Saturday, 25 March 2023 18:37

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by  ፋሲል የኔአለም
Rate this item
(0 votes)

“የዐቢይ መንግስት መቼ ይለወጣል?”
                     
          ተቀራራቢ ስነልቦና በሚጋሩ አገሮች የሚካሄዱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ይወራረሳሉ። ለምሳሌ ከ12 ዓመታት በፊት በቱኒዚያ የተነሳው ተቃውሞ፣ አብዛኛውን የአረብ ዓለም አገራት አዳርሶ ዛሬም ድረስ በወጉ አልተቋጨም። ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በተቃውሞ መናጥ ጀምረዋል።የእነዚህን ሁለት አገሮች ስነልቦና የሚጋሩ ብዙ የአፍሪካ አገሮች አሉ። ተቃውሞው ወደ እነዚህ አገሮች ይሸጋገር አይሸጋገር የምናየው ይሆናል።
ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ አቀማመጧና ከታሪኳ ጋር በተያያዘ፣ የብዙ አገሮችን አማካኝ (average) ስነልቦና ወራሽ አገር ትመስለኛለች። በዓረቡ ዓለም የነበረው ተቃውሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባውና ህወሃትን ያስወገደው ዘግይቶ ነው። በኬንያና ደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ተቃውሞ ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ምን ሊሆን ይችላል? እያሰብኩበት ነው። በዚህ አጋጣሚ ጉራ አይሁንብኝ እንጅ፣ ከአስር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በአስር ዓመት ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ ይጀመራል የሚል” ትንቢት” ብጤ ተናግሬ በመሳካቱ፣  ዛሬም ድረስ የዐቢይ መንግስት በምን ያህል ጊዜ ይወድቃል እያሉ የሚጠይቁኝ “የዋሆች” አሉ።
 ታዋቂው ጸሃፊ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ የዐቢይ መንግስት ከአንድ ወይም ሁለት ዓመት የዘለለ እድሜ አይኖረውም ሲሉ፣ ከባልደረባዬ ሲሳይ አጌና ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ሲናገሩ ሰምቻቸው ነበር። እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ንዴትና የለውጥ ፍላጎት፣ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ክብደት (critical mass) ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ከ2008ቱ ተቃውሞና ከህወሃት ጋር ከተደረገው ጦርነት ድባቴና ስልቹነት የተላቀቀ አይመስለኝም። መንግሥትና መንግሥት መለውጥ የሚፈልጉት ሃይሎች ሰላሙን አልሰጡት አሉ እንጅ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ከአብዮት ይልቅ፣ ሰላምና የተረጋጋ ሥርዓት የሚፈልግ ይመስለኛል። ያ ሲባል ግን ነገ ያልገመትነው ነገር አይፈጠርም ማለት አይደለም።



Read 1174 times