Monday, 27 March 2023 00:00

ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈው ጮቄ ተራራ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ወጣቱ ዕውቀትና ጊዜ ገንዘብ መሆናቸውን አይረዳም

     ወጣት አብይ ዓለም ከጥቂት አመታት በፊት ስለ ኢኮሎጅ ምስረታና ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል በቱሪዝም ተጠቃሚ ስለማድረግ ሲናገር፣ ብዙዎች ጤንነቱን ተጠራጥረው ነበር፡፡ “አውሮፓ ተንደላቅቆ መኖር እየቻለ ገጠር፤ ለገጠር ለመኳተን የሚቆዝመውስ በምን ምክንያት ነው?” በማለት እርሱ ወርቅ የሚለውን ሃሳቡን ያጣጥሉበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ የዛሬ አምስት ዓመት ኢኮሎጁን በመገንባት፣ ህልሙን እውን አድርጓል፡፡ አብይ ዓለም የ”ሙሉ ኢኮሎጅ” ሃሳብ አፍላቂ፣ መሥራች ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆን በሰዎች ዘንድ  የመሰረተው ተቋም፤ ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት አግኝቷል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከወጣት አቢይ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለ ኢኮሎጁ አመሰራረት፣ በምስረታው ወቅት ስላጋጠመው ውጣ ውረድ፣ ሎጁ ስላገኘው ዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት እንዲሁም በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አውግተዋል። እንድታነቡት ተጋብዛችኋል።

          “ሙሉ ኢኮሎጅ”ን ለመመስረት ስላነሳሳህ ዋነኛ ምክንያት ብታጫውተኝ…?
ሙሉ የሚለው የቱሪዝም ፍልስፍና በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በተለይ በኢትዮጵያ ቱሪዝም፣ በአብዛኛው የታችኛውን ማለትም የገጠሩን ማህበረሰብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቱሪዝሙን ተጠቅሞ ገበሬዎችንና ወጣቱን አስተባብሮ የአካባቢውን ተፈጥሮ፣ የተራቆቱ ቦታዎች እንዲለሙ በማድረግ የቱሪዝሙ አካል ካደረግን በኋላ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከቱሪዝም ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድልን ለመፍጠር በማሰብ ነው የመሰረትኩት። ማህበረሰቡ በቱሪዝም ተጠቃሚ ሲሆን ባህሉን፣ ተፈጥሮውን በመጠበቅ ለቱሪዝሙ የሚሆን ግብዓቶችን እያመረተ፣ አገልግሎት ሰጥቶ ገቢ ያገኛል፡፡ ያኔ ህይወቱ ይቀየራል ማለት ነው። በአጠቃላይ ሃሳቡ ቱሪዝምን በመጠቀም ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግና ህይወቱን መቀየር ብሎም ዘላቂ ልማት ማምጣትና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ  ነው።
ግን  እንዴት አሰብከው? ያንን አካባቢስ እንዴት መረጥከው? የትውልድ አካባቢህ ነው ወይስ?
ተወልጄ 8 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ በዚሁ አካባቢ ነው ያደግኩት፡፡ ወንድሞቼ ለተሻለ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ካመጡኝ በኋላ ወደ አካባቢው ሳልመለስ ለረጅም ጊዜ ቆየሁኝ። ትምህርቴ ላይ ትኩረት አድርጌ ነበር ለረጅም ጊዜ የቆየሁት፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የምማርበት ት/ቤት ከውጭ ብዙ እንግዶች ይመጡ ስለነበር ከእነርሱ ጋር መፃፃፍ ጀመርኩኝ፡፡ በተደጋጋሚ ከተፃፃፍኩ በኋላ አካባቢዬን ማሳየት ፈለግኩኝና ወደ ሀገሬ ይዣቸው ሄድኩኝ፡፡
የት ማለት ነው?
ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ ጣመ ጊዮርጊስ የሚባል ቀበሌ አለ፡፡ ከደብረ ማርቆስ  80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ እንግዶቹን ይዤ ስሄድ መብራትም ሆነ ሌሎችም መሰረተ ልማቶችም አልነበሩም። እኔ ካካባቢው ስወጣ ከነበረው ሁኔታ ብዙም የተለየ ነገር አልነበረም። እንዲያውም ደኑ ጠፍቶ፣ ሜዳው ተሸርሽሮና ተራቁቶ ይበልጥ ድህነት ተንሰራፍቶ ነው ያገኘሁት፡፡ ይህንን ሳይ በጣም ደነገጥኩኝ። ቁጭ ብዬ ማሰብና ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ”ይህን የተራቆተ አካባቢ እኔ ካላለማሁትና ማህበረሰቡን ካላነቃሁት፣ ይህ ህዝብ ሊሰደድና የባሰ ድህነት ሊመጣ ይችላል” የሚል ሃሳብ ያዝኩኝና ወደ ሃገሬ ተመልሼ መስራት እንዳለብኝ ወስኜ መንቀሳቀስ ጀመርኩኝ፡፡ ይህንን ሃሳብ ይዤ ከጎብኝዎች ጋር መመካከር ሌላው ቀርቶ ሌላ አገር ሄጄ የጎበኘሁትን ነገር እንዴት ሀገሬ ላይ ልተግብረው? ያንን ዕውቀት እንዴት አድርጌ ወደዚህ ላምጣው በሚል በትንሹ ለ15 ዓመት ይህንን ሃሳብ ሳብላላ፣ ሳወጣና ሳወርድ ነበር የቆየሁት፡፡ ከዚያ በኋላ ምን አደረግን መሰለሽ? የአሁኗ ባለቤቴ ያን ጊዜ ጓደኛዬ ነበረችና ሃሳቤን ሳካፍላት፣ በጣም ተደንቃ “ለምን ሄደን አናየውም” አለችኝ፤ ወሰድኳት። አየችውና “ይህንን ነገር እውን ማድረግ አለብን” የሚል ውሳኔ ላይ ደረስን። ይህ የሆነው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበሩትን ሁለቱን ዓመታት በወረቀት ደረጃ የቢሮና የመንግስት ሂደቶችን ስንሰራ ቆየን፡፡ መሬቱን ተረክበን ከማህበረሰቡ ጋር ተግባብተንና ተቀናጅተን ሃሳቡን በተግባር መሬት ላይ አውርደን መስራት ከጀመርን ግን አምስት አመት ሞልቶናል፡፡
አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተለይ ስልጣኔ እምብዛም ባልዘለቀበት  አካባቢ አዲስ ሃሳብ ይዞ መቅረብ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት ይታወቃል። አንተም የገጠመህ ተግዳሮት እንደነበር ሰምቻለሁ። እስኪ ስለሱ ንገረኝ…?
መጀመሪያ የጎዳኝ ነገር ምን መሰለሽ? ብዙ ጥሩ ምላሽ ጠበቅኩኝ፡፡ ወደ ጀርመን ሄጄ መኖር እየቻልኩ፣ አዲስ አበባም መኖር እየቻልኩኝ እሱን ነገር ትቼ ወደ ታች ስመለስ ብዙ ነገር ጠብቄ ነበር፡፡ አየሽ በእኛ አገር አስተሳሰብ ስኬት የሚባለው ከገጠር ወጥተሽ ወደ ተሻለ ከተማ ስትሄጂ እንጂ ወደ ገጠር ስትመለሺ አይደለም፡፡ እኔ ግን ከትልልቅ ቦታ ወደ ታች ስመለስ ሁሉም ምን እንደፈለኩና ምን ዓላማ እንዳለኝ ይረዳል ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ስለዚህ የጠበቅኩት ይህንን ሃሳብ ሳበስራቸው ሁሉም ይደሰታሉ ብዬ ነበር። እናም “መሬት ስጡኝ አካባቢውን የሚያሳድግ ጎብኝ አመጣለሁ፡፡ ጎብኚ ሲመጣ ማረፊያ ያፈልጋል፣ ማረፊያውን የምትሰሩት እናንተ ናችሁ፡፡ እኔ ለምትሰሩበት የሚያስፍልገውንና የምችለውን በጀት አቀርባለሁ። ከዚያ አገር ነው የምናለማው” ብዬ እቅዴንና ህልሜን በግልፅ አስረዳኋቸው፡፡ ሁሉም ሆ ብሎ ይቀበለኛል ብዬ ነበር፡፡ እርግጥ ህዝቡ ተቀብሎኛል። ከዚያ በኋላ ወደ ቢሮዎች መግባት ስጀምር “ነገ ተመለስ፣ ይህን አሟላ” እያሉ በእጅጉ አመላለሱኝ። ገጠር ነው፣ ትራንስፖርት የለም፣ ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው ስትሄጂ ምናልባትም 200 ኪ.ሜ ልትጓዢ ትችያለሽ። ብቻ ብዙ እንግልት ገጠመኝ። ልንሰራበት የነበረው ገንዘብ በቢሮክራሲና ከቢሮ ቢሮ በመንከራተት አለቀ። እሱ ብቻም ሳይሆን እኔም ነገሩ ስላበሳጨኝ “አገር ላልማ ባልኩ ለምን እንደዚህ ታደርጉኛላችሁ?” ብዬ ስጠይቅ፣ አንዳንድ ቅን ያልሆኑ ሰዎች ለማህበረሰቡ “እነዚህ ሰዎች እዚህ እንስራ የሚሉት መሬት ውስጥ ያለውን ወርቅና ሌላ ማዕድን አውጥተው ለመውሰድ እንጂ እውነት ህብረተሰቡን ለመጥቀም አይደለም” የሚል አሉባልታ በማሰራጨታቸው፣ መጀመሪያ ተቀብሎኝ የነበረው ማህበረሰብ ሃሳቡን ቀይሮ እምቢ አለኝ።
ሌሎች አንዳንድ ቅኖች ደግሞ አገርና ወገን ለመጥቀም ካልሆነ፣ እዚህ ገጠር ውስጥ የሚያንከራትታቸው ነገር የለም። በውጪ ሀገርም በአዲስ አበባም ተመቻችቶ  መኖር ይችላል ብለው ስላሰቡ፤ “ይህንን ፕሮጀክት እኛ እንስጥህ” ብለው ወሰዱኝ። “ሙሉ ኢኮሎጂ” የተገነባው መጀመሪያ ያሰብኩበት ሳይሆን ሌላ ቦታ ነው። ከማውቀው ማህበረሰብ ተገፍቼ የማላውቀው ማህበረሰብ ተቀበለኝ። በዋናነት ይህንን ሎጅ እነሱ ናቸው እያስተዳደሩት እየተንከባከቡት ያለው።
መጀመሪያ የት ነበር ያሰብከው? አሁንስ የመሰረትከው የት ነው?
በእርግጥ የሁለት ኪ.ሜ ልዩነት ላይ ነው የተመሰረተው። ብዙ አይራራቅም። እኔ ከዚያ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ያየሁት ደን ነበር፤ እዚያ መገንባት ነበር የፈለግኩት። አሁን ግን ሌላ ቦታ ነው።
እስከማወቀው ወደ ደጋ ዳሞት ለመሄድ ከደንባጫ ባልሳሳት 45 ወይም 50 ኪ.ሜ ወደ ሰሜን የሚገነጠል ኮረኮንች መንገድ አስታውሳለሁ። እዚያ አካባቢ ነው “ሙሉ ኢኮሎጅ” ያለው?
ልክ ነሽ፤ ከደንበጫ ወደ ሰሜን 51 ኪ.ሜ ተጉዘሽ፣ የደጋ ዳሞት ወረዳ ዋና ከተማን ፈረስ ቤት ከተማን ታገኛለሽ። የእኛ ሎጅ ያለው ፈረስ ቤት ሳይደርስ ከደንበጫ 23 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ጣመ ጊዮርጊስ የሚባል ቀበሌ ውስጥ ነው። የሚገርምሽ ትግሉ ከዚያም በኋላ ቀጥሎ ነበረ። ይህ የሆነበት ምክንያት አንደኛ ካለማወቅ ነው። ሁለተኛ፤ እኔ ቀጥታ መጥቼ ከማህበረሰቡ ጋር ተገናኘሁ። ማሟላት ያለብኝን ዶክሜንት አሟላሁኝ። በቃ ወደ ማህበረሰቡ መጣሁ። ከላይ ትዕዛዝ እያሰጠሁ አልመጣሁም። እኔ ከገበሬው ጋር ድንኳን ጥዬ እየዋልኩ እያደርኩ፣ ሀሳቤን ማስረዳት አላማዬን በአግባቡ ማሳወቁ ላይ ነው ያተኮርኩት። ምክንያቱም “የመጀመሪያው ማህበረሰብ፤ እምቢ ያለኝ አላማና ህልሜን በአግባቡ ስላላስረዳሁት ነው” የሚል ቁጭት ነበረኝ። እናም አዲስ አበባ ያለውን ቢዝነሴን ሁሉንም ትቼ ከገበሬው ጋር ውሎና አዳሬን አደረግኩ። በዚህም አርሶ አደሩን እያስተማርኩ የዚህን ሀሳብ ጥቅም፣ ጉዳቱን ነገ ሊመጣ የሚችለውን ችግር እያብራራሁ መስራት ጀመርን። መስራት ስንጀምር እነሱም እየገባቸው እየተረዱት መጡ። አንደኛ ባህላቸውን መመለስ ነው። ሁለተኛ እራሳቸው ናቸው የሚሰሩት፣ እንጨት ያቀርባሉ፣ እንጨት ለሚያቀርቡበትም ለሚሰሩበትም ይከፈላቸዋል። ይሄ በጣም አስደሰታቸው፤ ተጠቃሚም ሆኑ። ለምሳሌ እዚህ አካባቢ ቀርቀሃ ብዙ ጥቅም ላይ አያውሉም ነበር። ለዚህ ስራ ጥቅም ላይ ዋለ፤ በደንብ ይሸጥላቸው ጀመር።
በሌላ በኩል፤ በተለይ ክረምት ላይ ስንሰራ ተማሪዎች ትምህርት ቤታቸው ዝግ ስለሆነ ሁሉም እንዲሳተፉና የእኔነት ስሜት እንዲሰማቸው አደረግናቸው። በዚሁ እግረ-መንገዳችንን ባህላቸውና አገር በቀል እውቀታቸው ለዓለም እንደሚተርፍ ግንዛቤ እንዲያገኙ አደረግናቸው። ምክንያቱም እኛ አገር ሊቀረፍ የሚገባው አንድ አስተሳሰብ አለ። ይህ ምን መሰለሽ…? ከውጪ የመጣን ስልጣኔ ሁሉም ልክ ነው፤ ደግሞም ይበልጣል ብሎ የማመን፣ የራሳችንን እንደማይጠቅምና ኋላቀር እንደሆነ አድርጎ ዝቅ ዝቅ የማድረግ ነገር ነው። በዚሁ አጋጣሚ ይህንን አስተሳሰብ የመለወጥ ስራም ሰራንበት ማለት ነው። በነገራችን ላይ በዚህ ስራ ላይ ብዙ የውጪ ሀገር በጎ ፈቃደኞች ፈረንጆችም ተሳትፈውበታል። ይህ የፈረንጆቹ መሳተፍ ደግሞ የአካባቢው ህብረተሰብ ስለቱሪዝም አዲስ እውቀትና አስተሳሰብ እንዲያገኝ እድል ፈጠረ። ሁለተኛ ያንን አካባቢ ለዓለም ማህበረሰብ ማስተዋወቅ ቻልን፤ በህብረተሰቡም ላይ በዘርፉ ብዙ ንቃቶችን ጨመርን ማለት ነው። ይህን አድርገን እንግዳ መቀበያ ቤቶችን ሰርተን ካጠናቀቅን በኋላ፣ በቀጥታ እንግዳ መቀበሉን ገታ አድርገን ወደ ማህበረሰቡ መንደር ገብተን ስራ መሥራት ጀመርን።
ምን ዓይነት ሥራ?
በጣም ጥሩ!  ቤቱን ሰርቶ እንግዳ መቀበል ብቻውን ትርጉም የለውም፡ አየሽ እንግዶች መጥተው የሚያዩት የሚጎበኙት፣ የሚመገቡት፣ በማስታወሻነት የሚገዙት… ይህ ሁሉ ነገር ያስፈልጋል። ይህን ሲያደርግ የቱሪስቱ ቆይታ ጊዜ ይረዝማል። ቱሪስቱ በቆየ ቁጥር ገንዘብ ያወጣል። በዚህ አካባቢውም ማህበረሰቡም ይጠቀማል። ቱሪስቱ በሚያወጣው ገንዘብ ማህበረሰቡን መጥቀም ብቻ አይደለም አላማው። ቱሪስቱ እየቆየ ሲሄድ ነው የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግ፣ ስነ-ልቦና… ሁሉን የሚረዳው። መቆየታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። ያ የቆየ ቱሪስት ፊልም የመስራት፣ መጽሐፍ የመጻፍና ስለዚያ አካባቢ ብዙ መንገር የሚፈልገው ነገር ይኖራል። ስለዚህ የቆይታ ጊዜያቸው መራዘም አለበት። እኛ ደግሞ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸውን ነገር መፍጠር አለብን ማለት ነው።
ስለዚህ የጠፉ ባህሎችን መመለስ፣ የሚጎበኝ ካለ እሱን ማጎልበት፣ ከሌለ መፍጠር አለብን። ለምሳሌ በየወሩ የሚደረጉ ማህበር ቤቶችን ማጠናከር፣ እያንዳንዱን የገበሬ ቤት ንጽህና ማሻሻል፣ የምግብ አይነቶችን ማብዛት፣ ጓሮውን እንዲለማ ማድረግ። ለምሳሌ እኛ በይፋ ጠይቀን የተረከብነው 5 ሄክታር መሬት ነው። ማህበረሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ያጠረው ግን 10 ሄክታር ነው። ስለዚህ ያንን በመንከባከብ ደኑ እንዲመለስ አድርገናል። ህብረተሰቡ ፍየሎቹን እየሸጠ ወደ ሰጋር ፈረስ ግዢ ገባ። እሱ ብቻ አይደለም። ትምህርት ጨርሰው ተቀመጡ ወይም ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ማለፊያ ነጥብ ያልመጣላቸው ልጆች አስጎብኚ እንዲሆኑ ስለፈለግን፣አካባቢው ላይ ምግብ እየሰሩ ማቅረብ፣ ማስጎብኘት እንዲችሉ በቋንቋም እንዲጎለብቱ አደረግን።
በሌላ በኩል፤ ማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ችግሮች በማየት ለምሳሌ በሶላር መብራት ማመንጨት ወፍጮ፣ የውሃ ፓምፕ፣ ጭስ አልባ ምድጃ አሟላን። እንዲሁም የጓሮ አትክልት እንዲለማ፣ ንቦች እንዲረቡና ማር እንዲመረት፤ የዶሮ እርባታና እንቁላል በብዛት እንዲኖር በማድረግ ቱሪስቶች ሲመጡ የሚያገኙትንና የሚያዩትን አበዛን፤ አበረከትን።
ከዚህ በተጨማሪ የቋንቋ ማእከል፣ ፀጉር ቤት፣ በሶላር ቴሌቪዥን እንዲኖር አደረግን። አሁን ደግሞ መዋዕለ ህፃናት ከፍተናል። በተለይ በኮሮና ወቅት በመዋዕለ ህፃናቱ ልጆቹ ዳቦ በማር እየተመገቡ እንዲማሩ ድጋፍ ያደረግን ሲሆን አሁን እዚህ የሚመጣ እንግዳ እውቀቱንም ሁሉ እያካፈለ ይገኛል።
ኢኮሎጁ ሲገነባ ኢንቨስትመንቱ ምን ያህል ነበር። በዚህ ተቋም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምን ያህል ሰው ተጠቃሚ ሆኗል ማለትስ ይቻላል?
ይሄ ፕሮጀክት ከጅምሩም ችግር ፈቺና አስተማሪ እንዲሆን ነው የፈለግሁት። እናም እያንዳንዱን ነገር የሰራንበት መንገድ ሀሳቡ ረቂቅ ነው። ሆኖም በቀላሉ ለሰው የሚገባ መሆን እንዳለበትም አምናለሁ። ምክንያቱም እኔ ለወጣቱ ማስተማር የፈለግሁት ነገር እኔ ወጣት ነኝ፣ ጊዜ አለኝ፣ እውቀት አለኝ። እነዚህን ያሉኝን ነገሮች አቀናጅቼ ከሰራሁ ማልማት፣ መለወጥና ማደግ እችላለሁ የሚለውን ነው። እድገት ሲባል ባህር ማዶ ሄዶ ሰርቶ መምጣት ብቻ አይደለም፤ ወጣቱ አገሩ ላይ ሰርቶ ማደግ አለበት ብዬ አምናለሁ። ኢንቨስትመንትን በተመለከተ እዚህ አገር ላይ እኔ ያስተዋልኩት መጀመሪያ እውቀትና ሃሳብ አለሽ ሳይሆን ምን ያህል ብር አለሽ የሚለው እንደሚቀድም ነው። ስለዚህ በትንሽ ብር የሚሰራ ፕሮጀክት እንዲሆን ነው ያደረግኩት። ለምን ብትይኝ፤ “አቢይ ብር ስላለው ስራው ሳይሆን፤ አቢይ ሀሳብ እውቀት ጊዜ ስላለው ስራው” እንዲባል ነው የፈለግኩት። የሆነ ሆኖ ስራውን በ560 ሺህ ብር በጀት ነው የጀመርነው። 60 ሺህ ብሩን በቀጥታ ከራሴ አድርጌ ሌላውን በብድር ወስጄ ነው ስራውን የጀመርኩት። በ60 ሺህ ብር ስንጀምር ቢያንስ ድንኳን መጣያ ሻወር ቤትና መጸዳጃ ቤት ከሰራን፣ እንግዳው ይመጣል። ከዚያ ከድንኳን ወደ ሎጅ እያደገ ይሄዳል የሚል ሃሳብ ይዘን ነው የተጓዝነው። ከሎጅ ወደ ሪዞርት የሚያድግበትም ሁኔታ ይኖራል።
ወጣቱን “ለምን ስራ አትሰራም” ስትይው፤ “ገንዘብ የለኝም” ይላል። እውቀትና ጊዜ ገንዘብ መሆናቸውን አይረዳም። መንግሥትም ቢሆን ቅድሚያ ለገንዘብ መስጠት የለበትም። እኛ ይህን አስተሳሰብ መፍጠር ችለናል። እየሰራንም እያስተማርንም ነው ያለነው። ምን ያህል ሰው ተጠቃሚ ሆኗል ላልሽኝ ደግሞ፣ እኛ መጀመሪያ 5 ሄክታር መሬት ሲከለል የአርሶ አደሩ የግጦሽ ቦታ ስለነበር ይጎዳሉ፤ ምንም ጥያቄ የለውም። ስለዚህ እነዚህ የመሬቱ ባለቤቶች ቀጥታ ከቱሪዝሙ እንዲተቀሙ ነው ያደረግሁት። እነዚህ 60 አባወራዎች ናቸው፤ በስራቸው 300 ያህል ቤተሰብ አላቸው። ከዚህ ፕሮጀክት ቀጥታ እንዲጠቀሙና ማህበር አቋቁመው እንዲያስተዳድሩ ብሎም በየትኛውም የቱሪዝም እንቅስቃሴ ገቢ እንዲያገኙ አድርጌያለሁ። ሎጁ ደግሞ እንግዳ መጥቶ የመኝታ የምግብ ተጠቅሞ ከሚያገኘው ገቢ የእነዚህ አባወራዎች ልጆች በጥበቃ፣ በጽዳት፣ በምግብ አብሳይነት ተቀጥረው ይሰራሉ። ሎጁንም ለማስቀጠል በዚህ መልኩ እየተሰራ ነው። ከዚህ ተርፎ የሚገኝ ገንዘብ ካለ ያንን ትርፍ ወደ ት/ቤት፣ ወደ ክሊኒክ ግንባታ ነው የምናውለው። ትርፉ እዚያው ለማህበረሰቡ ጥቅም ነው የሚውለው።
ስራችን ነግዶ ማትረፍን ያለመ ሳይሆን ሶሻል ቢዝነስ ሆኖ ማህበረሰቡን የሚያለግል ነው። እስካሁን የነገርኩሽ ቀጥታ ተጠቃሚዎቹን ብቻ ነው። በተዘዋዋሪ የሚጠቀሙ ደግሞ አሉ። በተዘዋዋሪ ከ3ሺህ ህዝብ በላይ ይጠቀማል። የሶላር መብራቱን፣ የወፍጮ አገልግሎቱን፣ የእውቀትና ስልጣኔውን ስትመለከቺው ጠቀሜታው ብዙ ነው። ዋናው ነገር ይሄ ማህበረሰብ ከነቃና ከተቀየረ ሌላውም ማህበረሰብ ይቀየራል።
እስኪ ስለ ሎጁ አብራራልኝ። አሰራሩ ምን ይመስላል? ምን ያህል ማረፊያዎች አሉት?
በአሁኑ ወቅት ሎጁ ሁለት አይነት አሰራር ነው የሚጠቀመው። አንደኛ፤ ባልና ሚስት ሆነው ቢመጡ እንደልባቸው ሳይረበሹ እንዲስተናገዱ በማሰብ “ካፕል” ጎጆዎች ተሰርተዋል። እነዚህ ጎጆዎች 3 ናቸው። ከዚህ ውጪ ያሉት ትክክለኛ የገጠር ቤት ናቸው። ያ ማለት ቆጥ አላቸው፣ መደብም እንዲሁ። አንድ ጎጆ ውስጥ ከ6-8 የሚሆኑ ሰዎች ማረፍ ይችላሉ። ጎጆዎቹ በአጠቃላይ 11 ናቸው። ይህ ቁጥር ማደሪያን፣ እንግዳ መቀበያንም ሆነ ማብሰያን ያካተተ ነው። ገና  ተጨማሪም እየሰራን ነው። በአጠቃላይ ጅምር እንጂ ያለቀ ፕሮጀክት አይደለም። አሁን ባለበት ሁኔታ ከ20-30 ሰው በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላል። አቅማችንን 60 ሰው ተቀብሎ ወደማስተናገድ ለማሳደግ እየሰራን ነው። በአሁኑ ወቅት ከጎጆዎቹ በተጨማሪ የድንኳን ማረፊያ ካምፕ ሳይቶችም ስላሉን እነሱን ተጠቅመን እስከ 40 ሰው መቀበል እንችላለን። ለወደፊቱም ከ60 ሰው በላይ ለመቀበል እቅድ የለንም። ምክንያቱም ከዚያ ከበለጠ አካባቢው ከሚሸከመው በላይ ይሆንና ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። እዚህ ላይ ሰው ከማጨቅ ይህንን ፕሮጀክት በተለያዩ ቦታዎች ላይ በማስፋት ቁጥር 2፣3 እና 4 እያሉ መክፈቱን ነው ያሰብነው።
አንድ እንግዳ ስንት ቀን በሎጁ ቢያድር ነው ጥሩ እውቀት፣ ግንዛቤና መረዳት የሚያገኘው?
በትንሹ 3 ሌሊት ማሳለፍ ግድ ነው። ምክንያቱም የመጀመሪያው ቀን ተጉዘሽ ስትመጪ ይደክምሻል፤ ታርፊያለሽ። በሁለተኛው ቀን ማህበረሰቡ ምን ይመስላል እንዴት ተመሰረተ? የሚለውንና መሰል ነገሮችን እንግዶች እንዲያውቁ ገለጻ ይደረጋል። ይሄ በእንግዳውና በማህበረሰቡ መካከል ያለው መስተጋብር ጤነኛ እንዲሆንም ያደርጋል። ከሰዓት በኋላ አርሶ አደሮቹ ደናቸውን፣ ፏፏቴውን፣ አእዋፋትና ጉሬዛን ጨምሮ በርካታ የዱር እንስሳትን ያስጎበኟቸዋል። ምሽት ላይ ማህበረሰቡ ጠላውን ቆሎውን ሌላም ያለውን ይዞ ይመጣና የእሳት ዳር ጨዋታ ይቀጥላል። በሦስተኛው ቀን የመንደር ጉብኝት አለ። ጉብኝት ብቻ ሳይሆን የተግባር ስራዎችንም ይሰራል፤ መንደር ውስጥ ገብቶ። ተመልካች ብቻ ሳይሆን እየሞከረ ፕራክቲስ እያደረገ የግብርናን የገጠር ኑሮን ከባድነት ያያል፤ ያግዛል። ስለዚህ የግድ  3 አዳር በሎጁ ማሳለፍን እንደ ግዴታ አስቀምጠነዋል።
ይህ ከከተማ የራቀው መንደራችሁ “ድንቅ መንደር” በሚል በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) መመረጡንና መሸለሙን ሰምተናል እስኪ ስለሽልማቱ ትንሽ አውጋን…?
ለሽልማቱ አሸናፊነት ያበቃን ሎጁ ብቻውን አይደለም፤ ማህበረሰቡም ጭምር ነው። ሎጁን ገንብተን የተወሰነ ደረጃ ካደረስን በኋላ ማህበረሰቡ ግንባታው ጋብ ቢል እንኳን እራሱን እንዲችል በማህበር አደራጀነው- “ገነት የተፈጥሮ ሀብትና ቱሪዝም ሕብረት ስራ ማህበር” በሚል ቀደም ብዬ 60 አባወራዎች ተጠቃሚ ናቸው ያልኩሽ በዚህ ማህበር የተደራጁት ናቸው። ይህ ማህበርና እኛ ተቀናጅተን የፈጠርነው “የጮቄ ተራራ ስነ- ምህዳራዊ መንደር” የሚል አደረግነው። እኛ የጮቄ ተራራ ተፋሰስ አካል ስለሆንና ይህ ፕሮጀክት በመላው ጮቄ ይስፋፋል የሚል ሃሳብ ስላለን ጮቄንም አካትተን “ጮቄ ማውንቴንስ ኢኮቪሌጅ” በሚል ተወዳደረን። ውድድሩን የተባበሩት መንግስታት የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) በየዓመቱ ለአባል አገራት ዕድል ይሰጣሉ። ምርጥ መንደር ካለ ዝርዝር እንዲልኩ ያደርጉና መስፈርቱን ያሟላል አያሟላም የሚለውን በጠቅላላ ጉባኤያቸው ገምግመው ለአሸናፊው ሽልማት ይሰጣሉ። ባለፈው ዓመት የ2021ን ውድድር ወንጪ ነበር ያሸነፈው። ኢትዮጵያ የ2022ትን ደግሞ በእኛ ተቋም “የዓለም ድንቅ መንደር”ን ክብር መጎናጸፏ የሚያኮራ ነው። በተለይ በጣም ደስ ያለኝ በሀገራችን ሰሜኑ ክፍል ጦርነት ከተካሄደ በኋላ የቱሪዝም ዘርፍ ተዳክሞ ነበር። ለምን ብትይኝ ቱሪዝም ዋናው የሚፈልገው ነገር ሰላምና ጸጥታ ስለሆነ። ስለዚህ የእኛ ምርጥ መንደር ተብሎ ሲሸለምና ስናሸንፍ፣ ኢትዮጵያ ሰላም ፈላጊ፣ ህብረተሰቡም ሰላማዊ መሆኑን ማሳያም ጭምር ነው። እኛ ማህበረሰቡን መሰረት አድርገን ስላሸነፍን ማህበረሰቡም ቀድሞ የማያውቀውን የቱሪዝም አስተሳሰብ  ስላወቀና እየተጠቀመም ስለሆነ ጮቄም በትክክል ካልተጠበቀ አደጋ ላይ መሆኑን ትኩረት እንዲያገኝም ጭምር ስለሚያደርግ በዚህ ሁሉ ነው አሸናፊ የሆንነው።
ሽልማቱ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እንደተካሄደ ሰምቼ ነበርና ሽልማቱ እውቅና ነው ወይስ  የገንዘብም ሽልማት አለው? በዚህ ሂደት መንግስት ምን ያህልስ አግዟችኋል?
ሽልማቱ የገንዘብ ሳይሆን የእውቅና ሽልማት ነው። አካባቢው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ፣ ከዚያም ባለፈ ደግሞ፣ የቱሪዝም ገበያው ከዓለም ጋር እንዲተሳሰርና የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር ብሎም የልምድ ልውውጥ እንድናገኝና መንግሥትም ለዚህ ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጥ ያግዛል ሽልማቱ። ምክንያቱም ይህንን ስንሰራ እንኳን ድጋፍ ልናገኝ በትግል ነው እዚህ የደረስነው። ቀደም ብዬ በደንብ ነግሬሻለሁ የገጠመኝን ተግዳሮት። ስለዚህ ጥቂት ግለሰቦች አሁን የኢንሳ ም/ዳይሬክተር የሆነችው አስቴር ዳዊት በፊት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ዋና ዳይሬክተር ነበረች። ብዙ የቱሪዝም ሰዎችን አምጥታ እንዲተዋወቅ አድርጋለች። ቅን የሆኑ ጋዜጠኞች መጥተው አይተው እንዲተዋወቅ አድርገዋል። የኦዚ ሆቴልና ቱሪዝም ሾው ላይ እንድንቀርብና እንድንታይ ያደረገው አቶ ቁምነገር ተከተል ብዙ ረድቶናል። ከዚያ ውጪ በዚህ ውድድር እንድንሳተፍ ያደረገው ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው። ምክንያቱም እድል የሚሰጠው ለቱሪዝም ሚኒስቴር ስለሆነ። ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማና የቱሪዝም አማካሪው አቶ ንጉሴ አግዘውናል እናመሰግናለን። ያው ባለፈው እሁድና ሰኞ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በምትገኝ “አሉላ” በምትባል የዓለም ድንቅ መንደር ነው የሽልማት ስነስርዓቱ የተካሄደው። ይህ ለእኛም ለሀገራችንም ትልቅ ነገር ነው። ከተሰራ የማይመጣ ውጤት እንደሌለም አሳይተናል።


Read 1856 times