቱ እውነት ነው። በአንዱ ላይ ነው ሌላኛው የተመሰረተው። አንዱ ቢላጥ ሌላው ፈጦ አግጥጦ ብቻውን አይቆምም፤ ህያው አይሆንም። ስጋ የሌለው አፅም ህያው አይደለም፡፡
ለምሳሌ፡- አንዱ ግልፅ እንዲሆን የማይፈለግ እውነት፡- ሁሉም ሰው አንድ እንዲሞት የሚፈልገው ሰው ስለመኖሩ ነው። ይሄንን ማመን ፈፅሞ አለመፈለግ ይስተዋላል፡፡
ሁሉም በግልፅ ሲማማልና ሲመፃደቅ የሚደመጠውማ የማንም ህይወት መጥፋት እንደሌለበት ነው። ይህንን የሚሸከም ሙሉ የለቅሶ ሥርአት በየመንደሩና በየዕድሩ አለ። ሰው ባልተጠበቀ አጋጣሚ የሚሞትበትን ለማስተዛዘን ብቻ የተመሰረተ ሥርአት አይደለም፡፡
እኔ ማውራት የፈለኩትም ሰው በሰው እጅ ህይወቱ የሚያልፍበትን የተጠበቀ እና የታቀደ አጋጣሚ ሳይሆን ክስተት ነው፡፡ ከተግባሩ በፊት ምኞቱ ይቀድማል፡፡ እኔ ዛሬ እያሰብኩ ያለሁት ስለ አንድ እውነት ነው። ሁሉም አለባብሶ ማለፍ የሚፈልገው፣ ግን ሁሉም በልቡ ውስጥ በአንድም ጊዜ ሆነ በሌላ የሚመኘው እውነት።
እስቲ እኔ አጥንቱን ከስጋ ነጥዬ፣ አውልቄ፣ ሜዳ ላይ ዛሬውኑ ላስጣው። ሁሉም ሰው አንድ ወይንም ከአንድ በላይ፣ አንድ አይነት ወይም ብዙ አይነት፣ አንድ ዝርያ ወይንም የበለጠ ዝርያ አንድ የሀይማኖት ተከታይ ወይንም ብዙ የሀይማኖት ስርዐት እና ተከታዮቻቸው እንዲሞቱለት ይመኛል… አለቀ፤ “ተነፈስኩ ፈሰስኩ” እንዳለው ነው ገጣሚው። ይሄው ቁልጭ አድርጌ አስቀመጥኩት::
ለምን አንድ አይነት ሰው ሌላ አይነት ሰው እንዲሞትለት ይመኛል?  ይሄ ነው መሰረታዊው ጥያቄ። መልሱን ከመስጠቴ በፊት አንድ ከራሴ ተሞክሮ የማውቀውንና የሚደንቀኝን ታሪክ ልግለፅ። ባደግሁበት ሰፈር አንድ ወጣት ልጅ ይኖር ነበር። ምናልባትም አሁንም በመኖር ላይ ይገኛል። ልጁ በሆነ ወቅት ላይ፣ በሱስና በተስፋ መቁረጥ ክምር ስር እንደ ዳምጠው መኪና ጎማ ተደፍጥጦ ሲጥጥ ሊል የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡  
ህይወቱን በቀጥተኛ መንገድ ለማጥፋት ለምን እንደማይጥር፣ ከስቃዩ አንጻር እየመዘንን የምንደነቅ ሌሎች የጎን ተመልካቾች ነበርን።… መሞት እንደሚፈልግ ድርጊቱ ገላጭ ነበር። ግን የመረጠው የመሞቻ መንገድ ስቃዩን ከግቡ በላይ የሚያራዝም ስለሆነብን፣ ደም እየተፋና እየተንፏቀቀ ሲገባ፣ ከንፈር እየመጠጥን ከማስተዋል ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረንም።
በመሀል ብዙ ነገር ተከስቷል። ከእለታት አንድ ቀን እኔ ከሄድኩበት ወደ ድሮው ሰፈር ስመለስ፣ ልጁን ሌላ ቅርጽ ይዞ አገኘሁት። ፊቱም ተመልሷል። ከመሬት ጋር እየወደቀ የፋቀው ስጋው ከቅስሙ ጋር ተመልሶ ገጥሟል። የማላውቀውን ሰው በማውቀው ትዝታ ውስጥ ሰላም አልኩት። በራሱ ላይ ያለው መተማመን ጨምሯል። ሚስት አግብቷል። ልጅም ወልዷል። እየሸጠበት ያለው ሱቅ የራሱ መሆኑን ለማረጋገጥ ባለቤቱን መጠየቅ አላስፈለገኝም። መትረፉ አስደስቶኛል። ያንን የቁልቁለት አቅጣጫ የያዙ፣  ብዙውን ጊዜ ወደ ዳገቱ ተመልሰው ሲወጡ አይገኙም። አለቀ በቃ! ተብለው ተስፋ የተቆረጠባቸው- እውነትም ያልቅላቸዋል… ያበቃላቸዋል። እንደ አዲስ ቆፍረው ከገቡበት ጉድጓድ አይወጡም።
መጀመሪያ ከሱቁ ስርቅ ያገኘሁትን የሰፈር ሰው፣ ምን ተከስቶ ይሄ የህይወት መትረፍ እንደመጣ ሳላቅማማ  ነበር የጠየቅሁት። የመለሰልኝ ሰውም ቀጥተኛ መልስ አልሰጠኝም- የአባቱን ርስት መውረሱን በገደምዳሜ ነገረኝ።
“የሆነ ሰው ሞቶለት ነዋ!” ብዬ ጭጭ አልኩኝ። የማይባል ነገር ነው የተናገርኩት። የሚባል እና የማይባል ነገር አለ። የተገለጸ እና የተደበቀ ምስጢር አለ። ከውጭ ከንፈር የሚመጠጥበት፣ ከውስጥ ግን ጉሮ ወሸባዬ የሚያሸልል ድል አለ። ይህ ድል ሰው ሲሞት የሚገኝ ድል ነው።
 ልጁ እንደዛ ተስፋ ቆርጦ የነበረው የእሱ የህይወት ተስፋ ከአባቱ ሞት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ በመሆኑ ምክንያት ነው። ከላይ በአፍ የሚወራው ውሸቱ ነው። የውሸቱ ስጋ ነፍስ ዘርቶ መንቀሳቀስ እንዲችል ግን አጥንት ያስፈልገዋል። ይህ የሚታየው አጥንት ነው እውነቱ። የልጁ መንገድ የቁልቁለት ሆኖ የነበረው ለካ- አባቱ ዳገቱ ላይ ቆሞ ማለፊያውን ስለዘጋበት ነው። አበባ በብስባሽ ላይ ህይወት ዘርቶ እንደሚያብበው፣ ሰውም የሌላ ሰውን መሞት በግልጽ ባይናገርም ይመኛል፤ ይጠብቃል። ይሄንን የአሳ ስጋ ነው እንግዲህ እንዳይወጋው ሳያላምጥ ሁሉም የሚውጠው። የሆነ ሰው ሞት፣ የሆነው ተስፈኛ ደግሞ ትንሳኤ ነው።
በተፈጥሮ እጅ የሚሞተው እንዳለ ሆኖ የተፈጥሮን ህግ ወይንም ጊዜ መጠበቅ ያልቻለ ችኩል ደግሞ በራሱ እጅ የሌላውን ህይወት ይቀጥፋል። አንዱ የሚኖረው፣ ወይንም የሚኖር የሚመስለው በሌላው ሞት ብስባሽ ላይ ነው ብሎ እስካመነ ድረስ ሁሌ ሞት ይኖራል። ሞት ብቻ ሳይሆን የጅምላ ሞትም ይኖራል።
ጦርነት የማይቆምበት ምክንያቱም ይሄው ነው። ጥላቻ እና ጠላት የማይጠፋበት መንስኤም ይኼው ነው። “ተነፈስኩ-ፈሰስኩ።”
ይኼው ሆኖም በግልጽ ግን አይነገርም። የሰው ልጅ አስተሳሰብ እንደ አነጋገሩ ቅኔ ነው። ማለት ወይንም ማስረዳት የፈለገውን አይደለም የሚናገረው። ቀጥተኛ ንግግርም በዚህ መንገድ ይባላል ወይንም ተናጋሪውን ሞኝ ያስብላል።
የሚደረግ እንጂ የማይወራ ነገር አለ፤ የሚወራ እንጂ የማይደረግም እንደዚሁ። “የሰው ልጅ ሰላም ወዳድ ፍጡር” ስለመሆኑ ዘወትር የሚቀርበው ዲስኩር፣ የሚወራው ግን ሊተገበር የማይችለው አይነቱ ነው።
እንዲሆን፣ ከልብ በመነጨም ሆነ ከምላስ በተረጨ ቁርጠኝነት አልያም ንግግር፣ ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል አሳምሮ ይሰበካል። ግን ለማድረግ ያስቸግራል። ምኞቱ ከተጨባጩ እውነታ ጋር የማይገጥመው፣ ከሰው ልጅና ከተፈጥሮ እውነታ ጋር ስለሚሳከር ነው። ሰው ጥቅም፣ ስልጣን፣ ሀብት፣ ጉልበት የሚፈልግ ፍጡር ነው። የሰው ልጅ ህልውና በእግሩ ከተራመደበት እለት ጀምሮ ወደዚሁ ግብ ለመድረስ በመፍጨርጨር የሚባትት ነው። ሁሉም የሚሻማው ለተመሳሳይ ግብና ጥሪት (resource) እስከሆነ ድረስ… መሀል ላይ የፍላጎት ግጭት  መከሰቱ አይቀርም።
የአንዱ የፍላጎት የፀሐይ ግርዶሽ የሚመጣው ከሌላ አውሬ ሳይሆን ከመሰሉ ወይንም የበለጠ ሀቀኛ ልሁን ካልኩኝ ደግሞ በቅርብ ካለ ዘመዱ ውስጥ ነው። መንገዱን የሚዘጋው ራሱ መንገደኛው ነው። ከጓደኛህ ጋር አብረህ  መሰደድም አደጋ የሚፈጥረው ከዚሁ በመነጨ ህመም ይመስለኛል። (የመሰለኝ ሁሉ እውነት እንደሆነ መናገር ከዚህ በኋላ አያስፈልገኝም!!)
ነጥቡን አንድ ጊዜ ደግሜ ተናግሬው መድረኩን ለቅቄ እወርዳለሁኝ።
አዎ፤ ሁሉም የሰው ልጅ እንዲኖርለትም እንዲሞትለትም የሚፈልገው ሌላ የሰው ልጅ ወይንም አይነት አለው። እንዲኖርለት የሚፈልገው በአላማ የሚተባበረው እስከመሰለው ድረስ ነው። አይነቴ የሚለው ያኔ ብቻ ነው። እንዲሞትለት የሚፈልገው ደግሞ በአላማው ላይ ጋሬጣ ሆኖ እንዳያድግ፣ ምኞቱን እንዳይጨብጥ መሰናክል ሆኖ የቆመበትን ሁሉ ነው። ወይንም  የመሰለውን።
ፅኑ ወዳጅም ሆነ ዘላቂ ጠላት የለም። አላማ እና የመንገድ አቅጣጫ ሲለወጥ ሀብት ለመውረስ ሲል የአባቱን መሞት በግልጽም ባይሆን በድብቅ የተመኘው ልጅ መልሶ አባቱን ሊናፍቅ ይችላል። ልጆቹን ለማሳደግ ሲል ከአባቱ ጋር የተጣላው ልጅ፣ ልጆቹ ሲያድጉ የእሱን ሀብት እንዳይወርሱ የሚከላከል ሊሆን ይችላል።
በዚሁ መንገድ ሁሉንም ነገር ለቅጽበት ሳየው---ነገሩ ሁሉ ግልጽ የሆነልኝ፣ መስሎኝ ነበር። ግን ደግሞ ሁሌ የሚሞቱ ግን አንዴም የማይገድሉ የሰው አይነቶችም ዘራቸው በዝቶ፣ ቁጥራቸው አድጎ በመጥፋት ፋንታ ሲለመልሙ አይቻለሁኝ። በመብላትና መበላላት፤ በመግደልና መሞት ብቻ የማይገለጽ የእውነታና የሰው ልጅ ምንነትም ፍቺ… በሆነ ስፍራ አለ ማለት ነው። ምናልባት ቅድም ስለ ስጋ እና አጥንት ሳወራ ነው ስህተት የሰራሁት።
እውነትን እና ውሸትን በስጋ እና አጥንትነት መዋቅር ብቻ ካነበብኩት፣ በእርግጥም ፍላጎቱ ሁሉ ከአውሬ ግዛት የሚሻገር የመሆኑ ህልም ፍጹም የመከነ ይሆናል።
ምናልባት ከስጋ እና ከአጥንቱ… ከሽፋኑ ውሸት እና የሽፋን ውሸትን ህልውና ለማቆየት ብቻ ከስር እንደ አጥንት ጠንክሮ ከተሸሸገው እውነት ባሻገር ሌላ መንፈሳዊ ንጥረ ነገር ሊኖር እንደሚችል መጠርጠር ይገባኝ ነበር። ይህ ንጥረ ነገር በማግኘትም በማጣትም ምንነቱን የማይቀይር፣ የማይፈጥርም ሆነ የሚጠፋ፤ ከሰው እጅና ሥራ ወይንም ተፅእኖ በቀጥታ የማድረግ አቅም የወጣ መሆን መቻል አለበት።
ግራ እንዳይገባችሁ፣ ምስኪን አንባቢዎቼ፤ እያወራሁ ያለሁት “ነብስ” ስለተባለው ነገር ነው። በዚህ መንፈሳዊ ንጥረ ነገር ላይ የህልውና ሚስጢር ከተገነባ ስጋ ሆነ አጥንት ከዚህ ቀደም የነበራቸው ምድራዊ፣ አውሬአዊ ተፈጥሮ ይለወጣል። መለኮታዊ እና ሚስጢራዊ ምንነት ይወለዳል።
ነፍስ ካለ ሁሉም ሰው “ቢሞትልኝ” ብሎ የሚመኘው ሌላ ሰው የግድ መኖር አይኖርበትም። ሁሉም ቢኖር ወይንም መኖር ቢፈልግ ዞሮ ዞሮ ሁሉም ይሞታልና። በስተመጨረሻ፣ ማንም መሞቱ ስለማይቀር መኖሩ ያን ያህል የጦርነት እና የጥላቻ ምክንያት ሊሆን አይችልም።
***
አሁን ያለው እውነታ፣ ወይንም በተጨባጭ እየኖርንበት ያለው ትርፍና ኪሳራን በቅጡ ሳያሰላ በስለት የሚተራረዱበት እውነታ፤ የነብስን ህልውና ወይንም በህልውና ነብስ መኖሩ ምን ያህል የግድ እንደሆነ ዘንግቷል።
ነብስ በሌለበት ደግሞ ሌላ አማራጭ የለም። መጀመሪያ ላይ የገለጽኩት ፎርሙላ ብቻ ነው። አጥንቱ እንዳይወጋው የአሳ ስጋውን እየተጠነቀቀ ለመዋጥ የሚጣጣርበት። እለት በዕለት የሚከናወነውን፣ እለት በዕለት የመካሄጃ ብልሃት የማይታጣበት። የአንዱ ሰው መኖር አስፈላጊ እንደሆነ፣ የሌላ ሰው መሞት የግድ ስለመሆኑ አይንን በጨው አጥቦ የሚታሰብበት። “That which is only living can only die”

Read 865 times