Saturday, 25 March 2023 17:59

‘ሠሪው’ ሌላ፣ ‘በዪው’ ሌላ የሆነባት ዓለም!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)


          “-ደግሞ እኮ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ስብስቦች ብቻ ሳይሆን፣ ሚሊዮኖችን የሚነኩ ደስ የማይሉና ደስ ካለማለት የዘለሉም የፊት ለፊትና የጎንዮሽ ነገሮች እየሰማን ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ “መከራው ያላለቀለት በሬ ከሞተ በኋላ ቆዳው ነጋሪት ይሆናል፣” አይነት እየሆነ ነው፡፡-”
              
      እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...እንግዲህ እኛ ሀገር ከትምህርት ቤት ሲወጡ ወዲያው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ሥራ የማግኛ መስፈርቶች በ‘አይነት’ በዙ መሰለኝ፡፡ ይቺን የፈረንጅ ቀልድ ስሙኝማ...ሁለት እናቶች ረጅም ጊዜ ተጠፋፍተው ከከረሙ በኋላ አንድ ቀን የሆነ ቦታ ይገናኛሉ፡፡ እናም...ስለ ቤተሰብ መነጋገር ይጀምራሉ፡፡
“እኔ የምለው...ትልቀኛው ልጅሽ ጆርጅ እንዴት ነው?” ስትል አንደኛዋ ትጠይቃለች፡፡
“ምንም አይል፣ ደህና ነው፡፡ ገጣሚ ነው። በቅርቡ በሥነጽሁፍ ከዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡”
“በጣም ደስ ይላል፡፡ ሴቷ ሜሪስ?”
“እሷም እንደ ጆርጅ ጎበዝ ነች፡፡ በዘመናዊ ሥነ ጥበብ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡”
“በጣም ዕድለኛ ነሽ፡፡ ጎበዝ፣ ጎበዝ ልጆች ናቸው ያሉሽ፡፡ የመጨረሻው ፍሬዲስ እንዴት ነው?”
“ፍሬዲማ ያው የምታውቂው ፍሬዲ ነው። ኮሌጅ አልገባም፡፡ አናጢነት ሥራ ውስጥ ነው የገባው፡፡ ልጄ፣ እሱ ባይኖር ኖሮማ ይሄኔ ሁላችንም በረሀብ አልቀን ነበር፣” አለችና አረፈችው፡፡
ብዙ ነገር እየተለዋወጠ ነው...በአብዛኛው ደስ በማይል ሁኔታ! ባህሪያችንም... አለ አይደል... ብዙዎቻችን የነፋሱን አቅጣጫ እያየን መለዋወጥን የህይወት መርሆ አይነት ነገር እያደረግነው ይመስላል፡፡ እኔ የምለው...የአንዳንዶቻችን እኮ ‘ግልብጥ፣ ግልብጥብጥ’ የማለት ቅልጥፍና፣ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች እንዲቀኑብን የሚያደርግ ነው፡፡
 “እኔ አይደለሁ እንዴ በወርም፣ በሁለት ወርም ጥሬ ስጋ የምጋብዘው! በየቦታው እየዞረ አይደማውም፣ ቋጣሪ ነው ምናምን እያለ ስሜን አያጠፋው መሰለሽ! እኔ ነኝ ጥፋተኛው፤ እሱን ጥሬ ሥጋ መጋበዜ!” ምናምን ይባልበት የነበረው ዘመን ቀርቶ የለ! (ዘግይቶ የደረሰን ሰበር ዜና የሚባል ነገር አለ እንዴ!) ነገርዬው ተለውጦ፣ ዘመን ተለውጦ፣ ይኸው ሰው ቀደም ሲል ስለተቸው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው.... “ለእኛ ለእኛ ሹሮ እንኩዋ የፋይቭ ስታር ሆቴል ውድ ምግብ በሆነችብን ዘመን፣ አጅሬውማ በሳምንት አምስት ቀን ጥሬ ሥጋውን ሲነጭ ነው የሚውለው!”
“ትገናኛላችሁ እንዴ?”
“ኸረ እሱ ሥራም አላጣ! አሁንማ አይቶኝ እንዳላየኝ ጀርባውን ማዞር ጀምሯል፡፡”
ምን ይደረግ ተጋባዥ የነበረ ሰው ድንገት ዘመኖች በሚፈጥሩት መስፈርቶች መሰረት፣ ከብርሀን እጥፍ በሆነ ፍጥነት አጭርም ትሁን ረዥም፣ ብቻ የሆነች ቆጥ ቢጤ ላይ ጉብ ሲል፣ ወዳጅና ‘ጥሬ ሥጋ በጋበዘ’ ላይ ጀርባ ማዞሩን ለመድነው መሰለኝ፡፡ እናማ... “ወይኔ ያኔ እሱን ጥሬ ሥጋ የጋበዝኩባት ገንዘቤ ቆጨችኝ፣” አይነት ነገር ቅሽምና ነው፡፡
ለነገሩ ዘንድሮ ኑሮ እያደረገን እንዳለው ከሆነ፣ አይደለም ያኔ እሱን ጥሬ የጋበዝንባት ፍራንክ፣ እኛ በአንድ ጮርናቄ መዋል ስንችል ለሦስት ጮርናቄ  በማውጣታችን ምን ልንል እንችላለን መሰላችሁ... “እንደዛ ባልቀብጥ ኖሮ እኮ ይሄኔ የራሴ ቪትዝ ይኖረኝ ነበር!” ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ... በፎርቲ ምናምን እድሜው ዘጠነኛ ክፍል የተነጠቀችውን ገርልፍሬንድ እያሰበ የሚብሰለሰል አይነት... አለ አይደል.. “እሷ ከእኔ መለየት ፈልጋ ሳይሆን የሰፈር ልጆች ግሩፑን ሰብስቦ አስፈራርቷት ነው፣” አይነት ነገር፡፡ በህግ አምላክ! እሱዬው እሷን ከመጠቅለሉ በፊት አይደል እንዴ “አንተ ዘላለምህን ፉል፣ ፉል፣ ፉል ብቻ እየጋበዝከኝ አንደኛውን የባቄላ በርሜል ሳታደርገኝ በፊት ብንለያይ ይሻላል፣” ብላህ ቻዎ፣ ቻዎ የተባባላችሁት! ምንም እንኳን ያልታየውና ያልተሰማው በመሀላ የሚመሰከርበት ዘመን ላይ ብንሆንም፣ እኛ ግን ያየነው እንመሰክራለን፡፡ አሀ...በእሷ የተነሳ አይደል እንዴ እኛን ሁሉ ፉል መጋበዝ ያቆምከው! ቂ...ቂ...ቂ... እናማ እኛ ያኔ ጉራ ቢጤ እንደነሰንሰነው ‘እነኛም’ ጉራ ቢነሰንሱ “የፕሮሰስ ጉዳይ ነው፣” የሚል ‘ስማቸውን የማያስታውሳቸው ፈላስፎችን’ ጥቅስ መናገር የሚወድ ሊኖር ይችላል፡፡
እኔ የምለው፣ የጉራ ነገር ካነሳን አይቀር  ይቺን ስሙኝማ... ሦስት የተለያዩ እምነቶች አገልጋዮች በሆነ አጋጣሚ ይገናኙና ጉራ ቢጤ መለዋወጥ ይጀምራሉ፡፡ አንደኛው አገልጋይ... “ከእኔ ቅድመ አያቶች አንዱ ከመቶ በላይ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ደርሷል፣” ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “ከቅድመ አያቶቼ አንዱ ነው መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመው፣” ይላል፡፡ ይህን ጊዜ  ሦስተኛው ሰው የሁለቱን ካዳመጠ በኋላ ደረቱን ነፍቶ ምን ቢል ጥሩ ነው... “አስርቱ ትእዛዛትን የጻፈው ከቅድመ አያቶቼ አንዱ ነው፣” አለና አረፈው፡፡ እንግዲህ መቻል ነው፡፡
ስሙኝማ...ቀልድ ድሮ ቀረ ነው ወይስ ቀልድ የመዋቅር ለውጥ ተካሄደበት ነው የሚባለው! (ቂ...ቂ...ቂ...) ለነገሩ እኮ ቀልድ በዋነኛነት የአውሪው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአድማጭና የተመልካቹ ጉዳይ ነው፡፡ እናማ...ምን ለማለት ነው፣ በቀልዱ ከሚደሰቱት ይልቅ የሚከፉ በበዙ ቁጥር ቀልድ መሆኑ ያበቃል። በድሮ ቃና ድሮ የሚስቁባቸውን አይነት ቀልዶች አሁን ለመቀለድ ስለሞከሩ፣ ቅርባቸው ከነበሩ ወዳጆቻቸው ጋር ስለተቆራረጡ ሰዎች ሰምተናል፡፡
ቀልድና ፌዙ ይቅርና አሁን ግራ የገባን እኮ እንደ ልብ የመጣልንን ነገር ቀኝና ግራ ሳናይ የምንናገር ስንበዛ መንገዱ ተጣበበ መሰለኝ፣ እየዘለልን ከገደሉ ጫፍ “ፍላይ ሮቢን ፍላይ፣” አይነት ነገር የምንል እየበዛን ነው፡፡ ከማህበረሰብ ጋር ያሉትን ክሮች ሁሉ በጥሰን “ሰው ምን ይላል?”፣ “የምንናገረው ነገር ማንን ያስቀይም፣ የማንን መብት ይነካ ይሆን!”፣ “የምጽፈው ነገር በሰዎች መካከል አላስፈላጊ ቁርሾ ፈጥሮ ወደ አጉል ነገር ይመራ ይሆን!” ብሎ ነገር ቀረ እኮ፡፡ 
ብዙዎቻችን ብዕር በጨበጥን፣ ማይክ እጃችን በገባ፣ የቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ለፊታችን በተደቀነ ቁጥር በ“ማን አለኝ ከልካይ”፣ የፈለግነውን እንድንል ገደብ የሌለው ፈቃድ ያለን በሚመስል መንገድ፣ በርካታ አጓጉል ነገሮች እየሰማን፣ እያየንም ነው፡፡ ደግሞ እኮ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ስብስቦች ብቻ ሳይሆን ሚሊዮኖችን የሚነኩ ደስ የማይሉና ደስ ካለማለት የዘለሉም የፊት ለፊትና የጎንዮሽ ነገሮች እየሰማን ነው፡፡ ነገራችን ሁሉ “መከራው ያላለቀለት በሬ ከሞተ በኋላ ቆዳው ነጋሪት ይሆናል፣” አይነት እየሆነ ነው፡፡
ግርም እኮ የሚል ነው... ገሚሱ ቅልጥ ያለ ታሪክ ተንታኝ ይሆንና “ለምሳሌ የዘጠነኛው ክፍለ ዘመኗን አሜሪካ ብናይ...” አይነት ትንታኔ ሊሰጠን ይሞክራል፡፡ (መቼ ነበር ተገኘች የተባለው?) ገሚሱ ያኔ በርሊን ቁጭ ብለው አይተዋት የማያውቋትን አፍሪካ ካርታ ላይ እያሰመሩ “ከዚህ ወዲህ የእኛ፣ ከዚህ ወዲያ የእናንተ፣” እንደተባባሉት፣ እሱም መስመር እያሰመረ “ከዚህ ወዲህ የእናንተ፣ ከዚህ ወዲያ የእነአከሌ...” እያለ ሊያከፋፍለን የሚሞክር ይመስላል፡፡ 
በነገራችን ላይ የሆነ ነገር ጥፋት የሚሆነው እንደፈጸመው ሰው ማንነት ነው እንዴ! ግራ ስለገባን ነው፡፡ ጠያቂና ተጠያቂ ሊኖር ግድ ቢልም፣ ዋናው ጥያቄ፣ የተጠያቂና የጠያቂ መስፈርት ምንድነው፡፡ (“አምስት ኪሎ ስኳር ከሆነ ቦታ ገዝቼ እንደገና ሳስመዝነው አራት ተኩል ብቻ ሆነ፣” ያልሽው ፤ በሚዛንና በመስፈርት ላይ ያለሽ ኮንፊደንስ እንደ አቧራ ብን አለ እንዴ! አይ...እንደ አቧራ ብን እያሉ የሚገኙ ነገሮች ስለበዙብን ነው፡፡
‘ሠሪው’ ሌላ፣ ‘በዪው’ ሌላ የሆነባት ዓለም! ይቺን የሆነ ስፍራ ላይ የሰፈረች ጸሁፍ እዩልኝማ ...ማንኛውም ፕሮጀክት ስድስት ደረጃዎች አሉት፤ ይላል ጽሁፉ፡፡
አንደኛ፡- ከፍተኛ ፍላጎት፡፡
ሁለተኛ፡- ነገሮች እንዳሰቡት ያለመሄድ፡፡
ሦስተኛ፡- ድንጋጤ፡፡
አራተኛ፡- ጥፋተኞችን ፍለጋ፡፡
አምስተኛ፡- ንጹሀንን መቅጣት፡፡
ስድስተኛ፡- በፕሮጀክቱ ተሳትፎ ለሌላቸው ምስጋናና ሽልማት፡፡
‘ሠሪው’ ሌላ፣ ‘በዪው’ ሌላ የሆነባት ዓለም!
ይቺን ደግሞ እዩልኝማ...እሷዬዋ አዲስ መሥሪያ ቤት ለመቀጠር ታመለክትና ለቃለ መጠይቅ ትጠራለች፡፡ ቃለ መጠይቅ በሚደረግላት ጊዜም የራሷን ጥያቄ ትጠይቃለች።
“ኩባንያው የህክምና ኢንሹራንሴን ይከፍልልኛል?”
“ኩባንያችን የህክምና ኢንሹራንሱን የሚከፍለው ከሠራተኛው ደሞዝ ላይ ቆርጦ ነው፡፡”
“ቀድሞ በነበርኩበት መሥሪያ ቤት እኮ ድርጅቱ ራሱ ነበር የህክምና ኢንሹራንሱን የሚከፍለው፡፡”
“የሕይወት ኢንሹራንስም ይከፍልላችሁ ነበር?”
“አዎ፣ ኩባንያው ነበር የሚከፍልልን፡፡”
“የጥርስ ህክምና ወጪያችሁንስ ይችሉላችሁ ነበር?”
“አዎ፣” አለች፡፡ “ምን እሱ ብቻ፣ ገደብ የሌለው የህክምና ፈቃድም ይሰጠን ነበር፡፡ የሙሉ አንድ ወር ፈቃድ አለን፡፡ በገና በዓል ደግሞ በየዓመቱ ወፈር ያለ ቦነስ ይሰጠናል፡፡ ለምሳም ሁለት ሰዓት እረፍት ነበረን፤ በተጨማሪ ለልጆች እንክብካቤ ሙሉ ወጪውን ይሸፍኑልን ነበር፡፡”
“ታዲያ እንደዚህ ከሆነ ለምንድነው ያኛውን መሥሪያ ቤት የለቀቅሽው?”
“ድርጅቱ ከስሮ ስለተዘጋ፣” አለችና አረፈችው፡፡
እኔ የምለው፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ይሄ ድርጅት ከስሮ የተከረቸመው ለሠራተኞች የሚሰጣቸው ‘ጥቅማ ጥቅሞች’ በዝተውበት ይሆን እንዴ! አይ...እንደው ለጠቅላላ እውቀት ያህል ነው፡፡
እናማ...ያው የከሰረ ድርጅት መዘጋቱ ግድ ነው፡፡ ታዲያላችሁ...እዚቹ የእኛዋ መኖሪያ ውስጥ በቦተሊካው ዘርፍ  የከሰሩና የከሳሰሩ ቦተሊከኞችና፣ የቦተሊካ ስብስቦች ግን “ወይ ፍንክች!” ነው፡፡ የምር እኮ ‘ዩኒክ’ ነን!
‘ሠሪው’ ሌላ፣ ‘በዪው’ ሌላ የሆነባት ዓለም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 734 times