Print this page
Saturday, 18 March 2023 20:22

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “መሃይምነትና ድንቁርና ይለያያሉ”


     “...በነገራችን ላይ መሃይምነትና ድንቁርና ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መሃይም የሚባለው የትምህርት እድል ያላገኘ ነው። ድንቁርና ግን የትምህርት እድልም አግኝቶ በመሃይምነት ግርሻ የተጠቃው ነው። ፈረንጆች ምን ይላሉ --- arrogance (እብሪተኝነት) Ignorance (አለማወቅን) ያመጣል።  arrogance እና  Ignorance ይመጋገባሉ። መሃይምነት ሲያገረሽብህ እብሪተኛ ትሆናለህ፤ እብሪተኛ ስትሆን ደግሞ የበለጠ መሃይምነት ያገረሽብሃል። እናም ብዙዎቻችን በዲግሪያችን ጀርባ በድንቁርና ነው የምንኖረው። ሰውም እንዳይመክረን ዲግሪ አላቸው ይባላል። በእድርም ስትሄድ ዶክተር ይናገር ነው የሚባለው። ግን ሰውየው መሃይምነት ውስጥ ነው ያለው።.... እና ምንድነው እየሆነ ያለው ብላችሁ ያያችሁት እንደሆነ... መደማመጥ የሌለው፣ መነጋገር የሌለበት፣ የማንተማመነው፣ ለችግሮቻችን መፍትሔ የማናገኘው የምሁር ቁጥር እንጂ የአዋቂ ቁጥር ስለሌለ ነው። ለምን ያላችሁ እንደሆነ፤ አብዛኞቻችን በመሃይምነት ግርሻ ውስጥ ስላለን ነው። የዲግሪ ፎቶ በየቤቱ ስትሄዱ ግድግዳ ላይ ታያላችሁ። በትክክል ያ የሚያሳየው ሰውዬው በመሃይምነት መኖሩን ነው። ምክንያቱም ማረጋገጫው ያ ብቻ ነው። ሌላ ምን ያሳያል? ምን እናሳያለን ሌላ?....”
 (ዶ/ር አለማየሁ አረዳ፣ በአማራ
ቴሌቪዥን ከተናገሩት)
____________________________________

                 “እንደ ብልህ አብረን መኖር ካልቻልን፣ እንደ ሞኝ አብረን እንጠፋለን”
                      ዘላለም ጥላሁን


       ያለፈውን ዘመን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ ከሞከርነው ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ” እንዳለው ሎሬቱ፣ የኢትዮጵያ ልጆች ያልሞከሩት የእርስ በርስ ትግል የለም። ከወረቀት እስከ ጥይት፣ ከሐሳብ እስከ ሒሳብ፣ ከመንደር እስከ ሀገር፣ ከዘር እስከ ስናይፐር፣ ከረሃብ እስከ ጥጋብ፣ ከሰፈር ንትርክ እስከ ሀገር ታሪክ፣ ከገጀራ እስከ ሚሳኤል ሁሉንም አብሮ የመጥፊያ መንገዶችን ሞክረዋል።
ረጅሙ የንትርክ ታሪካችን፣ አድዋ፣ ማይጨውንና ካራማራን በመሰሉ አጭር የአብሮነት ታሪኮች ባይገመድ ኖሮ፣ ይኸኔ  ተበትነን ነበር። “እንደ ብልህ አብረን መኖር ካልቻልን፣ እንደ ሞኝ አብረን እንጠፋለን” እንዲሉ፣ መፍትሔው አብሮና አብ’ሮ መኖር ነው።
አብሮ ለመኖር “ትናንትን በይቅርታ እያለፉ፣ የዛሬን ቀዳዳ እየሰፉ፣ ነገን በተስፋ መንደፉ” ያልሞከርነው መንገድ ነው። ከሞከርነው ያልሞከርነው ብዙ ነው።
አብረን ከመጥፋት ይልቅ አብረን ለመኖር የምትመች ሀገር ለመፍጠር ህሊናዊ አስተውሎትና ብስለት ከመሪ እስከ ተመሪ ተነፈግን። ሁሉም ነገር የጅብ እርሻ ሆነ-እየጎለጎሉ ማረስ፣ እየገነቡ ማፍረስ።  ህሊናችን በጥላቻ ቆሸሸ፣ በመጠላለፍ ሟሸሸ። ተስፋችንና ህልማችን ሁሉ እንደ አመዳይ ወየበ። ስጋትና ብሶት የየቀን ቀለባችን ሆነ። ሁላችንም ከቃላችን ከህሊናችን ሸሸን።
ለአንድ ህይወታችሁ፣ ለአንድ ሆዳችሁ፣ ለአንድ የስልጣን ምኞታችሁ፤ ሀገርንና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ተንኮል ውስጥ የገባችሁ አደብ/ቀልብ ብትገዙ ምን አለበት? ቆም ብላችሁ ህሊናችሁን ጠይቁ፣ እራሳችሁ ለራሳችሁ ጥያቄ አርቅቁ (ህዝብማ መች ትሰሙና?)።
ሀገሪቱን  ሌላ ሴራ፣ ሌላ መከራ፣ ሌላ ኪሳራ ውስጥ  አትክተቷት። ቢያንስ ቢያንስ መጀመሪያ ከራሳችሁ ከህሊናችሁ ታረቁ። ከዚያ መንገዱ ቀላል ይሆናል.... ያልተሞከረውን ሞክሩ፣ ያልተሄደበትን መንገድ አሳብሩ..... .መጀመሪያ ከህሊናችሁ ታረቁ፣ ነፃ ውጡ። ነፃ ያልወጣ ህሊና፣ እንኳን ህዝብን ግለሰቡን ነፃ አያወጣም። አሊያ “እንደ ብልህ አብረን መኖር ካልቻልን፣ እንደ ሞኝ አብረን እንጠፋለን”፡፡
________________________________________

                      አጠቃላይ ቅኝት "እስከ መቼ በአጼዎቹ እያሳበብን እንሳነፋለን?"


         ሰሞኑን በመጠኑ የቃኘነዉ ኪታብ /ኢንቲሻር…/ ‹‹ታሪካችን በወጉ አልታጻፈም ወይም ሆነ ተብሎ ተዘሏል፤ ጠልሽቷል ወዘተ›› በሚለዉ በኃይማኖትና በዘዉግ ፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ በተለመደ ሙሾ የተወጠነ ነዉ፡፡ በኪታቡ መግቢያ (ተምሂድ) ለዚህ ሙሾ ይሁንታ ተችሮ ለዚሁ አገልግሎት በአማርኛ የተጻፈች አንዲት አርቲክል እንደወረደች ወደ ዐረብኛ ተተርጉማ ነግሳበታለች፡፡
ጥንትም ሆነ በቅርቡ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመጻፍ ብዕር ያነሱ ጸሀፍት፤ Selection, Omission, Demonization, Interpretation or misinterpretation የተሰኙ አራት ዘዴዎችን በመጠቀም  ታሪክ እንዳዛነፉ አርቲክሏ ታትታለች፡፡ ሌሎች ወንድሞችም አርቲክሏን የመጽሀፍ መግቢያ ሲያደርጓት ታዝቤያለሁ፡፡
በወጉ ያልተመዘገበ የታሪክ ክፍል ሊኖር ስለመቻሉ አልከራከርም፡፡ ሆኖም ታሪክ ላለመዘገቡ እንደ ምክንያት ሊመዘዙ ከሚችሉ በርካታ ሰበዞች መካከል ሴራን ለይቶ ሁሉንም ችግር በርሱ ላይ መደፍደፍ  የ‹‹conspiracy mentality›› አባዜ ነዉ፡፡ ለታሪክ ዘገባዎች ያልተሟሉ መሆን ሊጠቀሱ ከሚችሉ ሰበቦች መሀል፡-
1.  የጽሁፍ ባህል አለመዳበርን ማንሳት ይቻላል፡፡ በአሀዝ ረገድ በርከት የሚሉ የሀገራችን ጎሳዎችና ነገዶች ሳይቀር የጽሁፍ ባህል ሳያዳብሩ ለዘመናት በመኖራቸዉ ታሪካቸዉን በአፈታሪክ መልክ ከትዉልድ ትዉልድ ከማስተላለፍ በስተቀር በጽሁፍ መዝግበዉ ማሻገር አልቻሉም፡፡ በጽሁፍ ያልተሰነደ ነገር ደግሞ በጊዜ ሂደት መጥፋቱ፣ መበረዙና መከለሱ፣ መጨመሩና መቀነሱ አይቀርም። የጽሁፍ ባህል በአንጻራዊነት የዳበረባቸዉ አካባቢዎች ጸሀፍት የሚጽፉት በዙሪያቸዉ ስላለዉና ስለሚያዉቁት ህዝብ፣ ሀይማኖትና ባህል፣ በተለይም ደግሞ ስለ ነገስታቱ ገድል እንደሆነ ዕሙን ነዉ፡፡ ወንዝ ተሻግረዉ የሌላዉን ለመጻፍ የቦታ ርቀት፣ የቋንቋ አለማወቅ፣ የባህል ወዘተ ዉስንነቶች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ አንዳች አጋጣሚ ሲፈጠር የሌላዉን አካባቢ ከመጻፍ ወደ ኋላ እንደማይሉ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ አባ በሕሪይ የተባሉ የጋሞ መነኩሴ፣ በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበረዉን የኦሮሞ ታሪክ ክፍል በዓይን ምስክርነት አሳምረዉ ከትበዉታል፡፡ ይህ የመነኩሴዉ  ሥራ፣ የዚያ ዘመን ታሪክ አብይ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ኃይሌ ‹‹የአባ ባሕሪይ ድርሰቶች…›› በሚለዉ ድንቅ መጽሀፋቸዉ፤ ግዕዙን ወደ አማርኛ በመመለስ ከሌሎች የታሪክ ምንጮች ጋር እያሰናሰሉ ጠቃሚ ዳሰሳ አድርገዉለታል፡፡ አሁናዊ ሁኔታዎችን ሳይቀር በወጉ ለመረዳት በእጅጉ ስለሚጠቅም ብታነቡት ታተርፉበታላችሁ፡፡
2.  በሙስሊሙ ወገን የጽሁፍና የምርምር ባህል ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ የሀገራችን ሊቃዉንት የአትኩሮት ማዕከል ሀይማኖታዊ መጽሐፍትን ማዘጋጀትና መተንተን፣ እንዲሁም የነብዩ ሙሀመድ ዉዳሴ (መድህ) በመሆኑ፣ የሀገር ቤቱ የእስልምና ታሪክ በነርሱ ተገቢዉ ትኩረት አልተቸረዉም፡፡ ሊቃዉንቶቻችን ለሀይማኖታዊ ትምህርት አገልግሎት የሚዉሉ ኪታቦችን በአስደናቂ ብቃት መጻፋቸዉና ማብራሪያ (ሸርህ) መስራታቸዉ የሚታወቅ ነዉ፡፡ የነብዩ ዉዳሴ (መድህ) ድርሳኖቻቸዉም መሳጭና ዘመን ተሻጋሪ ናቸዉ፡፡ ዓለማቀፍ ዕዉቅናን ከተጎናጸፉ ጸሀፊዎቻችን መካከል በ662 ሂጅሪያ የሞቱት የሀዲስ ጥናት አዋቂ ጀማሉዲ ዐብደላህ እብን ዩሱፍ፤ ‹‹ነስቡራያ ፊተኽሪጂ አሀዲሲል ሂዳያ›› የተባለ መጽሐፍ አዘጋጅተዉ ለዓለም አሰራጭተዋል፡፡ በ643 ሂጅሪ የሞቱት የሀነፊ መዝሀቡ ሊቅ ፈኽሩዲን ዑስማን እብን ዐሊ ‹‹ተብይነል ሀቃኢቅ ፊሸርህ ከንዘ ደቃኢቅ››፣ ‹‹ሸርህ ጃሚዑል ከቢር›› የተሰኙና ሌሎችንም ለሀነፍይ መዝሀብ በዓለማቀፍ ደረጃ ‹‹ሪፈረንስ›› የሆኑ ዕዉቅ ኪታቦችን አዘጋጅተዋል፡፡
በ1230 ሂጅሪይ የሞቱት ጀማንጉስ፣ በ1240 የሞቱት ተማሪያቸዉ ሸኽ ሰይድ እብን ፈቂህ ዙበይር፣የራያዉ ጀማሉዲን አልዐኒ ወዘተ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ከሠሩ ሊቃዉንቶቻችን መካከል ናቸዉ፡፡ በዚህ ረገድ የሀገራችን ዑለሞች አስተዋጽኦ በ‹‹ኢንቲሻር…›› ኪታብ ዉስጥ በሚያምር ሁኔታ ተጽፏል። በነብዩ ዉዳሴ (መድህ) ቅኔዎች ረገድም እነ ሸኽ ጫሌ የመሳሰሉ ማዲሆች በዐረብኛም በአማርኛም እጅግ መሳጭ ሥራዎችን ለሀገር አበርክተዋል፡፡ አበልቃሲም የሊቃዉንቶቻችንን ብቃት ሲመሰክሩ፡-
‹‹በዚህ ዘመን በሙስሊሙም ሆነ በዐረቡ ዓለም ከሚገኙ ዑለሞች ዉስጥ የፊቅህና የነህዉ ረቂቅ ሚስጥራትን በመረዳቱ ረገድ የሀበሻ ዑለሞችን የሚገዳደር እንደሌለ ነዉ የማምነዉ። ይህም የሆነዉ የመማር ማስተማር ሂደታቸዉ የተበጠረና የነጠረ በመሆኑ ነዉ፡፡›› (አዕላም 159)
ሆኖም ይህን ያህል ብቃት ላላቸዉ ሊቃዉንቶቻችን ታሪክን መዝግቦ ለትዉልድ ማስተላለፍ የትኩረት ማዕከላቸዉ አልነበረም። አስበዉበት ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያችንን ታሪክ የተሟላ የሚያደርጉ ግሩም ጥናቶችን እናገኝ ነበር፡፡
ስለዚህ ታሪክን መዝግቦ የማስተላለፍ፣ ቅርስን ጠብቆ ለትዉልድ የማስቀረት ወዘተ ባህል በሊቃዉንቶቻችን ዘንድ እምብዛም አለመኖሩ ለታሪካችን በወጉ አለመጻፍ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህም ስለሆነ አብዛኞቹ የሊቃዉንቶቻችን (መሻኢኾቻችን) ገድሎች የተላለፉት በጽሁፍ ሳይሆን በአንደበት (በቂሷ) ነዉ፡፡ ታሪክን በጽሁፍ ያስተላለፉ በጣት የሚቆጠሩ ሊቃዉንት ቢኖሩንም የሚጽፉት በዐረብኛ በመሆኑና መኖሩም ስለማይታወቅ ለሀገራችን ታሪክ ጸሀፊዎች እንደ ምንጭ አላገለገለም፡፡ ከነዚህ የዐረብኛ ሥራዎች መካከል የህትመት ብርሀን ያገኙት ኢምንት ናቸዉ፡፡ አሁን አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል የተወሰኑ ኪታቦች ለሁለተኛና ለሶስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናት እየተሠራባቸዉ መሆኑ ጥሩ ጅምር ቢሆንም፣ ከሚፈለገዉና ከሚጠበቀዉ አኳያ የተሠራ ነገር አለ ለማለት ይቸግራል፡፡
በጥቅሉ በሙስሊሙ ወገን የተከወነዉን የኢትዮጵያ ታሪክ ክፍል፣ እንዲሁም ቅርሶቻችንን እምብዛም ጠብቀን ማቆየት አልቻልንም። ይህ መሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ያልተሟላ እንዳደረገዉ የታሪክ ጸሀፊዎች ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ በአባ ባህሪ ድርሰቶች ቅኝታቸዉ ዉስጥ ይህን መሰል ነጥብ አንስተዉ ‹‹ያልተሟላዉን ስለማሟላት›› ሀሳብ አጭረዋል፡፡ እናም በራስ በኩል የተፈጠረን ክፍተት ‹‹ከአጼዎቹ›› ወይም ከ‹‹ጭቆና›› እያገናኙ መነጫነጭ ፍትሀዊ አይደለም ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩ በትክክል ታዉቆ መፍትሄ እንዳይበጅለት እንቅፋት ይሆናል፡፡
ጥንት ይቅርና አሁንም በዕዉቀት፣በተለይም በታሪክ ዕዉቀት ምርትና ልማት ዘርፍ ሁነኛ ሚና አለን ብዬ አላምንም፡፡ ይህ የሆነዉ ‹‹አጼዎቹ›› ስለከለከሉን ወይም ‹‹ስለጨቆኑን››፣ ወይም ደግሞ ‹‹ደብተራዎች›› ስላሴሩብንና ‹‹ኦርቶ-አማራ›› ስላቀበን ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ ለትምህርትና ለዕዉቀት ልማት ያለን ግንዛቤ እጅግ አናሳ በመሆኑ ነዉ፡፡ ምን ያህል የፊሎሎጂ፣ የታሪክ ወይም የአንትሮፖሎጂ ወዘተ ተማሪዎች አሉን? ካሉት ተማሪዎቻችን መሀል ምን ያህሎቹ ትምህርታቸዉን በወጉ ያጠናቅቃሉ? ስንቶቹስ በተማሩበት መስክ ይሠራሉ? ስንቶቹ ወደ ላይ በትምህርት ይገፋሉ? ከነርሱ መካከል ብቁ ተመራማሪዎች ምን ያህል ናቸዉ? የትኞቹስ በሙስሊሞች ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን ይሠራሉ? ለመሥራት ቢያስቡስ ምርምር የሚጠይቀዉን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል የማህበረሰብ ክፍል ወይም ተቋም አለን? የቅርስ ጥበቃ ባህላችን ምን ይመስላል? ለነዚህና መሰል ጥያቄዎች የምንሰጠዉ መልስ ተጨባጫችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገዉ ወጣት የፊሎሎጂ ዶክተርና ተመራማሪ ሁኔታዎች ስላልተመቹት ዕድሜ ልኩን የለፋበትን ትምህርትና ምርምር እርግፍ አድርጎ ትቶ ልብስ እንደሚቸረችር አዉቃለሁ፡፡ አንድ ጉምቱ የታሪክ ፕሮፌሰር -ልክ እንደ ሀዲስ ሊቁ ሀጅ ራፊዕ- በደሳሳ የቀበሌ ጎጆ ዉስጥ ኖሮ አልፏል፡፡ ዕዉነታዉ ይህ ሆኖ እያለ ‹‹እገሌ ታሪኬን አልጻፈልኝም›› እያሉ አሁንም ድረስ ማላዘን፣ አጼዎችን መዉቀስ፣ የታሪክ ሰናጆቻችንን ‹‹በሙስሊም ጠልነት›› መክሰስና ሥራዎቻቸዉን ማራከስ ተገቢነቱ አይታየኝም፤ ጠቀሜታም የለዉም፤ ለችግራችንም መፍትሄ አይሆንም፤እንዲያዉም ራሳችንን በወጉ ፈትሸን ችግራችንን እንዳንረዳና ወደትክክለኛዉ አቅጣጫ ጉዞ እንዳንጀምር ማሳነፊያ ይመስለኛል፡፡ ችግርን ወደ ሌሎች ማላከክ ቅንጣት መፍትሄ አይሆንም፡፡ እስከ መቼ በአጼዎቹ እያሳበብን እንሳነፋለን?
3.  የሀገራችን ታሪክ ጸሀፊዎች ታሪክን በጎሳና በሀይማኖት ሸንሽነዉ የመጻፍ ልምድ እምብዛም አላቸዉ ብዬ አላምንም፡፡ በነርሱ አዕምሮ ዉስጥ የነበሩት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን እንጂ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ … አይደሉም። ስለአጤ ዮሀንስ ሲጽፉ ትግሬነታቸዉ፣ ስለአጤ ቴዎድሮስ ሲጽፉ አማራነታቸዉ፣ ስለጎበና ዳጬ ወይም ስለጅማ አባጅፋር ሲጽፉ ኦሮሞነታቸዉ ከጸሀፊዎቻችን ስሌት ዉስጥ እምብዛም አልገባም፡፡ ቢበዛ ከሸዋ፣ ከጎንደር፣ ከሀረር ወዘተ እያሉ አካባቢ ሊጠቅሱ ይችላሉ እንጅ ዘዉግ ዋነኛ ጉዳያቸዉ አልነበረም፡፡ ክስተቶችን (ለምሳሌ ዶጋሊን፣ የአምባላጌን፣ የጉደትና ጉራን ወይም የአድዋን ፍልሚያዎች) ሲዘግቡ የሚያተኩሩት በሂደቱና ‹‹በራስ እገሌ የተመራ ጦር እንዲህ አደረገ›› በሚሉት ጉዳዮች ላይ እንጅ በጎሳና ነገድ ሽንሸና ላይ አይደለም፡፡ የዘዉግ/ብሄር ነገር መላቅጡን እያጣ የመጣዉና የፖለቲካ መቧደኛ በመሆን ሀገር ሊያፈርስ የደረሰዉ ከ1960ዎቹ ወዲህ ነዉ፡፡ ስለዚህ ከዚያ በፊት ታሪክ የመዘገቡ ወገኖችን ከዚያ ወዲህ በመጣ እኩይ አስተሳሰብና ዝንባሌ መመዘን ተገቢ አይደለም፡፡
ባይሆን ለክስተቶች ሀይማኖታዊና መንፈሳዊ ትርጓሜ (interpretation) መስጠት የዚያ ዘመን አጻጻፍ ባህሪ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ጸሀፊዉ የርሱ ወገን ሲያሸንፍ ‹‹መላእክት ረድተዉት፣ ፈረሰኛዉ ጊዮርጊስ አብሮት ተዋግቶ፣ታቦቱ ተከትሎት…›› የሚል ምክንያት ይሰጥና ሲሸነፍ መሸነፉን ዘግቦ፣ ግና ከመንፈሳዊነት ጋር ሊያይዘዉ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሰይጣን ከጠላቶቹ ጎን ስለሆነ ወይም ጾም ጸሎት ስለተዘናጋ ወይም የማርያምን ቤተ ክርስቲያን ስላላሠራ፣ ስለቷን ስላላስገባ፣ በባዕል ቀን ስራ ስለሰራ ወዘተ›› እያለ ለሽንፈቱ መንፈሳዊ ምክንያት ይደረድር ይሆናል። ይህ ዓይነቱ አጻጻፍ በየትኛዉም ሀይማኖት ታሪክ ጸሀፊዎች ዘንድ የተለመደ ነዉ፡፡ ‹‹ፉቱሀል ሀበሽ››ን ለናሙና በማየት ይህን ማጤን ይቻላል፡፡ ዐረብ ፈቂህ የኢማሙን እንቅስቃሴዎች፣ ዉጊያዎች ማፈግፈጎች፣ ድሎችና ስኬቶች በአንድ በኩል፣ የተቃራኒያቸዉን ሁለንተናዊ ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች፣ በሌላ በኩል የሚገልጹበትና የሚተረጉሙበት መንገድ ከመንፈሳዊና ሀይማኖታዊ ቃናና ዝንባሌ ዉጭ አይደለም፡፡ የጥንት ዘመን የታሪክ አጻጻፍ መንገድ እንደዚሁ ስለሆነ ገለልተኛ ተመራማሪ ከሁለቱም ወገን መንፈሳዊ ትርጉሞችን፣ የተጋነኑ ገለጻዎችንና የዉገና ዝንባሌዎችን አበጥሮ በመለየትና ወደ ጎን በመተዉ ክስተቶችን ብቻ ወስዶ በሳይንሳዊ መንገድ ያጣራል፣ ያቀናጃል፣ ይተነትናል። የዘመናዊ የታሪክ አጻጻፍ ጅማሮ የሆኑት ተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹የግራኝ አህመድ ወረራ›› መጽሀፋቸዉ ዉስጥ በ‹‹ፉቱሀል ሀበሺ››ም በግእዙም የታሪክ ድርሳናት ወገን የሚገኙ ተመሳሳይ ገለጻዎችንና ግነቶችን እየተከታተሉ በመመርመር ሲሀይሱ በብዛት ይስተዋላል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሄር ጭቆና ነበር›› የሚለዉ ስሁት ተረክ፤ ሀሰቶች ተደርተዉበትና አለቅጥ ተጋኖ አየሩን በማጨናነቁ፣ ብዙ ጸሀፍት የዚህ ተረክ ሰለባ ሲሆኑና ከርሱ ባሻገር ለማየት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ የጭቆና ተረክ ባለፉት 700 ዓመታት የጊዜ ሂደት ዉስጥ ተፈጽመዋል ‹‹የሚባሉ›› ‹‹ክፉ ነገሮች›› ሁሉ ለአማራ የሚያሸክም አይዲዮሎጂ ሆኖ ይህን መከረኛ ህዝብ ላለፉት 30 ዓመታት ሲያስጨፈጭፈዉ ኖሯል፡፡ አሁንም እያስጨፈጨፈዉና በሚሊዮኖች እያፈናቀለዉ ይገኛል፡፡ ‹‹ኢንቲሻሩል ኢስላም…›› መጽሐፍ ከዚሁ ‹‹የብሄር ጭቆና›› ዝንባሌ ረገድ የደረሰበት ተጽእኖ ይኖር ይሆን? በምን ያህል መጠን? የሚሉ ጉዳዮችን በሌላ ጊዜ ከሌሎች መጽሐፍት ጋር በማሰናሰል እንመለስባቸዉ ይሆናል፡፡
እስልምና ለዘለዓለም ጭቆና የሚዳርግ ‹‹ንጥረ-ነገር›› በዉስጡ የያዘ፣ መጨቆን የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሁልጊዜ ‹ቀደር›› እስኪመስል ድረስ የሃይማኖት ጭቆና አቀንቃኞች ይህን የ‹‹ተጨቁነን ኖረናል›› ተረክ አብዝተዉ ሲያራግቡት ይስተዋላል፡፡ ለቅሶን ለፖለቲካ ዓላማ የሚጠቀሙ ወገኖችም እጅግ አጋነዉና አግዝፈዉ፣ ወይም የተሳሳተ የትንተና ስልትን ተጠቅመዉ በዚሁ ሙሾ የተቃኙ ድርሳን ማዘጋጀታቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ተረክ በ‹‹ኢንቲሻር…›› ኪታብ ላይ ጥላዉን በምን ያህል መጠን እንዳጠላ ተገቢዉን ፍተሻ ማድረግ አስፈላጊነቱ እንዳለ ሆኖ ተረኩ የፈጠረዉን ጭጋግ የሚገፍና በኢትዮጵያ የሙስሊሞችን የድልና የስኬት ክንዋኔዎች ጨምሮ ነባራዊዉን ሁኔታ ሳያጋንንና ሳያቀጭጭ እንዳለ የሚያቀርብ መጽሐፍ በባለሞያዎች የመሠራቱ አስፈላጊነት አሁን ጊዜዉ ይመስላል፡፡
የያዝነዉን መጽሀፍ ቅኝት ለጊዜዉ እዚህ ላይ ልግታ፡፡ የቀሩ ነጥቦች እንዳሉ ዕሙን ነዉ። ሆኖም ለፌስቡክ አቅም እስካሁን የቀረቡት ሀሳቦች ከበቂ በላይ ናቸዉ፡፡ ቀሪዎቹ ሰፋ ባለ ሌላ ‹‹ፕላትፎርም›› ይቀርቡ ይሆናል። ከመጽሀፉ ዉስጥ ለናሙና ያየናቸዉና ሌሎችም የ‹‹ፋክት››፣ የቅኝትና የትንታኔ እንከኖች እንደተጠበቁ ሆኖ መጽሐፉ በዉስጡ ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ ማንበቡ አትራፊ ያደርጋል፡፡
በመጨረሻም ደራሲዉ ዓመታትን ፈጅተዉ አድካሚዉን የምርምር ሥራ በማከናወን ለሀገራችን የታሪክ ምርምር ግብአት የሚሆን ድርሳን ስላበረከቱልን ሊመሰገኑ ይገባል። አሁን ያላቸዉን ጥሩ የምርምርና የመጻፍ ክህሎት የበለጠ አዳብረዉ ሌሎች ጠቃሚ የጥናት ዉጤቶችን እንደሚያስነብቡን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በወርሀ ረመዳን ሁኔታዎች ከተመቻቹ ከወሩ መንፈሳዊ ድባብ ጋር የሚሄዱ ጽሁፎችን አጋራ ይሆናል፡፡ የመጽሀፍት ዳሰሳዎችና ሌሎች አጀንዳዎችን ግን ከረመዳን ማግስት እመለስባቸዋለሁ፡፡
መልካም የዒባዳ ጊዜ!!!

Read 1610 times
Administrator

Latest from Administrator