Saturday, 25 March 2023 18:24

“የፕሮፌሰሩ ቀን”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

በህይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ልጃቸው በቴሌቪዥን እንደሚታይ ተነግሯቸው አፍጥጠው እየጠበቁ ነው፡፡ በዚያ ላይ ሰሞኑን በጎረቤታቸው ልጅ ሞት ምክንያት ሀዘን ስለተቀመጡ ድምፁን መቀነስ ግድ ብሏቸዋል፡፡
ወሬውን የነገረቻቸው የሰፈራቸው ልጅ አስካለ ናት፡፡ አስካለ ደግሞ ፈጣንና ዘመናዊ ስለሆነች ትታመናለች፡፡ ስለዚህ ቴሌቪዥኑን አስተካክላ አብረው አፈጠጡ፡፡ ሰፈር ውስጥ ልጃቸው ቴሌቪዥን ላይ በመታየቱ ተወዳዳሪ የሌላቸው እትዬ በቀለች ናቸው። እትዬ በቀለችን ቴሌቪዥን ተመልከቱ ብሎ የሚላቸው ሰው የለም፡፡ ሁሌ እንደታዬ ነው።
ሞት አይቀርምና ከሞተም በኋላ ሰሞኑን ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ የሚያወራውና የሚያሳየው የበቀለችን ልጅ ነው፡፡ ነጋ መሸ “ሀገራችን ታላቅ ሰው አጣች!” ይላሉ፡፡ መላኩን የሰፈሩ ሰው ለዚህ ይደርሳል ብሎ አልጠበቀውም ነበር፡፡ የዕድል ነገር ሆኖ ግን ተሳካለት። መንገደኛው ሁሉ አድናቂው ሆነ፡፡
ይልቅስ ትልቅ ይሆናል ብሎ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ቀልቡን የጣለበት ዘሪሁን ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ ስለነበር መምህራና ሌሎችም የሰፈሩ ሰዎች ታዋቂ ሰው ይሆናል ብለው ጠብቀዋል፡፡ አንድም ቀን ጊዜውን ያለ ስራና ንባብ የማያባክነው ዘሪሁን፤ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የስኬት መንገዱን እንደጀመረ ሁሉም ሰው አምኗል፡፡
በሌላ በኩል መላኩ ሰፈር ውስጥ ወዲያ ወዲህ ከማለትና ቀልድ ከማወቁ በቀር ወረቀት ከሚባል ነገር ጋር ያን ያህል ዝምድና የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ድንገት ተነስቶ ቴሌቪዥኑን ሲሞላው “የዕድል ነገር!” ተባለ። ወሮበላ ይሆንብኛል ብለው የሰጉት እናቱ በቀለችም የተገላቢጦሽ ሆኖ “ጀግና ወለድሽ!” ተባሉ፡፡
የዘሪሁን እናት ግን ልጃቸውን የሚያስታውሰውና የሚያደንቀው ስለሌለ ግር ይላቸዋል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አንደኛ እየወጣ አድጎ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ፣ ተመርቆም የሚያስታውሰው መጥፋቱ እንቆቅልሽ ይሆንባቸዋል፡፡
“ይቺ ዓለም ዕድል ናት!” ሲሉ፣
“ይቺ ሀገር ይበሉ!” ይሏቸዋል - አንዳንዶች፡፡
ቴሌቪቪን ላይ አፍጥተው ሳለ “አሁን ሰዓቱ ደርሷል፣ ዘጠን ሰዓት ላይ ነው!” አለች አስካለ፡፡
“መልኩን አሳይተውታል?”
“አዎ!”
“በዓይንሽ አይተሽዋል?”
“በዓይኔ - በብረቱ ነዋ! … ፕሮፌሰር ዘሪሁን አሰፋ ተብሎ፡፡”
“ምንድነው ደሞ እሱ?”
“ምኑ?”
“ፕሮፌሰር …  ያልሽው?”
“የዕውቀቱ ማሳያ ነዋ! … ያጠና የተመራመረበት ...”
“አይ ጥናት … ምናደረገለት?…”
“ደሀ ሀገር ስለሆነ ነዋ! … መቸም ከመላኩ አያንስ!”
“ተይ ሙት አታንሺ! … እሱ አገር አውቆት፣ ህዝብ አድንቆት አልፏል፡፡ እናቱንም ቢሆን አስከብሯል፡፡”
አስካለ አፏን አሞጥጣ መልሳ ተወችው፡፡
ቴሌቪዥኑ ላይ ፕሮግራም አዘጋጁ ብቅ አለ፡፡
“ይህ ነው ያስተዋወቀው” አለች አስካለ፡፡
በጣም በሀዘን ስሜት ሆኖ “እንደምን ዋላችሁ ተመልካቾቻችን … ሰሞኑን ያጣነውን ታላቅ ሰው በተመለከተ ያዘጋጀነው ፕሮግራም አለ፤ አሁን እናቀርባለን…” አለ፡፡
በእንባ የሞጨሞጨ አይናቸውን በዘቀዘቁት ነጠላ  ጫፍ ጠራረጉና ቴሌቪዥኑን ትክ ብለው አዩ፡፡
“እንግዲህ ለታላቁ የጥበብ ሰው ቅርብ የሆኑና አብሮ አደግ ጓደኛው ፕሮፌሰር ዘሪሁን ታላቅ ተመራማሪ መሆናቸውን ከቅርብ ሰዎቻቸው ሰምተናል። ጥናቶቻቸው በዓለም ደረጃ የሚደነቁ እንደሆኑ ባለፈው የጥበብ ሰው ስራዎች ላይ ሀሰሳ ስናደርግ ፍንጭ አግኝተናል፡፡”
አፍታ ቆይቶ ፕሮፌሰር ዘሪሁን መነጽራቸውን በጣታቸው ወደ ላይ ገፋ እያደረጉ ብቅ አሉ፡፡
“ይኸውልዎታ!”
“ጥቁር የለበሰው ለሀዘኑ ነው? አጠቆረው ደሞ!” አሉ፡፡
ጋዜጠኛው መጠየቅ ጀመረ፤
“ለመሆኑ መቼ ነው የምትተዋወቁት?”
“በልጅነታችን ነው፤ ያንድ ቤት ያህል ቅርብ ነን። የኢትዮጵውያንን ማህበራዊ ግንኙነት ታውቀዋለህ። የእኔ እናት የእርሱ እናት የሚባል ነገር የለም፡፡ እኛ ቤት እንጀራ ከሌለ እነርሱ ቤት እበላለሁ፡፡ እርሱም እንደዚያው ያደርጋል፡፡ የበዓላት ሰሞን አብረን የምናድርበትም ጊዜ ነበር፡፡ መላኩ ጨዋታ ወዳድና ቀልደኛ ስለሆነ በጓደኞቹ ዘንድ ይወደዳል ይልቅ እኔ ዝጋታም ነበርኩ!”
“የጥበቡን ችቦ ያኔም ለኩሶ ነበራ?” አለ ጋዜጠኛው
“አዎ ጨዋታ ወዳድ ነው! … እስክስታና ዳንስም ይወድዳል”
“ለጥበብ የተወለደ ሰው ነበር ማለት ነው … ገና በልጅነቱ ነፍሱ በጥበብ ታቅፋ ነበር።”
ፕሮፌሰሩ ትኩር ብለው እያዩት፤ “እንግዲህ ይሆናል…”
“በትምህርቱ ላይ እንዴት ነበር?”
“ትምህርት አይወድድም! … በዓመት አራት ቀን እንኳን ደብተር ይዞ ክፍል አይገባም ነበር፡፡
“ደብተሩ ልቡ ነዋ! … ምን ያደርግለታል!”
“ደብተርማ ለተማሪ የጦር መሳሪያው ነው፡፡ እኛ ሁላችን ደብተራችንን ብንጥል ማን ሀኪም ይሆናል? ማን ድልድይ ይሰራል? ማን ሀገር ያስተዳድራል?”
እናቱ እያዩት እንባቸው መጣ፡፡ “መማሩ ምን ጠቀመው?” አሉ በልባቸው፡፡ ደግነቱ ያለመታሰሩ ነው፡፡
የእርሱ ጓደኞች እስር ቤት ገብተው፣ ተገርፈው አልነበር? … እርሳቸው ዕድለኛ ናቸው፡፡
“ይቅር በለኝ ፈጣሪዬ! በጤና ወጥቶ መግባቱም ደግ ነው!”
“አንድ ክፍል ተምራችሁ ታውቃላችሁ?”
“አንድ ሁለቴ አብረን ነበርን፡፡”
“እንዴት ነበር?”
“ው! ይረብሻል? … ብዙ ጊዜ አስተማሪዎች አንበርክከው እጁን ወደ ላይ እንዲያደርግ ያስገድዱት ነበር፡፡
እንደዚያም ሆኖ አያርፍም፡፡ አንድ ቀን እዚያ ሆኖ ሲጠቅሰኝ ስለሳቅሁ መምህሩ ተቆጥተውኛል፡፡ ‹ከአንተ የዚህን ዓይነት ነገር አልጠብቅም!”› ብለውኛል።…
“ተንበርክኮ እስክስታ እያሳየ ተማሪዎችን ያስቅና ያስገርፋል፡፡ በጣም ኮሚክ ነበር፡፡”
ጋዜጠኛው እንደ መኩራራት ብሎ “የጥበብ ጀንበር የቅጣትን አድማስ ሰብራ ትወጣለች፡፡ ከያኔ የሚወለደው በየትኛውም ስቃይ ውስጥ ነው፡፡” ሲል ለመፈላሰፍ ሞከረ፡፡
ፕሮፌሰሩ ሳቁ፡፡
አስካለ እንደ መብሸቅ ብላ፤ “መላኩ ስለሞተ ፕሮፌሰሩን ማነጋገሩ ልክ አይደለም፡፡ ለምን ቢጤውን አይጠይቅም ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ዘሪሁን የሰራው ስራ‘ኮ ዓለምን የሚያስደንቅ ነው፡፡ በመድኃኒት ቅመማና ምርምር የሚነገርለት ስንት ነገር እያለ … መላኩ እስክስታ እንዴት እንደጀመረ ይጠይቁታል?” ብላ ብሽቅ ስትል እናትየው ጥሩ ስሜት ተሰማቸው፡፡
“አስኩ መላኩም ልጄ ነው፡፡ ዘሪሁንም ልጄ ነው። ግን የድካሙን አላገኘም፡፡ አስታዋሽም የለውም፡፡ ይኸው ዛሬ እርሙን ቴሌቪዥን ላይ ቢቀርብ ያወራው ስለ መላኩ ነው፡፡ የዕድል ነገር ነው እንግዲህ! … ያንንም ነፍሱን ይማረው!! ዕድለኛ ነው፡፡ በልጅነቱም እንደልቡ ተጫውቶ፣ ቦርቆ፣ አዋቂም ከሆነ በኋላ ሀገር ሁሉ አድንቆት አለፈ፡፡ የኔው ከልጅነቱ ጀምሮ ወረቀት ላይ እንደተተከለ አለ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ያመጣው ነገር የለም፡፡”
አስካለ ካፋቸው ነጠቀቻቸው “ዘሪሁንን እንኳ መውለድዎ ጀግና ነዎት! ህዝቡ አልገባውም እንጂ ታላቅስ የእርስዎ ልጅ ነው፡፡ … የህዝቡ ሚዛን ማጣት ነው፡፡”
ፈገግ አሉና ዝም አሉ፡፡
እዚያው እንዳሉ ልጃቸው ደወለ፡፡
“ውይ ዘርዬ … አሁን እያየሁህ!”
“ቴሌቪዥን ላይ”
“አዎ!”
“በቀደም‘ኮ የውጭ ቴሌቪዥን ላይ ታይቼ ነበር፡፡ ምን ያረግልሻል ብዬ ነው!”
“የፈረንጆቹ ላይ”
“አዎ!”
“እልልልል….”
“ኧረ ተይ ምንም እኮ አይደል! … ዋናው ለሀገር የሚጠቅም ስራ መስራት ነው! ዛሬ ስለ መላኩ ያወራሁትን እያየሽ ነዋ! … የእርሱም ዓይነት ሰዎች ያስፈልጉናል!”
“እሰይ በፈረንጁ እንኳን ታየህ! የኛማ ሰው ልቡ ከእስክስታ አያልፍም! ወይ ከድራማ!”
ከት ብሎ ሳቀና፤
“ይልቅ ሰሞኑን ዓለም አቀፍ ሽልማት ስላገኘሁ፣ በደስታዬ ፕሮግራም ላይ እንድትካፈይ ነው!”
“ከማን እጅ ተቀበልክ?”
“ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ልቀበል ነው ገና!”
“እልልልል … ድካሜ ከንቱ አልቀረም!”
የቴሌቪዥኑ ፕሮግራም ቀጥሏል፡፡
“ፕሮፌሰር ዕድለኛ ነዎት! .. ከዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ጋር ማደግዎ!”
“አዎ! … ሲያዝናናኝ ነው የኖርኩት! … አንዳንዴ ጥናት አቃጥሎኝ ስደክም መጥቶ እስክስታውን በያይነቱ እያሳየ ያዝናናኝ ነበር፡፡ ነፍሱን ይማር!”
****
(ውድ አንባቢያን፡- ከአዲስ አድማስ ድረገጽ ላይ በድጋሚ መርጠን ያተምነው ታሪክ ነው።)
Read 653 times