Saturday, 25 March 2023 17:26

በጠ/ሚኒስትሩ የጸደቀው የጌታቸው ረዳ ሹመት እያወዛገበ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 - “መቶ ሺዎችን ካስጨረሱ በኋላ እነሱ በይፋ ይሿሿሙብናል”
            - “ሹመቱ በትግራይ ህዝብ ደም ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው”
               
         ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው መሾማቸው እያወዛገበ ነው።
“ሹመቱ በምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ደም ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ ክህደት ነው” ብለዋል አስተያየት ሰጪዎች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ በኢፌደሪ መንግስትና በህውሃት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ግጭትን ለማስቆም በፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላምን ስምምነት መሰረት፣ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋም በማስፈለጉ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ተደርገው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሾማቸውን አመልክቷል።
“በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ሹመት የዜጎችን ስነልቦና በከፍኛ ደረጃ የሚጎዳና ከወራት በፊት የአገርን አንድትና ሉአላዊነት ለማስከበር በየሜዳው የወደቁ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደም ከንቱ ያስቀረ ሹመት ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሰጡና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድየምክር ቤት አባል ተናግረዋል።
አክለውም “ሺዎች የሞቱት፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትና ሃብት ንብረታቸውን ያጡት በእነዚህ ቁንጮ አመራሮች ጥጋብና ዕብሪት ሆኖ ሳለ ገና የሞተና የተረፈው እንኳ ሳይለይ እንዲሁም  ህውሃት ያሰለፋቸው ህጻናት ተዋጊዎች ቁስል እንኳን ሳይደርቅ ወንጀሉ በቀጥታ ሚመለከታቸውን ሰው አምጥቶ አስተዳዳሪ አድርጎ መሾም በህዝብ ደምና ህይወት ላይ መቀለድ ነው” ብለዋል። መቶሺዎችን  እርስ በርስ ካጫረሱ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ሁሉን ረስቶ መሿሿም የፖለቲካ አስቀያሚ ገጽታው ነው ያሉት እኒሁ ሰው ድርጊቱ ቢሆን እንኳን ትንሽ ጊዜ ቢሰጠውና ህዝብ ከገባበት ከባድ ሃዘንና ሰብአዊ ቀውስ እስኪያገግም እንኳን ፋታ ቢሰጠው የተሻለ ነበር ብለዋል።
የመቀሌ ከተማ ነዋሪውና የጤና ባለሙያው ሀብቶም ህሉፍ (ለጽሁፉ ስሙ የተቀየረ) “ የህውሃት አመራሮች ከመቀሌ ነዋሪ ህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ሆነዋል ያሉት የጤና ባለሙያው ሳለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትና ሴቶችን ሳይቀሩ ወስደው በጦርነት ሃዘንና ሰብአዊ ገና የት እንደደረሱ ያልታወቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች እያሉ መንግስት የሰጠው ሹመት አስደንግጠናል ብሏል።
ከአንድ ቤተሰብ የተወሰዱ አምስትና ስድስት ልጆች የት እንደገቡ የሚጠይቁ ወላጆች መልስ የሚሰጣቸው አጥተው አቤት የሚሉበት ቦታ ፍለጋ እያለቀሱ ባለበት በዚህ ወቅት አቶ ጌታቸው ያስተዳድርህ ከማለት በላይ በዚህ ህዝብ እንዴት ሊቀለድ ይችላል።
እነዚህ ሰዎች ለህዝቡ ምንም ደንታ የሌላቸው የራሳቸውን ስልጣን ከማራዘም የዘለለ ምንም ሃሳብ የሌላቸው ሰዎች ለመሆናቸው ማሳያው ሰሞኑን በጦርነቱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የክልሉ ወጣቶችና ህጻናት ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው እያለ በአስለቃሽ ጭስና በተኩስ እንዲበተኑ መደረጋቸው ነው። እነዚህ ወጣቶችና ህጻናት ለእነዚሁ ሰዎች የስልጣን ጥም ጭዳ የሆኑ ናቸው። ዛሬ ግን አካቸው ጎሎ ጎድሎ አትፈለጉም ተብለው ተጥለዋል። እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ነው አስተዳዳሪ አድርገው የሾሟቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ ሰዎች አገር ያወቀው አለም የሰማው ወንጀል የፈጸሙ፣ ንፁሃንን በማንነታቸው ብቻ ያስጨፈጨፉ  ናቸው።”
“በምንም ሁኔታ በወንጀል ከመጠየቅ ሊድኑ አይችሉም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው። መንግስት ግን እንደዚህ አይት ውሳኔዎችን ሲወስን በደንብ ሊያስብበት ይገባል” ብለዋል አስተያየት ሰጪው።
የአቶ ጌታቸው ረዳ ሹመት በመቀሌና አካቢው ነዋሪ ህዝብ  ዘንድ ግራ መጋባትን መፍጠሩንና ህዝቡ ብፍርሃት ውስጥ እንዳለ የጠቆሙት ከተማዋ ነዋሪ፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም የእርዳታ ቁሳቁሶችን ከረጂ ተቋማት በመውሰድ የማከማቸት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

Read 2101 times