Saturday, 01 April 2023 19:59

‹‹ዩቶፕያ›› ፋሲካ ኤክስፖ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)


ታላላቅ የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት የካበተ ልምድና ተቀባይነት ያለው ሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ያዘጋጀው ‹‹ዩቶፕያ ፋሲካ›› ኤክስፖ፤ዛሬ  መጋቢት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በሚሊኒየም አዳራሽ በድምቀት ይከፈታል፡፡

ከ300 በላይ ድርጅቶች ይሳተፉበታል የተባለው ይሄው የፋሲካ ኤክስፖ፤ በርካታ አዳዲስ ኹነቶችን አካትቶ መምጣቱን የሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ሀላፊዎች ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ረፋዱ ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ይዘልቃል በተባለው በዚህ ኤክስፖ ላይ ጤፍን ጨምሮ ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ በማሰብ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑንም የሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አዶኒክ ወርቁ ተናግረዋል፡፡

እስከ ዛሬ በድርጅቱ ከተዘጋጁት የንግድ ትርኢትና ባዛሮች የዚህኛውን ለየት የሚያደርጉት በርካታ ነገሮች እንዳሉት ያብራሩት የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሃና ኢተቻ በበኩላቸው፤ አውቶሞቲቭ ኤክስፖ፣ የሪል ስቴት ኤክስፖ፣ የባንክ ኮርነር፣ ለስራ ፈጣሪዎች የተዘጋጁ ቦታዎች፣ የዳንስና የውዝዋዜ ውድድርና ሽልማት፣ የሰርግ (ብራይዳል ሾው)፣ የፊትነስ ፌስቲቫል (የቴኳንዶና የቦክስ) እንዲሁም የዳይኖሰር ትርኢትና ሌሎች በርካታ አዳዲስ ዝግጅቶች እንደተካተቱበት ጠቁመዋል፡፡  

ከኤክስፖው መክፈቺያ እስከ መጠናቀቂያው ድረስ በየቀኑ ደማቅ የሙዚቃ ድግስ የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚህም ድግስ ላይ ተወዳጅና ዝነኛ አርቲስቶችና ዲጄዎች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

ኤክስፖው ምንም እንኳን ዛሬ በድምቀት ቢከፈትም፣ ማክሰኞ እለት ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት በልዩ ሁኔታ እንደሚከፈትም ተገልጿል፡፡

32ሚ.  ብር በጀት የተያዘለት ‹‹ዩቶፕያ›› ፋሲካ ኤክስፖ፤ እንደከዚህ ቀደሙ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነፃ ቦታን የፈቀደ ሲሆን ሜቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ከህዝቡ ጋር  እንዲገናኙና ድጋፍ እንዲያሰባስቡ ዕድል ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ ሰዓሊያን ሥራቸውን ለእይታና ለሽያጭ የሚያቀርቡበት የአርት ጋለሪ ኮርነርም እንደተዘጋጀ  ተጠቁሟል፡፡


 ኤክስፖውን በፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር ያደረገው ዳሽን ባንክ ሲሆን፤ ሌሎችም በወርቅና በብር ደረጃ ስፖንሰር እንዳደረጉት ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመግቢያ ዋጋን በተመለከተ ቀን ቀን 50 ብር፣ ማታ ማታ ደግሞ 100 ብር የሚያስከፍል ሲሆን፣ በዳሽን ባንክ አሞሌ በተሰኘው መገበያያ ትኬቶችን መግዛት እንደሚቻልም ታውቋል፡፡ ዩቶፒያ የፋሲካ ኤክስፖን ከ300 ሺህ ሰው በላይ ይጎበኘዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም የሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ሀላፊዎች በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡

Read 1774 times Last modified on Tuesday, 04 April 2023 19:38