Saturday, 01 April 2023 20:05

‹‹ ከዩጋንዳ የመጣነው የዓለምን ፍፃሜ ሽሽት አይደለም ››

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ከዩጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ ኛንጋቶም ወረዳ የገቡት የቴሶ ጎሳ ዩጋንዳዊያን፣ የዓለምን ፍፃሜ ሽሽት እንዳልመጡ ተገለፀ፡፡ ዩጋንዳዊያኑ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳደር በተለይ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ዩጋንዳዊያን በታሪክ እንደሚታወቀው ከአቢሲኒያ ምድር ከኛንጋቶም የወጡ ናቸው›› ያሉት የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ናኮራ ናሲኬ፣ በዚህ ምክንያት የነዚህ ጎሳዎች ቤተሰቦች በአብዛኛው ኛንጋቶም ውስጥ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
‹‹እነዚህ የቴሶ ጎሳ ዩጋንዳዊያን ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት አንዱ ምክንያት ኛንጋቶም የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ እንዲሁም ለነዚሁ ቤተሰቦቻቸውና ለኛንጋቶም ህዝብ የእግዚአብሄርን ወንጌል ለመስበክ ሲሆን፣ ሌላኛው ምክንያታቸው ደግሞ እነዚህ ጎሳዎች የተዋጣላቸው አርሶ አደሮች እንደመሆናቸው አርብቶ አደሩን የኛንጋቶምን ህዝብ እርሻ ለማስተማርና የስራ ባህሉን እንዲያዳብር ለማገዝም ጭምር ነው›› ሲሉ አቶ ናኮራ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋ፡፡የኛንጋቶም ወረዳ ባለፈው ታህሳስ ወር ትልቅ የሰላም ፊስቲቫል አዘጋጅቶ እንደነበር የገለፁት አቶ ናኮራ፤ የዚህ ፊስቲቫል ዋና አላማ የቀጠናውን የሰላም ትስስር ማጠናከር ነበር ብለዋል፡፡
በዚህ የሰላም ፊስቲቫል ላይ ከኛንጋቶም ጋር ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ  የአተከር ክላስተር አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሆኑትን አጎራባች አገራት ህዝቦች ማለትም - የደቡብ ሱዳኑ ቶፖሳ ጎሳ አርብቶ አደሮች፤ ‹‹ቱርካና›› የሚባሉት የኬንያ አርብቶ አደር ጎሳዎች፣ ካራሞጆንግ የተሰኙት ዩጋንዳ ውስጥ ያሉ አርብቶ አደር ጎሳዎች አሁን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ‹‹ቴሶ›› የተሰኙት አርሶ አደር የዬጋንዳ ጎሳዎች እና ጅዬ የተሰኘው የኛንጋቶም ጎሳዎች በሰላም ፊስቲቫሉ ላይ ተሳትፈው እንደነበር አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ዩጋንዳዊያን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የባለፈውን የሰላም ፊስቲቫል መነሻ በማድረግ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር የህዝብ ግንኙነት ስራ ለመስራት እንጂ የዓለምን ፍፃሜ ሽሽት እንዳልሆነ የወረዳ አስተዳደሪው አቶ ናኩራ ናሲኬ ገልፀዋል
‹‹የዓለምን ፍፃሜ ሽሽት ወደ ኢትዮጵያ መጡ›› እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው ሲሉም አስተባብለዋል፡፡‹‹የሰላም ፌስቲቫሉን ባካሄድን ጊዜ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ፤ በርካታ የፌደራልና የክልል የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተው ነበር›› ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ ‹‹እነዚህ ዩጋንዳዊያን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት ያደረባቸው በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይ አገር መሆኗ  በስፋት ይታወቃልና እናንተስ እንደ ኢትዮጵያዊያን እንግዶቹን እንዴት ተቀብላችሁ እያስተናገዳችሁ ነው?›› በሚል ለወረዳ አስተዳዳሪው ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣‹‹እኛ በጥሩ ሁኔታ ተቀብለናቸዋል፤ ይህንንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከዞን የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት መጥተው ጎብኝተዋል›› ያሉ ሲሆን ምንም እንኳን ሲመጡ ‹‹ህይወት ብርሃን›› የተሰኘ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ቢያርፉም ብዙ በመሆናቸው የኛንጋቶም ህዝብ ለእነዚህ እንግዶች ለእያንዳንዳቸው የመኖሪያ ቤት ሰጥቷቸው እየኖሩ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ናኩራ አክለውም፤ ወረዳውም ውሃ በቦቴ እያቀረበና የሚያበስሉበት እንጨት እየጫነ እያገዛቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡም ሩዝን ጨምሮ ማንኛውንም አይነት ምግብ እያቀረበላቸው ሲሆን እነሱም ከነህፃናት ልጆቻቸው ከዩጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ቀለብና አስፈላጊውን ሎጂስቲክስ ይዘው መምጣታቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
 ‹‹አዲስ አበባ ለሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉዳዩን ሪፖርት አድርገናል፤ ነገር ግን እስካሁን መረጃ ከመውሰድ ባለፈ የተሰጠ ምላሽ  የለም›› ያሉት አስተዳዳሪው፤ ቢሆንም እንግዶቹ  እስካሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ነው ለአዲስ አድማስ የተናገሩት፡፡
ወደ ኛንጋቶም ከመጡት ዩጋንዳውያን አብዛኞቹ ዲግሪና ማስተርስ ያላቸው ምሁራን ሲሆኑ በግብርና በጤና፣ በህግ፣ በአካውንቲንግና በሌሎችም የትምህርት ዘርፎች የካበተ እውቀትና ልምድ ያላቸው መሆኑን ያብራሩት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ናኩራ ናሲኬ፣ ‹‹እኛ ስራ የለመድን በመሆኑ ተቀምጠን ጊዜ ከማባከን እንደየሙያ መስካችን በበጎ ፈቃደኝነት ህዝቡን እናገልግል›› የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ እኛም ጥያቄያቸውን ተቀብለን የበጎ ፈቃድ ስራ እንዲሰሩ ለማሰማራት እንዲመቸን የሙያቸውን አይነትና የስራ ልምድ ዝርዝራቸውን እንዲሰጡን ጠይቀን ዛሬ ይሰጡናል ብለዋል፤ ለአዲስ አድማስ፡፡ እንግዶቹ እስከ መቼ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊቆዩ እንዳሰቡ የገለፁት ነገር አለ ወይ በሚል ለወረዳ አስተዳዳሪው ጥያቄ አቅርበን፤ ‹‹የሚታወቅ ነገር የለም፤ መመለሳቸውንም እንጃ›› ሲሉ በአጭሩ መልሰዋል።



Read 3132 times