Saturday, 01 April 2023 19:50

"ኑሃ" መንገድ ዳር የተበላሹ መኪኖች እርዳታ ሰጪ ድርጅትና መተግበሪያ በይፋ ሥራ ጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ፍፁም ዘካሪያስና ነብዩ ዘካሪያስ የተባሉ ወንድማማቾች ያበለፀጉትና በመንገድ ዳር ተበላሽተው ለሚቆሙ መኪኖች እርዳታ የሚሰጥ ‹‹ኑሀ›› ሮድ ሳይድ አሲስታንት›› ድርጅት ከነ ሞባይል  መተግበሪያው በይፋ ተመረቀ፡፡ ድርጅቱ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነችው ድርሻዬ ዳናን (ድርሹ ዳናን) በአምባሳደርነት ሾሟል፡፡

የዚህ ድርጅትና የሞባይል መተግበሪያ ዋነኛ አላማ በመንገድ ዳር ተበላሽተው ሲቆሙ አስቸኳይ እርዳታና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመ ሲሆን፤ ይህንን መተግበሪያ ለማበልፀግ 6 ወር፣ ለሙከራ ደግሞ 3 ወር እንደፈጀባቸው ወንድማማቾቹ ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም  ረፋድ ላይ በካፒታል ሆቴል፣ መተግበሪያውን በይፋ ባስመረቁበት ጊዜ ተናግረዋል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ለጊዜው በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይ በበርካታ ሀገርኛ ቋንቋዎች አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡ አንድ ግለሰብ የ‹‹ኑሃ›› ደንበኛ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በመኪናው ላይ ድንገተኛ ብልሽት አጋጥሞት ቢቆምና ድንገት መተግበሪያውን ለመጠቀም አመቺ ሁኔታ ላይ ባይሆን በአጭር የጥሪ ማዕከል 6515 ላይ በመደወል አፋጣኝ መፍትሄ ከኑህ ሮድሳይድ አሲስታንስ ድርጅት እንደሚያገኝ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡ የዚህ ድርጅት ደንበኛ በመሆን የአገልግሎት ክፍያ ለመክፈል በቴሌ ብር በኩል ክፍያ መፈፀም የሚቻል ሲሆን ደንበኛው ክፍያውን እንደየአመቺነቱ በ3 ወር፣ በ6 ወርና በዓመት የሚከፍልበት አሰራር መዘርጋቱንም ወንድማማቾቹ ፍፁም ዘካሪያስና ነብዩ ዘካሪያስ ተናግረዋል፡፡

ይህን አገልግሎት ለመስጠት እውቀትና ክህሎት የታከለበት ሥራ መሰራቱን የገለፁት ወንድማማቾቹ፤ በዘርፉ ልምድ ያካበቱትን ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡን በአማካሪነት በመያዝ፣ በኑሃ ጠንካራ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች መተግበሪያው መሰራቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹ኑሀ›› ያመጣው ትልቁ እፎይታ ባለመኪና ግለሰቦች መኪናቸው ሲበላሽ ከሜካኒኮች የሚጠራውን የተጋነነ እና ወጥነት የሌለው ክፍያ በማስቀረት ተመጣጣኝ ተመን ባለውና በወር በሚከፈል ክፍያ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ነው ብለዋል ሀላፊዎቹ፡፡ በመተግበሪያው ምረቃ እለት የድርጅቱ አማካሪ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረ ስላሴ፣ የቴክኖሎጂው ባለቤቶች ወላጆችና ቤተሰቦች፣ የቴሌ ብር ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  የኑሀ ባለቤቶች በ6 ወራት ውስጥ የደንበኞቻቸውን ቁጥር 120 ሺህ ለማድረስ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

Read 1290 times Last modified on Tuesday, 04 April 2023 19:21