Saturday, 25 March 2023 18:32

“በጎሀ ጽባሕ በኩል…ጎህ ሲቀድ”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

የውጭውን ዓለም በቅጡ ለማወቅ አያሌ ዕድል ከገጠማቸው የሃያኛው መቶ አመት ደራሲያን መካከል ህሩይ ወልደ ሥላሴን የሚስተካከል የለም ማለት ይቻላል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ደጃች ካሳን አጅበው በንጉሥ ጆርጅ 5ኛ ሥርአተ ንግሥ ላይ ለመታደም ወደ እንግሊዝ ከሄዱ ጀምሮ ሌሎች ዘጠኝ  ተከታታይ ጉዞዎችን በማድረግ ፈር-ቀዳጅ ናቸው። አሜሪካ፣ እየሩሳሌም፣ ግብፅ፣ ኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጄኔቭ…ወዘተ።
ህሩይን ከሌሎች ዘመነኞቻቸው ደራሲያን ልዩ የሚያደርጋቸው ብዙ የውጭ አገራትን መጎብኘታቸው ብቻ ሳይሆን ስለጉብኝታቸው ዘርዘርና ሰፋ ያለ ዘገባ መጻፋቸውም ጭምር ነው፡፡ በዚህ ረገድ  ካደረጓቸው ጉብኝቶቻቸው ስለ አምስቱ ዝርዝር ዘገባ ትተውልናል፡፡ ከእነዚህ አንዱ “የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ” የተሰኘው ሲሆን፤ ባህሩ ዘውዴ  አጠናቅረውና በግሩም  ሁኔታ አሰናኝተው፣ በኢትዮጵያ  አካዳሚ ፕሬስ  ታትሞ (ከአምስት አመት በፊት) ማስነበባቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ህሩይ በሚኒስቴር ደረጃ ላይ ያሉ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁለተኛው የጣልያን ወረራ በፊት የነበረው ትውልድ በገፍ እየፈለሰ፣ የምዕራባውያንን የቀለም ትምህርት ተምሮ መምጣቱ በታሪክ ይነገርለታል፡፡ በኋለኛው ዘመን እንግሊዝኛ በትምህርት ደረጃ ከመሰጠቱ በፊት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባዕድ ቋንቋው ፈረንሳይኛ፣ ባህሉም ፈረንሳዊ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የፈረንሳይኛ ቋንቋና ባህል ይበልጥ እንዲገኑ በጊዜው በአዲስ አበባ የሚገኙ አሊያንስ  ፍራንሲስ ትምህርት ቤቶች ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ታዲያ ፈረንሳይ ለትምህርት ለሚላኩት አያሌ ተማሪዎች፣ ብርዱን መቋቋም አዳጋች ነበር፡፡ በብርዱ ሳቢያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ተማሪዎች መሞታቸውም ተዘግቧል። የወቅቷ “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ ዘገባዋ ሁሉ በእነዚህ  ወጣት ኢትዮጵያውያን እረፍተ-ዜና የተሞላ ነበር፡፡ በ1923 ዓ.ም ለሞተው  መንክር ገ/እየሱስ ለተባለ ተማሪ፣ እህቱ ያወረደችው ልብ የሚነካ  ሙሾ  እንዲህ ይላል፡-
በፓሪስ ከተማ  ሠራህ አሉኝ ቤት
ዘመድ አይገባበት እህት አትኮራበት
አገር ምረጭ ቢሉኝ ፓሪስን አልወድም
ያይን አዋጅ አለበት ያየውን አይሰድም
ፓሪስ ከተማ ላይ ወድቀህ እንዳገዳ
ከእህቶችህ በቀር ሌላ ማን ተጎዳ
ከሃያኛው መቶ አመት የኢትዮጵያ ደራሲያን መካከል  ባሳተሙት የመጽሐፍት ብዛት ህሩይ ወልደሥላሴን የሚወዳደራቸው ፈጽሞ አይገኝም፡፡ (ባለሪከርድ ፀሐፊ ናቸው።) በህይወት እያሉ አሥራ ዘጠኝ  የተለያዩ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡ የታሪክ፣ የህይወት ታሪክ፣ ልቦለድ፣ የጉዞ ማስታወሻ፣ ምክር አዘል ድርሰቶች…፡፡ ከህልፈታቸው በኋላ ደግሞ ትልቁ የታሪክ መጽሐፋቸው “የኢትዮጵያ ታሪክ”፣ በልጅ ልጃቸው ታትሞ ለንባብ በቅቶላቸዋል፡፡
እነሆ በዚህ አመት ደግሞ “ጎሀ ጽባሕ” የተሰኘ ሌላኛው ሥራቸው፣ ጎህ ቀዶለት ዳግም የህትመት ብርሃን ለማየት ችሏል፤ በልጅ ልጃቸው፡፡ የእኔም ፅሁፍ አቢይ ትኩረት በዚህ ሥራቸው ላይ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያዊ ሐሳብን በኢትዮጵያዊ ቋንቋ የመግለጽ ዕጣ ፈንታ፣ የግዕዝ ሳይሆን የአማርኛ ሚና ነው በሚል፣ የቤተ-ክህነቱን ቋንቋ፣ በጊዜው በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ ከመጣው አማርኛ ጋር አጋብተው በመፃፍ፣ለብሔራዊ ቋንቋችንን መዳበር አስተዋጽኦ ካበረከቱ ታላላቅ ጸሃፍት መካከል ህሩይ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንደ ዛሬ በድህረ-ዘመናዊ ደራሲያን  ሥነጽሁፋችን ከመጥለቅለቁ ከመቶ አመት በፊት፣ የአማርኛ ቋንቋን እንደ አፈወርቅ ገብረእየሱስ እና ህሩይ ወልደ ሥላሴ የተካነበት አልነበረም ይባላል፡፡ በቃላትና ዘይቤ የበለፀገ ድርሰት በማበርከት በዘመናቸው የሚደርስባቸው እንደሌለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ህሩይ ስለ አማርኛ ሰዋሰው አያሌ ጽሁፎችን  አበርክተዋል፡፡ በተለይ በ”ጎሀ ጽባሕ” ከእነዚህ የዘይቤና የምሳሌ አንድምታቸው ባሻገር የአማርኛ ፊደላትን ለማሻሻል ያደረጉትን ጥረት በጉልህ እናይበታለን፡፡
“ጎሀ ጽባሕ”፤ ምክር-አዘል የሆነ መንፈሳዊ አስተምህሮቱ የበዛ ስራ ነው፡፡ በእርግጥ ህሩይ ባለስልጣንም፣ ለውጥ አራማጅም እንደመሆናቸው መጠን፣ ሥራዎቻቸው ምክር አዘል እንዲሆኑ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡ በርግጥ የሳቸው ብቻ አይደለም፡፡ በዘመኑ ጽሁፎቻቸው ተረት ቀመስና ምክር አዘል ያልሆነ በጣም ጥቂት ብናገኝ ነው፡፡ የህሩይን ስንመለከት ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልእክት ገና ከመፅሐፉ ርዕስ መገመት እንችላለን፡፡ “ለልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ”፣ “አዲስ አለም የቅኖችና የደግ አድራጊዎች መኖሪያ”…የመሳሰሉት፡፡ ህሩይ በ”ጎሀ ጽባሕ” አለማዊውን በዘዴ፣ መንፈሳዊውን ደግሞ በትርጓሜ… ከመምህራን ሳይማሩ ከልምድና  ከአዕምሮ ክህሎት ተመራምረው አያሌ ጉዳዮችን ያስተምሩናል፡፡ (ስጋዊና መንፈሳዊ ትርጓሜያቸውንም ሳይዘነጉ ነው ታዲያ) “ሀይልና እውቀት እንዲሁም ጥበብም  ብትሆን የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር የባህሪይ ገንዘቡ ናቸው…” የሚሉን ህሩይ፤ ልባችንን ከትዕቢት ደረጃ አውርደን፣ በህገ ልቦና አቅንተን፣ ከክፉ ሥራ እርቀን እንኖር ዘንድ በየምዕራፉና  በንዑስ ርዕስ ከፋፍለው በምሳሌዎቻቸው አዋዝተው አስፍረውልናል፡፡ ስለ ጤና ኑሮ፣ ስለ ባልና ሚስት መቃናት፣ ስለ ገዢና ተገዢ፣ ስለ የእውነትና የሐሰት ወሬ፣ ስለ ገንዘብ ጥቅምነትና ጎጂነት… የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ለአብነት ስለ ባልና ሚስት ባሉት ንዑስ ርዕስ ስር የትዳርን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡-
“ሚስት ማግባት በባህሪያችን ውስጥ ያለችውን እንደ እሳት የምታቃጥል የዘር ፈቃዳችንን ለማጥፋት ነው እንጂ ልጅ ለመውለድ ብቻ አለመሆኑን ፈጽሞ መረዳት ይገባናል፡፡ መብልና መጠጥ ለባህሪያችን በግድ እንደሚያስፈልግ፣ የዘር ፈቃድም ለባህሪያችን የምታስፈልግ ናት፡፡ ይህንንም የዘር ፈቃዳችንን በሥጋ ኑሮ ችግር ያመጣብናል ብለን ካልተውነው በቀር በነፍስ ኑሮ ኩነኔ ያመጣብናል ብለን ለመተው አልታዘዝንም” … ይሉናል፡፡
ህሩይ በተረትና በምክሮቻቸው ብቻ እያስተማሩ እንዲቸከን አያደርጉም፡፡ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ ተጠቅመው ምሳሌያዊና ያልተጋነነ አገላለፅ፣ በአጫጭር ነገር ግን እምቅ አረፍተ ነገሮች ሀሳባቸውን በመግለጽ፣ የግርማቸው ተ/ሀዋሪያትን “አርአያ” ዘይቤና ስልት በሚያስታውስ መልኩ ያወጉናል። ምሳሌያቸውም የተለየ ውበት አለው።  የሚያስተላልፉት መልእክት  የማያሻማና  ግልጽ ነው፡፡
የህሩይ አለማዊም ሆነ መንፈሳዊ አመለካከታቸው በዚህ ሥራ  ውስጥ ረቀቅ ባለ ሥነጽሁፋዊ መንገድ ተገልጿል ማለት ይቻላል፡፡ የህሩይ እውነተኛ የሥነጽሁፍ ባህሪይ፣ ሁሉንም አለማዊ የእውቀት ባህሪይ መንፈሳዊ ፍቺ ፍለጋ ዳክረው በልኩ መግለጽ ነው፡፡  የአጻጻፍ ዘይቤያቸው ምጡቅም-ተራም አይደለም፡፡ ዳሩ ግን የለት-ተዕለት ኑሮዋቸውም  ሲንፀባረቅ ይስተዋላል፡፡ ህሩይ ወልደሥላሴ  በአማርኛ ቋንቋና ሥነጽሁፍ ዕድገት ላይ ያላቸው ስፍራ ከብዙ አቅጣጫ ይመነጫል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት ሥራቸውም፣ ህይወታቸውም ሲተነተኑ ኖረዋል፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገራቸውንም ሆነ ያልተለመዱ ምክር አዘል ውብ ታሪኮቻቸውን መርምሮ መረዳት የተተው ለኛው ነው፡፡ (ትዕግስቱንም ሆነ ችሎታውን ይስጠንና)፡፡ ነባር ኢትዮጵያዊ ደራሲያን ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ  በጊዜያቸው ትልቅ ቅርስ ትተውልናል፡፡ እንደ ህሩይ የቋንቋ ልዕልናን የታደለ ደራሲ ስራ ሲገኝ ደግሞ፣ ከድርሰቱ  ባሻገር ዘመኑን  በቅርበት  ለማወቅና ለመረዳት ያግዛል፤ አስተዋጽኦም  ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡

Read 825 times