Saturday, 25 March 2023 18:26

“አትንገር ብዬ ብነግረው…”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

  “ወሬ ይዘው መጥተው፣ ዳር ዳር እያሉ በገደምዳሜ አድርገው የሚያወሩ እንዳሉት፣ “ያልሰሙ መስለው” (አልሰማሁም ብለው) አውቀው የቆዩትን ጉዳይ በሌላ አንደበት ሲተረክላቸው ከሀሜት ፍቅራቸው ብዛት በድጋሚ እየተደነቁ የሚሰሙ አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህ አይነቶች ሁሉም የሰው አይነቶች ናቸው፡፡--”
   
         የማወቅ ፍላጎት የሌለው እሱ ሰው አይደለም። የማወቅ ፍላጎት ያለው ሁሉ ፈራጅ ነው፡፡
… በማለዳ ከፍ ከፍ ያለ፣ ፀሐይ ሳትጠልቅ ቀድሞ የሚነጠፍ ነው፡፡ የሀሜት ድልድይነት ከዚህ ውስጥ  ይመነጫል፡፡ የማወቅ ፍላጎት፣ ሲቀጥል ደግሞ የመፍረድ ፍላጎት፡፡ ስለ ማንም ያልታወቀውን (የተደበቀውን) ማወቅ፣ ቀጥሎ መፍረድ፡፡ ሚስጥርን መግለጥ የሚያስፈልገው ይሄ ፍላጎት የግድ መርካት ስላለበት ነው። ሚስጥሩ መደበቁ ላይ ዋጋው ከፍ ይላል፡፡ የተደበቀውን አነፍንፎ፣ አባዝቶ እና አዋዝቶ መግለጥ የቻለበት በቀጥታ ወደ ሀሜት መዞር ይችላል፡፡ የራሱን ፍርድ ሰጥቶ ለሌሎች ዝግጁ ፈራጆች ሜዳውና ፈረሱን እነሆኝ ማለት ይችላል፡፡ የሀሜት አሰራጩ ባህሪ ከተቀባዩ ጋር በሰውነት የማወቅ ጉጉት የተሳሰረ ነው። የተጋጠመ ነው፡፡ በምድር ላይ ይሄንን  የጉጉት ሰንሰለት ሊሰብረው የሚችል ማንም የለም። “ሀገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው” ሆኖ የሚስጢሩ የወይን ዘለላ፣ ወደ ጠወለገ ዘቢብነት እስኪቀየር ድረስ የሀሜት ንዳዱ ይቀጣጠላል፤ መልሶ ይከስማል፡፡
ከመሰላሉ ውስጥ ነው የመውደቂያ ሸርተቴው የሚዘጋጅለት፡፡ አወጣጡ ላይ ሳይሆን አወዳደቁ ላይ የሚስጥሩ ፍቺ እንቆቅልሽነቱ ያበቃል፡፡ ዝም ማለት የሚያስፈልገው ሚስጥሩን ለመጠበቅ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሀሜት በራሱ ላይ የሚናገረው፣ እውቀቱን ይዞ በዝምታ ተቀምጦ የነበረውና ሚስጥሩን  መጠበቅ ያቃተው ራሱ የታሪኩ ባለቤት ነው፡፡
ለምሳሌ “ከበደ ሶስት ጉልቻ መሰረተ” የሚል ሊሆን ይችላል እውቀቱ፡፡ ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ ክብር የሚጨምር ነገር በመሆኑ የታሪኩ ባለቤት እንዲታወቅለት ይፈልጋል፡፡ ድግስ ይደግሳል፡፡ ተሰብሰቡ ይላል፡፡ ምርቃትም ሊሆን ይችላል። እንዲታወቅ የተፈለገው “ከበደ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቆ ከባህር ማዶ መመለሱ” ሊሆን ይችላል፡፡ ሚስጢር ተደርጎ የሚያዝበት ምንም ምክኒያት የለም፡፡ የኩራት እና የክብር ምንጭ ነው፡፡ ግን እንዲታወቅ ከተፈለገው ጋር የሚጣረስ ሌላ የማይፈለግ እውቀት ከመጣ የሀሜተኛ ስራ ይጀምራል፡፡
“የሆነ ከባህርማዶ በቅርቡ የመጣ ሰው አግኝቼ… ትምህርቱን ሳይጨርስ ነው የተመለሰው ብሎ አጫወተኝ” ይላል አንዱ፤ እዛው ከበደ ሰፈር የሚኖር ሰው፡፡ ይሄንን አምጥቶ የሚነግራት መጀመሪያ ለሚስቱ ነው፡፡ የከበደ ስም በመካከላቸው በአንዴ ቀላል መሆን ይጀምራል፡፡
“ሂድ ሂድ!” ትላለች ሚስቱ፣ማመን እንደማትፈልግ በሚያሳምን አኳሁዋን፤ ልቧን በእጇ ደግፋ፡፡ “ወይኔ ጉዷ ሚስቱ! ደግሞ በቅርቡ መንታ ነው የወለደችው … ከስራ ከተባረረ በምን ያስተዳድራት ይሆን?... ውይ ውይ አያድርግባት! አንተ ግን ከማን ነው የሰማኸው?” ትለዋለች ባሏን፡፡ የአፏ ሀዘን በገፅታዋ ከሚስተዋለው ጉጉት ጋር “ማች” አያደርግም፡፡
ባሏ ይዞላት የሚመጣውን ወሬ በቀላሉ ማመን አትፈልግም፡፡ ባታምንም ግን… ባታረጋግጥም… አንድ ሚስጢር ግን አውቃለች። የሀቅ እውቀት ካላገኘች እረፍት ማታገኝ ብትመስልም፣ የሀሜት ጥንስስ በማግኘቷ ግን የበለጠ ደስተኛ ናት፡፡ ብዙውን ጊዜ፣ ልቧን በእጇ የሚያስደግፍ ድንጋጤ በወሬ መልክ ተላልፎ ሲሰጣት ደስተኛ ናት፡፡ በአፏ ግን ደስታዋን ለመቃወም ደጋግማ ታማትባለች፡፡
ባሏ ከአጠገቧ ዞር ሲል ስልክ መደወል ትጀምራለች፡፡ ከበደን የሚያውቁ ጓደኞቿ ዘንድ፡፡ በእርግጥ ሀሜቷን ገና ስልክ እንደተነሳ ወዲያውኑ ላነሳው አትነግረውም፡፡ በሰላምታ ጀምራ፣ ስለ ልጆች ጤና እና ስለ ኑሮ እሳት መሆን አመስግና እና አማርራ… በአዘቦቱ አቀራረብ አጅባ… አጀብ ወደሚያስብለው ወሬዋ ታሳብራለች፡፡ “አንቺ ከበደ ከስራ የተባረረው የተማረበትን የትምህርት ማስረጃ አቅርብ ሲባል የለኝም ብሎ ነው የሚባለውን ሰምተሻል? እንደው የሆነ ሰው ሲያወራ እንዳጋጣሚ ሰምቼ ክው ስላልኩኝ ነው… እንደው ለመአዛና ለልጆቹ ሲባል እውነት ባልሆነ” በስልክ ውስጥ ባይታይም ታማትባለች፤ ጨዋዋ ሀሜተኛ፡፡
“ይሆናል ባክሽ” ትላለች ሚስጥር እየተነገራት ያለችው፡፡ “ከበደ የተባለው ሰውዬ ነገር ከመጀመሪያውም አላማረኝም፡፡ የተማረ ሰው እኮ ጥላው ትንሽ ይከብዳል… የፍራሽ ተራ ነጋዴ አይደለም እንዴ የሚመስለው… ቆይ ግን እስቲ አጣራለሁኝ” ትላለች የወሬ ዱላ ቅብብል ተቀባይዋ፡፡ ዋናው ወሬ ከተላለፈ ተልዕኮው ተጠናቋል፡፡ ግን ሀሜቱ ዋና የተደዋወሉበት ምክኒያት መምሰል ስለሌለበት፣ ሌላ ሌላ ነገር ይደርቱበትና ስልኩን ይዘጋሉ፡፡
ሀሜት ሰው ለሆነ ሁሉ የተሰጠ አቅም ነው፤ ወይንም እርግማን፡፡ እንደ ዲግሪ ወይንም እንደ መኪና ማሽከርከር ተምሮ የሚያገኘው ብቃት አይደለም፡፡ የሀሜት አሽከርካሪ፣ ከተሽከርካሪው (ወሬ) በፊት ከስጋ እና ከደም በተፈጥሮ ተላቁጦ የሚሰራ ነው፡፡ አፍ፣ እና አፍ የማጣመም ብቃትን ይዞ ከእናቱ ሆድ ይወጣል፡፡ የማንም ሰው ህይወት እሱ ማሾር የሚችለው የሀሜት ተሽከርካሪው ሊሆን ይችላል፡፡ የብቃቱ ግብ ሚስጥርን ገልጦ መፍረድ መቻል ነው፡፡
የሚነሳ ስም ላይ ሁሌ አንዳች ሚስጢር አለ። አንሺው አንዳንድ ጊዜ አውቶቡስ ተሳፍሮ ለብዙ ዘመን ያልጠየቀው ሰው ቤት “እንደው ሰው ሲጠፋ እንኳን የት ገባ አትሉም” ብሎ ሰተት ብሎ እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል፡፡ አመሳጥሮ፣ በሰም እና ወርቅ አደናግሮ፣ ስሜትን ወጥሮ እና የተዘጋ የወሬ አፐታይትን ከፍቶ፣ ሀሜተኛው ጭኖ የመጣውን ወሬ የጆሮ ወደብ ላይ ያራግፋል፡፡ ከዘረገፈ በኋላ ምሳ እንኳን ሳይበላ ቸኩሎ ሊነሳ ይችላል፡፡ የሚቸኩለው ሌላ ያልሰማ ጋ ወሬውን ለማድረስ ነው፡፡
ሀሜተኛ ወይንም ወሬኛ የሚባል የተለየ ሰብዕና የለም፡፡ የማወቅ እና የማሳወቅ ፍላጎት ያለው ሁሉ ሰው ነው፡፡ መስሎ ላለመታየት፣ ቀረት፣ ዘግየት ማለት አልያም የጅብ ችኩል መሆን እንጂ ሚስጥርን መግለፅ የማይወድ በመሰረቱ ከሰው መሀል የለም፡፡ ሀሜት የሰዎች የማይለወጥ ባህሪ ነው፡፡
ወሬ ይዘው መጥተው፣ ዳር ዳር እያሉ በገደምዳሜ አድርገው የሚያወሩ እንዳሉት፣ “ያልሰሙ መስለው” (አልሰማሁም ብለው) አውቀው የቆዩትን ጉዳይ በሌላ አንደበት ሲተረክላቸው ከሀሜት ፍቅራቸው ብዛት በድጋሚ እየተደነቁ የሚሰሙ አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህ አይነቶች ሁሉም የሰው አይነቶች ናቸው።
የታሪኩ ባለቤት ጋር ወሬው የሚደርሰው ቆይቶ ነው፡፡ የሚደርሰው እንደ አካሄዱ ዙር ሰርቶ በመመለሻው ወሬኛ በኩል ነው፡፡ ሀቀኛ መሳዩ ወሬኛ ለራሱ ለታሪኩ ባለቤት ወሬውን ይዞለት የሚመጣው የመልካም ፈራጅን ቅርፅ ተላብሶ ነው፡፡
“…ከበደ ለኔ ጓደኛዬ ስለሆንክ ልደብቅህ አልችልም፡፡ በዛ ላይ ሌላው የሚያወራውን ሳላረጋግጥ ተቀብዬ ማጋጋልን ህሊናዬ አይፈቅደውም… ከስራ የተቀነስከው የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻልክ ነው ብለው እያስወሩብህ ነው፡፡ እነማ አትበለኝ! ሀቁን ለማወቅ ስለፈለግሁ እንጂ አሉባልታን ማናፈስ ወይንም ሰዎችን እርስ በራስ ማናከስ አላማዬም ተፈጥሮዬም አይደለም”
…ከበደ የሚሰጠው ምላሽ ሀሜቱን መሰረት አልባ የሚያደርግ ቢሆን እንኳን የተከፈተው የሀሜት በር በቀላሉ አይዘጋም፡፡ በከበደ ላይ ቢዘጋ እንኳን በእንቶኔ ላይ ተከፍቶ ይቀጥላል። የሚያማውም ይታማል፡፡ የሚያሳምመው ይታመማል፡፡ ሲታመም፣ አዙሪቱ፣ እሱን የታሪኩን ባለቤት “ጆሮ ለባለቤቱ” አስብሎ በሚያስተርት ደረጃ አግልሎ ያው ነገር ይቀጣጠልበታል፡፡ ስምን ማፅዳት እስኪቆሽሽ ብቻ ነው፡፡ ወይንም ለመቆሸሽ ሰው አፍ እስኪገባ፡፡ “አትንገር ብዬ ብነግረው፣ አትንገር ብሎ ነገረው” የአዙሪቱ የደም ስር ነው፡፡ አትንገር ብሎ በመጨረሻ አምጥቶ የሚነግረው ለራሱ የታሪኩ ባለቤትም አይዶል?
የከበደ ጉዳይ እንኳን በቀላሉ እልባት ያገኛል። ተምሮ የጨረሰበትን ማስረጃ አውጥቶ ማሳየት ብቻ ነው ያለበት፡፡ ካሳየ በኋላ የሀሜት ምትሀቱ ካባውን ይገፈፋል፡፡ ግን ወደፊት የሄደው ወሬ ወደኋላ ሲመለስ፣ የሃሜተኞቹን አንደበት ዘግቶ ወይንም በይፋ ያልተጣራ ወሬያቸውን ባፋፋሙበት ሰው ፊት ራሳቸውን አዋርደው ይቅርታ በመጠየቅ አይደለም፡፡ ሀሜት ይሞቃል ወይንም ይቀዘቅዛል እንጂ አይሻርም፡፡ የሰው ልጆች የማወቅ እና የመፍረድ ባህሪ እስካለ ድረስ ሁሌ ሀሜት ይኖራል፡፡ ሀሜት በወሬ ዝውውር የደም ግፊቱን ከለካ በኋላ የወሬው ኢላማ የሆነውን ሰው በማግለል ወይንም መጠቃቀሻ በማድረግ ጊዜያዊ ማረፊያውን ያገኛል፡፡ ከአንዱ ተልዕኮው ሲያርፍ ወዲያው ሌላ ተልዕኮ አንግቦ ነው፡፡ ስለዚህ ሀሜት የተወሰኑ ሰዎች ባህሪ ሳይሆን ሰው የመሆን… ፀጋ ቀመስ እርግማን መገለጫ ነው፡፡ ይሄንንም ያንንም የማወቅ እና የማሳወቅ ፍላጎት፡፡ ሳይፈርድ የሚያውቅ ወይንም የሚያሳውቅ ሰው ሆኖ የለም፡፡ የማወቅ ፍላጎቱ ፀጋው ሲሆን የመፍረድ ፍላጎቱ ግን እርግማኑ ነው፡፡
ሀሜተኛ ሲያማ፣ እያማ መሆኑን አድማጭ ነቅቶ ተው ሊለው ቢሞክር፣ ሀሜተኛውን ያስቆጣዋል፡፡ ይቆጣል እንጂ አይቀበልም፡፡  አውቆ ለማሳወቅ እየጣረ መሆኑን እንጂ፣ አዛብቶ ፈርዶ ለሚፈርድ አሳልፎ እየሰጠ መሆኑን አያምንም፡፡ የፀጋው ጎን እንጂ የእርግማኑ ጎን አይታየውም፡፡
ለነገሩ ጮማ የሆነ ሚስጢር ገላጭ ወሬ እየተወራ ሳለ፣ አዙሮ ስለ ተናጋሪው የሞራል ልክ መመዘን የሚችል ማንም የለም፡፡ ሀሜት፤ የአድማጭን ጆሮ ቀስሮ ማቆም የሚችል የአዚም ሙዚቃ ነው፡፡ ከልቡ ሆኖ ከሚያደምጠው ይልቅ እንደ ማለዳ ፀሐይ ልቡ ጠፍቶ የሚሞቀው ይበዛል፡፡ ጮማ እየጎረሰ፣ የጎረሰው እሬት ሊሆን እንደሚችል በጣዕሙ ንዝረት ወቅት የሚገባው የለም፡፡ በወሲባዊ ተራክቦ መሃል እያለ ባለሱቁ የተሳሳተ መልስ እንደሰጠው ትዝ የሚለው ማንም እንደሌለው ማለት ነው፡፡ ወይንም ትዝ ቢለው እንኳን ተራክቦውን አቋርጦ ትክክለኛውን መልስ ከሱቅ ለማምጣት የሚሄድ ማንም የለም። መልሱ በኋላ ላይ ይደረስበታል። ሀሜቱ ሀሰተኛ እንደሆነ፣ ከባለቤቱ ባልተናነሰ እርግጡን የሚያውቅ ሰው እንኳን ቢሆን አድማጭ ሆኖ የተቀመጠው፣ የሰው ስም ሲጠፋ ከሚፈጠረው ቅፅበታዊ የሀሴት ድንዛዜ መናጠብ አይፈልግም። ስቆ ከጨረሰ በኋላ ምናልባት ሊፀፀት ይችላል፡፡ ወይንም መስማት የሌለበትን ለሌሎች አሰምቶ፣ አሻግሮ ከጨረሰ በኋላ፡፡ ሲነገረውም “አትንገር” ተብሎ ነው፤ ሲናገርም “አትንገሩ” ብሎ ነው፡፡ እርግማኑ ፀፀት አያጣውም፡፡
የውድቀት አጫፋሪው እውነቱን እያወቀ ሳለ ውሸት ሲነገረው መስማቱ ከፀፀተው “አይመስለኝም” ብሎ ሊያቅማማ ይችል እንደሆን እንጂ ሀሜተኛውን በተግባሩ ላይ ሳለ በዛው በእርካታው ቅፅበት ላይ “አቁም” ለማለት አያስችለውም፡፡ የከበደም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው፡፡
ለከበደ ወሬውን ይዞለት ለመጣው ሰው፣ የትምህርት ማስረጃውን አውጥቶ ቢያሳየውም እንኳን ይዞ ወደ መጣበት የተመለሰው ግን ሌላ የሀሜት አቅጣጫን የሚያበረታታ ጥርጣሬን ነው፡፡ “… የትምህርት ማስረጃ ካለው ታዲያ ለምን ከስራ ተቀነሰ… አንድ የደበቀው ሚስጢርማ አለ” የሚል ሌላ የማወቅ እና የመፍረድ አዲስ ተልዕኮ አንግቦ ነው የተመለሰው፡፡ ተጠራጣሪ መንፈስን የሚመጥን መረጃ ሀሜት አድርጎ ለማደራጀት፡፡
የማወቅ ፍላጎት የሌለው ካለ እሱ ሰው አይደለም፡፡ የማወቅ ፍላጎት ያለው ሁሉ ባወቀው ነገር ላይ ፈራጅ ነው፡፡ ነገርን ከጥሩ ውሃን ከስሩ ማወቅ አለመፈለጉ፣ አልያም መስነፉ ላይ ነው ፀጋው ወደ እርግማን የሚለወጠው፡፡ የእውቀት አቅም ደግሞ ወደ ሀሜት፡፡

Read 889 times